Saturday, 29 September 2018 14:22

የፖለቲካ ፓርቲዎች መብዛት ለግጭትና መከፋፈል ምክንያት እየሆነ ነው ተባለ

Written by  አለማየሁ አንበሴ
Rate this item
(2 votes)

 በቅርቡ ወደ ሃገር ቤት የተመለሰውን “አርበኞች ግንቦት 7” ጨምሮ 11 የፖለቲካ ድርጅቶች “የአማራ ህዝብ ጥያቄዎችና የፖለቲካ ፓርቲዎች ሚና” በሚል ርዕስ በባህር ዳር በተዘጋጀ የውይይት መድረክ ላይ የተሳተፉ ሲሆን በመድረኩ ጥናት፤ ያቀረቡ ምሁራን፤ የፖለቲካ ፓርቲዎች መብዛት ለግጭትና መከፋፈል ምክንያት እየሆነ ነው ብለዋል፡፡
በዚህ የውይይት መድረክ ላይ ሠማያዊ፣ ኢዴፓ፣ መኢአድ፣ አብን ጨምሮ በአማራ ክልል የሚንቀሳቀሱ የፖለቲካ ድርጅቶች የተሳተፉ ሲሆን፤ በምሁራን ጥናታዊ ጽሁፍ ቀርቦ ውይይት ተደርጐበታል፡፡
የአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ መምህር ዶ/ር ዳዊት መኮንንና አቶ ኢያሱ በካፋ ባቀረቡት ጥናታዊ ጽሁፍ፤ የፖለቲካ ፓርቲዎች ለሠላማዊ የስልጣን ሽግግር ሚናቸውን ሊወጡ የሚችሉባቸውን አቅጣጫዎች ጠቁመዋል፡፡
በመድረኩ ላይ የተሳተፉት የፖለቲካ ድርጅቶች ተወካዮች ስለ ውይይቱ ለአዲስ አድማስ እንዳብራሩት፤ “በሃገሪቱ የፖለቲካ ፓርቲዎች መብዛት ለግጭትና መከፋፈል ምክንያት እየሆነ ነው፡፡ ተመሳሳይ ሃሳብ ያላቸው ፓርቲዎች ወደ አንድነት መምጣት አለባቸው” የሚል ሃሳብ ከጥናት አቅራቢዎቹ ተሰንዝሯል፡፡
በፖለቲካ ውድድር ውስጥም ፓርቲዎች ጥላቻና ሃይልን በማስወገድ ሰላማዊና ዴሞክራሲያዊ አካሄዶችንና አማራጮችን ሊያዳብሩ እንደሚገባ ለማስገንዘብም የተለያዩ ሃገራት ተሞክሮ በማሳያነት መቅረቡንም የውይይቱ ተሳታፊዎች ተናግረዋል፡፡
በሃገሪቱ የሚንቀሳቀሱ ሁሉም ፓርቲዎች ለሠላማዊ የስልጣን ሽግግር በሚጠቅሙ መርሆዎች ላይ ቀጣዩ ምርጫ ከመድረሱ በፊት መግባባት ላይ መድረስ አለባቸው - ብለዋል ምሁራኑ፡፡
“ከዚህ ቀደም ለህዝቡ ከገዥዎች እየተላከ የሚመጣው ዲሞክራሲ ነፃ አውጪ ነኝ ባዩ እንዲፈለፈል፣ በአመፅ መብቱን ሊመልስ የሚፍጨረጨር ዜጋ እንዲኖር አድርጓል” ያሉት ጥናት አቅራቢው ዶ/ር ዳዊት መኮንን፤ “ህዝቡ ታላቅ ለመሆን ነው የሚጥረው፤ ለዚህ ታላቅ ለመሆን ለሚጥር ህዝብ ሃሳቡን የሚያቃናለት የፖለቲካ ውክልና ያለው ኃይል ያስፈልጋል” ብለዋል፡፡
“የህዝቡ ጥያቄ በፖለቲካ አንድነት የሚፈታ ነው” ያሉት ምሁሩ፤ “የፖለቲካ ፓርቲ አብዝቶ ህዝቡን ማደናገሩ አይበጅም” ሲሉ አሳስበዋል፡፡
በሃገሪቱ ለመከፋፈልና ለግጭት ምክንያት የሆኑ የታሪክና የፖለቲካ ትርክትን ማስተካከልና አዎንታዊና አሉታዊ ጐኖችን በሚገባ መፈተሽ እንደሚያስፈልግም ምሁሩ በአፅንኦት ተናግረዋል፡፡
በባህርዳሩ የውይይት መድረክ ላይ የአማራ ህዝብን የፖለቲካ እንቅስቃሴና ፍላጐት ያማከሉ የተለያዩ ሃሳቦች የቀረቡ ሲሆን ከእነዚህም “የአማራ ህዝብ እስካሁን ድምፅ አልባ ነበር፣ ብአዴን የጠራ አይደለም ብዥታ ውስጥ ነበር፣ ከአማራ ክልል ውጭ የሚኖሩ ተወላጆች ውክልና እንዲያገኙ መብታቸውን ማስከበር ያስፈልጋል፤ የአማራን ህዝብ ራስን በራስ የማስተዳደርና የወሰን ጥያቄን በወቅቱ መፍታት ያስፈልጋል” የሚሉት ይገኙበታል፡፡ ዘርና ቋንቋ ላይ የተመሠረተ ፌዴራሊዝም አያስፈልግም የሚል ሃሳብም ተሰንዝሯል፡፡
በውይይቱ የተሳተፉት የብአዴን ሊቀ መንበርና ምክትል ጠ/ሚኒስትር ደመቀ መኮንን በበኩላቸው፤ “እስከዛሬ የፖለቲካ ፓርቲዎችን አቅም በመጠቀም ፋንታ ስንበትናቸው ቆይተናል፤ ሃገር ለአንድ ድርጅት አልተሰጠችም፤ ከዚህ በኋላ ለዚህች ሃገር የሁሉም የፖለቲካ ኃይሎች ሃሳብ አስፈላጊ ነው” ብለዋል፡፡
“የአማራ ክልል ለብአዴን የተሰጠ ስጦታ አይደለም” ያሉት አቶ ደመቀ፤ “ከጥላቻና መጠላለፍ ወጥተን በትነን የቆየነውን አቅም መጠቀም አለብን” ብለዋል፡፡ ተባብረን እንስራ ሲሉም ጥሪ አቅርበዋል፡፡ የተጀመረው ለውጥም ከዳር እንዲደርስ በትብብር መስራት እንደሚገባ አስገንዝበዋል፡፡
የብአዴን ምክትል ሊቀ መንበርና የአማራ ክልል ፕሬዚዳንት አቶ ገዱ አንዳርጋቸው ባደረጉት ንግግር፤ “ሁላችንም አብረን ከሰራን በኢትዮጵያ ፖለቲካ ከፍተኛ ተፅዕኖ በመፍጠር ለውጥ ማምጣት እንችላለን” ብለዋል፡፡

Read 6065 times