Saturday, 29 September 2018 14:26

ተምኔታዊው አንቀጽ 39

Written by  ደረጀ ይመር
Rate this item
(1 Vote)


    መግቢያ
እንደ ጎሮጎሬሲያኑ አቆጣጠር በ1977 የተቀረጸው የቀድሞዋ ሶቪየት ኅብረት ሕገ መንግሥት አንቀጽ 72 እንደሚያትተው፤ የሶሻሊስት ፌደሬሽኑን የመሠረቱት 15 ሀገሮች(nation states) ባሻቸው ጊዜ ከፌደሬሽኑ መገንጠል የሚችሉበትን ዋስትና ይሰጣል፡፡ “Each union Republic shall retain the right freely to seced from the USSR” ይላል አንቀጹ፡፡ በዚህ ሕገ መንግሥታዊ ዋስትና መሠረት፤ ታላቋ ሶቪየት ኅብረት  ሉአላዊ ወደ ሆኑ ጥቃቅን ባናና ሪፐብሊኮች ለመቀየር የፈጀባት ጊዜ ሁለት አስርተ ዓመታት ብቻ ነበር፡፡ የሶቪየት ኅብረትን የመበታተን ሒደት ያለ ምንም ደም መፋሰስ ገቢራዊ እንዲሆን ከረዱት ነባራዊ እውነታዎች መካከል አንዱ፣ ሁሉም የፌደሬሽኑ አባላት፣ በኅብረቱ ከመታቀፋቸው በፊት ግልጽ ያለ እና የማያሻማ ወሰን ባለቤት በመሆናቸው ነበር፡፡ የፌደሬሽኑ አባል ሀገራት ቀደም ሲል በዓለም አቀፉ ማኅበረሰብ ዘንድ ጭቅጭቅ የማያስነሳ፣ የታወቀ ሉአላዊ ድንበር ስለነበራቸው፣ የመበታተኑን ሂደት በርችትና በፈንጠዚያ ለመከወን ተችሏል፡፡  
ይህንን የሶቪየት ኅብረትን የውድቀት ተመክሮ በሕገ መንግስቷ ያካተተች አፍሪቃዊት ሀገር ኢትዮጵያ ብቻ ናት፡፡ ምንም እንኳን ልክ እንደ 1977ቱ የሶቪየት ኅብረት ሕገ መንግሥት አንቀጽ 72፣ የኢፌዲሪ ሕገ መንግሥት አንቀጽ 39፣ ለመገንጠል መብት የይለፍ ፍቃድ  ቢሰጥም፣ ሀገራችን ካላት ውስብስብ ታሪካዊና ባህላዊ ነባራዊ ሁኔታዎች እንዲሁም በሌሎች ዓለም አቀፋዊ ኹነቶች ምክንያት፣ አንቀጹ ከወረቀት ያለፈ ፋይዳ እንደማይኖረው ተንታኞች ያስረዳሉ፡፡  
የመገንጠል ጥያቄ የሀገራችንን ፖለቲካ መጣባት የጀመረው ከተማሪዎች ንቅናቄ አንስቶ ሲሆን አጀንዳው በዚህ ዘመንም የአንዳንድ የጎሳ ድርጅቶች ዋንኛ ርዕሰ ጉዳይ መሆኑን ስንመለከት፣ ከ1960ዎቹ የፖለቲካ አዙሪት አሁንም እንዳልተላቀቅን  አንዱ ማሳያ ሊሆንልን ይችላል፡፡ የመገንጠል ጥያቄ የተማሪዎች ንቅናቄ አሻራ ያረፈባቸው የፖለቲካ ቡድኖች ለጥራዝ ነጠቅ የማርክሲዝም ሌኒኒዝም ርዕዮተ-ዓለም ያላቸውን አምልኮ በገሀድ ያስመሰከሩበት ነው፡፡ እስከ ቅርብ ጊዜ ድረስ የሀገሪቱን የፖለቲካ መንበር አውራ ሆኖ ሲዘውራት የነበረው ሕወሓት፣ በዛ በሩቁ ዘመን በ1968 ዓ.ም በቀረጸው ማኒፌስቶው ላይ ያሰፈረው ታላቋን የትግራይ ሪፐብሊክ የመመስረት ተምኔታዊ ህልም የተወለደው፣ ከዚሁ ከተንሸዋረረ የማርክሲዝም ሌኒኒዝም ቀኖና ነው፡፡
