Saturday, 15 September 2018 00:00

“በውድድሩ የአፍሪካ አምባሳደርነትን ማዕረግ ማግኘቴ ቀላል አይደለም”

Written by  ናፍቆት ዮሴፍ
Rate this item
(1 Vote)

ተወልዳ ያደገችው ድሬዳዋ ከተማ ውስጥ ነው፡፡ የልጅነት ህልሟ በጋዜጠኝነት ሙያ መቀጠል ነበር - ሞዴል ፈቲያ መሃመድ፡፡ ገና በለጋነት እድሜዋ ወላጆቿን ያጣችው የዛሬዋ እንግዳችን ፈቲያ መሃመድ ለቤተሰቧ የመጀመሪያ ልጅ መሆኗ በጣለባት ኃላፊነት፣ ታናሽ እህቷንና ወንድሞቿን ማሳደግና ማስተማር ጫና ትከሻዋ ላይ መውደቁን ትገልፃለች። ከትውልድ አካባቢዋም እህት ወንድሞቿን ይዛ ወደ አዲስ አበባ ለመምጣትም ትገደዳለች፡፡ በተለያዩ የቁንጅና ውድድሮች ላይ ተሳትፋ የተለያዩ ማዕረጐችን ያገኘችው ሞደል ፈቲያ መሀመድ፤ በቅርቡም ማሌዢያ ኳላላምፑር ላይ በተካሄደ ቀድሞ የቁንጅና ውድድር “Mrs Tourism Queen International Pageant” ላይ አገሯን ወክላ በመሳተፍ አሸንፋለች፡፡ እስከዛሬ በውድድሯ ያገኘቻቸው ማዕረጐችስ ምንድን ናቸው? በኳላላምፑር የነበረው ቆይታዋ ምን ይመስላል? በሚሉና በተያያዥ ጉዳዮች ዙሪያ ከአዲስ አድማስ ጋዜጠኛ ናፍቆት ዮሴፍ ጋር ተከታዩን ቆይታ አድርጋለች፡፡  


