Saturday, 22 September 2018 14:56

ፌደራሉ

Written by  ዮናስ ብርሃኔ
Rate this item
(1 Vote)


    ለአብዮት ፌደራል ፖሊስ ማለት በአጭሩ ዱላ ነው፡፡ ፌደራል ሲባል በሰው አናት ላይ የሚወርድ ፈንካች በትረ-ዝናብ መስሎ ነው የሚታየው። የተፈቀደላቸው ቀጥቃጮች አድርጎ ነው የሚቆጥራቸው፡፡ ሰዎችን ለማወላለቅ ጡንቻቸውን አፈርጥመው እያሟሟቁ የሚጠባበቁ “ሳዲስቶች” ናቸው - ለአብዮት፡፡ በትራቸው ካደቀቀው  አንዳንድ ወጣቶች ዘንድ የሚሰማቸው የፌደራል ፖሊሶችን ጭካኔ የሚገልጹ ምሬት ወለድ ቧልቶችና ፍተላዎችም ያንኑ የሚያንጸባርቁ ናቸው፡፡ ከምንም በላይ ግን በ97 ምርጫ ቀውስ ወቅት ለስኳር በሽተኛ እናቱ መድሃኒት ለመግዛት ወጥቶ፣ የወረደበትን የፌደራል ዱላ መቼም አይረሳውም፡፡ ዛሬም ድረስ ያንን ሲያስበው ውስጡን ይነዝረዋል፡፡ ያኔ ግን የስሜት ህዋሳቱ በድነውበት፣ የሚዘንብበትን የዱላ፣ የሰደፍና የቡጢ መዓት እንደ ሰፍነግ ምጥጥ አድርጎ ነበር የዋጠው፡፡ በህመም ውስጥ ያለ፣ ሁሌም የሚያስገርመው ነገር ነው፡፡
በአብዮት ጭንቅላት ውስጥ የተቀረጸው የፌደራል ፖሊስ የጭካኔ ምስል  የተፋቀው፣ ከኢሳያስ ጋር ከተዋወቀ በኋላ ነው፡፡ “እነዚህን ሰዎች ደፍጥጥ ስባል የምደፈጥጥ መሣሪያ የታጠቅኩ መሣሪያ እንደሆንኩ ሲሰማኝ ነው እራሴን የምጠላው!” ብሎ ከራሱ ጋር ሲጣላና ክፉኛ ሲማረር ደጋግሞ አይቶታል። ከዚያ በኋላ ነው ፌደራል ፖሊሶች እንደ ሰው ስሜት እንዳላቸው፣ መደብደብና መግደል የእንጀራ ጉዳይ ሆኖባቸው እንጂ የደስታቸው ምንጭ ላይሆን አንደሚችል ማሰብ የጀመረው፡፡ አብዮት ከኢሳያስ ጋር የተዋወቀው ደግሞ አሁን ቁጭ ብሎ የጀበና ቡና እየጠጣ ባለበት ትንሽዬ ቤት ውስጥ ነው፡፡ “መሲ ቡና” ትባላለች፡፡
መሲ ከጉልበት በታች ያለውን እግሯን የሚያሳይ ቀሚስ የምታበዛ ልስልስ፣እርግት ያለች ቆንጅዬ ጠይም ልጅ ነች፡፡ በካምፓስኛ ግሬድ ይሰጣት ከተባለ “ቢ” የሚከለክላት የለም፡፡ ቀጭን አይደለችም፡፡ መካከለኛም አይደለችም፡፡ በሁለቱ መሃከል ነች፡፡ የሰውነቷ ስጋ ምጥን፣ ልክክ ያለ ነው፡፡ ቅልብጭ ያለች ምርጥ ልጅ ነች፡፡ ስትስቅ ስርጉቶቿ በነጭ ባህር ዳርቻ ላይ ከርቀት የሚታዩ ቀጫጭን ቅጠሎች ነው የሚመስሉት። ተግባቢነቷ በልጅ የዋህነት ውስጥ የሚመጣ ነው። ባህሪዋ የሚከፉበት ሳይሆን የሚሳሱለት ነው፡፡ የሚገፏት ሳይሆን የሚስሟት፣ እምጵዋዬ የሆነች ልጅ። ለዚህም ነው፣ በጀበና ቡና የጀመረችበት የኮንቴነር ሱቅ ዳር ላይ በመሆኑ፣ የፈጠረላትን ነጻ የቀኝ ክንፍ ተጠቅማ፣ ከጎን ትንሽዬ የላስቲክ ዳስ ጥላ ምግብ ለመጀመርና  ገበያዋን እንድታጦፍ ያስቻላት፡፡
 አብዮት ከሷ ቀጥሎ ያለው ኮንቴነር ውስጥ ነው ጸጉር የሚያስተካክለው፡፡ ደንበኞች ከሌሉት ታዲያ  ከሷ ቤት አይጠፋም፡፡ የፌደራል ፖሊሶቹ በሙሉ ማለት ይቻላል እሷ ጋ ናቸው፡፡ ተሰባስበው የጀበና ቡና ይጠጣሉ፡፡ ከነሱ ካምፕ ጎን፣ ዳቦ ባረረበት ህዝብ ላይ ሊቀልድ የተቋቋመ የሚመስል ድርጅት አለ - “በአዲስ አበባ የወንዞችና የወንዝ ዳርቻዎች ልማት እና የከባቢያዊ አየር ለውጥ ማጣጣም ጽ/ቤት” ይባላል፡፡ የዚህ ድርጅት ሰራተኞችም እሷ ጋ በብዛት ይጠቀማሉ።
“እነ ኢሱን ከጠበቁት በላይ አስቆዩዋቸው አይደል?” አብዮት ነው ጠያቂው፡፡
“አይገርምህም?!” አለችው መሲ፤ “ትላንት ማታ ደውሎልኝ ነበር፤ነገሩ የረገበ ቢሆንም ትንሽ ግን ሳያቆዩዋቸው እንደማይቀር ነው የነገረኝ፡፡”
“ከኔ ጋር ከተደዋወልን አንድ አራት ቀን አይሆነንም ብለሽ ነው፤ ቅድም አስቤው እንደውም ስልኩ ከሰራ እሞክርለታለሁ እያልኩ ነበር--” አለና ቡናውን ተጎንጭቶ፣ መሬት ላይ የነበረው የስኒ ማስቀመጫ ላይ አኑሮ፣ ሞባይሉን ከኪሱ አወጣ፡፡
ነቀምትን አለፍ ብሎ በቤኒሻንጉል ጉሙዝ፣ ጉትን አካባቢ ህዝቡ እያፈራረቀ ይጠቀምበት የነበረው የግጦሽ መሬት ለኢንቬስተር መሰጠቱን ተከትሎ፣ የተቀሰቀሰውን ግጭት ለማብረድ፣ በተላኩበት ግዳጅ ላይ የብዙ ሰዎች ህይወት ማለፉን፣ ኢሳያስ የነገረውን እያሰበ “ኢሱ ፌደራል” የሚለውን ስም አውጥቶ ደወለ።
“በቃ እኮ እሱ ካልደወለልን፣ እኛ ልናገኘው አልቻልንም--” አላት ሞባይሉን መልሶ ኪሱ እየከተተ፡፡
“አዎ! ያው ያሉበት ቦታ የኔትዎርክ ችግር አለ አይደል?!” አለችው፣ የታዘዘችውን ሁለት ቡና በትሪ ይዛ እያለፈችው፡፡
