Saturday, 22 September 2018 14:41

ባልተዘራ ዘር፣ ፍሬ ፍለጋ!

Written by  ኤፍሬም እንዳለ
Rate this item
(6 votes)

  እንዴት ሰነበታችሁሳ!
አንዱ ሰው ምን አለ መሰላችሁ… “ለአዲሱ ዓመት እቅዴን ከጠየቃችሁኝ፣ እቅዴ ራሴን ማግኘት ነው” ብሏል፡፡ እኛን አይቶና መርምሮ የተናገረ ነው የሚመስለው፡፡ ራሳችንን ማግኘት የተሳነን፣ ቁጥራችን ቀላል አይደለምና፡፡ እንደውም ቁጥራችን እየጨመረ ሳይሄድ ቀርቷል ብላችሁ ነው! ራሳችንን እንድናገኝ ይርዳን!
ሴትዮዋ ሱፐርማርኬት ውስጥ እየተዘዋወረች እቃዎች ታያለች፡፡ አዲስ የአበባ መሸጫ ማስታወቂያ ታይና ወደዛው ትሄዳለች፡፡ ስትደርስም ባየችው ትደነግጣለች፡፡ አበባ የለ፣ የአበባ ማስቀመጫ የለ! …እዛ  የነበረው ‘አንድዬ’ ብቻ ነው፡፡
እናማ ’አንድዬ‘ ሴትዮዋን…“የምትፈልጊውን ማንኛውንም ነገር መጠየቅ ትችያለሽ” አላት፡፡
እሷም…“ደስተኛ መሆን እፈልጋለሁ፡፡ ሰላም፣ ገንዘብና ደግሞም ሰዎች ሀሳቤን እንዲረዱልኝ የሚያስችል አቅም እንዲኖረኝ እፈልጋለሁ፡፡ ይህም ነገር ለጓደኞቼ በሙሉ እንዲደረግላቸው እፈልጋለሁ” አለች።
‘አንድዬም’ ከጀርባው ከነበረ መደርደሪያ ጥቂት ማሰሮ ነገሮች ከፋፈተ፡፡ ከውስጥም የተለያዩ ዘሮች አፈስ አደረገና ለሴትዮዋ ሰጣት፡፡ እንዲህም አላት…“ዘሮቹ እኝሁልሽ፣ አሁን ጀምረሽ ዝሪያቸው። ምክንያቱም እዚህ የደረሱ ፍራፍሬዎችን አንሸጥም” አላት፡፡ የዘንድሮ ችግራችን ይኸው ነው… ባልዘራነው ዘር፣ ፍሬ ፍለጋ!
እኔ የምለው…እንግዲህ ጨዋታም አይደል…ይሄ በዛ ሰሞን ሲነጠፍ የከረመውና “ኢሮ! ኢሮ!” ሲባል የነበረው የእግረኞች መንገድ…ምንድነው ነገሩ? አንዳንድ ቦታዎች እየተነቃቀለ ነው እኮ! ነው ወይስ ማታ፣ ማታ “ሶኬቱን ንቅሉ” እንደሚባለው፣ ንጣፉንም እየነቀልን ቤታችን ወስደን፣ ጠዋት መልሰን እንድንተክለው ነው!
ስሙኝማ…እንግዲህ ጨዋታን ጨዋታ ያነሳው የለ…“መንገድ ላይ እንደ አሸዋ የመሳሰሉ የተለያዩ የግንባታ ቁሳቁስ የምትከምሩ ወገኖች ላይ እርምጃ ይወሰዳል” ሲባል መስማት የጀመርንበትን ጊዜ ማስታወሱ ራሱ አስቸጋሪ ነው፡፡ ግራ ገባና! አሁንም ይኸው የእግረኛ መንገዶችን የሚያነጥፉት  አሸዋውንና ኮብልስቶን ምናምኑን---እንደ ጉድ ይበትኑት የለ እንዴ! እኔ የምለው…እያንዳንዷ ጡብና ኮብልስቶን፣ እያንዳንዷ እፍኝ አሸዋ፣ ፍራንክ ወጥቶበት የለም እንዴ! ‘በጀት’ ምናምን የሚባል ነገር አለ አይደል እንዴ! እናማ… እንዲህ እንደፈለገው ነገርዬው ሁሉ ሲሰባበርና ሲበታተን…“በህዝብ ገንዘብማ እንዲህ አይነት ግዴለሽነት የለም!” የሚል ምነው ጠፋሳ!
