Saturday, 22 September 2018 15:03

“ሕዝበኛው” ማን ይሆን?...ያልጠረጠረ ሲመነጠር!

Written by  በጌታሁን ሔራሞ
Rate this item
(5 votes)

 “--በየትኛው ሀገር ነው ሕዝበኛ መሪ፤ ከእርሱ ርዕዮተ-ዓለም ጋር የማይገጥሙትን ፖለቲከኞች ያለ ገደብ እየጠራ፣ የፖለቲካ
ምህዳሩን የሚያሰፋላቸው? የትኛው ሕዝበኛ መሪ ነው ለሕዝቡ፣ “ከእኔም ውጪ ፍላጎታችሁን ሊያሟሉ የሚችሉ አማራጭ የፖለቲካ ፓርቲዎች ስላሉ፣ በዲሞክራሲያዊ ምርጫ የፈለጋችሁትን ፓርቲ ምረጡ” ብሎ ማስታወቂያ የሚሰራው? - -”
        

    (ክፍል 2)
በሕዝበኝነት መሠረታዊ ፅንሰ ሐሳቦች ላይ ያጠነጠነው የዛሬ ሳምንቱ  የክፍል 1 መሰናዶዬ፣ በሁለት መነሻ ርዕሰ ጉዳዮች ላይ ማተኮሩ ይታወሳል፡፡ የመጀመሪያው፣ የዶክተር ዐቢይን አመራር ከሕዝበኝነት ጋር አቆራኝተው አራት ፀሐፍትና ፖለቲከኞች ያንፀባረቁትን ሐሳብ የሚያትት ሲሆን ሁለተኛው ደግሞ የሕዝበኝነት ፅንሰ ሐሳብ ከዘርፉ ሳይንስ አንፃር ሲቃኝ ምን እንደሚመስል የሚጠቁም ነበር፡፡ ብዙዎች የፖለቲካ ሳይንቲስቶች ስለ ሕዝበኝነት ያስቀመጡትን ወቅታዊውን ግንዛቤ መጨበጥ፤ አራቱ የሀገራችን ፀሐፍትና ፖለቲከኞች፣ ፅንሰ ሐሳቡን በተመለከተ ያላቸውን እይታ ለመፈተሽ ቅድመ ሁኔታ ነው ብዬ አስባለሁ፡፡ በክፍል 1 መጣጥፌ ንዑስ ርዕስ ተ.ቁ 2፣ ፅንሰ ሐሳቡ ላይ መሠረታዊ ግንዛቤዎችን እንደቃኘን፣ በዛሬው ንዑስ ርዕስ ተ.ቁ. 3 እና 4 ላይ ለንፅፅሩ ትኩረት እንሰጣለን፡፡   
3. የአራቱ ፀሐፍት/ፖለቲከኞች የሕዝበኝነት ፍረጃ፣ ከዘርፉ ሳይንሳዊ እሳቤ አንጻር
ሳምንት የሕዝበኝነት ፅንሰ ሐሳብ የቱን ያህል ውስብስብ እንደሆነ በክፍል 1 መጣጥፍ ላይ ለመዳሰስ ሞክረናል፡፡ ይሁንና ፖለቲከኞቻችን ዶ/ር ዐቢይ ሕዝበኛ እንደሆኑ ያሰመሩበትን አካሄድ፣ ከፅንሰ ሐሳቡ ሳይንሳዊ መሠረት ጋር ስናነፃፅረው፣ የቱን ያህል ክፍተት እንዳለው ማጤን አይከብድም፡፡
ቀደም ሲል እንዳየነው፤ ሁሉም ፖለቲከኞች ማለትም አቶ ልደቱ አያሌው፣ አቶ ዓለማየሁ ወ/ማሪያም፣ አቶ ዘዐተ መድህኔና የተከበሩ አቶ አስመላሽ ወ/ሥላሴ፤ ሕዝበኝነትን በዋናነት ያቆራኙት ከንግግር (Rhethoric) ጋር ነው፡፡ ሆኖም ግን አነቃቂና ስሜት ኮርኳሪ ንግግሮችን ማድረግ፤ በሕዝበኛ መሪዎች ዘንድ ብቻ የሚገኝ ነፀብራቅ አይደለም። እንዲያውም ሕዝበኝነታቸውን በንግግራቸው ሳይገልጡ በተግባር ግን ሲፈተሹ ሕዝበኛ የሆኑ አያሌ መሪዎች በዓለማችን ታይተዋል፡፡ ለዚህም ነው Weyland የተባለው ፀሐፊ ከሕዝበኛ መሪዎች ንግግር ይልቅ ለፖለቲካዊው አዝማሚያቸው ቅድሚያ ትኩረት ሰጥተን እንድንፈትሻቸው የሚመክረን፦ “This conceptualization (of populism) focuses not on what populists say, but on what they actually do, especially how they pursue and sustain political power.”
