Saturday, 29 September 2018 14:28

ዘጠኝ ሞት ሲመጣ፤ አንዱ ይግባ አንልም

Written by  ተፈሪ መኮንን
Rate this item
(3 votes)

 ኢህአዴግ ሥር በሰደዱ ችግሮች ተጠልፎ በመውደቅ፤ የስርዓት ቀውስ ሊጋብዝ የማይችል ጠንካራ ድርጅት መሆኑን በሚያምኑ በርካታ የድርጅቱ አባላትና ደጋፊዎች ዘንድ፤ ያለፉት ሦስት አራት ዓመታት የከባድ ድንጋጤ ዓመታት እንደነበሩ አያጠራጥርም፡፡ አባላትና ደጋፊዎቹ ቀርቶ የፌዴራላዊና ዴሞክራሲያዊ ስርዓቱ ጸንቶ መቆየት ከኢህአዴግ ጋር ተያይዞ የሚታያቸውና ኢህአዴግን የስርዓቱ አለኝታ አድርገው ይመለከቱት የነበሩት እና ድርጅቱን ከእነ እንከኑም ለመደገፍ የተገደዱ ዜጎችም፤ ራሱ ኢህአዴግ ‹‹የስርዓቱ ጠላት›› ከመሆን የሚያደርስ ችግር ውስጥ ገብቶ በመመልከታቸው እጅግ ከፍተኛ ድንጋጤ አድሮባቸዋል፡፡
ድርጅቱ በመንግስትና በፓርቲ መዋቅር የሚያሳየው አመራር እየተበላሸ፤ ከአንድ የከሸፈ ተሐድሶ ወደ ሌላ ተሐድሶ እየተንከባለለ፤ ችግሮች ከመሻሻል ይልቅ እየተባባሱ በሐገሪቱ ከፍተኛ ውጥረት ነግሶ የተመለከቱ ሰዎች፤ ኢህአዴግ በህዝቡ ዘንድ ይታይ የነበረውን ተስፋ የማጣት ዝንባሌ ቀልብሶ በተስፋና በእርካታ ለመተካት ባለመቻሉ፤ በሁሉም ማዕዘናት የሚታየው ችግር አሳሳቢና ለሐገር ህልውናም ጭምር አስጊ ወደ መሆን ሲያመራ፤ ከፀሎት በቀር ሌላ መፍትሔ ማየት ከማይችሉበት ነጥብ ደርሰው ነበር፡፡
በዚህ ዓይነት ሐገራዊ ድባብ ውስጥ እንደሆንን፤ በመጨረሻ የገዢው ፓርቲ ኢህአዴግ ሥራ አስፈጻሚ ግምገማ አካሄደ፡፡ ከዚያም ግምገማው ወደ አባል ድርጅቶች የሥራ አስፈጻሚ ወይም ማዕከላዊ ኮሚቴዎች እንዲሸጋገር አደረገ፡፡ የግልና የአካል ግምገማ ተደረገ። አቅጣጫ ተቀመጠ፡፡ ግምገማው ወደ መካከለኛው አመራር ወረደ፡፡ የበላይ አመራሩ የለያቸውን የግምገማ ነጥቦች መሠረት በማድረግ በወረዳ የታችኛው መዋቅር የራሱን ግምገማ አካሄደ፡፡ ይህ ከተደረገ በኋላ መላውን ህዝብ የሚያሳትፍ የውይይት መድረክ ተከፈተ፡፡ ይህ ሁሉ ከሆነ በኋላ የህዝብ ቅሬታና ቁጣ ምክንያት የሆኑት ችግሮች የሚል ተስፋ ተፈጥሮ የነበረ ቢሆንም፤ ተስፋው እውን ሳይሆን ቀረ፡፡ ቀውሱም ተጠናክሮ ቀጠለ፡፡ ‹‹የበሩም መንኳኳት በዚያው ልክ ቀጠለ፡፡››
