Saturday, 22 September 2018 14:46

ተፎካካሪ ፓርቲዎች፤ የህግ የበላይነት ለማስፈን እንሰራለን አሉ

Written by  አለማየሁ አንበሴ
Rate this item
(0 votes)

• መንግስት በውስጡ ያሉ የለውጥ አደናቃፊዎችን መንጥሮ ማውጣት አለበት
 • ህዝብን ከህዝብ የማጋጨት ተግባር በትዕግስት ሊታይ አይገባውም
 • ለውጡ በሁሉም ኢትዮጵያዊ ትግል የመጣ ስለሆነ አይቀለበስም
 • ችግሮችን በዘላቂነት ለመፍታት ፖለቲካዊ ውይይቶች ያስፈልጋሉ
 • ሀገሪቱ የገባችበትን አጣብቂኝ እንቀንሳለን ብለን ነው የመጣነው

    ባለፈው ቅዳሜ በቡራዩ በተደራጁ ሃይሎች በዜጎች ላይ በተሰነዘረው  ብሔር ተኮር ጥቃት 58 ሰዎች መሞታቸውን አምነስቲ ኢንተርናሽናል ባወጣው ሪፖርት ያስታወቀ ሲሆን በሺዎች የሚቆጠሩም ከመኖርያቸው ተፈናቅለው በተለያዩ መጠለያዎች ውስጥ ይገኛሉ፡፡ በሳምንቱ አጋማሽ ላይ ተፈናቃዮችን በተጠለሉበት የመድኃኒያለም ት/ቤት ተገኝተው ያጽናኑት ጠ/ሚኒስትር ዐቢይ አህመድ፣ ጥቃቱን፣ “አሳፋሪና የኢትዮጵያ የውርደት ታሪክ” ሲሉ ገልጸውታል - በሃዘን ተሞልተው፡፡ የአርበኞች ግንቦት 7 ሊቀመንበር ፕሮፌሰር ብርሃኑ ነጋ በበኩላቸው፤ “ወገኖቻችን በገዛ አገራቸው እንዲህ ያለ ግፍ ሲፈጸምባቸው ያሳዝናል--እንደ ኢትዮጵያዊነቴ አፍሬአለሁ--” ብለዋል፡፡ “-- መንግስት የዜጎችን በፈለጉበት በነጻነት የመኖር መብት ለማስከበርና የህግ የበላይነትን ለማረጋገጥ በሚያደርገው ጥረት የሚከፍለው መስዋዕትነት ካለ፣ እኛም ለመክፈል ዝግጁ ነን” ያሉት ደግሞ የድርጅቱ ዋና ጸሃፊ አቶ አንዳርጋቸው ጽጌ ናቸው፡፡
በቅርቡ ወደ ሃገር ቤት የገቡ አራት የፖለቲካ ፓርቲዎች፤ መሰል ብሄር ተኮር ጥቃቶች እንዳይከሰቱ ምን ማድረግ እንደሚገባ፣ ከተፎካካሪ ፓርቲዎች ምን እንደሚጠበቅ፣ የተጀመረው ለውጥ ሳይቀለበስ ለማስቀጠል የሚጠይቀውን መስዋዕትነት ወዘተ-- በተመለከተ ለአዲስ አድማስ ሃሳባቸውን ሰንዝረዋል፡፡ ጋዜጠኛ አለማየሁ አንበሴ፣ የአመራሮቹን አስተያየቶች እንደሚከተለው አጠናቅሮታል፡፡


              “መንግስትና ተቃዋሚዎች ተቀራርበው መስራት አለባቸው”
                 አቶ ቶሌራ አዳባ (የኦሮሞ ነፃነት ግንባር አመራር)