በነገራችን ላይ የየትኛውም ርዕዮተ-ዓለም አራማጅ ፖለቲከኛ፣ ስሜት ኮርኳሪ ንግግርን ማድረግ ይጠበቅበታል፡፡ ይህ የታዳሚውን ስሜት ሰቅዞ የመያዝ የንግግር አቅም፣ ከንግግር ጥበብ (Rhethoric) አላባዎች ውስጥ “Pathos” የተባለውን ይወክላል። ሆኖም ግን ንግግር ስሜትን ከመኮርኮር ባለፈ ተናጋሪው ንግግሩን ባቀረበበት አመክንዮአዊ ብቃቱም ( Logos) ይመዘናል። ከዚህም ጋር በተያያዘ፣ የተናጋሪው ተአማኒነትና ሞራላዊ ብቃቱም (Ethos) በንግግር ጥራት ደረጃ አሰጣጥ ላይ የራሱ ሚና አለው። ስለዚህም የንግግሩ ስሜት የመኮርኮር ብቃትን ለብቻው ነጥሎ መመዘንና ይህንንም ከሕዝበኛ መሪዎች ባሕርይ ጋር ለማገናኘት መጣር ትክክለኛ አካሄድ አይደለም፡፡  
በክፍል1 ፅሑፌ ለማስቀመጥ እንደሞከርኩት፤ አንድን መሪ “ሕዝበኛ ነው ወይስ አይደለም” ብሎ ለመፈረጅ በፅንሰ ሐሳቡ ላይ ለአያሌ ዓመታት ጥናት ሲያደርጉ የነበሩ የዘርፉ ምሁራን ያስቀመጡትን የፅንሰ ሐሳቡን ትርጓሜንና ዝርዝር ገለፃን መነሻ ማድረግ ግድ ይላል፡፡ ሕዝበኛ መሪ፤ የአንድን ሀገር ማሕበረሰብ ለሁለት ይከፍላል፡፡ በአንድ ወገን ያለው ከእርሱ የፖለቲካ አቋም ጋር ስምሙ የሆነው የሕዝብ አካል ሲሆን በሌላው በኩል ደግሞ ሕዝበኛው መሪ፣ “ሙሰኛ ልሂቃን” (The Corrupt Elite) የሚል ታፔላ ለጥፎባቸው፣ ወደ ሌላኛው ጽንፍ የሚገፈትራቸው የማህበረሰቡ አካላት ናቸው፡፡ እነዚህ “ሙሰኛ” ተብለው በሕዝበኛ መሪ የሚኮነኑ ልሂቃን የፖለቲካው (ተቃዋሚ ፓርዎችን ጨምሮ) የኢኮኖሚው፤ የሚዲያውና የሥነ ጥበብ ዘርፍ ልሂቃን ሲሆኑ በፖለቲካዊ አቋማቸውም ከሕዝበኛው መሪ ያፈነገጡ ናቸው፡፡ የሀገራችን ፀሐፊዎች ስለ ሕዝበኝነት በሚሰጡት ገለፃ ሁሌም የሚዘነጉት እነዚህን ልሂቃንን ነው፡፡ የሕዝበኝነት ማብራሪያቸው ከሞላ ጎደል የሚሽከረከረው፣ “ሕዝብ” በሚለው ቃል ዙሪያ ብቻ ነው፡፡
ስለዚህም ዶ/ር ዐቢይ፣ “ሕዝበኛ” መሪ እንደሆኑ ድምዳሜ ላይ ከደረስን በኋላ በመቀጠል ማጤን ያለብን፣ በሕዝብ ዘንድ ስላላቸው ተሰሚነትና ስላተረፉት ተወዳጅነት ብቻ ሳይሆን በእኚሁ መሪ ከፖለቲካው ምህዳር ስለተሰናበቱ ልሂቃንም ጭምር ነው፡፡ ለምሳሌ ጠቅላይ ሚኒስትሩ ከእሳቸው የፖለቲካ አቋም በተቃራኒ ላሉ የፖለቲካ ልሂቃን ያላቸው አመለካከት ምን ዓይነት ነው? ራሳቸውንስ እንደ ብቸኛ የሕዝብ ድምፅ ውክልና ባለቤት ይቆጥሩ ይሆን? ሕዝብ ማለት ዶ/ር ዐቢይ፣ ዶ/ር ዐቢይ ማለት ሕዝብ ነው የሚል አቋም ያራምዳሉ? ለነዚህ ጥያቄዎች ምላሽ የምናገኘው ከአቶ አለማየሁና ከአቶ ዘዐተ ፅሑፍ ውስጥ ነው፡፡ ሁለቱም ፀሐፍት፣ ዶ/ር ዐቢይ ከፖለቲካዊ አቋማቸው የተነሳ “The Corrupt Elite “ የሚል ስያሜ ለጥፈውባቸው፣ ወደ ፅንፍ የሸኙዋቸው አካላት እንደሌሉ በግልጽ አስቀምጠዋል። ይህ በጣም እውነት የሆነ ማብራርያ ነው፡፡ እኔን ያልገባኝ ግን ይህን እንዴት አድርገው ከሕዝበኝነት ጋር እንዳቆራኙት ነው፡፡ አቶ ዓለማየሁ ወ/ማሪያም፣ ዶ/ር ዐቢይ ከኢሕአዴግ የፖለቲካ ፕሮግራም የተለየ አመለካከትን የሚያራምዱ ተቃዋሚዎችን በተመለከተ የወሰዱትን እርምጃ የሚያስገነዝቡን እንደዚህ በማለት ነው፦ “Another set of Abiy’s statesmanship will come when dealing with the consequence of his liberalizing acts