ታዲያ ነገሩ ገደብ የሌለው አይደለም፡፡ ከገደቡ ሲደርስ፤ ‹‹የግል ክብርና ሥልጣን ገደል ይግባ፡፡ የእኛ ክብርና ሥልጣን ከሐገር አይበልጥም›› ከሚል አቋም የደረሱ አመራሮች ተፈጠሩ፡፡ በዚህ መንፈስ የተጀመረውና ‹‹ከሰማይ በታች ያለ እና ሊነሳ የሚችል ነገር ሁሉ የተነሳበት›› በተባለ መድረክ ለአስራ ሰባት ቀናት ውይይት ተደርጎ የመፍትሔ አቅጣጫ ተቀመጠ። እንደጋሸበ እህል ፍሬ አልባ በሆኑት መድረኮች የተሰላቸው ህዝብ የመጨረሻ ተስፋ ይዞ፤ የጉባዔውን ውጤት በጉጉት ጠበቀ፡፡ የድርጅቱ አባላትና ደጋፊዎች ብቻ ሳይሆኑ፤ ለወትሮው የፖለቲካ ነገር ፈጽሞ ደንታ የማይሰጣቸው ዜጎች ጭምር አንድ መፍትሔ ሊገኝ ይችላል ብለው አቆብቁበው ጠበቁ፡፡ በመጨረሻ ድርጅቱን በሊቀመንበርነት ሲመሩና ሐገሪቱን በጠ/ሚኒስትርነት ሲያስተዳድሩ የቆዩት አቶ ኃይለ ማርያም ደሳለኝ፤ ‹‹የመፍትሔው አካል ለመሆን፤ የያዝኩትን ስልጣን በገዛ ፈቃዴ ለመልቀቅ ወስኛለሁ›› አሉ። ኢህአዴግም ጥያቄአቸውን መቀበሉን አስታወቀ፡፡ አዲስ አመራር ለመምረጥ ዝግጅት ማድረግ ተጀመረ። በዚህ ሂደት የለውጥ ኃይል የሆኑ የድርጅቱ አባላት ወደፊት መምጣትና ከፍተኛውን የመንግስትና የድርጅት ኃላፊነት ለመያዝ የሚችሉበት ዕድል ተመቻቸ፡፡  አዲስ ጠቅላይ ሚኒስትር ተመረጠ፡፡
ህዝቡ አዲሱ ጠቅላይ ሚኒስትር ምን አዲስ ነገር ይዘውለት እንደ መጡ እንኳን ሳያውቅ፤ በኢህአዴግ ምክር ቤት ምርጫ ብቻ ከፍተኛ ደስታ እንደ ተሰማው በይፋ መግለጽ ጀመረ፡፡ ከዚህ በኋላ ለሦስትና አራት ዓመታት በሐገራችን አንዣብቦ የቆየው የጨለማ ድባብ መግፈፍ ያዘ፡፡ አዲሱ ጠቅላይ ሚኒስትር፤ በተወካዮች ምክር ቤት ፊት ቀርበው፤ የመጀመሪያ ንግግራቸውን አድርገው፤ የፖለቲካ ራዕያቸውን በገለጹ ጊዜ፤ የህዝቡ ስሜት ናረ፡፡ የህዝቡ ተስፋ ማንሰራራትና ለሦስትና ለአራት ዓመታት የቆየው የጨለማ ድባብም ተገለጠ፡፡ በዚህ ሁኔታ ለሦስትና ለአራት ዓመታት ከብዶ የቆየው ጨለማ ተወግዶ ለሐገራችን ህዝቦች እፎይታን የቸረ የለውጥ እንቅስቃሴ ተጀመረ፡፡
የአዲሱ አመራር የለውጥ እንቅስቃሴው፤ ኢትዮጵያን ከጥፋት አፋፍ ከመመለስና ሐገርን ከቀውስ ከመጠበቅ ባሻገር፤ ለተጀመረው የዴሞክራሲ ስርዓት ግንባታ እንቅስቃሴ ዘላቂ ፋይዳ ሊያስገኝ የሚችል የፖለቲካ ባህል ለውጥም እንዲፈጠር አደረገ፡፡ አዲሱ አመራር ሁሉም ወገን ሰከን ባለ መንፈስ እንዲንቀሳቀስ የሚያደርግ የእርቅ መንፈስ ፈጥሮ፤ ኢትዮጵያውያን ለአንድ ሐገራቸው በአንድ ልብ መስራት የሚችሉበትን ድባብ ከማመቻቸት ተሻግሮ፤ አዲስ ምዕራፍ መክፈት የቻለ ሆነ፡፡ በተለያየ ጊዜ ከሰላማዊ የፖለቲካ መድረኩ እየሸሹ ወደ ስደት የገቡ፤ ነፍጥ ያነሱ የፖለቲካ ድርጅቶችና ግለሰቦች ወደ ሐገር ቤት ገቡ፡፡ ‹‹አክቲቪስቶች›› እና የተሰደዱ ጋዜጠኞችም መጡ፡፡
እንዲህ ያለ ተስፋና ከተስፋ ጀርባ ደግሞ ስጋት እንደቆመ፤ ከአንዴም ሁለት ጊዜ የተላለፈው የኢህአዴግ ድርጅታዊ ጉባዔ በሚቀጥለው ሣምንት ይካሄዳል። ጉባዔው በብዙዎች ዘንድ በጉጉት የሚጠበቅ ነው። በርግጥም፤ ከእያንዳንዱ አባል ድርጅት ጉባዔዎች የተሰማው ነገር ጉባዔውን በጉጉት እንድንጠብቅ የሚያደርግ ነው፡፡ ህዝቡ ባለፉት ዓመታት የነበረውን ክራሞትና ከምን ዓይነት ችግር ጋር ተጋፍጦ እንደ ቆየ ያውቃል፡፡ ስለዚህ በሐገሪቱ ሰማይ ሥር ሲያንዣብብ የቆየውን የስጋት ጭጋግ በመግፈፍ ደማቅ የተስፋ ጮራ እንዲፈነጥቅ ያደረገው የለውጥ ሂደት ተጠናክሮ እንዲቀጥል ይፈልጋል፡፡ በመሆኑም ህዝቡ ከኢህአዴግ ድርጅታዊ ጉባዔ የያዘውን ተስፋ ይበልጥ እንዲለመልም የሚያደርግ ውሳኔ ይጠብቃል፡፡
ከዚህ አንጻር አባል ድርጅቶቹና ግንባሩ ለአዲሱ መድረክ ብቁ የሚያደርጋቸውን ድርጅታዊ የማሻሻያ እርምጃዎች በመውሰድ፤ በፌዴራልና በክልል ደረጃ የተሸከሙትን የመንግስት ኃላፊነት በብቃት ለመወጣት፤ የሐገሪቱን ሰላም ለማስፈን፤ የህግ የበላይነትን ለማረጋገጥና የህዝቡን ጥያቄዎች አሟልቶ ለመመለስ ወይም እርካታን ለማረጋገጥ የሚያስችል ብቃት ያለው የፖለቲካ አመራር ለመስጠት የሚያበቃ ውሳኔ እንዲያሳልፉ ይፈልጋል፡፡ ህዝቡ በአንዳንድ አባል ድርጅቶች መካከል የሚታየውን የቀዘቀዘ ስሜትና የአካሄድ መዘበራረቅ በመመልከት፤ የኢህአዴግን ድርጅታዊ ጉባዔ በጉጉትና በስጋት እየተመለከተው ነው፡፡
ከዚህ በተጨማሪ የፖለቲካ ምህዳሩ በቀውስ ውስጥ የቆየና ባልተመለሱ ብዙ ጥያቄዎች የተወጠረ ህብረተሰብ የሚገኝበት ምህዳር ነው፡፡ የተወሳሰቡ የፖለቲካ ፍላጎቶች የሚንጸባረቁበት ምህዳር ነው። በርካታ መሰናክሎች የተጋረጡበት እና በለውጥ ሂደት ውስጥ የሚገኝ የፖለቲካ ማህበረሰብ ነው፡፡ ገዢው ፓርቲም በራሱ ችግሮች ተተብትቦ የቆየ እና ከዚህ ችግር ለመውጣት ጥረት በማድረግ ላይ የሚገኝ በመሆኑ፤ በውጭና