ይህ የባእድ ሀገርን ዕውቀትና ፍልስፍና ሳይፈትሹ እንዳለ የመቅዳት አባዜ፣ ሲወርድ ሲዋረድ መጥቶ፣ የ1987ቱን  ሕገ መንግሥት አንቀጽ 39 ሊወልድ ችሏል፡፡ አንቀጹ በኢህአዴግ ዓይን፣ የሕገ መንግሥቱ የማእዘን ድንጋይ ነው። በዚህ አንቀጽ መደለያ መሠረት፤ የሀገራችን ሕዝቦች በግድ ከላይ የተጫነባቸውን ድንበር እንደ ዘላቂ ወሰን በመቁጠር ወደፊት ለሚፈጥሯት ሉዓላዊ ሀገራቸው፣ ራሳቸውን ተምኔታዊ  ቅርቃር ውስጥ እንዲጨምሩ ተፈርዶባቸዋል፡፡

የአንቀጹ ተምኔታዊ ባሕሪያት
 በ1987ቱ ሕገ መንግሥት ላይ ከሰፈሩት አወዛጋቢ አንቀጾች መካከል የራስን ዕድል በራስ የመወሰን ዕድል እስከ መገንጠል የሚለው አንቀጽ 39 ዋንኛው እንደሆነ ይታወቃል፡፡
ነገሩን ውሉን የሳተ ነው የሚያስብለው ደግሞ፣ ይህንን ለፖለቲካ ትርፍ ሲባል እንደ ዋዛ ሕገ መንግስታዊ ግርማ ሞገስን እንዲላበስ የተደረገው ጠንቀኛ አንቀጽ፤ ለአፍሪካ አንድነት (ፓን-አፍሪካኒዝም) ምልክት በሆነችው ሀገራችን ኢትዮጵያ ላይ መተከሉ ነው፡፡
በአንቀጽ 39 መሠረት፤ አንድ ክልል ከፌደራል መንግሥቱ ተገንጥሎ፣ ሉአላዊ ሀገር ለመሆን የሚከተሉትን ቅደመ ሁኔታዎች ማሟላት ይጠበቅበታል፡- በቅድሚያ መገንጠል የፈለገው ክልል ምክር ቤት፣ ጥያቄውን በ2/3ኛ ድምጽ ማሳለፍ ይኖርበታል፡፡ በመቀጠል ይህንን ውሳኔ ተቀብሎ የፌደሬሽን ምክር ቤት ለሕዝብ ውሳኔ የሚረዳ ሪፈረንደም ያዘጋጃል፡፡ ሪፈረንደሙ በአብላጫ የሕዝብ ድምጽ መደገፍ አለበት። በመቀጠል የፌደራል መንግሥቱ ሉአላዊ ሥልጣኑን መገንጠል ለሚፈልገው ክልል ያስተላልፋል። ምናልባትም ይህኛው ንዑስ አንቀጽ፣ በአንጻሩ ውስብስብ ይመስላል። በአጠቃላይ አንቀጹን ተምኔታዊ /utopia/ ባህሪያትን ተላብሷል የሚያስብሉትን ምክንያቶች በዝርዝር ላቅርብ፡፡
ይህን አንቀጽ ከተጻፈበት ወረቀት ባለፈ ተጨባጭ እንዳይሆን የሚያደርጉት ውስጣዊ እና ውጫዊ ነባራዊ ሁኔታዎች ናቸው፡፡ ከውስጣዊው ነባራዊ ሁኔታዎች ስንነሳ በክልሎች መካከል የተፈጠረውን ድንበር ታሪካዊ መሠረት መለስ ብለን ማጤን ይኖርብናል፡፡ የክልሎች ወሰን የተበጀው በትጥቅ ትግል የበላይነት ባገኘው ቡድን ህወሓት/ኢህአዴግ ፊታውራሪነት የተዘጋጀውን ሰነድ (ሕገ መንግሥት) ተከትሎ፣ ከላይ ወደ ታች በዘፈቀደ በመጫን ነበር፡፡ የድንበር አወሳሰኑ የታሪክ፣ የመልክአ ምድር ኩታገጠምነት፣ የስነልቦና ትስስርንና ባህልን ወደ ጎን በመግፋት፣ ለጊዜያዊ የፖለቲካ ትርፍ ሲባል በወጉ ያልተከወነ ነው፡፡ ኩታገጠም ዘውጌ ማኅበረሰቦች ያለ አበሳቸው ማዶ ለማዶ ሆነው በጎሪጥ እንዲተያዩ ተፈርዶባቸዋል፡፡ በዚህም ምክንያት ላለፉት ሁለት አስርተ ዓመታት ያስተናግድናቸው የድንበር ግጭቶች ለቁጥር የሚታክቱ ናቸው፡፡