which have included welcoming parties previously designated as terrorist organizations. Now, all factions of the OLF, Patriotic Ginbot-7, and the so called loyal oppositionists, old and new, are invited to operate in the politics of the homeland.” እንግዲህ የአቶ ዓለማየሁ ፅሑፍ በጣም ግራ የሚያጋባው እዚህ ላይ ነው፤ ዶ/ር ዐቢይ በሕዝበኝነት ማዕበል እየጋለቡ እንደሆነ ካወሱን በኋላ በተቃራኒው እኚሁ ሕዝበኛ  መሪ፣ እንደ ግንቦት 7፤እና ኦነግ ያሉና ቀደም ሲል ሽብርተኛ ተብለው ለተፈረጁት ድርጅቶች፣ የፖለቲካ ምህዳርን በሀገር ቤት እንዳሰፉላቸው ይነግሩናል፡፡ የትግራይ ኦን ላይኑ አቶ ዘዐተም ተመሳሳይ ሐሳብ ሰንዝረዋል፦  “In summary, Abiy’s Populist demagogic group is bringing together the worst parts of different views, ideologies and interests.” አቶ ዘዐተም፤ ዶ/ር ዐቢይ ለልዩ ልዩ አመለካከቶች፤ ርዕዮተ-ዓለሞችና ፍላጎቶች በሩን በርግደው እንደከፈቱ ይነግሩናል፡፡ በየትኛው ሀገር ነው ሕዝበኛ መሪ፤ ከእርሱ ርዕዮተ-ዓለም ጋር የማይገጥሙትን ፖለቲከኞች ያለ ገደብ እየጠራ፣ የፖለቲካ ምህዳሩን የሚያሰፋላቸው? የትኛው ሕዝበኛ መሪ ነው ለሕዝቡ፣ “ከእኔም ውጪ ፍላጎታችሁን ሊያሟሉ የሚችሉ አማራጭ የፖለቲካ ፓርቲዎች ስላሉ በዲሞክራሲያዊ ምርጫ የፈለጋችሁትን ፓርቲ ምረጡ” ብሎ ማስታወቂያ የሚሰራው? የትኛውስ ሕዝበኛ ፖለቲከኛ ነው፣ “ተቃዋሚ” ፓርቲዎችን “ተፎካካሪ” ብሎ ስማቸውን የሚቀይርላቸው?  የሚገርመው የዚህ ዓይነት የፖለቲካ ባሕርይ የሚንፀባረቀው፣ በሕዝበኛ መሪ ሳይሆን የሕዝበኛ መሪ ተቃራኒ በሆነው “Pluralist” መሪ መሆኑ ነው፡፡ ሕዝበኛ መሪ ግን ሁሉን አቃፊ አይደለም፤ ብዝሃነትን ፈጽሞ አይደግፍም፤ አያበረታታም፡፡ ተቃዋሚ ፓርቲዎችን የሚቀበል ፖለቲካዊ ምህዳር አይፈጥርም፡፡ ሕዝበኛ መሪ፣ ፀረ ብዝኃነትን “Antipluralism” ያበረታታል፡፡
አቶ ዓለማየሁና አቶ ዘዐተ፣ ዶ/ር ዐቢይን በሕዝበኛ መሪነት መፈረጃቸውን  ከሕዝበኛ ፅንሰ ሐሳብ ጋር ለማስታረቅ የአልሞት ባይ ተጋዳይነትን ጥረት ማድረጋቸውን መሸሸግ አይቻልም፡፡ በእነርሱ ዕይታ፣ ዶ/ር ዐቢይ ልክ እንደ ሕዝበኛ መሪ፣ ወደ ፅንፍ የገፈተራቸው የፖለቲካ ልሂቃን  አሉ፡፡ በዚህ ረገድ አቶ ዘዐተ እንደዚህ ይላሉ፦”The populist group led by Abiy Ahemed found its constituency in a group of people and entities who hate TPLF. They hate TPLF because they perceive it as the vanguard of the Federal order.” አቶ ዓለማየሁም የዶ/ር ዐቢይን አግላይነት የሚገልጹት እንደዚህ በማለት ነው፦ “His rhetoric of love and unity should start at home with his own political base. TPLF , for example, it seems to be still wondering whether Abiy is doing EPRDF’s bidding, or his ego’s….It