የምር ግን…የመንገዶቹን ነገር ልብ ብላችሁልኝማል…ዛሬ ትንሽ ይሠራል፣ ይተዋል…ከቀናት በኋላ ትንሽ ይሠራል…ይቆማል፡፡ ምን እየተካሄደ  እንደሆነ የሚነግረን እንፈልጋለን፡፡ የተጀመሩ ነገሮች ወዲያው ለምን እንደማይጠናቀቁ፣ ተቋማት ወይም ግለሰቦች ሃላፊነታቸውን ባለመወጣታቸው ህብረተሰቡ ለምን እንደሚጉላላ የሚነግረን እንፈልጋለን፡፡ ስንትና ስንት ሚሊዮን ተመድቦላቸው እየተሠሩ ነው የተባሉት የእግረኛ መንገዶች፣ ሩብ ዓመት እንኳን ሳይቆዩ ለምን እንደሚወላልቁ፣ ብሎም በውሀ ልክ የተሠሩ ናቸው ብለን ሀሳባችንን ጥለን የምንረማመድባቸው ‘ለጥ ያለ ሜዳ’ የሚመስሉ የእግረኛ መረማመጃዎች ለምን ያደናቅፉን እንደጀመሩ የሚነግረን እንፈልጋለን፡፡
እኔ የምለው… በዛ ሰሞን የሰማናት ‘ባለቤት አልባ ህንጻዎች’ የምትለዋ ነገር ‘እንደተመቸችኝ’ ነገር!… አንድ የፌስቡክ ተጠቃሚ ‘ድሮ ባለቤት አልባ የሚባሉት’ ‘አሁን ባለቤት አልባ የሚባሉት’ በሚል አይነት የውሾችና የህንጻዎች ምስሎች ጎን ለጎን አስቀምጦ ያወጣው አሪፍ ማነጻጸሪያ አለ፡፡ እናማ… ይህን ሁሉ ሳናውቅ እንኳን እኮ ነው፣ በሌሎች በምናያቸው ነገሮች፣ “ባለቤት የሌላት ከተማ መሰለች…” “ባለቤት የሌላት አገር መሰለች…” ስንል የከረምነው፡፡ ስንት ገና ያልሰማናቸው ጉዶች ይኖሩ ይሆን! በአጠቃላይ ለምን ‘ባለቤት አልባ’ የሚያስመስሉ የግብር ይውጣ ነገሮች እንደበዙ የሚነግረን እንፈልጋለን፡፡ (ይኸዋ… ‘ባለቤት አልባ’ የምትለው ሀረግ…አለ አይደል… መዝገበ ቃላታችን ውስጥ በጆከርነት ገባችና አረፈችው!)
