Saturday, 15 September 2018 00:00

ጡሩምባው

Written by  ዳግማዊ አዱኛ
Rate this item
(7 votes)

 እጅግ ከተጐሳቆሉት የአዲስ አበባ መንደሮች መካከል በአንደኛው መንደር ውስጥ አቶ አደፍርስ ቁምላቸውና ወ/ሮ ሙሉ ገብሬ የሚባሉ እድሜ የጠገቡ አዛውንት ባልና ሚስት የጡረታ ደሞዛቸውና የፈጣሪ ስውር ክንድ በደገፈው አንድ ከግማሽ ጐጆአቸው ይኖራሉ፡፡ በአንደኛው ክፍል የሚገኘው ትልቅ የባልና ሚስት የሽቦ አልጋ አብዛኛውን የቤቱን ክፍል ሲይዝ፣ ከፊት ለፊቱ አሮጊቷ ቡና የሚያፈልቡት አነስተኛ መደብ ትገኛለች፡፡ ከሴትየዋ የቡና እቃ ድርድር ውጭ ለመተላለፊያ የሚሆን ቦታ ሊተርፍ ችሏል፡፡ በተረፈ በግማሹዋ ክፍል ውስጥ በአሮጌ ሸራ ተጠቅልለው የተቀመጡ ባለቤቶቹ የዘነጉአቸው ኮተቶች እና አይጦች ይኖራሉ፡፡
ግድግዳው ላይ የተሰቀለው ፎቶግራፍ መስታወቱ ተሰነጣጥቆ በስንጥቁ በኩል የገባው አቧራ ምስሎቹን ቢከልላቸውም፤ በከረባቱና በአንገት ዶቃዋ፣ የአንድ ወጣትና የአንዲት ልጃገረድ ምስል መሆኑን በመገመት የአቶ አደፍርስና የወ/ሮ ሙሉ የጥንት ማስታወሻ መሆኑን መናገር አይከብድም፡፡ ግድግዳው ቀሪ የፎቶግራፍ ቦታ ቢኖረውም፤ እንደወጡ የቀሩ ሁለት ዘማች ልጆቻቸውን ለመዘከር አልታደለም፡፡
ዘወትር አመሻሽ ላይ ጋሽ አደፍርስ በመንደሩ በታወቀው አረቄ ቤት ላለመገኘት ቢፈልጉም የአረቄ ሱሳቸው ምኞታቸውን ሽሮባቸዋል፡፡ ከአረቄው ጐን ለጐን ባለቤታቸውን ሳያሙ ላለመውጣት የተገዘቱ ይመስል “…ከዚች አጋንንት ጋር ያስቀመጠኝ ፈጣሪ…ሳላውቅ ብበድለው ነው እንጂ ከእንዲህ ያለችው ጋር መኖርስ ለኔ የሚገባ ነው ወይ…” ብለው በጥያቄ ያላስጨነቁት የአረቄ ቤቷ ደንበኛ ማግኘት ይከብድ ነበር፡፡ የጠጪነታቸው ምስጢር የአረቄ ሱሳቸው ሳይሆን የባለቤታቸው ክፋት መነሻ ሆኖ እንዲታይላቸው ተመኝተው፡፡ አረቄ በማውጣት በሚታወቁት ወ/ሮ ደብሬ ቤት አንድ ሁለት መለኪያ አረቄ ከወረወሩ በኋላ፣ የሴትየዋን ባለሙያነት አድንቀው ሲያበቁ፣ አገጫቸውን በእጃቸው ደግፈው የተለመደ ምሬታቸውን ማሰማት ይጀምራሉ፡፡