ኢሳያስና መሲ ቅልጥ ያለ ፍቅር ውስጥ ናቸው። በተላከበት ግዳጅ ውስጥ መካተቱን ሲነግራት፣ “ተመራቂ መሆንህንና ለዚያም ማሟላት የሚጠበቁብህን አንዳንድ ነገሮች ለማድረግ የግድ እዚህ መሆን እንዳለብህ ለአለቆችህ ነግረህ፣ ለምን እንዲያስቀሩህ አታደርግም?!” በማለት ሊቀር የሚችልበትን መንገድ በየዋህነት እየጠቋቆመች ብዙ ወትውተዋለች፡፡ ግን ወታደር ቤት እሷ እንደምትለው ዓይነት ነገር እንደሌለ ከማስረዳት አልፎ፣ ከአዛዡ ጎን እንደሚሆንና “ያን ያህልም ወደ ሞት እንደምሄድ አታስመስዪው--” እያለ ስጋቷን ሊያለሳልስ ቢሞክርም፣ ውስጧ ግን እሺ አላለውም፡፡ እንዲሁ እንደ ደበራት ነው የሄደው፡፡
አብዮት የሁለቱም የልብ ወዳጅ ነው፡፡ የኢሱም የመሲም፡፡ ከሱ የሚደብቁት ምንም ነገር የለም፡፡ ምንም ነገር ሲያደርጉ እሱን አማክረው ነው፡፡ ኢሳያስ የሚሞሸርበትን ሱፍና ጫማ የገዙትም ሦስቱ አብረው ሆነው ነው፡፡
መሲ በግሏ አዛዣቸው ድረስ ሄዳ፣ የሁለት ወር ነፍሰ ጡር እንደሆነችና የምርቃቱ ዕለት ቀለበት ሊያስሩ መሆኑን ጭምር በመግለጽ፣ ኢሳያስን እንዲያስቀሩላት ተማጽኖዋን ስታቀርብም፣ ከጎኗ የነበረው አብዮት ነው። ይህ ያልተሳካ ሙከራዋ ለኢሳያስ የተነገረው ግዳጅ ከሄደ በኋላ ነበር፡፡
ኢሳያስ የቡታጅራ ልጅ ነው፡፡ እናቱ ወ/ሮ አዳነች፤ የባለቤታቸው አስር አለቃ በላቸው መርዶ ከሰሜኑ ግንባር ሲደርሳቸው፣ ኢሳያስ ገና የ7 ዓመት ልጅ ነበር፡፡ ወ/ሮ አዳነች ከመዝገብ ሰዳሪነት ተሽኳለው እስከ ጽዳት በሰሩበት የመንግስት ት/ቤት ውስጥ ከአንድያ ልጃቸው ዕድሜ በላይ አገልግለው ጡረታ የወጡ ብርቱ ሴት ናቸው፡፡ እሱም የተማረው እዚያው ነው፡፡ ትምህርቱ ላይ አስራ ምናምንኛ መውጣትን ባህሉ ያደረገ የደረጃ “ለ” ተማሪ ነበር፡፡ በእናቱ ብርቱ እቅፍ ውስጥ በእንክብካቤ አድጎ፣ ዩኒቨርሲቲ የሚያስገባ ነጥብ ማግኘት ባለመቻሉ ነበር፣ ዘሎ የፖሊስ ማሰልጠኛ ተቋም ውስጥ የገባው፡፡ ኮሜርስ አካውንቲንግ የማታ ተምሮም፣ በዲፕሎማ ሊመረቅ የጋውን እንደከፈለ ነው ግዳጅ የተላከው፡፡
ለስድስት ዓመት ያህል ባገለገለበት ሥራው ላይ በሚገጥሙት ግዳጆች እየተስተጓጎለ ነው እንጂ መጨረስ የነበረበት ከሁለት ዓመት በፊት ነው፡፡ ብቻ የሆነውን ሁሉ ሆኖ አለፈና፣ አሁን ሊመረቅ ነው፡፡ ደስታውን እጥፍ ድርብ ያደረገለት ደግሞ በፌደራል ፖሊስነቱ የሚጠበቅበትን የአገልግሎት ዘመንም ለማጠናቀቅ ጥቂት ጊዜ የቀረው መሆኑ ነው፡፡