እኔ የምለው…የሆነ ነገር ትዝ አለኝማ…ነጋዴዎች ዋጋ ሲተምኑ…አለ አይደል…ኪሳችን ውስጥ ያለች ከአውቶብስ ትኬት ብዙም የማትወፍር ብር… እኛ ዘንድ በአደራ ያስቀመጧት የእነሱ ንብረት ትመስላቸዋለች እንዴ! የምር እኮ ግርም የሚል ነው። “ስንት አወጣሁበት፣ ስንት ብሸጠው ተገቢውን ትርፍ አገኛለሁ?” ብሎ ከማስላት ይልቅ ደስ እንዳለው… “እሱን ሸሚዝ ስምንት መቶ ብር በለው” የሚል ይመስላል። ሸሚዙ እኮ ቡቲኩ መደርደሪያ ላይ እስኪደርስ ድረስ ሁለት መቶ ሀምሳ ብር እንኳን አልፈጀም እኮ! “ጫማውን ሦስት ሺህ ብር…”  (ሺህ እንዲህ ‘የረከሰችበት’ ዘመን!) “በራስህ ገንዘብ ሂድና ሁለት ጫማና ሦስት ሱሪ ግዛ!” የሚል ሀረግ በሆነ ጥፋት የተነሳ የሚጣሉ ቅጣቶች ዝርዝሮች ውስጥ ቢገባ፣ ያንን ጥፋት የሚያጠፉ ሰዎች፤ በ85% ገደማ ባይቀንስ ነው!
እናማ…ለምን ይዋሻል፣ አሁን እኮ በዓል ብቅ ሲል ተበድረንም፣ ተለቅተንም ለሙክት ሸመታ የምናወጣው ፍራንክ…አለ አይደል… ትንሽዬ መኪና ለመግዛት ቀብድ የመክፈል ያህል ሊሆን ምንም አልቀረው፡፡
‘እንጀራ ሲያርፍባት’ ቡን ለማለት ምንም የማይቀራት…ለአንዲት ፈሰሴ ሹሮ፣ ዘጠና ምናምን ብር ዋጋ ላይ ቫት ተጨምሮ… የአሳላፊዎቹ ‘ቲፕ’ ተጨምሮ …“ከሰው ላለማነስ” የሚሉት ነገር ተጨምሮ፣ ከሁለት ‘ሳይንቲስት’ በላይ!
የምር…ዘንድሮ እኮ ከውጪ የመጣ ዳያስፖራም ይሁን አገር ውስጥ በራስ ተነሳሽነት ዳያስፖራ የሆነውን… “እስቲ አንድ ጊዜ እንኳን ግልምጫውን እንዲተወኝ ምሳ ልጋብዘው!” ማለት አስቸጋሪ ነው። አሀ… አንዳንድ ቦታ እኮ የሚጠየቀው ፍራንክ… “ምሳ ከምገዛለት ለምን የጤፍ እርሻ በሊዝ ገዝቼ ስጦታ አልሰጠውም!” ሊያስብል ምንም አይቀር።  (“ቦምቦሊኖ እንኳን እንዲህ ስትወደድ!” የምትሉ ወዳጆች…ቦምቦሊኖ ዘይት ስለሚበዛው ለአንጀታችሁ ጥሩ አይደለም፡፡ (ቂ…ቂ…ቂ…) የምር እኮ የሆነ ነገር፣ አይደለም በህልም… አምስተኛ ብርሌያችን ላይ ያለ ስክሪን ማየት የምንጀምረው ‘ፊልም’ ላይ እንኳን ውል እንዳይልብን አሪፉ መንገድ ምን መሰላችሁ …ማጣጣል! በቃ፣ ያንን ነገር አንስቶ ማፍረጥ! ከእነ ምናምኗ ከሁለት መቶ እየዘለለች ያለችውን…“ምንም አይነት የቅመም ዘር የለውም እኮ! ዝም ብለው አተሩን ወቅጠው ነው እኮ ምጥን ሹሮ፣ ምናምን ሹሮ የሚሉን!” ማለቱ ፓራሲታሞልን የምታስንቅ ‘ፔይንኪለር’ ነች፡፡
የምር፣ እንግዲህ ጨዋታም አይደል…ይቺ ማጣጣል፣ ጥሬ ስጋ በሌለበት ምን የመሰለች የኮሶ መድሀኒት መሰለቻችሁ፡፡ “ሁለት ሺህ ብር ስላሉት ጥራት ያለው ጫማ መሰለህ! ሁለት ወር ሳይሞላው የፈረሰውን የውቤ በረሀ ሰፈር ነው የሚመስልልህ!