will also be wise to include the TPLF leadership in the dialogue with Eritera…” እንግዲህ ሁለቱም ፀሐፍት፣ ዶ/ር ዐቢይ፣ ህወሓትን እንዳገለሉ በአንድ ሐሳብ ይስማማሉ፡፡ ነገር ግን በየትኛው መድረክ ይሆን ዶ/ር ዐቢይ፣ ህወሓትን ከፖለቲካው መድረክ አውግዘው ያስወገዷቸው? በየትኛውስ ንግግራቸው ነው፣ ህወሓትን እንደ ፓርቲ፣ የሕዝብ ጠላት ነው ብለው የፈረጁት? እዚህ ጋ ልብ በሉልኝ፤ ሁለቱም የሚሞግቱት ዶ/ር ዐቢይ፣ ግለሰቦችን ሳይሆን ፓርቲውን (ህወሓትን) በለውጡ ሂደት እንዳላካተቱ ነው! ይህም ሲበዛ ግራ አጋቢ ነው፤ ሙሉ በሙሉ በሐሰት ላይ የተመሰረተ ውንጀላ (False Accusation) ነው፡፡ በተቃራኒው ማን ማንን እንዳገለለ፣ ሚዛናዊ የሆነ አዕምሮ ካለው ሰው የተሰወረ አይደለም። እዚህ ጋ አንድ ጀርመናዊ መምህሬ ከዓመታት በፊት ስለ እንግሊዞች ባሕርይ የነገረኝን ላካፍላችሁ፤ ነገሩ እንደዚህ ነው፦ እንግሊዝ በአውሮፓ ሕብረት አባላት ውስጥ ሁሌም ከሌሎቹ የሕብረቱ አባላት የተለየ አቋም በማንፀባራቋ ትታወቃለች፡፡ ከዚያም እንግሊዝ በአንድ ፅንፍ፣ የቀሩቱ አባላት ደግሞ በሌላኛው ፅንፍ ይሆናሉ። የሚገርመው መጨረሻ ላይ እንግሊዝ ከሌሎቹ የአውሮፓ ሀገራት ተነጠልኩ ከማለት ይልቅ የአውሮፓ ሕብረት ከእንግሊዝ ተነጠለ ማለቱን ማዘውተሯ ነው፡፡ አሁንም በእኛ ሀገር የተስተዋለውም ይኼው ነው፤ አግልሎ ተገለልን ማለት፤ ገፍቶ ተገፋን ማለት፤ እርቆ አራቁን ማለት..ወዘተ፡፡  ከዚህ ውጪ ግን ዶ/ር ዐቢይ፣ በበዓለ ሲመቱ ማግስት ትግራይ ድረስ በመሄድ ስለ ህወሓትም ሆነ ስለ ትግራይ ሕዝብ ምን ብሎ እንደተናገረ ከማንኛችንም የተሰወረ አይደለም፡፡ ሌላው ቀርቶ በቅርቡ በተደረገው ፕሬስ ኮንፍረንስ ወቅት እንኳን ከለውጡ ሂደት ጋር በተገናኘ ከህወሓት ጋር ስለነበረው ግንኙነት ተጠይቀው፤ ለውጡ ያልተዋጠላቸው ግለሰቦች ህወሓት ውስጥም ሆነ ኦህዴድ ውስጥ ሊኖሩ እንደሚችሉ፣ ሚዛናዊ በሆነ መልኩ ከማስቀመጥ ባለፈ ህወሓትን እንደ ፓርቲ ሲያገልለው አልተስተዋለም፡፡ ከዚህም ባለፈ አቶ አለማየሁ፣ የኢትዮጵያ መንግስት ከኤርትራ ጋር በነበረው የዕርቅ ሂደት፣ ዶ/ር ዐቢይ ህወሓትን እንዳገለሉ አድርገው ላቀረቡት ዘገባ ተዓማኒነት እንዲኖረው፣ ማስረጃዎቹንም አያይዘው ቢያቀርቡልን መልካም ነበር፡፡
ከሁሉም በላይ የተከበሩ አቶ አስመላሽ ወ/ሥላሴ፣ ስለ ሕዝበኝነት የሰጡት ፅንፍ የያዘ ማብራሪያ፣ የፖለቲካ ሳይንስ ምሁራን ከሚሉት በእጅጉ የራቀ ነው፡፡ ከነዚህም ውስጥ ቀደም ሲል በክፍል 1 የጠቀስኳቸው….መርህ አልባነት፤ የሕዝብን ቀልብ ለመሳብ ሲባል ስሜት ኮርኳሪ ንግግሮችን ማድረግ፤ ሕዝብን በውሸት ቃል መደለል፤ ፀረ ዲሞክራሲ፤ ፀረ ልማት፤ ፀረ ሰላም፤ ኋላ ቀርነት፤ አድሀሪነትና መጨረሻውም ጥፋት ነው…የሚሉ ይገኙባቸዋል፡፡  አሁንም ደግሜ እላለሁ፦ ሕዝበኝነት መርህ አልባነት አይደለም፤ ምክንያቱም አሁን ባለንበት ነባራዊ ሁኔታ ሕዝበኝነት በተለይም በአውሮፓዎቹ ዘንድ እንደ አይዲዮሎጂ እየተቆጠረ ነው፡፡ ላቲን አሜሪካኖቹ ዘንድ ደግሞ ዋናውን አይዲዮሎጂ ወደ ግብ ለማድረስ እንደ አንድ ስትራቴጂ፣ ሕዝበኝነት ጥቅም ላይ እየዋለ ነው፡፡ እንዲሁም ሕዝበኝነትን በጥቅሉ ፀረ ዲሞክራሲ ብሎ መፈረጅም ትክክለኛ አይደለም፡፡ በተለይም አምባገነን መንግስታት ባሉበት ሀገራት፣ የሕዝበኝነት ንቅናቄ ሕዝቡን በፖለቲካዊው እንቅስቃሴ ከማሳተፍ አኳያ ለጅምር ዲሞክራሲ ማበብ የበኩሉን አስተዋፅዖ አዎንታዊ በሆነ መልኩ ያበረክታል፡፡ ሊብራል ዲሞክራሲ በሰፈነበት ግን ሕዝበኝነት በዲሞክራሲው ላይ ያለው ተፅዕኖ አሉታዊ ነው፡፡  ከሁሉም በላይ አቶ አስመላሽ፣ ሕዝበኝነትን “በውሸት ቃል ከመደለል” ጋር አጣምረው ያነሱበት አመክንዮአዊው ዳራ ግልጽ አይደለም፡፡ ይህ ደግሞ በቀጥታ ዶ/ር ዐቢይን የሚመለከት ከሆነ የበለጠ አወዛጋቢ አባባል ነው። ምክንያቱም ዶ/ር ዐቢይ የተስተዋሉት ቀደም ሲል ለፖለቲካ ትርፍ እየተባለ፣ ለኢትዮጵያ ሕዝብ ይተላለፍ የነበረውን የውሸት ሪፖርት ሲያጋልጡ እንጂ ሲሸፋፍኑ አልነበረም፡፡  ሌላው ቢቀር የሕዳሴውን ግድብ ጉድ፣ ግልጽ ያደረገው ማን ነበር? ቀደም ሲልስ ስለ ግድቡ ፕሮጀክት አፈፃፀም የሐሰት መረጃን እየፈበረከ፣ ሕዝብን “በውሸት ቃል ሲደልል” የነበረውስ ማን ነው? መላ ሀገሪቱን ለከፍተኛ ድንጋጤ የዳረገውን የሜቴክን ለ30% ክንውን፣ 65% ክፍያ የመቀበልን ቅሌትስ ወደ አደባባይ ያወጣው ማን ነበር? ቀደም ሲል የሀገሪቱ ኢኮኖሚ በየዓመቱ በሁለት ዲጂት እያደገ ስለመሆኑ የሚለፈፈው ዲስኩር፣ ታች መሬት ላይ ካለው እውነታ ጋር መጣጣም አለበት በማለት የውሸት ድለላውን ያመከነው ማን ነበር?  
በእኔ እምነት፤ ምናልባት ዓለም የማያውቀው ሌላ ዓይነት የሕዝበኝነት ዓይነትና ትርጓሜ ከሌለ በቀር፣ ዶ/ር ዐቢይ ሕዝበኛ ናቸው የሚለው ድምዳሜ፣ ሙሉ በሙሉ የፖለቲካው ሳይንስ ምሁራን ካስቀመጡት የሕዝበኝነት መስፈርት ጋር የሚላተም ነው፡፡ ከዚህም ባለፈ ዶ/ር ዐቢይ አሁን እየተጫወቱ ያለው ሚና፣ የሽግግር መንግስት ሚና በመሆኑ ስለሚከተሉት ርዕዮተ-ዓለም ባንሟገት መልካም ነው፡፡ በነባሩ የኢሕአዴግ  ርዕዮተ-ዓለም ላይ ማሻሻያ ወይም ለውጥ ካስፈለገም፣ ዶ/ር ዐቢይ ከፓርቲያቸው ተነጥለው ብቻቸውን የሚወስኑት ጉዳይ አይመስለኝም፡፡  ያም ሆኖ አሁን ጠቅላይ ሚኒስትሩ እያራመዱ ያለው የመደመር መርህ፣ ከሕዝበኝነት ይልቅ ለፖለቲካዊ ብዝኃነት (Political Pluralism) የቀረበ ነው፡፡ ብዝኃነት ደግሞ የሕዝበኝነት ተቃራኒ ስለመሆኑ ከላይ መጥቀሴ ይታወሳል፡፡
4. ሕዝበኛው ማነው?
4.1. ማኦ ሴቱንግ ቀንደኛ የማርክሲዝምና ሌኒንዝም ርዕዮተ-ዓለም አራማጅ ነበር፤ ግን ሕዝበኝነትን እንደ አንድ የፖለቲካ ስትራቴጂ ይጠቀም ነበር፡፡ በዚህም ስትራቴጂው “The people” የሚለውን ሥፍራ የሚይዙለት ገበሬዎቹ ነበሩ፡፡ ማኦ “Agrarian Populist” እንደነበር በክፍል 1 ፅሁፌ በስፋት አንስቼአለሁ፡፡ አሁን ደግሞ ከራሳችን አውድ አንጻር እንቃኘዋለን፡፡
የተከበሩ አቶ አስመላሽ፣ መለስ ዜናዊ፣ ሕዝበኝነትን አጥብቀው እንደሚቃወሙ ቢነግሩንም፣ የኛው መለስ ዜናዊም ልክ እንደ ቻይናው ማኦ ሴቱንግ በተለይም በሥልጣን ዘመን ጅምር ላይ ድብን ያሉ “Agraian Populist” ነበሩ፡፡ ለፖለቲካው ንግድ አዋጪነትም ሆነ ለምርጫው ከ80 ፐርሰንት በላይ የሆነው ገበሬ ከጎናቸው መሆኑን እያበሰሩ፣ ከተሜውንና ሐሳቡን የማይጋሩትን ልሂቃንን ወደ ጎን ይገፈትሯቸው ነበር፡፡ እዚህ ጋ የሚገርመው ነገር፣ የህወሓት ገበሬውን ከጎኑ የማሰለፍ ውሳኔ ከማኦ ሴቱንግ ጋር ተመሳሳይነት መኖሩ ነው፡፡ ይህን በተመለከተም የህወሓት ነባር ታጋይ የነበሩ አቶ ገብሩ አስራት “ሉዓላዊነትና ዴሞክራሲ በኢትዮጵያ 2007 ዓ.