በውስጥ ተግዳሮቶች ተሰናክሎ እንዳይወድቅ ከፍተኛ ጥረት እያደረገ ነው፡፡ ስለሆነም፤ ኢህአዴግና አባል ድርጅቶቹ ድርጅታዊ የዓላማና የተግባር አንድነታቸውን ከማረጋገጥ ተሻግረው፤ የተለያየ የፖለቲካ አመለካከት ይዘው ወደ ፖለቲካ ምህዳሩ የገቡት የፖለቲካ ኃይሎች ተጠፋፊ እንቅስቃሴ ውስጥ እንዳይገቡ እና ዓይናቸውን ከትልቁ ስዕል ሳያነሱ እንዲጓዙ፤ እንዲሁም ከፖለቲካ ድርጅቶች ፍላጎት አብልጠው ሊመለከቱት የሚገባ እንደ ሰላምና ፀጥታ ያሉ የህዝብና የሐገር ጥቅም መኖራቸውን እያሰቡ እንዲንቀሳቀሱ የሚያደርግ አርዓያነት ያለው የመሪነት ሚናውን መጫወት ይኖርበታል፡፡
ሰሞኑን በአሜሪካ ምክር ቤት የውጭ ጉዳይ ንዑስ ኮሚቴ ፊት ቀርበው ሙያዊ አስተያየት የሰጡ አሜሪካውያን ለውጡን እንደሚደግፉና የዶ/ር ዐቢይ አመራርንም የሚያደንቁ መሆናቸውን ቢገልፁም፤ ‹‹ኢትዮጵያ አሁንም መረጋጋት የማጣት ችግር የተጋረጠባት ሐገር›› (The potential for Ethiopia to destabilize persists) እንደሆነች ተናግረዋል። ‹‹አሜሪካ ለክፉ ሁኔታ መዘጋጀት አለባት›› (The United States must prepare for worst-case scenarios) ጭምር ብለዋል፡፡ አንዳንዶቹ የፖለቲካ ኃይሎች አሰላለፍን ወይም የኢህአዴግን ድርጅታዊ ቁመና በመመልከት ሳይሆን፤ የለውጡን ፍጥነት፤ ሰፊው የፖለቲካ ምህዳር የጋበዛቸውን የፖለቲካ ኃይሎች ጥንቅርና መረጋጋት የማያውቀውን የአፍሪካ ቀንድን ዐመል በመመልከት ብቻ ስጋት ተሰምቷቸዋል።
በአንዳንድ የፖለቲካ ፓርቲዎች መካከል ተስፋ ሰጪ የመነጋገርና የመከባበር ሁኔታ ቢታይም፤ በዚሁ አንጻር አደገኛ የመወጋገዝ አዝማሚያም እየታየ ነው፡፡ በመሆኑም፤ የሐገራችን የፖለቲካ ፓርቲዎች ለሐገሪቱ ችግሮች መፍትሔ ብለው በሚያቀርቧቸው ጉዳዮች ወይም በችግሮቹ ምንጮች ዙሪያ ልዩነት ቢኖራቸውም፤ አብረው መስራት የሚያስችል መንፈስ መፍጠር ካልቻሉ፤ ፈተናው ከባድ ይሆናል፡፡
አሁን በገዢው ፓርቲና በተፎካካሪ የፖለቲካ ፓርቲዎች መካከል የሚታየው ዝንባሌ ጥሩ ነው፡፡ የጋራ ችግርን በጋራ ለመፍታት ተጋግዘው የሚሰሩና በአንድነት መንፈስ ለጋራ ሐገር ጥረት የሚያደርጉ የአንድ ቡድን ተሰላፊዎች እንጂ፤ ለመሸናነፍ የሚጫወቱ ተቀናቃኞች አድርገን እንዳንወስዳቸው የሚያደርግ ነው፡፡ ይህ በጣም ጥሩ ነው፡፡ በዴሞክራሲያዊ እሴቶች ዙሪያ የጋራ አመለካከት ሲኖር፤ ገዢው ፓርቲና ተፎካካሪ የፖለቲካ ፓርቲዎች፤ የአንድ ቡድን ተጫዋቾች እንጂ ባላንጣዎች አይሆኑም፡፡ ይህ ሁኔታ እንደ ትልቅ መዋቅራዊ ለውጥ ሊታይ የሚችል አስደሳች ለውጥ ነው፡፡ ሆኖም የፖለቲካ ምህዳሩ ስጋትም ያንዣበበበት ነው፡፡
