Saturday, 29 September 2018 14:25

የብብታችንን ሳንጥል፤ የቆጡንም ማውረድ!

Written by  ሰገሌ - ከጀሞ
Rate this item
(1 Vote)


              የበጎ አድራጎት ድርጅቶችና ማህበራት አዋጅ ይሻሻል ወይስ ይሻር?
              

    የዚህ ጽሁፍ ዓላማ፣ በቅርቡ በመንግስት የተጀመረውን በጎ ለውጥ ተከትሎ፣ “የሲቪል ማህበረሰብ ድርጅቶች ረቂቅ አዋጅ” በሚል ርዕስ  ለውይይት የቀረበውን ሰነድ በመዳሰስ፣ በተመረጠ አንድ ዐቢይ ጉዳይ ላይ አስተያየት መስጠት ነው፡፡ ረቂቅ አዋጁ፤ በኢፌዲሪ ጠቅላይ ዓቃቤ ህግ ጽ/ቤት የህግ ጉዳዮች ማሻሻያ ምክር ቤት ተዘጋጅቶ፣ በወርሃ ነሐሴ 2010 ዓ.ም፣ በባለ ድርሻ አካላት፣ በመዲናችን አዲስ አበባ ውይይት ተደርጎበታል፡፡ በመገናኛ ብዙሃንም እንደተገለጸው፤ በያዝነው ወር፣ በተለያዩ የአገሪቱ ከተሞች፣ የሕብረተሰብ ተወካዮች በረቂቁ ላይ ይመክሩበታል፡፡  
ይህ ረቂቅ በየካቲት 6 ቀን 2001 ዓ.ም በነጋሪት ጋዜጣ የወጣውንና የበጎ አድራጎት ድርጅቶችና ማህበራት ቁጥር 621/2001 በመባል የሚታወቀውን አወዛጋቢ አዋጅ ይተካል ወይም ያሻሽላል ተብሎ ይጠበቃል፡፡ በረቂቅ አዋጁ መግቢያ ከሰፈሩት ጠቅለል ያሉ ሃሳቦች መካከል፤ “በኢትዮጵያ ፌዴራላዊ ዲሞክራሲያዊ መንግስት አንቀጽ 31 እንዲሁም ኢትዮጵያ ፈርማ በተቀበለቻቸው የተባበሩት መንግስታት የሲቪልና የፖለቲካ መብቶች ስምምነትና የአፍሪካ የሰዎችና ህዝቦች ቻርተር የተረጋገጠውን የመደራጀት መብት፣ በተሟላ መልኩ ተግባራዊ ለማድረግ፣ ህግ ማውጣት አስፈላጊ በመሆኑ…የሲቪል ማህበረሰብ ድርጅቶች ተጠያቂነትና ለዚህም የድርጅቶች የራስ በራስ አስተዳደርና ቁጥጥር የሚኖረውን ጉልህ ሚና በመረዳት….” የሚለው ክፍል የዚህ ጽሁፍ ማጠንጠኛ ነው፡፡  
እንደኔ፤ የራስ በራስ አስተዳደርና ቁጥጥር፣ የረቂቅ ዓዋጁ አስኳል ነው፡፡ የራስ በራስ አስተዳደርና ቁጥጥር፤ ከግልፅነት፣ ተዓማኒነትና ተጠያቂነት አንፃር በማየት፣ የረቂቅ አዋጁን ጥንካሬና ክፍተት በቅጡ  ለመረዳት፣ አሁን በስራ ላይ ያለው ህግ፣ መቼና እንዴት ባለ ሁኔታ እንደተዘጋጀ ማስታወስ ያስፈልጋል፡፡
