Saturday, 12 May 2012 10:40

የሃይማኖት መቻቻልና መከባበር ሥጋት በድሬ

Written by  መታሰቢያ ካሳዬ
Rate this item
(0 votes)

ለሃይማኖት መቻቻል፣ ለመከባበር፣ አብሮ በሰላም ለመኖር ምሳሌ በመሆን ሁሌም የሞት ጠቀሰውና የበረሃው ንግስት በሚል ስያሜ የምትታወቀው የድሬዳዋ ከተማ ዘሬ ሥጋት አላት ነፃ የሆነና በዘመኑ ቋንቋ ያልተካበደ ህይወትን የሚመሩት ህዝቦቺ ሁሉም ነገር በፍቅር በመከባበርና በመተሳሰብ ሊሆን እንደሚችል ከህይወት ተምረዋል፡፡ በፍቅር ያምናሉ፡፡ የሃይማኖት የዘር፣ የጐሳ ልዩነት እምብዛም አያስጨንቃቸውም “አቦ አታካብድ” ቋንቋቸው ነው፡፡ ይህንን ለዘመናት የኖረ አንድነተና አብሮነት ሊንድ የሚችልና የህዝቦቿን ተከባብሮ መኖር የሚያፈርስ አደጋ እያንዣበበ መሆኑ የሚያሳስባቸው አንዳንድ ነዋሪዎቿ ስጋታቸውን ይገልፃሉ፡፡ የሐረር ብዙሃን መገናኛ ኤጀንሲ የኦሮምኛ ቋንቋ ዳይሬክተሯ ዋረዳ አብዲ በእምነት ሽፋን ለዘመናት አብሮ የኖረውን የተጋባ፣ የተዋለደውን ማህበረሰብ ለመከፋፈል እና ለመለያየት መሞከሩ ያሳስባታል፡፡ ዋረዳ በኖረችበት አካባቢ በእስልምናና በክርስትና እምነት ተከታዮች መካከል ለዘመናት የኖረ የመቻቻል የመከባበርና የመተሳሰብ ባህል ነበረ፡፡ የሁለቱም እምነት ተከታዮች በሐዘን፣ በለቅሶ፣ በደስታ፣ በሰርና ሳይለያዩ አንዱ ላንዱ እየተደጋገፉና እየተከባበሩ ይኖራሉ፡፡ ይህ ለዋረዳ ከምንም የበለጠ ትልቅ እሴቷ ነው፡፡ ለዋረዳ የልብ ጓደኛዋና አብሮ አደግ ባልንጀራዋ የክርስትና እምነት ተከታይ ነች፡፡

ቤተሰብ ለቤተሰብ የተሳሰረው ጓደኝነታቸው ሁለቱንም ወጣቶች የበለጠ አቆራኝቷቸዋል፡፡ ረመዳንን አብረው እየፆሙ ቅበላውን አብረው እየተቀበሉ የፋሲካን ፆም በጋራ እየፈቱ አስከዛሬ ቆይተዋል፡፡ ለክርስቲያን የመስቀል በዓል ደመራ ለማየት ከጓደኞቿና ከወንድሞቿ ጋር ወደስፍራው ሰታመራ ስለሃይማኖቷ ልዩነት ለአፍታም አስባ አታውቅም፡፡ ይህን ፀጋ የሰጠችኝ እናቴ ነች፡፡ እናቴ ሙስሊም ብትሆንም ለክርስቲየን ጓደኞቿ በጣም የምትመች ነች፡፡ እናቴ በተወለደችበት አካባቢ ‘የመስላ ጊዮርጊስ’ የሚባል ታቦት አለ፡፡ እስከዛሬመ ድረስ እናቴ ዕቃ እንኳን ሲወድቅባትና ስትደነግጥ ‘የመስላው ጊዮርጊስ’ ድረስ ነው የምትለው፡፡ እኔ እኮ ሀሁን ያስቆጠሩኝ የኔታ ናቸው ትለናለች ለቤተክርስቲያን ማሰሪያ በማደረግ መዋጮ ቤተሰቦቼ አይለዩም የምትለው ዋርዳ እሷ በዚህ የመቻቻልና የመከባበር ባህል ውስጥ እንድትኖር ቤተሰቦቿ ምክንያት ሆነዋታል፡፡ ይህን የመቻቻልና የመከባበር ባህል ስጋት ላይ ሊጥል የሚችል በአካባቢው ያልተለመደና እስከዛሬ የሌለ ነገር እየተፈጠረ ነው፡፡ አዲስ ሃይማኖት አምጥቶ አብሮነትን ሊያጠፋ የሚችል አይነት ሰበካ እየተሰበከ ነው፡፡ እንደ ዋረዳ እምነት ይህ ጉዳይ እጅግ አደገኛና አስፈሪ ነው፡፡ ይህ ሁኔታ ለሁለቱም ሃይማኖት ተከታዮች የማይበጅ ለዘመናት የኖረውን ውድና ጥሩ ባህል የሚያጠፋ ሲብስም ለከፋ ችግር የሚዳርግ ነው፡፡

