Saturday, 29 September 2018 14:24

የለውጥ ሂደቱ ከስሜት የፀዳ እንዲሆን የፖለቲካ ድርጅቶች ጠየቁ

Written by  አለማየሁ አንበሴ
Rate this item
(10 votes)

በሃገሪቱ የሚካሄደው ፖለቲካዊ ለውጥ ከስሜት የፀዳ እንዲሆን አርበኞች ግንቦት 7 እና ኦነግ የጠየቁ ሲሆን፤ ዜጐች የለውጥ ኃይሉን ተግባር ለማደናቀፍ ከሚደረጉ እንቅስቃሴዎች እንዲታቀቡ አሳሰቡ፡፡
የሁለቱ ድርጅቶች አመራሮች ከአሜሪካ ድምፅ ጋር ባደረጉት ቆይታ፤ ዜጐች ሕገወጥ በሆኑ ሰልፎች ከመሳተፍ፣ ግጭት ቀስቃሽ የሆኑ መፈክሮችን ከማሰማትና የለውጥ ሂደቱን ከሚያደናቅፉ እንቅስቃሴዎች መታቀብ አለባቸው ብለዋል፡፡   የኦነግ ሊቀ መንበር አቶ ዳውድ ኢብሣ፤ “ሰላማዊ እንቅስቃሴ ለማድረግ ወስነን የመጣን እንደመሆኑ አባሎቻችንና ደጋፊዎቻችን በትዕግስት እንዲንቀሳቀሱ እንመክራለን፤ እየመከርንም ነው” ብለዋል፡፡
መንግስት የህዝብን ሠላም የመጠበቅ ግዴታ እንዳለበት ያስታወሱት ሊቀመንበሩ፤ በሃገሪቱ የተለያዩ አካባቢዎች ለሚፈጠሩ አለመረጋጋቶች መንግስት መፍትሄ ለማበጀት የሚያደርገውን ጥረት እንደግፋለን ብለዋል፡፡
አባሎቻችንና ደጋፊዎቻችን ግጭት ቀስቃሽ ከሆኑ መፈክሮችና ሰልፎች እንዲታቀቡ እየመከርን ነው ያሉት የአርበኞች ግንቦት 7 የህዝብ ግንኙነት አቶ አበበ ቦጋለ በበኩላቸው፤ በቅርቡ በአዲስ አበባ በተደረገ ድንገተኛ ሠልፍ ላይ የተሰሙ “የኦሮሞ መንግስት ከአዲስ አበባ ይውጣ”፣ “ከንቲባ ታከለ ኡማ ከስልጣን ይልቀቁ”፣ “ዶ/ር ዐቢይ አህመድ ከስልጣን ይውረዱ” የሚሉ መፈክሮች የትኛውንም የፖለቲካ ድርጅት የማይወክሉ፣ ተገቢነት የሌላቸው መፈክሮች ናቸው ብለዋል፡፡
ህዝቡም ከእንዲህ አይነት የለውጥ እንቅፋት ድርጊቶች መታቀብ አለበት ብለዋል - አቶ አበበ፡፡
በለውጥ ኃይሉ የአንድነት ጥሪ እየቀረበ ባለበት በአሁኑ ወቅት ልዩነትንና ክፍፍልን የሚፈጥሩ ሃሳቦችን ህዝቡ መቀበል እንደሌለበት አርበኞች ግንቦት 7 አስታውቋል፡፡
የእርስ በርስ ግጭት የለውጥ እንቅፋት ነው ያሉት የፖለቲካ ድርጅቶቹ፤ ወደ ቀድሞ አፋኝ አካሄድ ላለመመለስ መጠንቀቅ አለብን ብለዋል፡፡

Read 5371 times