እንግሊዛዊው ፈላስፋ ቶማስ ሆብስ፤ ጠንካራ መንግሥት በሌለበት ሀገር ውስጥ ሁሉም የአዳም ዘር እርስ በርሱ የሚጫረስበትን የእልቂት ነጋሪት ይጎስማል እንዳለው ሁሉ፣ ተምኔታዊውን አንቀጽ ወደ ገሀዱ ዓለም ለማምጣት ብንነሳ፣ በሺ በሚቆጠሩ የድንበር ይገባኛል ጥያቄዎች ምክንያት፣ በሰው ልጅ የታሪክ ሂደት ታይቶ ወደ ማይታወቅ ፍጹም ገሀነማዊ ዓለም ውስጥ ሰተት ብለን መግባታችን የግድ ይሆናል፡፡ በክልሎች መካከል የተፈጠረው ድንበር ከዚህ ቀደም በዓለም አቀፍ ማኅበረሰብ ዘንድ እንደ ሉአላዊ ወሰን ተቆጥሮ አያውቅም፡፡ ስለዚህ በሕግ ፊት ቅቡልነት ሊኖረው አይችልም፡፡ የትኛውም የዘውጌ ማኅበረሰብ የአባቶቹን አፈ-ታሪክ ዋቢ በማድረግ፣ የግዛት ይገባኛል ጥያቄ ለማንሳት ምንም አይነት የሞራልም ሆነ የሕግ እቀባ ሊያግደው አይችልም፡፡ ልክ እንደ ጥንቱ ዘመነ-መሳፍንት፣ አቅሙና ጉልበቱን የታደለ ኃይል ሰፊ ግዛት ለመጠቅለል በሚል መነሻ በሁሉም አቅጣጫ የዕልቂት አውድን ይከፍታል፡፡
ሩቅ ሳንሄድ ባለንበት ዘመን፣ ጽንፍ የረገጡ የዘውጌ ፖለቲካ አራማጆች፣ የግዛት ይገባኛል ጥያቄ የሚያስነሳ ካርታን እንደነደፉ በገሀድ እየተመለከትን ነው፡፡ ለአብነት ያህል አክራሪው የኦሮሞ ብሔርተኛው ቡድን፣ ድንበሩ እስከ ደቡብ ትግራይ ድረስ የሚዘልቅ ካርታ አለው። በተመሳሳይም፤ የአማራው ወገን ከራያ አዘቦ አንስቶ፣ በራራን (አዲስ አበባን) አካትቶ፣ እስከ ፋጥጋር (አርሲ) ድረስ የሚዘልቅ ካርታ ባለቤት ነው፡፡ ስለዚህ አሁን በክልሎች መካከል የተፈጠረውን ድንበር ተንተርሰን፣ አንቀጽ 39ን ለመተግበር ብንነሳ፣ ኃይልና ጉልበቱን የታደለ ቡድን፣ ወሰኑን በቀላሉ እንደሚያፈርሰው ለመተንበይ አዋቂ መሆንን አይጠይቅም፡፡
አብዛኞቹ የመገንጠልን አቋም የሚያቀነቅኑት የዘውጌ ድርጅቶች፣ ጊዜያው የፖለቲካ ትርፍን እንጂ ኋላ ላይ ስለሚመጣው ጦስ ቁብ ሰጥቷቸው አያውቅም፡፡ ሕዝባቸውን እንደ የቤተሰብ ርስት ነው የሚቆጥሩት፡፡ የአንድነት አቀንቃኝ ኃይሉን፣ ርስታቸውን ሊቀናቀናቸው እንደመጣ ባላንጣ ስለሚቆጥሩት፣ ባለ በሌለ ሃይላቸው ይረባረቡበታል። እነዚህ የዘውጌ ድርጅቶች፣ የሕዝባቸውን አንድነት የሚገመግሙት፣ ከአመክንዮ በተራቆተ፣ አጥንት ቆጠራን  መሠረት ባደረገ፣  ደመ-ነፍሳዊ መለኪያ ነው። ይህ ግን በአንድነት ለመኖር ዋስትና እንደማይሆን፣ የሶማሊያን ተጨባጭ ሁኔታ መመልከት ብቻ በቂ ነው።  ሶማሊያ አንድ ኃይማኖት፣ ቋንቋና ዘር ያላቸው ህዝብ ሆነው፣ አንድ ሀገር መመስረት ተስኗቸዋል፡፡ የደቡብ ሱዳንንም ጉዳይ ማንሳት ይቻላል፡፡