     እንዴት ነበር የሞዴሊንጉን ዘርፍ የተቀላቀልሽው?
እርግጥ እኔ ከፍተኛ ፍቅር የነበረኝ ለጋዜጠኝነት ነው፡፡ በሀይስኩል ቆይታዬ ሚኒ ሚዲያ ላይ በንቃት እሳተፍ ነበር፡፡ በፀረ-ኤድስና መሰል ክበባት ማለቴ ነው። በዚህ እንቅስቃሴዬ ላይ እያለሁ አንድ የሞዴሊንግ ኤጀንት አገኘሁና ዘርፉን ተቀላቀልኩ - በዚያው ቀጠልኩበት፡፡ አሁንም በሞዴሊንግ፣ በማስታወቂያ ስራዎችና በፋሽን ዘርፍ ውስጥ ነው ያለሁት፡፡
እስኪ እስከዛሬ የተሳተፍሽባቸውን ውድድሮችና ያሸነፍሻቸውን ማዕረጐች ንገሪኝ?
እ.ኤ.አ. በ2005 ዓ.ም እዚህ አገር ሁለተኛ ወጥቼ፣ ወደ ቻይና ለውድድር ከሄድኩ በኋላ “The best Africa Queen” የተሰኘ ማዕረግ አግኝቻለሁ።  ጃፓን ሄጄ “Mis Good will” የተሰኘ ማዕረግ ተሰጥቶኛል፡፡ በተሳትፎ ደረጃ በርካታ የቁንጅና ውድድሮችን በአገር ውስጥና በውጭ አድርጌ፣ በዘርፉ ያለኝን ልምድና የሙያውን ምንነት በደንብ ለማዳበር ችያለሁ፡፡
እስኪ በቅርቡ በማሌዢያ ኳላላምፑር ስለተሳተፍሽበት ውድድር አጫውቺኝ?
በቅርቡ ኦገስት ውስጥ የተካሄደው ውድድር ቀድሞ ከተወዳደርኳቸው ለየት ይላል፡፡ ምክንያቱም ይሄኛው ውድድር ቀደም ብለው በወ/ሪት ደረጃ የቁንጅና ውድድር ላይ አሸንፈው ማዕረግ ያላቸው ሞዴሎች ሆነው፣ አግብተው የወለዱና ራሳቸውን ጠብቀው፣ በሙያው የቀጠሉ “ወይዘሮ ሞዴሎች” የሚሳተፉበት መሆኑ ነው የሚለየው፡፡ እኔም ከዚህ ቀደም ብዬ የገለፅኩልሽ ማዕረጐች የነበሩኝ ሲሆን፤ ከዚያ በኋላ አግብቼ ሁለት ልጆች ብወልድም ከሙያው ሳልወጣ ራሴን ጠብቄ ሙያውን ወድጄው ቀጥዬበታለሁ፡፡ ይሄ ለብዙ በሙያው የነበሩና ከወለዱ በኋላ ራሳቸውን ባለመጠበቅ ከሙያው ለሚወጡ ሞዴሎች ትልቅ ማስተማሪያ ይሆናል የሚል አምነት አለኝ፡፡
ይህ ውድድር በዋናነት “ወ/ሮ ሞዴሎች” አገራቸውን የሚያስተዋውቁበት ነው ብለሽኛል፡፡ እስኪ አብራሪልኝ?
አገራቸውን ወክለው ከአውስትራሊያ፣ ብራዚል፣ ኢስቶኒያ፣ ቡልጋሪያ፣ ፊንላንድ፣ ፈረንሳይ፣ ህንድ፣ ጃፓን፣ ካዛኪስታን፣ ኬኒያ፣ ማሌዥያ፣ ሜክሲኮ፣ ሞንጐሊያ፣ ማይናማር፣ ኔፓል፣ ከኒውዚላንድ፣ ፊሊፒንስ፣ ፖርቹጋል፣ ሮማኒያ፣ ሩሲያ፣ አሜሪካ፣ ቬትናም፣ ስዊዲን፣ ከታይላንድና ከ30 በላይ ሞዴሎች የተወዳደሩበት ነው፡፡ ውድድሩ በአካላዊ ቁንጅና ብቻ ላይ የተመሰረተ ሳይሆን ተወዳዳሪዎች ባላቸው ተሰጥኦ፣ በራስ መተማመንና የአገራቸውን ባህልና ቱሪዝም በማስተዋወቅ ብቃት ላይ ሁሉ የተመሰረተ ነበር፡፡ እኔም በተለይ የአፋርን ባህላዊ ልብስ በመልበስ ኢትዮጵያ ምድረ ቀደምት (Land 0f Origin) ስለመሆኗና በአጠቃላይ ባህሏን በደንብ ለማስተዋወቅ ሞክሬያለሁ፡፡ ቆይታችን ጥሩ ነበር፡፡ ከሌላው ዓለም ሞዴሎች ጋር የነበረው ግንኙነትና ልምድ ልውውጡም ቀላል አልነበረም፡፡
በዚህ ውድድር በዓለም አቀፍ ደረጃ አንደኛ የወጣችውና “Mrs Tourism Queen International” ማዕረግ ያገኘችው ጥቁር ብራዚላዊት ናት፡፡ አንቺ ምን ውጤት አስመዘገብሽ?
ውድድሩ በጣም ከባድና ፈታኝ ነበር፣ እንደነገርኩሽ፤ እዛ ድረስ ሄዶ መሳተፉም ትልቅ ነገር ነው፡፡ ልምድ ከመቅሰም አኳያ፡፡ ስሄድ ዓለም አቀፉን እንደማሸንፍ እርግጠኛ ነበርኩኝ፤ ግን ቢሆንም “Mrs Tourism Queen Africa” የሚል ማዕረግ አግኝቼ በአህጉር ደረጃ አሸንፌያለሁ፡፡ ይህም የውድድሩ ሁለተኛ ማዕረግ ነው፡፡ ትልቅ ውጤት ነው፡፡