የማማት ሱስ ከባለቤታቸው የተጋባባቸው ባለቤታቸው፣ በበራቸው ላይ ቁጭ ብለው ቡና አፍልተው ጐረቤታቸውን ይጠሩና የባለቤታቸውን ገመና አውጥተው ሲያቀሏቸው መንፈሳቸውን ቀለል ይላቸዋል፡፡ “ከዚስ ጋርስ ከምኖር ምናለ እመቤቴ ከልጆቼ ጋር ብትቀላቅለኝ…ከዚህ ጋርስ ከመኖር ልጆቼ የገቡበት መቃብር መውረድ ይሻላል፡፡ ጭቅጭቅና ንትርኩን እኔ ሆኜ ነው እንጂ ማን ይችልለታል…የቅናቱስ ብትይ ይሄ አተላ…” ይላሉ በአንድ በኩል መጥፎ ህይወታቸውን ጠቅሰው፣ በሌላ በኩል የአፍ ልማድ ስለሆነባቸው፡፡
ጋሽ አደፍርስና እትዬ ሙሉ በየፊናቸው ለሚያገኙት ሰው ሁሉ የሚናገሩት ይኸው ቢሆንም፤ በጐጆአቸው ሽሮና ወግ ሳይጐድልባቸው የራሳቸውን ትዳር ይኖራሉ፡፡
******
ሃሳብ የጋሽ አደፍርስ አዕምሮ ውስጥ ከገባ ሰነበተ፡፡ የህይወትን ውጣ ውረድ አልፈው በተረፈቻቸው እንጥፍጣፊ እድሜ አረቄ እየጠጡ፣ በእፎይታ እየኖሩ እያለ፣ ጭንቀትና መባዘን የህይወታቸው አካል ከሆነ ሶስት ሳምንት ሆናቸው፡፡ ምክንያቱም ስድስት እድሜ ጠገብ የመንደራቸው ነዋሪዎች በተከታታይ ከቆረቆሩትና ከኖሩበት ሰፈር ወደ መቃብር ከተሸኙ በኋላ፣ አቶ አደፍርስ በመንደራቸው ብቸኛው እድሜ ጠገብ ሆነው ቁመታቸው ልቆ ታየ፡፡ አውሎ ነፋስ ያለአቅጣጫ እንደሚያወዛውዘው በሜዳ ላይ ሳይቆረጥ ብቻውን እንደቀረ ባህር ዛፍ ሆኑ፡፡ ከሟቾቹ ውስጥ ደግሞ ሁለቱ የእድራቸው ሊቀመንበርና ገንዘብ ያዥ መሆናቸው ከእሳቸው አልፎ መንደሩንም ያስገረመ ነበር፡፡
መንደሩ ወዙን አጣ፡፡ ጋሽ አደፍርስ አላምርብህ አላቸው…ቆሌ ራቃቸው…አድባር ሸሻቸው፡፡ በድንገት ሰውነታቸው ሲቀዘቅዝ ነፍሳቸው ወጥታ ትመለሳለች፡፡ ያቺን ሞት የሚያተራምሳት መንደር መሃል ያለችው ጐጆአቸው የአጥር ሽንቁር መልአከ ሞትን ለማሾለክ ያህል በቂ መስላ ታስጨንቃቸው ጀመር፡፡ አጥራቸውን እንደገና ያጠብቁ ቀዳዳ ይደፍኑ ጀመር፡፡
ሞት ፍትሃዊ ነው ቢባልም በደከመው ላይ ይበረታል፡፡ ሞት ፍትሃዊ አይደለም፡፡ ይልቅ ሞት ጆሮ ቢኖረው ወደ የት ሃገር እንደሚልኩት በሃሳብ ይመትራሉ፡፡ ማምሸትም ዕድሜ ነው፡፡
“የደጁን በር ዘጋሽ?” ብለው ይጠይቃሉ፤ ጋሽ አደፍርስ ከሃሳባቸው ሲባንኑ፡፡ ባለቤታቸው አልጋው ላይ ከተመቻቹ በኋላ “ዛሬ ደግሞ ስራዬን ሊነግሩኝ ነው እንዴ? ምናለ እርሶ ሰውዬ አርፈው ቢተኙ…መቼ ክፍቱን አድሮ ያውቃል?...ሰላም አሳድረኝ ነው ሚባለው” ይላሉ የጋሽ አደፍርስ፣ ጭንቀት አልፎ አልፎ በደምስራቸው የሚዞረው ባለቤታቸው፡፡