እንደምታስታውሱት፤ የሥራ አስፈፃሚ ኮሚቴ በነሐሴ አጋማሽ ባካሄደው መደበኛ ስብሰባ፤ የጥልቅ ተሃድሶውን አፈፃፀምና  ያስገኘውን ውጤት ገምግሞ ነበር፡፡ ሥራ አስፈጻሚ ኮሚቴው ከነሐሴ 14 እስከ 16/2010 ዓ.ም ባደረገው በዚህ ግምገማ፤ በጥልቅ ተሐድሶው የተቀመጠውን አቅጣጫ ተከትሎ የተወሰዱት የለውጥ እርምጃዎች፤ ፈጠራ ታክሎባቸው አመርቂ ውጤቶች ማስመዝገብ መቻላቸውን አረጋግጧል፡፡ የኢህአዴግ ሥራ አስፈፃሚ ኮሚቴ በተለመደው ድርጅታዊ ባህል፣ ዴሞክራሲያዊነትን በተላበሰና በሰከነ አግባብ የለውጡን ትሩፋቶች በጥልቀት መገምገሙን ለመገናኛ ብዙሃን በላከው መግለጫ ጠቁሞ፤ ቀደም ሲል በድርጅቱ የሚተላለፉ ውሳኔዎችና የተቀመጡ አቅጣጫዎች በአግባቡ የማይተገበሩበት ሁኔታ እንደነበር፤ ሆኖም ይህ የአፈፃፀም ድክመት ታርሞ፤ አሁን በአዲሱ አመራር ወቅት በድርጅቱ የተላለፉ ውሳኔዎችና የተቀመጡ አቅጣጫዎች በፍጥነት መፈፀም መጀመራቸውን አመልክቷል፡፡ በጣም በአጭር ጊዜ ሊመዘገቡ ይችላሉ ተብለው የማይታሰቡ ድሎች መመዝገባቸውን የገለጸው የኢህአዴግ ሥራ አስፈፃሚ ኮሚቴ፤ እነዚህ ድሎች የመላ ኢትዮጵያውያንን ተስፋ ያለመለሙ ድሎች መሆናቸውንና ሰፊ የህዝብ ድጋፍ ማስገኘታቸውንም አረጋግጧል፡፡
እነዚህ እርምጃዎች የህዝቡን ድጋፍ ያገኙ፤ እንደ ሐገር የመቀጠል ሥጋት ውስጥ ገብተን ከነበረበት ተጨባጭ አደጋ በመውጣት አንፃራዊ ሰላም እንዲመጣ ያስቻሉና በውጭ የሚኖሩ ኢትዮጵያውያንና ትውልደ ኢትዮጵያውያን  በሐገራቸው ጉዳይ በነፃነት እንዲሳተፉ ያስቻሉ ውጤታማ ሥራዎች መሆናቸውንና ይህም ተጠናክሮ መቀጠል እንደሚገባው ኮሚቴው በመግለጫው ጠቅሷል፡፡
