Saturday, 22 September 2018 14:45

የኢትዮ-ኤርትራን ስምምነት ተከትሎ የንግድ እንቅስቃሴ ተጠናክሯል

Written by  አለማየሁ አንበሴ
Rate this item
(2 votes)

 - ሲሚንቶ ወደ ኤርትራ፤ አልባሳት ወደ ኢትዮጵያ …
               - ኤርትራ በድንበር አካባቢ የሰዓት እላፊ ገደብ ጥላለች


    በኢትዮጵያ እና በኤርትራ መካከል ባለፈው ሳምንት ሚኖረውን ግንኙነት የሚደነግግ ባለ 7 አንቀጽ ስምምነት፣ የሁለቱ ሃገራት መሪዎች የተፈራረሙ ሲሆን፤ በሳዑዲ አረቢያ ጂዳ የተደረገውን ስምምነት ተከትሎ፣ በሁለቱ ሃገራት ድንበር ከወዲሁ የንግድ እንቅስቃሴ መጧጧፉ ታውቋል፡፡
ፖለቲካዊ፣ ኢኮኖሚያዊ፣ ማኅበራዊ፣ የፀጥታና ደህንነት ጉዳዮችን ታሳቢ ያደረገ ነው የተባለው ስምምነት፤ በሁለቱ ሃገራት መካከል የጋራ የኢኮኖሚ ትስስር እንዲፈጠር የሚያግዝ እንደሚሆን ተገልጿል፡፡
ሁለቱ ሃገራት በጋራ የኢኮኖሚ ዞን ለመመስረት፣ የንግድ እንቅስቃሴውም ነፃ እንዲሆን የተስማሙ ሲሆን ስምምነቱን ተከትሎም፣ በድንበር አካባቢ ከሰሞኑ የንግድ እንቅስቃሴ ተጠናክሮ መታየቱን ኤርትሪያን ፕሬስ ዘግቧል፡፡
የኢትዮጵያ ሲሚንቶ የኤርትራን ገበያ ማጥለቅለቁን፣ በአንፃሩ የኤርትራ የአልባሳት ምርት ደግሞ ወደ ኢትዮጵያ እየገባ መሆኑን ዘገባው አመልክቷል፡፡
ይህ በዚህ እንዳለ፣ የኤርትራ መንግስት፤ ለደህንነት ሲል ድንበር ማቋረጥ የሚቻለው ከጠዋቱ 12 ሠዓት እስከ ምሽቱ 12 ሠዓት ብቻ እንዲሆን የሰዓት እላፊ ገደብ መደንገጉን ኤርትሪያን ፕሬስ ዘግቧል፡፡
የሁለቱ ሃገራትን ነፃነት፣ ሉአላዊነትና የድንበር ክልሎችን ባከበረ መልኩ የተፈረመ ነው የተባለው ባለ ሰባት ነጥቡ ስምምነት፣ የመጀመሪያው አንቀፅ፤ በሁለቱ ሃገራት መካከል የነበረው ጦርነት በይፋ መቆሙንና አዲሱ የሰላም፣ የወዳጅነትና የትብብር ዘመን፤ መጀመሩን ይገልፃል፡፡
ሁለተኛው ስምምነት፤ ሁለቱ ሃገራት በፖለቲካ፣ በፀጥታና ደህንነት፣ በመከላከያ፤ በኢኮኖሚ፣ በንግድና ኢንቨሰትመንት፣ በባህልና በማኅበራዊ መስኮች በትብብር እንደሚሰሩ ያትታል፡፡
ሁለቱ ሃገራት በጋራ የልማት እንቅስቃሴ፣ የተለያዩ ኢንቨስትመንቶችን በጋራ ሊያከናውኑ እንደሚችሉና የጋራ የኢኮኖሚ ዞን ማቋቋም የሚለው ደግሞ በሦስተኛው ስምምነት ላይ ተቀምጧል፡፡
ሁለቱ ሃገራት የተባበሩት መንግስታት የድንበር ኮሚሽን ውሣኔን ለመተግበር መስማማታቸውም በአራተኛው ስምምነት ላይ የተመለከተ ሲሆን ሁለቱ ሃገራት በአካባቢያዊ ሠላምና ደህንነት ላይ በትብብር ይሰራሉ የሚለው ደግሞ በአምስተኛው ስምምነት ላይ ሰፍሯል፡፡ ሁለቱ ሃገራት በጋራ ሽብርተኝነትን፣ ሕገ ወጥ የሰዎች ዝውውርን፣ የጦር መሣሪያና የአደንዛዥ ዕፅ ዝውውርን እንደሚከላከሉ ስድስተኛው የስምምነቱ አንቀፅ የሚደነግግ ሲሆን ሰባተኛው አንቀፅ፤ ሁለቱ ሃገራት ግንኙነታቸውን የሚከታተልና የሚያበለፅግ ከፍተኛ የጋራ ኮሚቴ ያቋቁማሉ ይላል፡፡
ስምምነቱ በአማርኛ፣ ትግርኛ፣ አረብኛና እንግሊዝኛ ቋንቋ የተዘጋጀ ሲሆን ችግር ቢፈጠር የእንግሊዘኛው ቅጂ የመጨረሻውን ትርጉም ይሰጣል ተብሏል፡፡
ለበሳውዲ ዓረቢያ ጅዳ የተባበሩት መንግስታት ዋና ፀሐፊ በተገኙበት የተፈረመው ስምምነት፤ በሁለቱ ሃገራት መካከል ዘላቂ ሠላማዊ ግንኙነትን ይፈጥራል ተብሎ ታምኖበታል፡፡ በሌላ በኩል፤ ኢትዮጵያና ኤርትራ ያለ ሦስተኛ ወገን ለ20 ዓመታት ለዘለቀው ግጭት በአጭር ጊዜ ውስጥ ላሰፈኑት ሰላምና እርቅ የሳዑዲው ንጉስ፤ ለጠ/ሚኒስትር ዐቢይ አህመድና ለፕሬዚዳንት ኢሳያስ አፈወርቂ፣ የአገሪቱን ታላቅ ኒሻን ሸልመዋቸዋል፡፡ የተባበሩት አረብ ኤምሬትስ ንጉስም በቅርቡ ተመሳሳይ ኒሻን ለመሪዎቹ መሸለማቸው አይዘነጋም፡፡

Read 7762 times