“በሩን ክፍት ረስተሽ እንደሆን ነው ያልኩሽ…አርባ ክንድ ነው ምላስሽ መቼም…”
“ኡኡቴ…!” አፋቸውን ያጣምማሉ ሴትየዋ…ልባቸው ሲረጋጋ…ድምፃቸው እየተንቀጠቀጠ፡፡ ጋሽ አደፍርስ ከዚህ በላይ መጠየቅ አልፈለጉም፡፡ በጋቢያቸው ተጠቅልለው፣ በብርድልብስ ተጀቡነው፣ በንቃት ግቢያቸውን ይጠብቁ ጀመር፡፡ ሊነጋጋ ሲል እንቅልፍ አሸነፋቸው…፡፡
…ብዙም አልተኙም፤ የመንደሩ እድር ጡሩምባ ጩኸት አባነናቸው፡፡ በላብ ተጠምቀዋል፡፡ ባለቤታቸው እንዲያዩአቸው ባይፈልጉም፣ በክንዳቸው እየጐሸሙ አሮጊቷን መቀስቀስ ጀመሩ፡፡ “ሙሉ …አንቺ ሙሉ! እስቲ ብድግ በይና ምን እንደሚል ስሚ…” ጡሩምባው ወይዘሮዋንም አባንኗቸው ነበርና፣ አባወራው ሲቀሰቅሷቸው በቅልጥፍና ከአልጋቸው ወርደው በቁልፍና በመቀርቀሪያ የተከረቸመውን በር ለመክፈት ሲታገሉ ትንሽ ጊዜ ወሰደባቸው፡፡ ደንገዝገዝ ባለው ንጋት ጆሮአቸውን ቀሰሩ፡፡ የአረቄ አውጪዋ የወ/ሮ ደብሬ መርዶ ነበር፡፡ “ውይ ደብሬ፣ ውይ ደብሬ…” እያሉ ነጠላቸውን ፍለጋ ማታ ያጣጠፉትን ጨርቃቸውን ያተረማምሱ ጀመር፡፡ “ምን ሆነች ደብሬ?” ሲሉ ጠየቁ፤ አቶ አደፍርስ…ሞቱ ብለው ለማሰብ ፈርተው…በአዋጅ ጡሩምባ እየተነፋ እድሜ እንደማይታደል ሆዳቸው እያወቀ፡፡
“እንደሰራ አይገድል…እንደሰራ አይገድል” አሉ ባለቤታቸው ነጠላቸውን መሬት እየጐተቱ፣ ከጐጆዋ ሊወጡ ሲሉ፡፡
“ደብሬ የትኛዋ?” ሲሉ አቶ አደፍርስ እንደገና ጠየቁ፤ ሌላ ደብሬ አስታውስ እያሉ አዕምሮአቸውን እያስጨነቁ፡፡ ወይዘሮዋ ግን አጥሩን ከፍተው በመውጣታቸው የመጨረሻውን የባለቤታቸውን ጥያቄ ሳይሰሙ ቀሩ፡፡ አባወራው ገርበብ ብሎ የተከፈተውን የአጥሩን በር በትካዜ እየተመለከቱ፣ ጀንበር ወጥታ ህፃናት መንጫጫት ጀመሩ፡፡
*****
ከቀብር በኋላ በድንኳን ውስጥ፣ ሰሞኑን በተከታታይ ያረፉትና ዋና የመወያያ ርዕስ የነበሩት የመንደሩ አዛውንቶች በድንኳኑም እንደአዲስ መነሳታቸው አልቀረም፡፡…ሲመከር አልሰማ ያለው ሰካራሙ አቶ ግርማ እና ቀን ደህና ሲጫወቱ ውለው ሌሊት በድንገት ያረፉት አረቄ አውጪዋ ወ/ሮ ደብሬ…”ከሴት ጋር ከሆነ፣ እንኳን አልጋ ላይ እሳት ላይ እተኛለሁ” የሚሉት ሴት አውል አዛውንትና በኑሮ ውድነቱ ተወጥሮ የነበረውን ጭንቅላቱን አሮጌ የጭነት መኪና ከመሬት ጋር ያዋሃደው እድለቢስ ምስኪን…ሌትም ይሁን ቀን፣ መጠጥ ሲቀምስ እየጮኸ የሚዘምረው የመንደሩ ተረበኛና በሞቱ በሦስተኛው ቀን በራቸው ተሰብሮ አስከሬናቸው የተቀበረው ወዳጅ አልባ ሽማግሌ…ሁሉም በየተራ እየተነሱ ሲወድቁ እኩለ ሌሊት ሆነ፡፡