ሌላው አንቀጽ 39ን ተምኔታዊ ባህሪያትን ተላብሷል የሚያስብለው ውጫዊ ነባራዊ ሁኔታ፣ የአፍሪቃ አንድነት ቻርተር ነው፡፡ የ1964ቱን የካይሮ ዲክላሬሽንን በውስጡ ያካተተው የአፍሪካ አንድነት ቻርተር፣ ቅኝ ገዢዎች ለአፍሪቃ ሀገራት ያሰመሩትን ድንበር ቋሚ (ሣክሮሳንት) ብሎ ደንግጓል፡፡ የዚህ ዲክላሬሽን ዋንኛ ዓላማ፣ የአፍሪቃ ሀገራት በቅኝ ገዢዎች ፍላጎት፣ ከዚህም ከዚያም ተቀይጠው ሀገር ስለሆኑ፣ ወደፊት ሊነሱ የሚችሉትን ለቁጥር የሚታክቱ የመገንጠል ጥያቄዎችን አስቀድሞ ለመከላከል በሚል እሳቤ ነው፡፡ የአፍሪቃ አንድነት (ኀብረት) ለመገንጠል ጥያቄ መለሳለስን ቢያሳይ ኖሮ፣ እስካሁን በሺህ የሚቆጠሩ ለአቅመ ሀገር ያልበቁ ጥቃቅን ግዛቶች፣ አህጉሪቷን በተዋረሷት ነበር፡፡ ስለዚህ የግዛት አንድነትን ለመጠበቅ ብቸኛው አማራጭ፣ በቅዥ ገዢዎች ፍላጎት የተፈጠሩትን ሀገሮች እንደ ሕጋዊ አካል መቀበል ብቻ ነው፡፡
የማእከላዊውን መንግሥት መዳከም ተከትሎ፣ ራሱን ከሉአላዊው ሀገር ገንጥሎ፣ እንደ ነፃ ሀገር የሚያውጅ ማንኛውም የአፍሪቃ ግዛት ቢኖር እንኳን፣ በቀሪው ዓለም ዘንድ የሚታወቀው የማእከላዊው ግዛት አካል እንደሆነ ነው፡፡ ከሁለት አስርተ ዓመታት በፊት ከትልቋ ሶማሊያ እንደተገነጠሉ በይፋ ያወጁት ሶማሊላንድ እና ፑንትላንድ እስካሁን ሉአላዊ ሀገር መሆን አልቻሉም፡፡ ኪዘህ ቀደም የቢያፍራ የመገንጠል እንቅስቃሴ በናይጄሪያ፣ የካታንጋ እንቅስቃሴ በኮንጎ ተሞክሮ፣ በብዙ እልቂትና በኅብረቱ ኮናኝነት እውን ሳይሆን ቀርቷል፡፡
ከዚሁ ጋር ተያይዞ የኤርትራ የመገንጠል መብት በአፍሪቃ ኅብረት ዘንድ ተቀባይነት የማግኘቱ ጉዳይ ግርንቢጥ እውነታ ይመስላል፡፡ ሁለት መሰረታዊ ኹነቶች የመገንጠሉን ጥያቄ ስኬታማ እንዲሆን አድርገውታል፡፡ አንደኛው፣ ኤርትራ ቅኝ ገዢዋ ጣሊያን በዓለም ዓቀፍ ኅብረተሰቡ ዘንድ የታወቀ ድንበር ስላሰመረችላት ሂደቱን ሊያቀለው ችሏል። የመገንጠሉን ቅቡልነት የበለጠ እውን እንዲሆን ያስቻለው ሌላው ምክንያት ሕወሓት ከትጥቅ ትግል አንስቶ ያነገበው የፖለቲካ አድርባይነት ነበር፡፡ ሕወሓት ከበረሃ ትግል ጀምሮ ለሻዕቢያ ካሳያቸው የፖለቲካ አድርባይነት መገላጫዎች መካከል ዋንኛው፣ ኢትዮጵያን የኤርትራ ቅኝ ገዢ እንደሆነች አምኖ መቀበሉ ነበር፡፡ ይህንን አቋሙን ከትጥቅ ትግል በኋላም በቀድሞው የድርጅቱ ሊቀ መንበር ጠቅላይ ሚኒስትር መለስ ዜናዊ ፊታውራሪነት፣ የአፍሪካ አንድነት አባላት የኢትዮጵያን ቅኝ ገዢነት እንዲቀበሉ ያላሰለሰ ዲፕሎማሲያዊ ጥረት በማድረግ፣ ኤርትራ ሉአላዊ ሀገር ሆና እንድትገነጠል የማይተካ ሚና ተጫውቷል፡፡