ም.” ባሳተሙት መጽሐፍ፣ ገጽ 103 እና 104 ላይ በግልፅ አስቀምጠውታል፡፡ ነገሩ እንደዚህ ነው፦ አቶ ገብሩና የትግል አጋሮቹ፣ ማሌሊትን በረሃ እያሉ ከመሰረቱ በኋላ ከጀርመን ሀገር ካፍካ የተባለ የማሌ ፓርቲ ተወካይ፣ በሱዳን በኩል በረሃውን አቆራርጦ ሊጎበኛቸው ይመጣል፡፡ ካፍካ በጉዞው ወቅት  ወልቃይትን ፀገዴን አቋርጦ፣ ደጀና በሚባለው የህወሓት መናኸርያ ወርዒ እስከሚደርስ ድረስ አንድም የኤሌክትሪክ መስመር አላየም፤ ፋብሪካም አስፋልትም ብሎ ነገር የለም፡፡ ግን “የላብ አዳር አንድነት ይለምልም” የሚል መፈክር ነበር፦ እዚያው በበረሃ በእነ አቶ ገብሩ አስራት ሰፈር! በዚህ ጉዳይ ላይ አቶ ገብሩ በገፅ 104 ላይ እንደዚህ ይላሉ፦ “የማሌሊት ጉባዔ በሚካሄድበት ዳስ ከመድረኩ በስተ ጀርባ የማርክስ፣ ኤንግልስ፣ ሌኒንና ስታሊን ትላልቅ ሥዕሎች ተሰቅለው፣ “የላብ አደሩ አንድነት ይለምልም “ የሚል መፈክር ተፅፎ ነበር፡፡ ጀርመናዊው ካፍካ በዚህ አውላላ በረሓ፣ የሶሻሊስት ርዕዮተ ዓለም መስራቾች ምስል ሲያይ፣ ሕብረተሰቡ እንኳን የነርሱን ርዕዮተ ዓለምና ዓላማ ሊከተልና ፎቶ ግራፎቹንም ሊሸከም የሚችል መስሎ አልታየውም ነበር፡፡ የላብ አደሩ ዓለም አቀፋዊነት መለምለሙን ቢደግፍም፣ አንድም ላብ አደር በሌለበት እንዴት ርዕዮተ ዓለሙ ተግባራዊ ሊሆን እንደሚችልም ግራ ገብቶት ነበር፡፡” ማኦም ግራ ተጋብቶ ፊቱን ወደ “Agrarian populism” የመለሰው የማሌሊት ዓይነት ችግር ስላጋጠመው ነበር፡፡ ህወሓት ግን አዲስ አበባ ሲገባ በወቅቱ የማሌ ርዕዮተ ዓለም በዓለም አቀፍ ደረጃ ቁልቁል እየነጎደ ስለነበር ቀደም ሲል በረሃ እያለ ያመነበትን የላብ አደሩን የበላይነት ወደ ግብርና ተኮር ሕዝበኝነት ለመቀልበስ የማዖው ዓይነት ሥቃይ አልገጠመውም፡፡
4.2. በእኔ ዕይታ፤ አቶ መለስ “Ethnopopulist”ም ነበሩ ማለት ይቻላል፡፡ በዚህ ረገድ “The People” የሚለውን የሚተኩለት፣ የኢትዮጵያ ብሔር ብሔረሰቦች ናቸው፡፡ መለስም ሆነ ድርጅቱ ለኢትዮጵያ ብሔር ብሔረሰቦች ችግር ብቸኛ ፍቱን መድኃኒት እንደሆኑ በተደጋጋሚ ሲያሳውቁን ነበር። ሀገሪቱ የነርሱን የብሔር ብሔረሰቦች አጀንዳ የተቃወመች ዕለት፣ ዕጣ ፈንታዋ መፈረካከስ እንደሆነም በመጠቆም ያስፈራሩንም ነበር፡፡ ታዲያ መለስ ዜናዊ፤ ለሌሎች ብሔር ብሔረሰቦች ጥብቅና ስለ መቆማቸው በሚገልጹት ልክ፣ እንደ አንድ ብሔር-ተኮር ሕዝበኛ፣ ወደ ሌላ ፅንፍ የገፋው ብሔር ነበር። ይህም ብሔር የአማራው በተለይም የሸዋው አማራ እንደሆነ ከቀድሞው አሜሪካዊው ዲፕሎማት ኸርማን ኮህን ጋር በነበራቸው ቆይታ በግልፅ መናገራቸው ይታወሳል፡፡ መለስ ዜናዊም አዲስ አበባ እንደገቡም፣ ከወሰዷቸው እርምጃዎች ቀዳሚው፣ 40 ያህል ምሁር ልሂቃንን፣ እርሳቸው፣ የ”ትምክህተኞች አሲምባ” እያሉ ከሚጠሩት የአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ ሲያባርሩ፣ የአማራው ብሔር ልሂቃን ከ80% በላይ ነበሩ፡፡  አቦይ ስብሃትም ቢሆኑ በብሔራዊ ትያትር በነበረው የፕሮፌሰር መስፍን መፅሐፍ ምረቃ ፕሮግራም ላይ በአማራው (እንዲሁም በኦርቶዶክስ ቤተክርስቲያን ላይ) ስለነበራቸው አሉታዊ አቋም ደግመው ይፋ ማድረጋቸው ይታወሳል፡፡ (በነገራችን ላይ ኢሕአዴግ በ”Ethnicity” ፅንሰ ሐሳብም ላይ ያለው ግንዛቤ የዘርፉ ምሁራዊ መሠረት የሌለው ነው፡፡ ለምሳሌ ኢሕአዴግ ስለ “Sociology” ሆነ “Anthropology of Ethnicity” ያለው መረዳት ምን እንደሚመስል ማወቅ አይቻልም፡፡ ይልቁን ለባዮሎጂው ትኩረት ይሰጣል፤ ከባዮሎጂውም ደግሞ ነጥሎ ለአባት የብሔር ሐረግ ዕውቅናን ይሰጥና የእናትን ብሔር ደብዛውን ያጠፋል። በዚህም ኢ-ሚዛናዊ ፣ፆታዊ አቋሙ፣ ኢሕአዴግ ላለፉት 27 ዓመታት በተለይም ከፌሚኒስቶቹ ጎራ ተገቢውን ኩርኩም ሳይቀምስ መዝለቁ በራሱ ገራሚ ነው፡፡ በዚህና በተያያዥ ርዕሰ ጉዳዮች ላይ ወደ ፊት ጊዜና ሁኔታው ሲፈቅድልኝ የምመለስበት ይሆናል፡፡)    
4.3. በምርጫው ረገድም አቶ መለስ Electorate Populist ነበሩ፡፡ በክፍል 1 ለማየት እንደ ሞከርነው፣ ሕዝበኛ መሪዎች፣ መቶ ፐርሰንት የሕዝብ ውክልና እንዳላቸው በንግግራቸው በመግለጥ ይታወቃሉ፡፡ እስቲ ይህን ሁኔታ ከሀገራችን የ2007 ዓ.ም. ምርጫ ጋር እናነፃፅረው፦! ይህ ምርጫ ለሰሚ ግራ በሚያጋባ ሁኔታ ኢሕአዴግ 100 ፐርሰንት የሕዝብ ውክልና እንዳገኘ ያለ ሀፍረት የገለፀበት ነበር፡፡ በክፍል 1 መጣጥፌ Jan Werner Muller የተባለው የፖለቲካ ፕሮፌሰር ያስቀመጠውን ሐሳብ እዚህም ደግሜ ላስታውሳችሁ፦ “Populists claim that they alone, represent the people….Put simply, populists do not claim ‘We are the 99 percent.’ What they imply instead is ‘We are the 100 percent.’”  ይህ እንግዲህ ለተቃዋሚ ፓርቲዎች ልክ እንደ ቱርኩ ሕዝበኛ መሪ ጠይብ ኤርዶጋን…. “We are the people; who are you?” የሚለውን መልዕክት እንደ ማስተላለፍም  ይቆጠራል፡፡ በነገራችን ላይ ህወሓትም ከዶ/ር ዐቢይ ሹመት በኋላ ገራሚ የሆነና ምናልባት ወደ ፊት በኢትዮጵያ የሕዝበኝነት ፖለቲካ ዙሪያ ጥናት የሚያደርጉ ምሁራን፣ ልክ እንደ ቱርኩ ጠይብ ኤርዶጋን ንግግር፣ ለሕዝበኝነት በምሳሌነት የሚጠቀስ አባባልን አስቀምጦልናል፤ ይኸውም፦ “ህወሓትና የትግራይ ሕዝብ አንድ ነው” በማለት ያስቀመጠው ሀቲት ነው፡፡ ይህች የህወሓት አባባል “We are the people ; who are you?” የምትለውን የኤርዶጋን አባባልን የምታስንቅ፤ “ቅመም” የሆነች ምርጥ የሕዝበኝነት አባባል ነች፦! ሆኖም እንደዚህ ዓይነቱ አመለካከት በሕዝበኛ መሪዎች ምናብ ውስጥ ብቻ ያለ ቅዠት”.Fantasy” ስለመሆኑ በክፍል 1 ማስገንዘቤን ልብ በሉልኝ፡፡   
4.4. በመጨረሻም አቶ መለስ ዜናዊ በሌላው ዓለም ያሉ ሕዝበኛ ፖለቲከኞች፣ ሕዝብን ከጎናቸው ለማሰለፍ ይጠቀሙ የነበሩበትን ቴክኒኮች በሙሉ እስከ ወዲያኛው ይጠቀሙ እንደ ነበር መግለፅ ግድ ይላል፡፡ እያንዳንዱን መንግስታዊ ተቋም፣ የመንግስትን የፖለቲካ አጃንዳ በሚደግፉ ካድሬዎች ማስወረር (Stae colonization) በተለይም በምርጫ ወቅት ከሕዝቡ ድጋፍን ለማግኘት ልዩ ልዩ ጥቅማ ጥቅሞችን በእጅ መንሻነት መስጠት(Clintelism) በዲሞክራሲውና በሰብዓዊ መብት አያያዝ ዙርያ መንግስትን የሚያሔሱ መንግስታዊ ያልሆኑ ድርጅቶችን አዋጅ አስወጥቶ እስከ ማሽመድመድ ድረስ እርምጃ መውሰድን አቶ መለስ ዜናዊ፣ በየደረጃው በግልጽ ሲጠቀሙበት እንደነበር፣ የአደባባይ ምስጢር ነበር፡፡