    በዚህ የለውጥ ሂደት ውስጥ የተለያዩ ግጭቶች ተፈጥረዋል፡፡ ለምሳሌ በሶማሌና በኦሮሞ መካከል ከዚህ ቀደም ያልነበረ ግጭት ተከስቷል፡፡ እነዚህ ህዝቦች በመካከላቸው ችግር የሌለ፣ አልፎ አልፎ  አርብቶ አደሮቻቸው በግጦሽ ሲጋጩ እንኳን በባህላዊ እርቅ ችግራቸውን በቀላሉ የሚፈቱ ነበሩ፡፡ ፖለቲካዊ ይዘት ያልነበራቸው ግጭቶች ነበሩ የሚከሰቱት፡፡ አሁን ግን ሌላ ኃይል ከበስተጀርባ መኖሩን በሚያመለክት ሁኔታ ነው ግጭቱ ሲቀጣጠል የሚታየው፡፡ ይህ ኃይል በተለያዩ አካባቢዎች ተመሳሳይ ጥፋት ለመፈፀም ጥረት ሲያደርግ ታዝበናል፡፡ አሁን በሃገሪቱ ላይ እየመጣ ያለው ለውጥ የማይዋጥላቸው፣ መንግስትም ማስተዳደሩን  አልቻለም ለማለት የሚዳዳቸው ፀረ-ለውጥ ኃይሎች ናቸው - ይሄን ችግር የሚፈጥሩት፡፡
ለዚህ ችግር ዘላቂ መፍትሄው ዲሞክራሲን ማጐልበት ነው፡፡ በህዝቦች መካከል የሚፈጠርን ችግር በትዕግስት ማለፍ አያስፈልግም፡፡ ህዝብን ከህዝብ የማጋጨት ተግባር በትዕግስት ሊታይ የሚገባው አይደለም፡፡ አሁን እየታዩ ያሉ ችግሮችን መንግስት ብቻውን ሊቀርፈው አይችልም፡፡ ተፎካካሪ ፓርቲዎች የድርሻቸውን መወጣት አለባቸው። መንግስት በውስጡ ያሉ የለውጥ አደናቃፊዎችን መንጥሮ ማውጣት አለበት፡፡ ችግሮች ከመፈጠራቸው በፊት ነው መንግስት መስራት ያለበት፡፡ ተፎካካሪ ፓርቲዎች፤ ደጋፊዎቻቸው ለሠላም፣ ለመከባበር፣ ለዴሞክራሲ እንዲሰሩ ማስተማር አለባቸው፡፡ መንግስትና ተፎካካሪ ፓርቲዎች ተደጋግፈው ከሰሩ ለውጡም ቀጣይነት ይኖረዋል፡፡ አሁን የሚታዩ ችግሮችም እየተፈቱ ይሄዳሉ፡፡


-----------


            “አጥፊዎች ያለ ማቅማማት በሕግ መጠየቅ አለባቸው”
               አቶ ግደይ ዘርአፅዮን (የትግራይ ዴሞክራሲያዊ ትብብር አመራር)