በአጠቃላይ አንቀጽ 39  የመገንጠል አጀንዳን ለሚያራምዱ የፖለቲካ ድርጅቶች ማማለያ ሆኖ ነው ያገለገለው፡፡ ሕዳጣኑ የጎሳ ድርጅት ሕወሓት፣ በሀገራችን ሕዝቦች ላይ ሁለንተናዊ ጭቆናን ለማንገስ፣ ይህ ማማለያ አንቀጽ ምቹ ሁናቴን ፈጥሮለት አልፏል። ኦነግ በዚህ ተምኔታዊ  ቅርቃር ውስጥ በመግባቱ የተነሳ፣ በሕወሓት ከሥልጣን ተገፍቶ፣ ሰፊውን የኦሮሞ ሕዝብ ላለፉት 27 ዓመታት ለጭቆና ዳርጎት ኖሯል፡፡ በኦህዴድ ውስጥ እንደ ተፈጠረው የእነ አቶ ለማ ቡድን (team lemma) የለውጥ አስተዳደር፣ የኦሮሞ ሕዝብን መብትና ጥቅም ያለ ኢትዮጵያ አንድነት ማሳካት እንደማይቻል አስቀድሞ አቋሞ ይዞ  ቢሆን ኖሮ፣ የሕወሓት ፍጹም የበላይነት አገዛዝ ይህን ሁሉ ዘመን ባልተሻገረ ነበር፡፡  
ነፃነትን የማያውቁ ነፃ አውጪዎች በሚለው የአንዳርጋቸው ጽጌ መጽሐፍ ገጽ 279 ላይ አንቀጹን በተመለከተ ግሩም ቁምነገር በእንዲህ መልኩ ሰፍሮ ይገኛል፡-
--በእንደኛ ዓይነት ሀገር ውስጥ አንቀጽ 39 የመሰለውን ሕግ እንደማይሰራ እያወቁ፣ እንደሚሰራ አድርጎ በማስቀመጥ ሊመጣ የሚችለው ማኅበራዊ ጉዳት በቀላሉ የሚገመት አይሆንም፡፡ እርግጥ ነው ሁላችንንም ተብትቦ የያዘን የጨለምተኝነትና የአውዳሚነት የፖለቲካ ባህል አሰፍስፎ በሚጠብቀን መአት ፊት አይናችንን ሊያስጨፍነን ይችላል፡፡ ዓይን በመጨፈን ግን ከመአት ማምለጥ የተቻለበት ሁኔታ በታሪክ ተከስቶ ስለማያውቅ፣ አንቀጽ 39ኝን እና የጡት አባቶቹን (sponsors) አምረርን መታገል ይኖርብናል።--
በእርግጥም ይህንን ተምኔታዊ አንቀጽ ለሀገራችን ህልውና ስንል በጽኑ ልንታገለው ይገባል፡፡   
ማሰሪያ ነጥብ
የፖለቲካ ጠበብቶች፤ “Politics is the art of possible”ይላሉ፡፡ ፖለቲካ ሳይንስ ፊክሽን አይደለም። ሊተገበር የሚችል ትልምን እውን የማድረጊያ ጥበብ ነው፡፡ በመሆኑም ይህ የሀገራችንን ሕዝቦችን አንድነት በማላላት፣ እርስ በርስ በጥርጣሬ እንዲተያዩ የሚያደርግ ተምኔታዊ አንቀጽን በማስወገድ፣ እውነተኛ የሕዝብ ተሳትፎ የተንጸባረቀበት ሕገ መንግሥት በታሪካችን  ለመጀመሪያ ጊዜ ለመቅረጽ፣ ሁሉም ባለድርሻ አካላት መረባረብ ይኖርባቸዋል፡
በርግጥ በዚህ የሽግግር ወቅት ስለሕገመንግሥት መሻሻል ማውራት ቅንጦት ነው፡፡ የመንግሥት ሙሉ ትኩረት የዜጎችን ደህንነት ማስጠበቅ ነው መሆን ያለበት፡፡ የሽግግሩን ሕደት በስኬት ካገባደዱ በኋላ የሕገመንግሥቱ ጉዳይ ቅድሚያ መነሳት ይኖርበታል፡፡


Read 3639 times