ጋሽ አደፍርስ ይህን ሁሉ በአዕምሮአቸው ሲያብሰለስሉ፣ ሰዓቱ መግፋቱን አላስተዋሉም ነበር፡፡ ትንሽ አረቄ የቀማመሱ ወጣቶችም አንድ ጥግ ላይ የካርታ ጨዋታ ይዘዋል፡፡ በዚህ መሃል ነው ታዲያ የጋሽ አደፍርስን ጭንቅላት ያዞረ ጨዋታ ከአንድ ነባር የአረቄ ደንበኛ የተሰነዘረው፡፡ ሁኔታው እንደሚከተለው ነበር፡፡
የወ/ሮ ደብሬ ደንበኞች የነበሩ በፍጥነት አዲስ ኮማሪት ደንበኛ ማግኘታቸው ለሽማግሌው ባይዋጥላቸውም፤ የእድር አመራርነታቸውን ወንበሮቹ፣ ሳህኖቹና ኩባንያዎቹ እንዲቆጠሩና እንዲመዘገቡ እንግዳ በማስተናገድ ቀኑን ሙሉ ሲደክሙ የነበሩትን ማሳሰብ ጀመሩ፡፡ ከእድሩ እቃ በወጣና በገባ ቁጥር ጋሽ አደፍርስ መፈረም ነበረባቸው፡፡ በዚህም ነባር ህግ መሰረት፣ የሳህኖቹና የዕድሩ ንብረቶች ሁሉ ተቆጥረው ዝርዝሩ በነጋታው ጠዋት እንዲቀርብላቸው ይጠይቃሉ፡፡ ይሄን ጊዜ ነው ባለገበሩ ሰካራም “ጋሽ አደፍርስ፤ እነዚህን አሮጌ የብረት ሳህኖችና ኩባያዎች ማን ይነካል ብለው ነው?...
ዘመናዊና ቀላል የፕላስቲክ ሳህኖችና ኩባያዎች መጥተዋል…እድሩ አሁን የብረቶቹን ትቶ የፕላስቲኮቹን መግዛቱ አይቀርም…ጡሩምባውም ቢሆን በዘመናዊው ቩቩዜላ ይተካል…እርስዎ በቁም እያሉ አናደርገውም ብለን እንጂ የበፊቱን ኮተታ ኮተት ሁሉ ከባለቤቶቻቸው ጋር ቆፍረን እንቀብራቸው ነበር…እኔ ልሙት ጋሽ አደፍርስ በአዳዲስ ሳህኖች ይተካሉ እንጂ የእርሶን ብረታ ብረትም ሆነ ፊርማዎን አንድ ሰው አይነካብዎትም…እንዳማረባቸው…” በአረቄ ሞቅታ የሚጮኸው የቀጭኑ ወጣት መሳይ ድምጽ፣ ድንኳኑን ባናጋው የሳቅ ሁካታ ተተካ፡፡ ጋሽ አደፍርስ ከዚህ በላይ ሊቆዩ  አልቻሉም፡፡
****
ጋሽ አደፍርስ ከዚህ በኋላ በማንኛውም የዕድር ስብሰባ ላይ መገኘት ተው፡፡ መንደሩ እንደጥላ ከበዳቸው፡፡ በነጋታው ወደ ደጅ ብቅ ሳይሉ አልጋቸው ላይ ተኝተው አመሹ፡፡ የሰውየው በቤት መዋል ለሴትየዋ አልተመቸም፡፡ ሴትየዋ ጐረምሳ የጠላ ደንበኛቸውን ወሽመዋል ተብለው በመንደሩ እንደሚታሙና የባለቤታቸው ከቤት መዋል ለዚሁ እንደሆነ ጠርጥረዋል፡፡