አንደኛ ወጥተሽ ዓለም አቀፉን ማዕረግ እንዳታገኚ እንቅፋት ሆኖብኛል የምትይው ነገር ምን ነበር?
እውነት ለመናገር ከአገሬ በኩል በአግባቡ ድጋፍ ቢደረግልኝ ኖሮ፣ አንደኛ መውጣቱ ቀላል ነበር፡፡ ዞሮ ዞሮ የሌሎቹም ሀገር ተወዳዳሪዎች፣ በውድድሩ ላይ የተሳተፉት አንደኛ ለመውጣት አልነበረም። ነገር ግን የአገራቸውን ባህል፣ የቱሪዝም ሀብትና ተፈጥሮ ለማስተዋወቅ ነው፡፡ ምክንያቱም ከ250 በላይ ዓለም አቀፍ ብዙኃን መገናኛ፣ ከፍተኛ ሽፋን የሰጡት ውድድር ነበር፡፡ ስለዚህ አንደኛ መውጣት ጉዳያቸው አልነበረም፡፡ ሲመጡም ተከታይ ነበራቸው። ያደጉ ልጆች ያሏቸው፣ ከልጆቻቸውና ከባላቸው ጋር፣ በቡድን የመጡ ነበሩ፡፡ ቤተሰባቸው አብሯቸው ያልመጡት ቢያንስ ግን ናሽናል ዳይሬክተራቸው አብሯቸው ነበር፡፡ ወይ ደግሞ ፎቶግራፈርና ኮስቹም ሰራተኛቸው አብሯቸው ነው የመጡት፡፡ በአጠቃላይ ከአገራቸው በልዩ ድጋፍና ብርታት መጥተው ነው የተወዳደሩት፡፡
አንቺ ከማን ጋር ነበር የሄድሽው?
እኔ ብቻዬን ነው የሄድኩት፡፡ እርግጥ ባለቤቴ አብሮኝ መሄድ ፈልጐ ነበር፡፡ ባለፈውም ልጆቻችንን ትተን ሱዳን ደረስ አብሮኝ ሄዶ ነበር፡፡ አሁን ደግሞ ለሁለተኛ ጊዜ ለ10 ቀን ትተናቸው ሁለታችንም መሄድ ከበደን፡፡ ለምን? ልጆቹ ገና የሦስት ዓመት ተኩልና የሁለት ዓመት ህፃናት ናቸው - ብዙ አላደጉም፡፡ ቀደም ብዬ እንደነገርኩሽ፤ በመንግስት በኩልም ድጋፍ ስላልተደረገልኝና ባለቤቴም አብሮኝ ስላልሄደ ብቻዬን መሆኔ ተፅዕኖ አሳድሮብኛል ማለት እችላለሁ፡፡ ይህ ሁሉ ተፅዕኖ ኖሮ እንኳን በአህጉር ደረጃ አሸናፊ ሆኜ ማዕረግ ማግኘቴ ትልቅ ነገር ነው፡፡ እንዳልኩሽ ዓለም አቀፉን የማግኘት እቅድ ስለነበረኝ በአህጉር ደረጃ ሳሸንፍ ከፍቶኝ ነበር፡፡ ቆይቼ ሳስበው ትልቅ ነው፡፡ በዚህ ውድድር የአፍሪካ አምባሳደር ነኝ፡፡
በመጨረሻ የምትይው ካለ?
በዚህ አስቸጋሪ ሰዓት ከጐኔ የሆኑ ድርጅቶችና ግለሰቦች ነበሩ ውድድሩ ላይ እንድሳተፍ ድጋፍ ያደረጉልኝ፡፡ እነሱን በይፋ አለማመስገን ንፉግነት ስለሆነ ማመስገን እፈልጋለሁ፡፡ የኢትዮጵያ አየር መንገድ የጉዞዬን ትኬት ችሎኛል፤ አመሰግናለሁ፡፡ ኮካ ኮላና ካፒታል ሆቴል የሱዳኑን ወጪዬን ለመሸፈን ሞክረዋል፡፡ ቢሊያር ዲዛይነር አምሮብኝ እንድታይ ዘመናዊ የሀበሻ ቀሚስ ሰርታ የድርሻዋን አድርጋለች። እጅግ አመሰግናለሁ፡፡ ናሽናል ኮስቹም ያቀረብኩት፣ የአፋርን ባህላዊ ልብስ ነው፤ ምክንያቱም “Land of Origin”  (ምድረ ቀደምት) የሚለውን በደንብ ማስተዋወቅ ስለፈለግኩ፣ አፋርም ተያያዥነት ያላት ቦታ ስለሆነች፣ እግረመንገዴንም ልብሱን ብለብስ አንድም ይተዋወቃል ሁለትም በጣም ያምራል፡፡ በሌላም በኩል ሁሉም ሞዴሎች የሰሜኑን አለባበስ ስለሚያዘወትሩ፣ እኔ ለየት ለማድረግ ነበር የለበስኩት፡፡ ከዚህ በፊትም የሀረር ልጅ እንደ መሆኔ ውድድሮች ላይ የሐረርን ልብስ ለብሼ ወጥቼ አውቃለሁ፡፡ እናም የአፋር ክልላዊ መንግስት የአፋር ልብስ ልኮልኛል፡፡ ከልብ አመሰግናለሁ፡፡ እኛ በአህጉር ደረጃ ያሸነፍነው በቀጣይ ቱሪዝምን በተመለከተ አገራችንንና አህጉራችንን ለማስተዋወቅ፣ አብረን ልንሰራ የምንችልበትን መንገድ ለመፍጠር አዘጋጁ ቃል ገብቷል፡፡ ያን ጊዜ ለአገራችን ብዙ የምንሰራው ይኖረናል፡፡ በአጠቃላይ በውድድርና በውጤቴ በጣም ደስተኛ ነኝ፡፡ ለዚህ ስኬት በሀሳብ ደረጃ ሳይቀር ድጋፍ ያደረጉትን ግለሰቦችና ድርጅቶች በድጋሚ አመሰግናለሁ፡፡

Read 607 times