በሥራ ላይ ያለው ዓዋጅ 621/2001 የፀደቀበት ነባራዊ ሁኔታ አስገራሚም አስደማሚም ነበር። በአገሪቱ ሕጋዊ ሆነው በሚንቀሳቀሱ ፓርቲዎች መካከል አስደናቂ ሙግት የታየበት፣ መዲናችን አዲስ አበባ ሁለት ታላላቅ መሬት አንቀጥቅጥ ሕዝባዊ ሠልፎችን ያስተናገደችበት፣ ብዙሃን በምርጫው የተሳተፉበት፣ ለመጀመሪያ ጊዜ አዲስ አበባ ከተማ ላይ ተቃዋሚዎች አሸንፈዋል ሲል መንግስት ያመነበት፣ በ”ፓርላማ እንግባ-አንግባ” አተካሮ በተቃዋሚዎች መካከል ልዩነት የተፈጠረበት፣ ምርጫ ተጭበርብሯል በሚልና ሌሎች ምክንያቶች ህዝብ ወደ አደባባይ የወጣበት፣ ፖሊሲና የፀጥታ ሃይሉ ያልተመጣጠነ እርምጃ ወስደዋል ተብለው የተነቀፉበት …..ወዘተርፈ ታሪካዊው የ97 ምርጫ ማግስት ነበር፡፡
መንግስትና ደጋፊዎቹ በተደጋጋሚ እንደገለጹት፤ “የበጎ አድራጎት ድርጅቶችና የሲቪል ማህበራት በምርጫ ሂደቱ ውስጥ አሌ የማይባል ሚና ነበራቸው፡፡ በተለይ በከተሞች አካባቢ ሕዝቡ ለመብቱ እንዲታገል አስተምረዋል፣ ድምፁንም ይጠቅመኛል ብሎ ላመነበት ተወዳዳሪ እንዲሰጥ ቀስቅሰዋል፤ ነፃና ገለልተኛ መሆናቸውን እየሰበኩ፣ በተግባር አድሎአዊነትን አሳይተዋል” በማለት ይከሷቸዋል፡፡
በሌላ በኩል፤ የተቃዋሚ ጎራው መሪዎች፣ አገር በቀልና ዓለም አቀፍ የበጎ አድራጎት ድርጅቶች፣ የተባበሩት መንግስታት ድርጅቶች እንዲሁም ምዕራባዊያን መንግስታት፤” በምርጫው ሂደትና ውጤት ባልገመተውና ባላሰበው መጠን ፍልሚያ የገጠመው ገዢው ፓርቲ፣ አፈር ልሶ ከተነሳ በኋላ ከንክሻ እንዳመለጠ አውሬ ተገዳድረውኛል ያላቸውን አካላት፣ በግልጽም በስውርም ለመበቀል እንዲያመቸው፣ “አጥፊውን ከአልሚው” ሳይለይ መፈናፈኛ አሳጥቶ፣ በሞትና በሕይወት መካከል የሚያኖር፣ አስጨናቂ ሕግ አርቅቆ አፅድቋል” ሲሉ መንግስትን ክፉኛ ይተቹታል፡፡ ለምሳሌ ያህል ከሰኔ 11 ቀን እስከ 19/2004 ዓ.ም የተባበሩት መንግስታት የሰብዓዊ መብት ጉባኤ ላይ እንዲቀርብለት አምነስቲ ኢንተርናሽናል፤ ሰኔ 4 ቀን 2004 ዓ.ም ያረቀቀውን ሠነድ ማየት ብቻ በቂ ነው፡፡ አምነስቲ ኢንተርናሽናል፤ የኢትዮጵያ መንግስት ያፀደቀውን የበጎ አድራጎት ድርጅቶችና ማህበራት አዋጅ ሲገልፀው፤ “በሰብዓዊ መብት ተሟጋች ድርጀቶች ላይ ከልክ ያለፈ ጫና የሚያሳድር፣ በበጎ ስራዎቻቸውም እንቅፋት የሚፈጥርና በመሪዎቻቸውም ላይ ፍርሃት የሚያነግስ ነው” ይለዋል፡፡ በዚሁ ሰነድ ገፅ ሁለት ደግሞ፤ ሕጉ በበጎ አድራጎት ድርጅቶችና ማህበራት ላይ ባደረሰው