በአንድ በኩል ጐረምሳ ነው መባሉን ቢወዱትም፣ በሌላ በኩል ባለቤታቸውን በነገር መጠዝጠዙን ማቆም አቃታቸው፡፡ አቶ አደፍርስ ግን ሁሉን ትተው በፀጥታ አልጋ ላይ ሰፍረዋል። ከእንቅልፍ እንደራቁ በጐደጐዱት አይኖቻቸው ማወቅ ይቻላል፡፡ እጃቸው መንቀጥቀጥ ጀምሯል።
“ኧረ ከደጅ መግባቴ ነው አንቱ ሰውዬ እስቲ አረፍ ልበል!” አሉ አሮጊቷ። ሽማግሌው ቢደነግጡም ጭንቀታቸውን ሴትየዋ እንዳያውቁባቸውና የመንደሩ መሳቂያ እንዳያደርጓቸው ሚስጥራቸውን ለመሸሸግ “በሩን ዝጊ እኮ ነው ምልሽ!” ሲሉ በሚንቀጠቀጥ ድምጽ ተቆጡ፡፡ ጭንቀታቸውን ለመሸፈን የሚያደርጉት ተግባር ሁሉ የጐላ ጭንቀት አላበሳቸው፡፡
ጠዋት የጡሩንባ ድምጽ ተሰማ፡፡ ጡ…ጡ…ጡ…የድል ጮራ መንደርተኞች በሙሉ ለመንደራችን ጽዳት….የሽማግሌው ልብ ጥላቸው ለመሮጥ በሀይል ታገለች፡፡ የጽዳት ዘመቻ ጥሪ ነበር፡፡ አቶ አደፍርስ ላብ አጥምቋቸው አድሯል፡፡ አይኖቻቸው ጐድጉደዋል፡፡ የሰውነታቸው መንቀጥቀጥ አላቋረጠም፡፡ ከንፈራቸው ቢንቀሳቀስም ትርጉም ያለው ቃል ማውጣት ተስኗቸዋል፡፡ የጡሩንባውን ድምጽ እንጂ መልዕክቱን ማዳመጥ ስለተሳናቸው፣ ጡሩንባው በተነፋ ቁጥር እየተሳቀቁ ባለቤታቸው ላይ ያፈጣሉ፡፡
ጡ…ጡ…ጡ…በከፍተኛ ቅናሽ ስንዴ በቀበሌያችን ስለሚገኝ…
ጡ…ጡ…ጡ…የፖሊዮ ክትባት ልጁን ያላስከተበ ካለ የመጨረሻ…
ጡ…ጡ…ጡ… የድል ጮራ ነዋሪዎች እድር ዓመታዊ ስብሰባ…
አሮጊቷም የየእለቱን ወሬ ሳያጓድሉ ያቀርቡላቸዋል፡፡ በመንደሩ እንደ ወትሮው ፀሐይ ወጥታ ብትውልም፤ አቶ አደፍርስ ከአልጋ መውረድ ሳያስቡና ለማንም ምንም ሳይተነፍሱ ከቅዠታቸው ጋር ትግል ገጠሙ፡፡ ሰይጣን የሚፈልገውን ሰው እንዳጣ ሁሉ እየተበሳጨ፣ ከርቀት በጡሩምባ ቀዳዳ መንደራቸውን ሲያስተውል እያለሙ በላብ ተጠምቀው ሌሊት ይባንናሉ፡፡ የመንደሩ ሰው ሁሉ ተመካክሮ ለቅቆ ሄዶ ከቁራዎችና ከድመቶች ጋር ብቻቸውን የቀሩ ይመስላቸዋል፡፡ …ሬሳ ቀባሪ ሰዎች ከደጅ በራቸው ላይ ቀጠሮ ሲቃጠሩ ይሰማሉ፡፡ በቀዳዳ እያጮለቁ ይንሾካሾኩባቸዋል፡፡ ….በዚህ ሁኔታ ብዙ ቀናት አለፉ፡፡
….ከእለታት አንድ ቀን የእድሩ ጡሩንባ ነፊ የተለመደ ስራውን ለመስራት ጐህ ሳይቀድ ተነሳ፡፡ “ጡ…ጡ…ጡ…አቶ አደፍርስ ቁምላቸው ስላረፉ…”
ከአ

Read 2874 times