“አሁን እኛ ማሰብ ያለብን ስለእድገታችን ነው፡፡ እንዴት እንለወጥ ብሎ ማሰብ ነው ያለብን፡፡ ምን እንብላ ከሚለው ነገር መውጣት አለብን እንጂ ወደኋላ ተመልሰን ለላ ነገር ውስጥ መግባት አይጠበቅብንም፡፡ ሁሉም የየራሱን እምነት ይዞ የሰውንም እያከበረ መኖር አለበት፡፡ ይህ ካልሆነ ትልቅ ችግር ነው፡፡ ከተማችን የምትታወቅበትን የፍቅር ከተማነት ልታጣ አይገባም ፍቅር እኮ ደስ ይላል፡፡ የሚያስጠላው ክፋት፡ ሁከት፣ ጥላቻ ነው” የምትለው ዋረዳ አሁን ያለው ጊዜ እጅግ አሳሳቢ መሆኑን ትናገራለች፡፡

በባጃጅ ሹፍርና ሥራ የሚተዳደሩትና ሐረር ከተማ ውስጥ መወለዳቸውን የነገሩኝ አቶ ታረቀኝ ጌትነትም ተመሳሳይ ስጋት አላቸው፡፡ ከጊዜ በኋላ የመጣ ነው በማሉት ጉዳይ ሁለቱ ሃይማኖቶች ለአመታት የኖሩበትን የመቻቻልና የመከባበር ባህል ያጣሉ የሚል ስጋት አላቸው፡፡ ከሐረር ወደ ድሬደዋ የመጣሁት ትዳር ከያዝኩ በኋላ ነው፡፡ አራት ልጆችን የፈራሁትም እዚሁ ድሬደዋ ውስጥ ነው፡፡ የመጀመሪያዋ ልጅ አብሮ አደጓ የሰፈሯ ልጅ የሆነውን ሙስሊም ወጣት ነው ያገባቸው፡፡ ልጅ ወልዳ የልጅ ልጅም አሳይታኛለች፡፡ ይህ ሁኔታ በእኔም ሆነ ባገባችው ልጅ ቤተሰቦች መሀል እምብዛም የከፋ ነገር አልፈጠረም፡፡ እንዲህ አየነት ነገር በእኛ ባህል የተለመደ ነው፡፡

