Print this page
Saturday, 22 September 2018 14:45

መከራ የሚያጸናው ኢትዮጵያዊነት

Written by 
Rate this item
(0 votes)

  • ድርጊቱ አሳፋሪና የኢትዮጵያውያን የውርደት ታሪክ ነው
       - ጠ/ሚ ዐቢይ
     • በተፈጸመው ጥቃት እንደ ኢትዮጵያዊነቴ አፍሬአለሁ
       - ፕ/ር ብርሃኑ ነጋ
     • ከኢትዮጵያዊነት ባህል የዘለለና ከሰው ልጅ ሞራል ያፈነገጠ ነው
        - ቴዲ አፍሮ
     • ኢትዮጵያውያን የተፈተንበት ነው፤አይዟችሁ እናልፈዋለን
       - አርቲስት ታማኝ
 

     በቡራዩ በዜጐች ላይ ለደረሰው አሠቃቂ ግድያ፣ ዘረፋና መፈናቀል መንግሥት የማያዳግም ሕጋዊ ርምጃ እንዲወስድ የፖለቲካ መሪዎች፣ዝነኛ አርቲስቶች፣ አክቲቪስቶችና ታዋቂ ግለሰቦች የጠየቁ ሲሆን፣ በሺዎች የሚቆጠሩ የጥቃት ተጎጂዎችንና ተፈናቃዮችን ሲጎበኙና ሲያጽናኑ ሰንብተዋል፡፡
የአዲስ አበባ ነዋሪዎች በተለይም ወጣቶች ከተፈናቃዮቹ ሳይለዩ ላሳዩት ኢትዮጵያዊ ፍቅርና ሰብአዊነት ከተጎጂዎቹም ሆነ ከጎብኚዎች ከፍተኛ ምስጋና ጎርፎላቸዋል፡፡
ወትሮም ኢትዮጵያዊነት ሲመቱት እንደሚጠብቀው ምስማር፣ በመከራ የሚጸና ነው፡፡ በቡራዩና አካባቢው የተፈጸመው ግፍ አሳዛኝ ቢሆንም የታየው የወገናዊነትና የብርታት መንፈስ ኢትዮጵያዊነት በመከራ የሚጸና መሆኑን አስመስክሯል፡፡ ተጎጂዎቹን በተጠለሉበት ሥፍራዎች ተገኝተው የጎበኙት የፖለቲካ መሪዎችና የጥበብ ባለሙያዎች የተንጸባረቀው ስሜትና መልዕክትም ይኸው ነው፡፡ ኅዙነ ልብ ቁፅረ ገጽ ሆነው ተጎጂዎችን በመድሃኔአለም ት/ቤት የጎበኙት ጠ/ሚኒስትር ዐቢይ አህመድ፤ “ድርጊቱ አሳፋሪና የኢትዮጵያውያን የውርደት ታሪክ ነው፤” ብለዋል፡፡ መንግሥታቸው ተፈናቃዮችን ለማቋቋም የሚቻለውን ሁሉ እንደሚያደርግ የጠቆሙት ጠ/ሚኒስትሩ፤ ከእንግዲህ ጉልበተኞችን እንደማይታገሥም አስጠንቅቀዋል፡፡
በአካባቢው ለተፈጠረው ግጭትና ጥቃት መነሻ ምክንያቱ የአንዲት የ6 ዓመት ሕፃን በአሠቃቂ ሁኔታ ተገድላ መገኘት መሆኑን የጠቆሙት የኦሮሚያ ክልል ርዕሰ መስተዳድር አቶ ለማ መገርሳ፤ ይህን አጋጣሚ ለውጡን ለመቀልበስ የሚፈልጉ ኃይሎች ተጠቅመውበታል፤ ብለዋል። የክልሉ መንግሥት ከእንግዲህ ለእንዲህ ያለው ብሔር ተኮር ጥቃት ትዕግሥት እንደሌለው የጠቆሙት ፕሬዚዳንት ለማ፤ ድርጊቱም የኦሮሞን ሕዝብ አይወክልም፤ ብለዋል፡፡
ተጐጂዎችን በርካታ የፖለቲካ መሪዎችና ታዋቂ ግለሰቦች በተጠለሉበት ተገኝተው የጐበኙ ሲሆን፤ ከእነዚህ መካከልም የአርበኞች ግንቦት 7 አመራሮች ፕ/ር ብርሃኑ ነጋ እና አንዳርጋቸው ጽጌ ይገኙበታል፡፡ ድርጊቱ ዲሞክራሲን ያለ አግባብ መጠቀም በመሆኑ፣በኢትዮጵያዊነቴ አፍሬአለሁ፤ ብለዋል፡፡ በአጥፊዎች ላይም ህጋዊ እርምጃ እንዲወሰድ አሳስበው፤ለዚህም መንግስት የሚከፍለው መስዋዕት ካለ ለመክፈል ዝግጁ እንደሆኑ ተናግረዋል፡፡
አርቲስትና አክቲቪስት ታማኝ በየነም በተጎጂዎቹ መጠለያ ተገኝቶ እያነባ ሃዘኑን ከገለጸ በኋላ “አሁን ኢትዮጵያውያን የተፈተንበት ወቅት ላይ ነን፤ አይዟችሁ እናልፈዋለን” በማለት ተጎጂዎቹን ያጽናና ሲሆን ኢትዮጵያውያን Go Fund me በተሰኘው የማኅበራዊ ድረ ገፅ የእርዳታ ማሰባሰቢያ አማካኝነት ወገኖቻቸውን እንዲያቋቁሙ በተማጸነው መሰረት፣በ24 ሰዓት ውስጥ ከ2 መቶ ሺህ ዶላር በላይ (9 ሚ. ብር ገደማ) ማሰባሰብ መቻሉ ታውቋል፡፡  
አርቲስት ቴዎድሮስ ካሣሁን (ቴዲ አፍሮ) በበኩሉ፤በተጎጂዎች ላይ በደረሰው ጥቃት ማዘኑን ገልጾ፤ድርጊቱ ከኢትዮጵያዊነት ባህል የዘለለና ከሰው ልጅ የሞራል ህግም ያፈነገጠ ነው፤ከዚህ በኋላ መደገም የለሌበት” ብሏል፡፡ ከባለቤቱና ጓደኞቹ ጋር ተጎጂዎቹን የጎበኘው አርቲስቱ፤ለጥቃቱ ተጎጂዎች ማቋቋምያ ይሆን ዘንድ የ1 ሚሊዮን ብር ድጋፍ ያደረገ ሲሆን ለዚህ ሳምንት ተላልፎ የነበረውን የሙዚቃ ኮንሰርቱንም እንደሰረዘ አስታውቋል - “ወገኖቼ ባዘኑበት ሁኔታ ኮንሰርት የማቀርብበት አንጀት የለኝም” በማለት፡፡
ፖሊስ በበኩሉ፤ እስካሁን ከጥቃቱ ጋር በተገናኘ ከ500 በላይ ተጠርጣሪዎችን በቁጥጥር ስር ማዋሉን ገልጾ፤ ከዚህ በኋላ ለሚፈጠር ተመሳሳይ ችግር ምህረት የለሽ እርምጃ እንደሚወስድ አስታውቋል፡፡

Read 1817 times
Administrator

Latest from Administrator