ይህን ረዘም ያለ መጣጥፌን እያዘጋጀሁ በነበረበት ጊዜና ካጠናቀቅኩም በኋላ ምናልባትም በመለስ ዜናዊ የሕዝበኝነት ባህርይ ዙሪያ የተደረጉ ጥናቶች ካሉ በማለት አቅሜ በፈቀደ መጠን ከሌሎች ገለልተኛ ምንጮች መረጃ ለማፈላለግ ሞክሬ ነበር፡፡ ብዙም ባይሆን መቀመጫውን ጀርመን ሀገር ያደረገና በመላው ዓለም 78 ቢሮዎችን ከፍቶ፣ በመቶ ሀገራት ውስጥ በፖለቲካዊ ፅንሰ ሐሳቦች ዙሪያ ምርምሮችን በሚያደርግ Konrad Adenaauer Stiftung (KAS)  ፋውንዴሽን መጠነኛ የሆነ መረጃ አግኝቼአለሁ፡፡ ይህ ፋውንዴሽን እ.ኤ.አ. በ2012 ዲሴምበር 16-17 “Populism within Europe and beyond its borders” በሚል ርዕስ የዘርፉን ኤክስፐርቶች ያሳተፈ ኮንፍረንስ አዘጋጅቶ ነበር። በዚሁ ኮንፍረንስ ላይ ከሕዝበኝነት ጋር በተቆራኘ ጥናታዊ ፅሑፍ ከቀረበባቸው የአፍሪካ ሐገራት መሪዎች መካከል አቶ መለስ ዜናዊ አንዱ ነበሩ፡፡ በኮንፍረንሱ ላይ በመለስ ዜናዊ አመራር ላይ የተንፀባረቁ የሕዝበኝነት ምልክቶች ላይ ጥናታቸውን ያቀረቡት ጀርመናዊው Dr. Stefan Brune ነበሩ፡፡ የኚህን ምሁር ጥናታዊ ጽሑፍ ሙሉ ይዘት ባላገኝም የጥናቱ መግቢያ ግን የሚለው እንደዚህ ነው፡፦ “Melese Zenawi Regime over the years meandered between autocracy and populism.  …However Meles Zenawi,the enigmatic Ethiopian leader who passed away surprisingly end of Augst left behind a system which widely suppresses opposition and human rights defenders and journalists are facing climate of fierce intimidation” ከዚህ ከዶ/ሩ ፅሑፍ መግቢያ ተንደርድሮ ጥናታዊ ፅሁፉ…መለስ ዜናዊ፣ በአምባገነንነትና በሕዝበኝነት መካከል ሲዋዥቁ የነበሩ መሪ ስለ መሆናቸውና (“ሲሞቅ በማንኪያ ሲበርድ በእጅ” እንደሚባለው!) እንደ አንድ ሕዝበኛ መሪ ደግሞ ለራሳቸው የመቶ ፐርሰንት የሕዝብ ውክልናን ሸልመው፣ ተቃዋሚዎችን፤ ለሰብዓዊ መብት ተሟጋች የሆኑ መንግስታዊ ያልሆኑ ተቋማትንና ጋዜጠኞችን ወደ ፅንፍ ስለ መገፍተራቸው (The Corrupt Elit)…መተንበይ ያን ያህል አዳጋች መስሎ አይታየኝም፡፡ በበኩሌ መልኩን ልክ እንደ እስስት በሚቀያይረው የመለስ ዜናዊ የአመራር ስልት ላይ የሀገራችን የፖለቲካ ምሁራን ሰፊ ጊዜ ሰጥተው ጥናት ቢያደርጉ የሚል ጥቆማ ለመስጠት እወዳለሁ፡፡ ለእኔ መለስ ዜናዊ ራሳቸው፣ ልክ እንደ ሕዝበኝነት ፅንሰ ሐሳብ ውስብስብ ናቸው፤ ከላይ ዶ/ር Stefan Brune እንዳስቀመጡትም፤ በአምባገነንነትና በሕዝበኝነት መካከል ዥዋዥዌን የሚጫወቱ፣ ባለ ተለዋዋጭ የአመራር ስልት ባለቤት ናቸው፡፡
እንግዲህ ቀደም ብዬ እንዳሠፈርኩት፣ ክፍል 1 እና 2 በቀረበው ዳሰሳ የተለያዩ ምሁራንን ትንታኔ መሠረት በማድረግ ማን ሕዝበኛ መሪ እንደሆነ ለመግለፅ ሞክሬአለሁ፤ በዚህም ሂደት ዓሳ ጎርጓሪው ዘንዶን እንዳወጣ፤ ያልጠረጠረም እንደተመነጠረ ማስተዋል ያን ያህል የሚያዳግት አይመስለኝም፡፡ እንግዲህ ምን ይባላል? አንድዬ ከዘንዶውም ከመመንጠሩም ይሰውረን እንጂ!

Read 2376 times