አሁን አሁን የሚታየው ነገር ግን የሚያስፈራ ይመስላል፡፡ ቀድሞ ያልነበረ አዳዲስ ነገር እየመጣ ነው፡፡ በተለይ ወጣቶቹ እያሳዩ ያሉት ነገር ጥሩ አይመስለኝም፡፡ እኛ እኮ ጌጣችን፣ መቻቻላችን፣ መከባበራችን፣ መዋደዳችን ነው እንዲህ ስንሆን ነው የሚያምርብን፡፡ በጐርፍ አደጋው ወቅት የሃይማኖት ልዩነታችንን ፈፅሞ ረስተነው ነበር፡፡ የክርስቲያኑን ልጅ ሙስሊሙ፣ የሙስሊሙን ልጅ ክርስቲያኑ ሲደግፍና ሲረዳ ነበረ፡፡ በአደጋው የሞቱ ወገኖቻችንን እኩል አዝነን ቀብረናቸዋል ሙስሊሙ ተርቦ ሲያይ ዝም ብሎ የሚያልፍ ክርስቲያን እንደሌለ ሁሉ የደከመ ክርስቲያን ወገኑን እያየ የሚጨክን ሙስሊምም የለም፡፡ በመሃከላችን ለመናት የኖረውን የመከባበር፣ የመተሳሰብና የመቻቻል በዓል እንዲጠፋ የሚፈልጉ ወገኖች አሉ፡፡ እነዚህን ነቅቶ መጠበቅ ነው፡፡ አቶ ታረቀኝ ስጋታቸው የብዙ ጓደኞቻቸውና የቤተሰቦቻቸው ስጋትም እንደሆነ ነግረውኛል፡፡

የድሬ ከተማ ነዋሪውና በንግድ ሥራ የሚተዳደሩት ሼህ አብዱልጀሊል ቃሲምም የአቶ ታረቀኝን ስጋት ይጋራሉ፡፡ የሙስሊሙና ክርስቲያኑ አብሮ መኖር መቻቻል መተሳሰብ ትናንት የመጣ አዲስ ነገር አለመሆኑን የሚናገሩት ሼህ አብዱልጂላል ክርስቲያኑ የኢትዮጵያ ንጉስ ለሙስሊም ስደተኞች ማረፊያ መስጠታቸውን ታሪክ ጠቅሰው ያወጋሉ፡፡ “ነቢያችን ሂዱ ወደ ኢትዮጵያ በዚያ እውነተኛ ፍርድን የሚያውቅ ክርስቲያን ንጉስ አለ፡፡ እሱ ይቀበላችኋል ብለው አምነው ነው ስደተኞቹን ወደ ኢትዮጵያ የላኳቸው፡፡ ንጉሱም አላስፈራቸውም ስደተኞቹን ተቀብሎ ማረፊያ ሰጥቷቸዋል፡፡ ይህ እውነተኛ ታሪክ ነው፡፡ ተረት ተረት አይደለም፡፡ እኔ በዚህች ከተማ ለ38 አመታት ኖሬአለሁ፡፡ ከክርስቲየን ጓደኞዤ ጋር እኩል ለቤተክርስቲያን ማሰሪያ ገንዘብ አዋጥተን፣ መስጊዱን አብረን ገንብተን ነው እዚህ የደረስነው፡፡ በየበአላቶቻችን፣ በፋሲካው በገናው በጥምቀቱ፣ በኢዱ፣ በመውሊዱና በአረፋው ሳንለያይ አብረን ነው የኖርነው፡፡

ይህንን የመተሳሰብ የመረዳዳት የመተጋገዝ ባህል ያወረሱን ቤተሰቦቻችን ናቸው፡፡ አያቶቻችን ለአባቶቻችን፣ አባቶቻችን ለእኛ አውርሰውናል እኛ ጋር ሲደርስ ግን እንቅፋት እያጋጠመው ነው፡፡

ልጅ ደረሰ ቤት ፈረሰ እንዲሉ ዛሬ የሚታየው ነገር የሚያስደስት አይደለም፡፡ ያስፈራል፡፡ ሙስሊሙን እራሱ እርስ በርሱ የሚከፋፍል ነገር ይታያል፡፡ እርስ በርስ አለመተማመን፣ በጐሪጥ መተያየት በስፋት ይታየል፡፡ እኛ ከክርስቲያን ወዳጆቻችን ጋር አሁንም በፍቅር ነው ያለነው፡፡ ልጆቻችን ግን ይህንን ፍቅር ይዘው ይቀጥላሉ ወይ የሚለው ጉዳይ ላይ ስጋት አለኝ፡፡

 

 

Read 2892 times Last modified on Saturday, 12 May 2012 11:28