    አሁን በተከፈተው የፖለቲካ ምህዳር ብዙ ኃይሎች ወደ ሃገር ውስጥ እየገቡ ነው፡፡ የተለያዩ አቋሞች በተለያየ አግባብ እየተገለፁ ነው - በሚዲያም በሰልፍም። በእነዚህ መድረኮች ደግሞ ባለፉት ዓመታት ከነበረው የብሔር ሥርዓት ጋር የተያያዙ  ችግሮች ሲንፀባረቁ እንመለከታለን፡፡ ሥርዓቱ በብሔር ላይ መሠረት ያደረገ ስለነበር፣ በብሔር የመጠላላት፣ የመጠላለፍ ሁኔታዎች እንደነበሩ አስተውለናል፡፡ ያለን የዴሞክራሲ ልምድ ደካማ ከመሆኑ አንፃርም፤ ብዙ ችግሮች እያየን ነው፡፡ አፋኝ ከነበረ ሥርዓት ወደ ነጻነት ስንሸጋገር እንዲህ ያለ ችግር ማጋጠሙ አይቀርም፡፡ ያልደፈረሰ እንደማይጠራው ሁሉ እንዲህ ያለው ለውጥም መጀመሪያ ደፍርሶ ነው የሚጠራው። በዚህ ሂደት ውስጥ ፖለቲከኞች፣ መንግስትና ምሁራን በኃላፊነት ነው መንቀሳቀስ ያለባቸው፡፡ አሁን የተፈጠረውን ሁኔታ የማይወዱ ኃይሎች፣ ነገሩን ለማደፍረስ ጥረት እንደሚያደርጉ አስበን መታገል አለብን፡፡ እንዲህ ያሉ መደፍረሶች የሰሞኑን ዓይነት የከፋ ጉዳት እንዳያደርሱ፣ የሕግ የበላይነትን የማስከበር ሥራ መስራት ያስፈልጋል፡፡ በፊት መንግስት አፈነን ነበር ጩኸቱ፤ አሁን ደግሞ እባክህ ሕግ አስከብር እያልን ነው፡፡ ስለዚህ መንግስት ሚዛናዊ ሆኖ ሕግ ማስከበር አለበት፡፡ አጥፊዎች ያለ ማቅማማት በሕግ መጠየቅ አለባቸው፡፡ ነገሮች ሳይስፋፉ በአጭሩ ነው መቀጨት ያለባቸው፡፡
በለውጥ ሂደት ላይ ስጋትና ተስፋ ይኖራል። ትልቁ ነገር ስጋቱን እየቀነሱ ተስፋውን እያጐለበቱ መሄድ ነው፡፡ አሁን ያሉት የለውጥ ኃይሎች ወይም ፖለቲከኞች የበሰሉ ናቸው ብዬ አምናለሁ፡፡ ነገሮችን የማረጋጋት አቅም አላቸው፡፡ ስለዚህ ከእነሱ ብዙ ስራ ይጠበቃል። የተረጋጋና መስመር የያዘ ሂደት ለመፍጠር ከተፈለገ፣ መንግስት ከተቃዋሚዎች ጋር በመነጋገር፣ የሃገሪቱን አቅጣጫ የማስቀመጥ ስራ መሠራት አለበት። ይሄ ጊዜ ሊሰጠው የሚገባ ጉዳይ አይደለም፡፡


------------


           “የሕግ የበላይነት የሠፈነባት ሃገር መፍጠር አለብን”
              አቶ ኤፍሬም ማዴቦ (የአርበኞች ግንቦት 7 አመራር)

     እነዚህ በሃገሪቱ የሚፈጠሩ የሰው ህይወት የሚቀጥፉና ንብረት የሚያወድሙ ጥቃቶችና ግጭቶች ለ27 ዓመታት የዘለቁ ችግሮች ውጤት ናቸው። ባለፉት ዓመታት ብዙ አጥፊ ነገሮች ተሰርተዋል፡፡ ከሰሞኑ በአዲስ አበባና አካባቢው የተፈጠረው ብቻ ሳይሆን፤ በአጠቃላይ በተለያዩ ቦታዎች የተከሰቱት ችግሮች ተቋማዊ ናቸው፡፡ ተቋማዊ ችግር ስንል ሃገሪቱ የተሰራችበት ሁኔታ ነው፡፡ አሁን የምናያቸው የዘር ግጭቶች በደርግና በአፄ ኃይለሥላሴ ጊዜ አልነበሩም፡፡ እነዚህ ሁለት ሥርዓቶች ጥሩ ሥርአቶች ናቸው ማለቴ ሳይሆን፤ ያኔ ሰው እርስ በርሱ ሲጨራረስ፣ ሲጨካከን አናይም ነበር፡፡
 የተወለድኩት ሐዋሳ ነው፡፡ እኔ በእድሜዬ ሐዋሳን ለቀቄ እስክወጣ ድረስ አንድም ቀን ወላይታና ሲዳማ ተጣሉ ሲባል ሰምቼ አላውቅም፡፡ ኦሮሞና ሶማሌ ተጋጩ ሲባል ሰምቼ አላውቅም፡፡ በአንድ ሃገር ውስጥ ሁለት ክልሎች መጣላታቸው አስገራሚ ነው፡፡ ይሄን የፈጠረው የዘር ፌዴራሊዝም ነው የሚል እምነት አለን፡፡ በሃይማኖትና በብሔር መደራጀት በተፈጥሮው የሰው ልጅን በሙሉ አያቀራርብም፡፡ ለዚህ ነው ከክልሌ ውጣልኝ እየተባለ ህዝብ መከራውን የሚበላው። ከዚህ ችግር ውሰጥ ለመውጣት ይሄ አደረጃጀት መስተካከል ያስፈልገዋል፡፡ ሁሉም አካላት በጠረጴዛ ዙሪያ ቁጭ ብለው፣ ባለፉት 27 ዓመታት የመጣንበትን መንገድ ገምግመው፣ እንዴት ከዚህ ችግር እንውጣ ብለው መምከር አለባቸው፡፡ አንድ ላይ እንድንሆን የሚረዳን ምን አይነት የፖለቲካ ተቋም ብንገነባ ነው? ምን አይነት ተቋማት ብንገነባ ነው ከዚህ አይነት ችግር የምንላቀቀው? ብለን ውይይት መጀመር አለብን፡፡ እኔ አዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ ስማር አብረውኝ የነበሩ የዶርም ተጋሪዎችን ብሔር አላውቅም ነበር፤ ለማወቅም ጥረት አላደርግም ነበር፡፡ አሁን ግን ገና የገቡ ዕለት ነው፣ ብሔር ከብሔር ተለያይተው የሚተዋወቁት፡፡
በሀገራችን የነገሰው የቡድን ማንነትና ፖለቲካ ነው። ይሄ ሃገራችንን አበላሽቷል፡፡ ይሄን ችግር ለመፍታት በፅኑ መነጋገር አለብን ማለት ነው። መንግስት ጊዜያዊ መረጋጋት ብቻ ሳይሆን ዘላቂ የማረጋጊያ መንገዱንም መተለም አለበት፡፡ ኢትዮጵያ አሁን ካለችበት የፖለቲካ ሥርዓት ወጥታ እንዴት ወደ ሕግ የበላይነት የሰፈነባት ሃገር እናሸጋግራት የሚለው ሁሉም ሊተጋበት የሚገባ ጉዳይ ነው። ምሁራኖች፣ ፖለቲከኞች፣ የሃገር ሽማግሌዎች፣ የሃይማኖት አባቶች የወደፊቷ ኢትዮጵያ ምን ትምሰል የሚለውን ሊሰሩበት ይገባል፡፡ መንግስት ብቻውን ምንም ሊሰራ አይችልም፡፡ እንደ ሃገር የምንድንበትን አቅጣጫ የምናገኘው ከንግግርና ውይይት ነው፡፡ እኛ ከውጪ ሃገር ወደዚህ ስንመጣ፣ ሃገሪቱ አጣብቂኝ ውስጥ መሆኗን አምነን፣ አጣብቂኙን እንቀንሳለን ብለን ነው የመጣነው፡፡ አሁንም ከመንግስት ጋርም ሆነን ማድረግ የምንፈልገው፣ ለውጡ እንዳይቀለበስ ማገዝ ነው፡፡ አንድ ላይ የሚያኖረንን ሥርዓት፣ አንድ ላይ እየተመካከርን ከሰራን፣ ሃገራዊ መግባባት መፍጠር እንችላለን፡፡ ይሄን ለማድረግ ከትናንትና ዛሬ ይሻላል የሚል እምነት አለን፡፡


-----------------


               “ሁሉም ኢትዮጵያዊ በነፃነት የሚኖርባትን ሃገር ለመገንባት እንፈልጋለን
                  አቶ አሚን ጁንዲ (የኦሮሞ ነፃነት ግንባር - ለአንድነት አመራር)

    እኛ አሁን በሃገሪቱ እየተካሄደ ያለውን ለውጥ ከልብ እንደግፋለን፡፡ መንግስት ይሄን የፖለቲካ መድረክ ለማስፋት ያደረገውን ጥረት እናከብራለን፡፡ በውጪ ለነበሩ እኛን መሰል የፖለቲካ ድርጅቶች ጥሪ ማድረጉ፤ ታስረው የነበሩ ፖለቲከኞችና ጋዜጠኞችን መፍታቱ፣ በከፍተኛ ሁኔታ የምንደግፈው ነው፡፡ በዚህ የለውጥ ሂደት መሀል በአንድ በኩል መንግስት የመደመርን ፖለቲካ እየሰራ፣በሌላ በኩል ደግሞ ሁሉም በሕግ የበላይነት እንዲገዛና ጥፋት አጥፊዎች መቀነስ እንዳለም እንዲያውቁ ማስተማሩ አስፈላጊ ነው፡፡ ሕግ ባለበት ሃገር ውስጥ ነው ዴሞክራሲ መተግበር የሚችለው። ስለዚህ አሁን የሚታዩትን ችግሮች በዘላቂነት ለመፍታት ፖለቲካዊ ውይይቶች ያስፈልጋሉ፡፡ ይሄን ውይይት ለማድረግ የተረጋጋ ሠላም አስፈላጊ በመሆኑ፤ መንግስት የሕግ ማስከበር ኃላፊነቱን መወጣት አለበት። መንግስት ይሄን ኃላፊነቱን እንዲወጣ በእኛ በኩል ድጋፍና ግፊት እናደርጋለን፡፡
ደጋፊዎቻችንና አባሎቻችን ደግሞ ከሁሉም ህብረተሰብ ጋር በሰላም ተቻችለው እንዲኖሩ ነው እየመከርን ያለነው፡፡ ሌሎች ተቃዋሚ ድርጅቶችም በባንዲራችንና በአርማችን ስም ደጋፊዎቻችን መስለው የሚንቀሳቀሱትን፣ በሕዝቦች መካከል ጥላቻን ለማራገብና የለውጡን ሂደት ለመቀልበስ የሚሰሩ ኃይሎች፣ የኛን አርማ እየተጠቀሙ፣ ህዝባችንን እንዳያሳስቱ፣ ከአላማችን ውጪ እንደሆነ በይፋ ማሳወቅ አለብን፡፡ እኛ የምንፈልገው፣ ህዝቦች ከህዝቦች ጋር በፍቅር የተሳሰረ ግንኙነት እንዲኖራቸው ነው፡፡ ስንታገልለት የነበረው የነፃነት ትግል፣ የኦሮሞን ህዝብ ብቻ ነፃ የሚያወጣ ሳይሆን፤ ሁሉም ኢትዮጵያዊ በነፃነት የሚኖርበትን ሃገር ለማየት ነው የምንፈልገው። ነፃ የሆነች ሃገር ውስጥ ነው፣ ኦሮሞ ነፃ ሆኖ መኖር የሚችለው፡፡ ስለዚህ ፍቅር፣ ሠላም፣ መረጋጋት ኦሮሚያ ውስጥ ሊኖር የሚችለው ጐንደርና ሶማሌ ውስጥ ሠላምና መረጋጋት ሲኖር ነው ብለን እናምናለን። በእኩልነት ላይ የተመሰረተ፣ አንድ ሃገር የመገንባት አላማ ነው ያለን፡፡ ለዚህም በእኛ ስም የተደራጁትን ወሮበላዎች፣ ህዝባችን እንዲያጋልጥ ጥሪ እያስተላለፍን ነው፡፡
በእኛ እምነት ይሄን ለውጥ ለመቀልበስ ጥረት ሊደረግ ይችላል፤ ነገር ግን የሚቀለበስ አይደለም፡፡ ምክንያቱም ለውጡ የመጣው በአንድ ቡድን፣ በአንድ ድርጅት ወይም በአንድ ህዝብ አይደለም፡፡ በሁሉም ኢትዮጵያዊ የመጣ ለውጥ ነው፡፡ ስለዚህ የ27 አመታት የግፍ አገዛዝን የቀጨው ትግል እንደማይቀለበስ ሙሉ እምነት አለኝ፡፡ ህዝቡ ታግሎ ያመጣውን ለውጥ እንዳይቀለበስ በእርግጠኝነት ይጠብቀዋል፡፡ ህዝባችን ለለውጡ እንቅፋት የሆኑትን እያወቃቸው ነው፡፡ በተለይ በሁለቱ ታላላቅ ማኅበረሰቦች፡- አማራና ኦሮሞ መካከል ጥርጣሬ መፍጠር ነው አላማቸው፡፡ ሴራው አይሳካም፡፡ በዚህ በኩል ምንም ስጋት የለኝም፡፡  

Read 1134 times