ጫና በተለይም የገቢ ምንጫቸውን በማድረቁ ብቻ ታዋቂ የሠብዓዊ መብት ተሟጋች ተቋማትን ጨምሮ፣ 17 ያህል ድርጅቶች ዓላማቸውን እንዲቀይሩ አስገድዷቸዋል፡፡ የኢትዮጵያ ሠብዓዊ መብት ጉባዔና የሴት ሕግ ባለሙያ ማህበርን ጨምሮ፣ በተመሳሳይ የስራ ዘርፍ የተሰማሩትን ደግሞ ተሳትፏቸው እንዲቀንስና እንዲሽመደመዱ አድርጓቸዋል፤ ይላል፡፡
በአሁኑ ወቅት እራሱን  “በጥልቅ የሚያድሰው” ገዢው ፓርቲ፣ ያለፈ ጉድለቱን ሳይኮንን፣ የነባሩን ሕግ አፈፃፀም ሳይገመግምና ለማሻሻያው በቂና አሳማኝ ምክንያት ሳያስቀምጥ፣ በሕግ አግባብ፣ በበጎ አድራጎት ድርጅቶችና ማህበራቱ ላይ የፈፀመውን አፈና ተጣድፎ የሚያነሳው ይመስላል፡፡
የበጎ አድራጎት ድርጅቶችና የሲቪል ማህበራቱ፤ በየትኛውም አገር በበርካታ ዘርፎች ተሳትፎ በማድረግ፣ የሰውን ልጅ የኑሮ ደረጃ የሚያሻሽሉ ሥራዎችን በማከናወን፣ የመንግስትን ክፍተት የሚሞሉ፣ በተለይም የሠው ልጆችን መብት ለማስከበር የሚተጉና ማህበራዊ አገልግሎት የሚሰጡ ተቋማት ናቸው። ኢትዮጵያ ሀገራችን በዘመናት መካከል የገጠማትን የረሃብ፣ የእርስ በርስ ግጭት፣ የጦርነትና ኋላቀርነት አደጋን ለመመከት ባደረገቻቸው ትግሎች፣ በተለይ የውጭ ሀገራት በጎ አድራጎት ድርጅቶች አስተዋጽኦ ከፍ ያለ ነበር፡፡ መንግስትና እነዚህ ለትርፍ ያልተቋቋሙ አካላት፤ ዴሞክራሲንና መልካም አስተዳደርን በማስፈን፣ ፍትሐዊ የሀብት ክፍፍል እንዲፈጠር በማድረግ፣ የህብረተሰብ ተሳትፎ ከፍ እንዲል፣ የኑሮ ደረጃው እንዲሻሻልና በሌሎች በርካታ ጉዳዮች ላይ በትብብር ይሰራሉ፡፡ ከላይ በጥቂቱ ከተዘረዘሩት በጋራ የሚሰሩባቸው ጉዳዮች በተጨማሪ፣ የሃብት ክፍፍል፣ የሥራ ዘርፍና ቦታ/ አካባቢ መረጣ፣ የሰው ልጆች መብት አረዳድና አተረጓጎም እንዲሁም ግልፅነት፣ ተዓማኒነትና ተጠያቂነት የመሳሰሉ በተደጋጋሚ የሚወዛገቡባቸው አልፎ አልፎም የሚጋጩባቸው ስስ ብልቶች አያጡም፡፡
መንግስታዊ ያልሆኑ ድርጅቶች፤ ጊዜያዊና አስከፊ አደጋ ሲያጋጥም፣ በእለት ደራሽ እርዳታቸውና ርህራሄያቸው፣እንዲሁም ዘላቂ ልማትን ለመደገፍ በሚያሳዩት ያልተቆጠበ ጥረትና የሰብዓዊ መብት እንዲከበር በሚከፍሉት ዋጋ ያስደነቁንን ያህል በሰጪና ተቀባይ መርህና ፍልስፍናቸው፣ ጫና ሊያሳድሩ ሲሞክሩ አይመቹንም፡፡ አብዛኞቹ የበጎ አድራጎት ድርጅቶች በተገቢው መንገድ የሚንቀሳቀሱ ቢሆንም፣ እናገለግለዋለን የሚሉትን የሕብረተሰብ ክፍል ኑሮ የማያውቁ፣ በአንደበታቸው የሚናገሩትንና በወረቀት ያሠፈሩትን ያህል አገልግሎት የማይሰጡ፣ ከተረጂውና ተጠቃሚው ችግርና ሥቃይ ይልቅ የረጂዎችን የልብ ትርታ የሚያዳምጡና የተጠያቂነት ርዕስ ሲነሳባቸው፣ ብርክ የሚይዛቸውም አይጠፉም፡፡ በነዚህና ሌሎች አያሌ ምክንያቶች ሥራን የሚያቀላጥፍ፣ በነገሮችና መሪዎች መለዋወጥ የማይናወጥ፣ ሁሉን በእኩል የሚያይ ወጥ የሆነ ሥርዓት ወይም ህግ ያስፈልጋል፡፡
ሕግ ከዚህ አትለፍ፣ ከዚህም አትትረፍ --- ባለ ጊዜ የሰውን መብት የሚወስን አይደለም፡፡ ነገር ግን የሰጠውን የግሉንም የማህበራዊውንም መብት በመጠበቅ፣ ለሰው ልጅ ሁሉ ሚዛናዊ ሕይወት ሰጥቶ፣ ዓለሙን እንዲጠቀምበት ያደርገዋል፡፡ (ቀዳማዊ ኃይለሥላሴ፤ ከመጽሐፍ ሕግጋት ዓበይት)
ሕግ የሰውን የግሉንም የማህበራዊውንም መብት በመጠበቅ፣ ከዚህ አትለፍ ከዚህም አትትረፍ ማለት አለበት፡፡ ሕግ፤ ግለሰቦችም ሆኑ ቡድኖች፣ የሌሎችን የኑሮ ዘይቤ ሳያፋልሱ እንዲኖሩ የሚረዳ ሥርዓት ነው። ዋናው ርዕሳችን፣ የራስ በራስ አስተዳደርና ቁጥጥር መርህም የሚመሠረተው፤ ግልጽነት ተዓማኒነትና ተጠያቂነት በሚረጋገጥበት የሕግ አግባብ ነው፡፡ ሕጉ፤ ለማንም ሶስተኛ ወገን በሚገባ ቋንቋ/አገላለጽ፤ የድርጅቱ ክንዋኔ፣ ከራዕዩ ከዓላማውና ዕሴቶቹ ጋር የሚጣጣም መሆኑን በማረጋገጥ ለአፈፃፀም፣ ክትትል፣ ቁጥጥርና ግምገማ ሁኔታዎችን ማመቻቸትና መደገፍ አለበት፡፡ የራስ በራስ አስተዳደርና ቁጥጥር፣ በአግባቡ በሚሰራባቸው ያደጉና አንዳንድ የእስያ አገራት፣ መንግሥታዊ ያልሆኑት ድርጅቶች፣ ከመንግሥት ጣልቃ-ገብነት ነፃ በሆነ መንገድ፣ የሚተዳደሩበት ሁኔታ እንዳለ ይታወቃል፡፡ እነዚህ አገራት ወደተጠቀሰው የአሠራር ደረጃ ለመድረስ፣ ብዙ ውጣ- ውረድ አሳልፈዋል፡፡ በአገራችን ተጨባጭ ሁኔታና ጥድፊያ፣ ከተረቀቀው ሕግ አንፃር፣ ሁሉም መንግሥታዊ ያልሆኑ አካላት፣ በተፈለገው ደረጃና ዝግጅት ላይ መሆናቸውን የሚያሳይ በጥናት የተደገፈ ማስረጃ አይገኝም፡፡ ረቂቅ ሕጉም፤ የመንግሥት እርዳታና ጣልቃ ገብነትን መጠን፣ በበቂ ሁኔታና ዝርዝር አላካተተም፡፡ የመንግሥት እርዳታና ጣልቃ ገብነት፣ በዋነኛነት የሚያስፈልገው፣ የድርጅቶቹን አሠራር ሳያደናቅፍና ሕልውናቸውን ሳይጋፋ፣ የሕብረተሰቡ ድርሻ/ ተጠቃሚት ሳይጓደል፣ መድረሱን/ መፈፀሙን ለማረጋገጥ ነው፡፡