“ጥሬ ስጋ ማለት እኮ በገዛ እጅ በሽታ መግዛት ነው። ህዝቤ ሪህ በሪህ የሆነው፣ በጥሬ ስጋ አይደል እንዴ!”
“እሷ እምቢ አለችህ አላለችህ ምን ታደርግልሀለች! ቆንጆ ብትሆንም ይሄኔ ቤት ውስጥ  ጭራዋን ሚኒባስ ታክሲ ላይ የተመነተፈች ሰይጣን ልትሆን ትችላለች።” ምን እናድርግ…ዘንድሮ እንደፈለግናት የማናገኛትን ‘ደስታ’ የሚሏትን ነገር ቢያንስ በ‘አርቲፊሻል’ መልኳ ጠጋ እንድትለን ዘዴ እንፈልግ እንጂ!
የደስታን ነገር ካነሳን አይቀር ይቺን ስሙኝማ…በአንድ ወቅት ሀምሳ ሰዎች አንድ ሴሚናር ላይ እየተሳተፉ ነበር፡፡ ንግግር የሚያደርግላቸው ሰው ድንገትም ንግግሩን አቋረጠና… “የቡድን ልምምድ እናድርግ” አላቸው፡፡ ለእያንዳንዱ ተሳታፊም አንድ፣ አንድ ፊኛ ሰጠ፡፡ እያንዳንዳቸውም ማርከር በመጠቀም፣ ፊኛቸው ላይ ስማቸውን እንዲጽፉ አደረገ፡፡ ከዛም ሁሉም ፊኛዎች ተሰበሰቡና አንድ ክፍል ውስጥ ተቀመጡ፡፡
ቀጥሎም ተሳታፊዎቹ እዛች ክፍል እንዲገቡ ተደረገና፤ “በሉ የየራሳችሁን ፊኛ ምረጡ” ተባሉ፡፡ ሁሉም እየተገፋፋ፣ እየተገጫጨ፣ እየተተረማመሰ፣ ስሙ የተጻፈበትን ፊኛ ፍለጋ ጀመረ፡፡
ከአምስት ደቂቃ በኋላ አንዳቸውም የራሳቸውን ፊኛ ማግኘት አልቻሉም፡፡ ከዛም እያንዳንዳቸው የፈለጋቸውን ፊኛ እያነሱ፣ ስሙ ለተጻፈበት ሰው እንዲሰጡ ተነገራቸው፡፡ በጥቂት ደቂቃዎች ውስጥ ሁሉም ሰው ስሙ የተጻፈበትን ፊኛ አገኘ፡፡
ንግግር አድራጊውም እንዲህ አላቸው፤…“በህይወታችን ውስጥ እየሆነ ያለው እንዲሁ ነው። ሁሉም ሰው ደስታን ፍለጋ ይባዝናል፣ የት እንደሚያገኘው ግን አያውቅም፡፡ የእያንዳንዳችን ደስታ ያለው በሌሎች ደስታ ውስጥ ነው፡፡ የህይወትም ዓላማ ይኸው ነው…ደስታን ፍለጋ!”
እኛ ዘንድ…ዘመኑ ሆነና የሌላው ሰው ስም የተጻፈበት ፊኛ ስናገኝ፣ ለሰውየው ከማስተላለፍ ይልቅ በእኛ ላይ ጨምረን “ሁለት አለኝ፣ ሦስት አለኝ” አይነት ነገር ማለት ነው የምንፈልገው፡፡ ከዚህ አይነት አስተሳሰብ የምንወጣበትን ጊዜ ያቅርብልንማ! ለሁሉም… «ባልዘራነው ዘር ፍሬ ፍለጋ» ከመባዘን ይጠብቀንማ!
ደህና ሰንብቱልኝማ!!

Read 6051 times