Saturday, 29 September 2018 13:46

ንጉሥ ሆኖ ሳይከሳ የሚሰናበት የለም የዐረቦች ተረትና ምሳሌ

Written by 
Rate this item
(13 votes)

ከአንድ ጋዜጣ ያገኘነው ተረት የሚከተለውን ይመስላል፡- ተረቱ በተለያየ አገር የሚነገር ቢሆንም በዚህ መልኩ የተነገረው እኛ ጋ ነው፡፡ እንደሚያመች አድርገን አቅርበነዋል፡፡
እነሆ፡-
ከዕለታት አንድ ቀን ጅብና ቀበሮ ቤት ፍለጋ ይሄዳሉ፡፡ ጅብ ትልቅ ቤት ሲያገኝ፣ ቀበሮዋ ብዙ ቀዳዳዎች ያሉት ትንሽ ቤት አገኘች፡፡
ቀበሮዋም፤
 “አንበሳ ቢመጣብህ በየት በኩል ታመልጣለህ? እኔ በቀዳዳዎቹ ለማምለጥ እችላለሁ” ትለዋለች ለጅቡ፡፡
 ጅብ ብዙም አርቆ ሳያስተውል፣
 “እባክሽ እንቀያየር?” ይላታል፡፡
 እሺ፤ ብላው ተቀያየሩ፡፡
ሌላ ቀን ጅቡና ቀበሮዋ ምግብ እንፈልግ ተባባሉ፡፡
ጅብ፤ “ወፍራም በሬ አግኝቻለሁ፤ አንቺስ?” አላት፡፡
ቀበሮ ያገኘችው ተባይ የሞላው አህያ ነው፡፡
“እኔ ያገኘሁት አህያ ነው፡፡ ግን ተመልከት ጮማ ነች! እንቀያየር” አለችው፡፡
ተቀያየሩ፡፡
የማረጃ ቢላዋ ፍለጋ ተሰማሩ፡፡
ጅብ ቢላ አገኘ፡፡ ቀበሮ ዶሮ ላባ አገኘች፡፡
 “ዶሮ ላባ በጣም ጠቃሚ መሳሪያ ነው፡፡ ቢጠፋብኝ በቀላሉ እተካዋለሁ፡፡ ያንተ ቢላ ግን ቢሰበር መተኪያ የለህም፤እንቀያየር” አለችው፡፡
ጅብ ተስማማ፡፡ ተቀያየሩ፡፡
በሬውን ለማረድ ጅቡ አልቻለም፡፡ ቀበሮ ግን ቢላውን በላባ ሸፍና በሬውን አረደችና አብረው በሉ፡፡ ቆይተው በመንገድ ላይ ማርና ቅቤ የተሸከመ ግመል አዩ፡፡
 ቀበሮ፣ ግመሉን ለሚነዱት ሐማሎች፤
“ደክሞኛል፤ እባካችሁ ግመሉ ላይ ጫኑኝ” አለች፡፡ ጫኗት፡፡
ማሩንና ቅቤውን ግጥም አድርጋ በላች፡፡
“አውርዱኝ ቤቴ ደርሻለሁ” አለች፤ጥግብ ስትል፡፡
አወረዷትና ወደ ገበያ ሄዱ፡፡
እዚያ ሲደርሱ “ጉድ!” አሉ። የተሰሩት ገባቸው፡፡ በቁጭትና በንዴት የአካባቢውን ቀበሮዎች ሁሉ ሰበሰቡና፤ “ዝለሉ!” አሉ፡፡ ያቺ ቀበሮ ቅቤና ማሩ ስለሚከብዳት እንደ ልቧ ስለማትዘል በቀላሉ ሊለይዋት ነው! እውነትም እመት ቀበሮ መዝለል አቅቷት ተያዘች። ታሰረች፡፡
“በኋላ እንገርፋታለን” ብለው ወደ ገበያው ሄዱ፡፡
ያ ጅብ መጣና አገኛት፤
“ለምንድነው የታሰርሺው?” ሲል ጠየቃት፡፡
“ቅቤና ማር ብይ ሲሉኝ እምቢ ብዬ!” አለችው፡፡
ጅቡም፤ ብልጥ የሆነ መስሎት፤
“በይ ቦታ እንለዋወጥ!” አላት፡፡ ፈታትና ቦታ ተለዋወጡ፡፡
ነጋዴዎቹ ሲመለሱ፣ በቀበሮዋ ቦታ ጅቡን አገኙ፡፡
“ምን ልትሰራ መጣህ?” አሉት፡፡
“ቀበሮ ቅቤና ማር ታገኛለህ ብላኝ ነው!” አላቸው፡፡
ቀበሮ ዛፍ ላይ ሆና፣
“ዐይኑን አትግረፉት! ጆሮውን አትንኩት! ሌላ ቦታ ላይ ግን ግረፉት” ትላለች፡፡
 ሰዎቹ እንዳይሞት እንዳይድን አድርገው ገረፉት፡፡ ቆዳው ተልጦ ሥጋው ይታይ ጀመር፡፡
ከዚያ ጥለውት ሄዱ፡፡
 ጅቡ ወደ ቤቱ ሄደ፡፡ ቤት ሲደርስ ልጆቹ ሲያዩት፤
“አባታችን ስጋ ይዞልን መጣ” ብለው ራሱን ተቀራመቱት!