በሌሎች አገራት እንደታየው፤ መንግሥታዊ ያልሆኑት ድርጅቶች፣ የራስ በራስ አስተዳደርና ቁጥጥርን አጥብቀው የሚሹት፣ በነፃነት እንዲገቡና እንዲወጡ በመፈለግ ብቻ ሳይሆን የመንግሥትን ጣልቃ ገብነትና ቢሮክራሲን ለመቀነስ/ለመከላከል፣ የመገናኛ ብዙሃንና ተቆርቋሪ ተቋማትን፣ በተለይም የመርማሪ ጋዜጠኞችን ክትትል፣ ማጋለጥና ነቀፋ ለመሸሽም ጭምር ነው፡፡ በእርግጠኝነት ለመናገር ባይቻልም፣ የራስ በራስ አስተዳደርና ቁጥጥር፣ በከፊል ውጤታማ የሚሆነው፣ ከምዕራባውያን ለጋሽ አገራትና ታላላቅ ዓለም አቀፍ ድርጅቶች ከሚገኝ እርዳታ ጋር ተያያዥነት ባላቸው ዘርፎች ብቻ ነው፡፡ ይህም የሆነው ምዕራባውያኑ አገራትና ታላላቅ ዓለም አቀፍ ድርጅቶች፣ ለዘመናት ያዳበሩት ክእርዳታ ማመልከቻ ቅጽ መሙላት ጀምሮ፣ ወጪንና የሥራ አፈፃፀምን የሚከታተሉበት፣ የሚገመግሙበትና ሃብት ባልተፈለገ መንገድ ባክኖ ሲገኝ፣ ኃላፊዎችን ተጠያቂ የሚያደርጉበት ሥርዓት ስላዳበሩ ነው፡፡ መንግሥታዊ ያልሆኑ ድርጅቶችና ማህበራቱ ደግሞ የገቢ ምንጫቸው ከላይ የጠቀስናቸው አካላትና ጥብቅ የቁጥጥር ዘዴ የሌላቸው በርካታ የንግድ ድርጅቶች፣ ቸር ግለሰቦችና የሃይማኖት ተቋማትም ጭምር ናቸው።
ረቂቅ አዋጁ በግርድፉ ሲታይ፣ መንግሥታችን፣ ይበል የሚያሰኝ፣ የለውጥ ሥራ መጀመሩን በገሃድ ያሳያል፡፡ ነገር ግን በሥራ ላይ ያለው ሕግ ያካተታቸውንና ለአገርና ለሕዝብ ጠቃሚ የሆኑትን አንቀጾች ጠራርጎ አጥፍቷቸዋል፡፡ ይህን ስጋት በትክክል መረዳት የሚችለው፣ በ112 አንቀጾች ተደራጅቶ የተዘጋጀው የቁጥር 621/2ዐዐ1 ነባር አዋጅና በ51 ክፍሎች አካባቢ ተቀንብቦ ለውይይት የቀረበውን ረቂቅ ሰነድ ጎን-ለጎን አስቀምጦ፣ በዕውቀት የገመገመ ባለሙያ ብቻ ይመስለኛል፡፡
ረቂቅ አዋጁ፣ በጎውን ለመትከል፣ሁሉንም መንቀል አይጠበቅበትም፡፡ ለምሣሌ፣ በአወዛጋቢው ሕግ 621/2ዐዐ1 አንቀጽ 88 የተጠቀሰውን የ7ዐ/30 ቀመርን፣ በአስረጂነት ማንሳት መልካም ነው፡፡ በአዋጁ ውስጥ ከተካተቱት በርካታ አፋኝ ደንቦች ሁሉ የሚብሱት - 70/30 እና 90/10 ተጠቃሽ ናቸው፡፡ የመጀመሪያው፣ በክፍል ሰባት አንቀጽ 88፣ የአስተዳደራዊና የዓላማ ማስፈፀሚያ ወጪዎችን ጣሪያ ሲያስቀምጥ፣ ሁለተኛው፣ በክፍል አንድ ትርጓሜው ሥር፣ ቁጥር 2፡2 