Saturday, 29 September 2018 14:24

የሰኔ 16ቱ የቦንብ ጥቃት ጠ/ሚኒስትሩን ለመግደል ያለመ ነበር ተባለ

Written by  አለማየሁ አንበሴ
Rate this item
(16 votes)

 - “ጥቃቱን ያቀነባበረችው ግለሰብ ነዋሪነቷ በኬንያ ነው” - ዐቃቤ ሕግ
   - ኦነግ ጉዳዩ አይመለከተኝም ብሏል

    ሰኔ 16 ቀን 2010 ዓ.ም በአዲስ አበባ መስቀል አደባባይ ለጠቅላይ ሚኒስትር ዶ/ር ዐቢይ አህመድ በተጠራው የድጋፍና የምስጋና ህዝባዊ ሰልፍ ላይ የተፈፀመው የቦንብ ጥቃት ጠ/ሚኒስትሩን ለመግደል ያለመ መሆኑን ዐቃቤ ሕግ የገለፀ ሲሆን ጥቃቱን ያቀነባበረችው ግለሰብ ነዋሪነቷ በኬንያ መሆኑን ለፍ/ቤት ተናግሯል፡፡
ትናንት አርብ ዐቃቤ ሕግ በአምስት ተጠርጣሪዎች ላይ የሽብርተኝነት ክስ የመሠረተ ሲሆን፤ ተከሳሾቹም አቶ ጌቱ ግርማ፣ አቶ ብርሃኑ ጃፋር፣ አቶ ጥላሁን ጌታቸው፣ አቶ ባህሩ ቶሎሳና አቶ ደሣለኝ ተስፋዬ ናቸው፡፡
“ተከሳሾቹ ጥቃቱን ለመፈፀም ያነሳሳቸው የአገሪቱ መንግስት መመራት ያለበት ቀድሞ በተመሠረተው የኦሮሞ ነፃነት ግንባር (ኦነግ) ነው” የሚል አላማ ይዘው መሆኑን ዐቃቤ ሕግ አስረድቷል፡፡
ዶ/ር ዐቢይ በኦሮሞ ህዝብ ዘንድ ተቀባይነት የላቸውም በማለት ተከሳሾቹ ለድርጊቱ መነሳሳታቸውን የጠቆመው ዐቃቤ ሕግ፤ ጠ/ሚኒስትሩ የኦሮሞ ህዝብን ፍላጐት አያስፈፅሙም የሚል እምነት ሰንቀው ለጥቃቱ መንቀሳቀሳቸውን ከምርመራ ግኝቱ ማረጋገጡን አሰታውቋል፡፡
የቦንብ ጥቃቱን ያቀነባበረችውም ነዋሪነቷ በኬንያ ናይሮቢ የሆነች ገነት ታምሩ (ቶለሺ ታምሩ) የምትባል ሴት መሆኗን ዐቃቤ ሕግ በክስ መዝገቡ ጠቁሟል፡፡
አንደኛ ተከሳሽ ጌቱ ግርማ፣ ከሁለተኛ ተከሳሽ ብርሃኑ ጃፋር ጋር ሱሉልታ ላይ በመገናኘት፣ “ሰልፉን የጠራው ኢህአዴግ ነው፤ በአሜሪካ ኮንግረስ የተላለፈው ኤች አር 128 ተግባራዊ እንዳይሆን ለማድረግ ነው፤ ስለዚህ ሰልፉ በቦንብ መበተን አለበት” በሚል መመካከራቸውን ዐቃቤ ሕግ በክሱ አመልክቷል፡፡
ተከሳሽ ጌቱ ግርማ ለሶስተኛ ተከሳሽ ደውሎም ቦንብ የሚወረውር ሰው እንዲያፈላልግ ተልዕኮ እንደሰጠው፣ ሁለተኛ ተከሳሽ በበኩሉ ሁለት “ኤፍ 1” እና አንድ የጭስ ቦንብ እንዳለው ገልጾ፣ ተከሳሾቹ ሱሉልታ ከተማ ላይ ተገናኝተው፣ የቦንቡን ጥቃት በሚያደርሱበት ሁኔታ ላይ ምክክር ማድረጋቸውን የክስ ዝርዝሩ ያስረዳል፡፡  ሶስተኛ ተከሳሽ ጥላሁን ጌታቸው፤ ቦንቡን እንዲያፈነዳ በአንደኛ ተከሳሽ እንደተነገረው፣ ከአራተኛ ተከሳሽ ባህሩ ቶላ ጋር በአምስተኛ ተከሳሽ ደሣለኝ ተስፋዬ መኖሪያ ቤት (ቡራዩ) መገናኘታቸውንና እዚያው አድረው ሰኔ 16 ቀን 2010 ዓ.ም ከንጋቱ 11 ሠዓት ላይ ሁለተኛ ተከሳሽ ብርሃኑ ጃፋር በሚያሽከረክረው የግል መኪና ቦንቦቹን በመጫን፣ አንደኛ ተከሳሽ ቤት ማስቀመጣቸውን የዐቃቤ ሕግ ክስ ያብራራል፡፡
በኋላም ሁሉም ፒያሣ አካባቢ በመገናኘት በምን መልኩ የቦንቡን ጥቃት ማድረስ እንዳለባቸው መወያየታቸውን፣ ከዚያም የዶ/ር ዐቢይ አህመድ ምስል ያለበትን ቲ-ሸርት በመልበስ ከሰልፈኞች ጋር በመቀላቀል በአምባሳደር አቅጣጫ ወደ መስቀል አደባባይ መግባታቸውንና ጠቅላይ ሚኒስትሩ ንግግር አድርገው ሲጨርሱ ቦንቡን ከመድረኩ በቅርብ ርቀት ወርውረው ማፈንዳታቸው በዐቃቤ ሕግ ክስ ላይ ተመልክቷል፡፡
ሰኔ 16 ቀን 2010 በተፈፀመው የቦንብ ጥቃት ሁለት ሠዎች ህይወታቸውን ሲያጡ፣ ከ160 በላይ የሚሆኑት ከባድና ቀላል አካላዊ ጉዳት እንደደረሰባቸው  ይታወቃል፡፡ የኦሮሞ ነፃነት ግንባር (ኦነግ) በበኩሉ፤ የቦንብ ጥቃቱም ሆነ ጥቃት አቀነባባሪና አድራሾቹ ከኔ ጋር ምንም አይነት ግንኙነት የላቸውም ብሏል፡፡ ጉዳዩ በፍ/ቤት የተያዘ በመሆኑ በሰፊው መነጋገር እንደማይቻል የገለፁት የኦነግ አመራር አባል አቶ ቶሌራ አዳባ፤ በክሱ የተጠቀሱት ግለሰቦች በሙሉ የኦነግ አባላት አይደሉም ብለዋል፡፡
የጥቃቱ አቀነባባሪ ተብላ የተጠቀሰችውና ነዋሪነቷ ኬንያ ነው የተባለችውንም ግለሰብ ኦነግ በአባልነት እንደማያውቃት የገለፁት አቶ ቶሌራ፤ ጉዳዩ በምንም አይነት መልኩ ኦነግን አይመለከትም ብለዋል፡፡  

Read 10494 times