*       *       *
ከላይኛው ተረት የቤትን ችግር ማስተዋል አያዳግተንም፡፡ ነገ ጠላት ቢያጋጥም ለማምለጥ ማስተዋል እንዳለብን ልብ እንላለን፡፡ ቦታ በመቀያየር ዙሪያ ብዙ ጅልነት እንደሚኖር እናጤናለን፡፡ ምግባችንን መለዋወጥም የራሱ ጣጣ እንዳለው እንገነዘባለን፡፡ ማረጃችን ቢላ ወይስ ዶሮ - ላባ? የሚለውንም እናሰምርበታለን፡፡ ቢላ በላባ ሸፍነው ማረድ ግን ማኬቬሊያዊ አካሄድ ነው! የማርና ቅቤ ተሸካሚ ግመል፣ ግመሉንም የሚነዱ ነጋዴዎች ብዙ ናቸው፡፡ ግመሉ ላይ የሚጫኑ ብልጣ - ብልጦች ግን አያሌ ናቸው፡፡ ያም ሳይበቃቸው እንደ ጅቡ ሁሉ ለብዙዎች መታሰር ምክንያት የሚሆኑ አያሌ ናቸው! በልተው፣ መብላታቸው ተነቅቶባቸውም በአፋቸው ሌሎችን አስቀፍድደው፤ ዛፍ ጫፍ ላይ ሆነው የሚያላግጡ በርካቶች ናቸው! ለማን አቤት ይባላል?! ጅልነት በራስ ወገን እስከ መበላት ያደርሳል!
“አብዮት ልጇን ትበላለች!” ይሉ ነበር የዱሮ ገዢዎቻችን፡፡
 ሎሬት ፀጋዬ እንዳለው፤
 “አንዲት የዱር አውሬ፣ በአንዳንድ የመከራዋ ሰሞን
 ልጇን ትበላለች አሉ፣ ምጥ የጠናባት እንደሆን!