ኢሳያስ ለትምህርቱ የከፈለው መስዋዕትነት በባልደረቦቹ ዘንድ የሚታወቅ ነው፡፡ የምግቡንና የትምህርቱን ወጪ ከሸፈነ በኋላ እጁ ላይ የምትቀረው 85 ብር ብቻ ነበረች፡፡ እሷም ለቡና፣ ለሳሙናና ለትራንስፖርት ትውላለች፡፡ ከዚያ በተረፈ መዝናናት የሚባል ነገር አያውቅም፡፡ ከጽናቱ ይልቅ ምስኪንነቱን ማቀፍ ለሚቀናቸው ግብዞች ግብዣ እንኳን የማይመች፣ ስብስብ ያለ ልጅ ነው፡፡ እንዲያም ሆኖ “ምናለ በዚህ ግዳጅ ላይ ባይልኩት--” የሚሉ እልፍ ከንፈር መጠጣዎች አላጣም፡፡
***    
መሲና አብዮት፣ ኢሳያስ ከግዳጁ እንደተመለሰ ለማካሄድ ስለታቀደው የቀለበት ሥነ ስርዓት እያወሩ ሳለ ነው፣ ረከቦቱ ላይ የነበረው ሞባይሏ የጮኸው፡፡ “ውይ ኢሱ ነው!” አለችውና ፈጠን ብላ አነሳች፡፡ “ወዬ ኢሱ!” ብላ ጀመረች፡፡ ከወዲያኛው መስመር  ያገኘችው ድምጽ እንግዳ እንደሆነባት፣ ለአብዮት የፊቷ ገጽታ ነገረው፡፡ ግራ የተጋባ ፊቷን ይበልጥ እንደቋጠረች፣ ግማሽ ደቂቃ ያህል እንኳን አላዳመጠችም፡፡ ሰውነቷ ከዳትና ሞባይሏ  ከእጇ ወደቀ፡፡ ከተቀመጠችበት ዱካ ላይ ወደ ምድር ፈሰሰች፡፡
አብዮት ከመቅጽበት መሲ አጠገብ ደርሶ፤ “ምንድን ነው እሱ?” እያለ አንገቷን ቀና አድርጎ፣ ክንዱን አንተራሳት፡፡ ከደቂቃ በፊት ያወጋ የነበረው አንደበቷ ለዘመናት ተዘግቶ የከረመ ይመስል በአንድ ጊዜ ድርቅ ብሎ ኮቾሮ ሆነ፡፡ በትክክል እንዲህ ነው እንኳን ልትለው አልቻለችም፡፡
አብዮት፤ ከየት መጣ ሳይባል አጠገቡ መጥቶ ቁጢጥ ያለው  የፌደራል ፖሊስ፤የወደቀውን የመሲን ሞባይል አንስቶ እንዲያቀብለው በምልክት ነገረው፡፡ ከአዛዡ ጋር ሆኖ በፓትሮል እየተጓዘ የነበረው ኢሳያስ፣ በጥይት ተመትቶ  እንደ ሞተ ተነገረው፡፡ “ወይኔ ወንድሜን-- ወይኔ ኢሱዬ “ አለ አብዮት፤ ስልኩን ደረቱ ላይ ለጥፎ እንደያዘ፡፡ እንባው በጉንጮቹ ላይ እየተንከባለሉ፣ መሲ ጭን ላይ ይንጠባጠቡ ጀመር፡፡ ፍቅረኛዋን አጥታ እንደሱ እንኳን ልታነባ ያልቻለችውን መሲን፣ ደረቱ ላይ አቅፎ፣ “እዬዬ” እያለ ተንዘፈዘፈ፡፡


Read 752 times