የኢትዮጵያ በጎ  አድራጎት ድርጅት ወይም ማህበር የሚላቸው አገር በቀል ተቋማት፣ ከውጭ አገር የሚያገኙት ገቢ ከአሥር በመቶ እንዳይበልጥ ያገደበት ርህራሄ-የለሽ ደንብ ነው፡፡  ይህ የ90/10 ሕግ፤ አፋኝ፣ ትርጉም የሌለውና ሀቅንም የሚክድ ሆኖ ስለሚቆጠር ቢነቀል የሚከፋው ያለ አይመስለኝም፡፡ ነገር ግን ማንኛውም ባለ አእምሮ ሰው እንደሚረዳው፤ ከ70/30 አጠቃላይ ቀመር ይልቅ አሳሳቢው ጉዳይ፣ በአዋጁ ውስጥ “አስተዳደራዊ ወጪ ማለት--” ተብሎ የተሰጠው ትርጓሜና ለአፈፃፀም በተዘጋጀው መመሪያ ውስጥ ምን ምን ወጪዎች፣ በ3ዐ ወይም 7ዐ ሥር ተካተቱ የሚለው መሆን አለበት፡፡ በማንኛውም ዘዴ ተሰብስቦ ለሕዝብ ጥቅም የሚውልን  ሃብት፤ የአስተዳደራዊ ወጪን ጣሪያ እንደ ሥራው ጠባይ ተመካክሮ መወሰን ስህተት ሊሆን አይችልም፡፡ ደጋግሞ መታሰብ ያለበት፤ ምን ምን ወጪዎች አስተዳደራዊ፣ የትኞቹስ ቀጥተኛ የኘሮጀክት ናቸው የሚለው ሃሣብ ነው፡፡ የአስተዳደራዊ ወጪ፤ ገደብ ተጣለበትም አልተጣለበት፣ መጠኑ አነስተኛ እንዲሆን ይጠበቃል፡፡
ወደ ዋናው ጉዳያችን ስንመለስ፤ረቂቅ አዋጁ፣ በገጽ 4 ቁጥር 2፡10 ላይ “የራስ በራስ አስተዳደር ማለት-- የሲቪል ማህበረሰብ ድርጅቶች፣ እራሳቸውን ለማስተዳደር ተሰባስበው በሚያወጡት የሥነምግባር ደንብ መሠረት የሚቋቋም፣  የቁጥጥርና አስተዳደር ሥርዓት ነው” ይላል፡፡ በገጽ 1ዐ ላይ ደግሞ ስለሚቋቋመው ተቆጣጣሪ ኤጀንሲ ቦርድ፤ ሥልጣንና ተግባራት ሲያትት፤”የሲቪል ማህበረሰብ ድርጅቶች፣ የራስ በራስ ቁጥጥርና ተጠያቂነትን ለማጠናከር ሊወሰዱ የሚገባቸው እርምጃዎች ላይ ምክረ ሃሣብ ያቀርባል” ይላል፡፡ በሰነዱ ክፍል ሁለት፤ ሂሣብና ሪፖርቶች ተብለው በተዘረዘሩት ቁጥሮች ውስጥ በአጠቃላይ የድርጅቱን ወጪና ገቢ በተመለከቱ ጉዳዮች ዙሪያ፣ ስለሚዘጋጀውና በተፈለገ ጊዜ ስለሚቀርበው ሪፖርት በስተቀር ድርጅቶቹ በአገሪቱ ሕግ መሠረት ሊከተሉት ስለሚገባቸው አሠራሮች ፍንጭ አይሰጥም፡፡ ይህ ክፍል መንግሥታዊ ያልሆኑትና ለትርፍ ያልተቋቋሙት ድርጅቶች፣ለሚወስዱት እርምጃ ሁሉ ተጠያቂነት እንደሚኖርባቸው፣ ግልጽነት በተለይም በገንዘብ አጠቃቀም ረገድ አስፈላጊ መሆኑን፣ ተዓማኒነትን በተመለከተ መንግሥት እንደማይደራደርና በሕዝብ ላይ ጉዳት ቢደርስ፣ የማያወላዳ እርምጃ ሊወስድ እንደሚገደድ ማሳወቅ ሲገባው፣ ሁሉንም አሳሳቢ ጉዳይ በየራስ በራስ አስተዳደርና ቀጥጥር ሥር ወሽቆታል፡፡ አገራችን ያለችበት ሁኔታ ከግንዛቤ ሳይገባ፣ በሥራ ላይ ያለው ሕግ በአግባቡ ሳይገመገም፣ የሲቪል ማህበራቱ መረዳት፣ ችሎታና ተሞክሮ ሳይመዘን፣ ሁሉንም ነገር ጠቅልሎ፣ በየራስ በራስ አስተዳደርና ቀጥጥር ዕሳቤ ሥር ማስገባቱ፣ ትክክለኛው አካሄድ አይመስለኝም፡፡
በዚህ የውይይት ወቅት ዕድሉን ያገኘን ተቆርቋሪዎች፣ በስሜት ሳይሆን በዕውቀትና በማስረጃ እየደገፍን፣ ለሕግ አውጭዎች ቀናውን መንገድ ማሳየት በተለይም የራስ በራስ አስተዳደርና ቁጥጥርን በጎ ጎንና ጉድለቱን፣ የሲቪል ማህበራቱም ሊከተሉት የሚገባቸው መርሆዎችና ከመንግሥት ጋር ስለሚመሰርቱት ጥብቅ ትብብር አስፈላጊነት በዝርዝር መነጋገር እንደሚያስፈልግ ማሳሰብ ይጠበቅብናል፡፡
የመንግሥትና መንግሥታዊ ያልሆኑ ድርጅቶች ትብብር ስኬት የሚረጋገጠው፣ ሁሉም አካላት የሚግባቡባቸው መሠረታዊ መርሆዎችን በግልጽ ሲያስቀምጡ፣ መረጃ የሚለዋወጡበትን መስመር ሲዘረጉና ውጤታማ ለሆነ የሥራ ክንዋኔ አቅም ሲያዳብሩ ነው፡፡ መንግሥት ለትርፍ ያልተቋቋሙትን ብቻ ሳይሆን የማንኛውንም ሕጋዊ አካል ግልጽነት፣ ተዓማኒነትና ተጠያቂነትን ለማረጋገጥ በቅርበት እንደሚሠራ መግለጽ አለበት፡፡ ሕጉ በአንድም ይሁን በሌላ መንገድ የድርጅቶቹ መሪዎች፣ ሠራተኞቹም ሆኑ ሸሪኮቻቸው፤ ለሚፈጽሙት ተግባር፣ በተጠየቁ ጊዜ ምክንያት እንዲያቀርቡና ኃላፊትንም እንዲወስዱ አስገዳጅ የተጠያቂነት ሥርዓት ማኖር አለበት፡፡ ድርጅቶቹ ከሥራቸው ጋር ተያያዥ የሆኑ መረጃዎችን  ሰብስበው በማደራጀት፣ ለማንኛውም ሕጋዊ አካል የሚያቀርቡበትን የግልጽነት ባህል በማዳበር፣ ለደጋፊዎቻቸው ለመንግሥትና ለሚያገለግሉት ሕዝብ ማሳየት ይጠበቅባቸዋል፡፡ እራሳቸውም ሆኑ ጥምረቶች ለሚያወጡት ደንብ ተፈፃሚነት ተግተው የሚሰሩ እንዲሆኑም ምሪት ያስፈልጋቸዋል፡፡ በአጠቃላይ የረቂቅ አዋጁ ዋና ሃሣብ፣ የራስ በራስ አስተዳደርና ቁጥጥርን ማካተት ከሆነ፣ ነባሩና በሥራ ላይ ያለውን ሕግ ተጣድፎ ከመሻርና ጎዶሎ ሕግም ከማርቀቅ፣ የታለመውን ግብ ሊያሳኩ የሚችሉ ነጥቦችን አካትቶ፣ የተጣመመውን በማቅናትና አፋኙን ለይቶ በማስወገድ፣ ማሻሻያ ቢደረግ፣ የብብታችንን ሳንጥል፤ የቆጡንም ማውረድ ያስችለናል፡፡
ዕድሜ ይስጥልኝ!!

Read 2314 times