ዕውነቱ ሁሌም አይቀሬ ነው፡፡ ዩኒቨርሳል እንደሆነው ሁሉ “የቤት - ጣጣም” አለበት፡፡
 ዲበ - ኩሉ ይሰውረን እንጂ በሹም - ሽር የምንገላገለውስ አይደለም! “ጉልቻ ቢቀያየር ወጥ
 አያጣፍጥም” የሚለው ተረት ዱሮ ይሰራ ነበር፡፡
 አሁን ግን፤
‹‹የጣፈጠ ወጥ በጉልቻ መቀያየር የሚበላሽበት ዘመን መጣ›› በሚለው መተካት ሳያሻው አይቀርም፡፡ ሁሉን ነገር በሙከራ ብቻ አንዘልቀውም፡፡ ከወገናዊነት ነፃ እንሁን፡፡ ከልባችን ወደፊት እንጓዝ!!  አገሪቱ ከቤተ ሙከራነት መውጣት አለባት፡፡ በመካከለኛው የቢሮክራሲ ማዕድ የሚነሳውን ቢሮክራሲያዊ ሙስና አባዜ መላቀቅ ያሻል! ግምገማ ዕውነተኛ መሆኑ መፈተሽ አለበት፡፡ ባጠፉ አመራሮች ላይ እርምጃ እንወስዳለን ሲባል፣ ሁለት ነገሮች ግንዛቤ ውስጥ መግባት አለባቸው፡፡ አንደኛው ገምጋሚዎቹ ምን ያህል ንፁሀን ናቸው? ሁለተኛ የሚወሰደው እርምጃ ምን ያህል ሥር ነቀል ነው? ለእነዚህ ጥያቄዎች አዎንታዊ ምላሽ ማግኘት ወሳኝ መሆኑን አንዘንጋ! ከዚህ ሁሉ በኋላ ደግሞ በቦታቸው የሚተካውስ ማነው? አስተማማኝ ነውን? ብሎ መጠየቅም ያባት ነው! ዞሮ ዞሮ ከሥርዓቱ መመሪያ ውጪ አዲስ ነገር የለም! ጆርጅ ፍሪድማን፤ ‹‹ቀጣዮቹ መቶ ዓመታት›› (The next 100 years ) በሚለው መጽሐፉ፤
‹‹ኦባማ የቡሽን የውጪ ጉዳይ ፖሊሲ አራማጅ ነው፡፡ ቡሽ በኢራቅ ላይ ያወጣው መመሪያ እንዳለ አለ። ከአውሮፓውያን በተለይም ከጀርመን ያለው ግንኙነት ያው ነው፡፡ ከኢራንና ከኩባ ጋር ለመግባባት የሞከረው ውጤቱ ፍሬ ቢስ ነበር፡፡ ከሩሲያ ጋር ያለውም ዝምድና የቡሽ እንደነበረው ነው፡፡ ከጆርጂያ፣ ከዩክሬን.. ከፖላንድም ያለውን ዝምድና ማዝለቅ ነው፡፡ ኦባማ ለፕሬዚዳንትነት በመወዳደርና ፕሬዚዳንት በመሆን መካከል ያለውን ልዩነት ጥርት አድርጎ ያውቃል፡፡ እንደ ተመራጭ ብዙ ነገር ትናገራለህ፡፡ እንደ መሪ ግን ከነባራዊው ዕውነታ ጋር ትጋፈጣለህ። እንደ ቼዝ ተጫዋች የምትሄድበት አቅጣጫ ይጠፋሃል፡፡ መሪነት የዋዛ ነገር አይደለም፡፡”
ዶናልድ ትራምፕም ከመመሪያው ውጪ እንዳይደለ ከላይ ካነሳነው ሁኔታ መገንዘብ አያዳግተንም፡፡ የሀገራችንን አመራሮችም ሆነ የመካከለኛ ቢሮክራሲ ሹማምንት በዚህ ረገድ መገምገም አዳጋች አይደለም፡፡
 እንደ ፀሀፊው አሪፍ አገላለፅ፤
‹‹United States is a bizarre mixture of overconfidence and insecurity›› (አሜሪካ ከመጠን ያለፈ ልበሙሉነትና ደህነነቷን የማጣት ሥጋት ቅልቅል የሆነች አገር ናት እንደ ማለት ነው) ይላታል፡፡ እኛስ ብንሆን? ብሎ መጠየቅ አስማታዊነትን አይጠይቅም፡፡ የትኛውም መሪ፣ መካከለኛ መሪ፤ ወይም ታህታይ መሪ፤ በፓይለቶች ቋንቋ፡-
‹‹Soft-Landing›› በሰላም መሬት መድረስ ካጋጠመው ዕድለኛ ወይም የበቃ ሰው ነው፡፡ አብዛኛውን ጊዜ አያጋጥምም፡፡ እጅግ ወደ ፅርሃ-አርያም ለወጣ ምድር ሩቅ ናት፡፡
ስለዚህ አዕምሮውን ማዘጋጀት አለበት - ለመውረድ። አለበለዚያ ዐረቦች፤
‹‹ንጉሥ ሆኖ ሳይከሳ የሚሰናበት የለም!” የሚሉትን ተረትና ምሣሌ ልብ እንድንል እንገደዳለን!

Read 8751 times