ነገር ግን በጣም አስተዋይና የሰከነ የአመራር ኃይል የሚፈልግ ጅምር የለውጥ ሂደት ውስጥ የምንገኝ በመሆናችን፤ ከፊታችን የተደቀኑት ፈተናዎች እንዲህ ቀላል አይደሉም፡፡ በርግጥ በማናቸውም የለውጥ ሂደት ችግሮች እንደሚያጋጥሙ ይጠበቃል፡፡ ሆኖም ችግሮች ያጋጥማሉ ብለን፤ የለውጥ ሂደቱን እየተገዳደሩት ያሉ ችግሮችን አቃልለን ማየት አይገባንም፡፡ አንዳንዶች የተገኘውን ነፃነት በአግባቡ መያዝ እየተሳናቸው የሚፈጥሩት ችግር መኖሩንም እያየን ነው፡፡ እነዚህ ወገኖች የተገኘውን ነፃነት እንደ ዓይን ብሌን በመጠበቅ፤ ነፃነቱ እየተጠናከረ እንዲሄድና ተቋማዊ እንዲሆን የበኩላቸውን አስተዋጽዖ በማድረግ ፋንታ፤ ከዚህ ተቃራኒ በሆነ መንገድ እንቅስቃሴ ሲያደርጉም ተመልክተናል፡፡ ይህ እንቅስቃሴ ከወዲሁ ካልተገታ ስርዓት አልበኝነት እንዲነግስ ሊያደርግ የሚችል ዝንባሌ ነው፡፡ በመሆኑም፤ እንዲህ ያሉ ችግሮችን በአንክሮ ተመልክቶ የህግ የበላይነት ለማስፈን የሚያስችሉ ሥራዎች በጥብቅ ክትትል እንዲሰሩ ማድረግ ያስፈልጋል፡፡ በዚህ ረገድ ህዝቡ ያለውን ችግር የተገነዘበው የኢህአዴግ ሥራ አስፈፃሚ ኮሚቴ የፀጥታና የደህንነት አካላት፤ በለውጡ መንፈስ የህግ የበላይነትን ለማስፈን የበኩላቸውን ሚና እንዲጫወቱ ጥሪውን አስተላልፏል፡፡
የኢህአዴግ ሥራ አስፈፃሚ ኮሚቴ ለሦስት ቀናት ባካሄደው መደበኛ ስብሰባ፤ የለውጥ እንቅስቃሴውን ተከትሎ በሁሉም መስኮች በተከናወኑ ሥራዎች አመርቂ ውጤቶች የተመዘገቡ መሆናቸውንና ለውጡን የሚገዳደሩ ችግሮች መኖራቸውን፤ ችግሮቹንም ተቋማዊ አሰራርን በመከተል፤ እንዲሁም ህዝቡን በተደራጀ መንገድ በማሳተፍ እየፈቱ መሄድ እንደሚያስፈልግ ተገንዝቦ፤ የተጀመረውን ለውጥ ዳር ለማድረስ፣ የህግ የበላይነትን የማስፈን ጉዳይ የወደፊት የትኩረትና የርብርብ ማዕከል ሆኖ እንዲቀጥል አቅጣጫ አስቀምጧል፡፡ ለዚህም ስኬት ህዝቡ እያሳየ ያለውን የለውጥ ባለቤትነትና ድጋፍ ይበልጥ አጠናክሮ እንዲቀጥል ጥሪ አቅርቧል፡፡ ኢህአዴግ፤ ህዝቡ እስካሁን ለለውጡ ላሳየው ድጋፍ አድናቆቱን በመግለጽ ምስጋና ያቀረበ ሲሆን፤ የድርጅቱ አባላትና አመራሮች የተጀመረው የለውጥ ጉዞ ዳር እንዲደርስ በህዝባዊነት መንፈስ በትጋት እንዲንቀሳቀሱ ጥሪ አስተላልፏል፡፡ በመሆኑም፤ ወደፊት የሚካሄደው ድርጅታዊ ጉባዔ የሐገሪቱን ወቅታዊ ሁኔታ በአግባቡ ገምግሞ የተጀመረውን የለውጥ ሂደት በላቀ ደረጃ ማሳካት የሚያስችል ደርጅታዊ ቁመና ይዞ ለመገኘት የሚያበቃ ውሳኔ ማሳለፍ ይኖርበታል፡፡ ዘጠኝ ሞት መጣ ሲሉት፤ ‹‹አንዱን ግባ በሉት›› እንዳለው ሰውዬ፤ የጅል ውሳኔ ከመወሰን መጠንቀቅ ይኖርብናል፡፡

Read 1194 times