Saturday, 29 September 2018 14:49

አዳማው ወጣት ከያኔና የጥበብ ነፍሱ

Written by  ናፍቆት ዮሴፍ
Rate this item
(1 Vote)


  ሀገር ከተራበ ወገን ከተጠማ
 ሊጡ ኩፍ ብሎ ምጣዱ ካልሰማ
 ማገዶ አትጨርስ በዋዛ ፈዛዛ
 ይሄን ስበርና አዲስ ምጣድ ግዛ፡፡---
 (“የወፍ ጐጆ ምህላ” የግጥም መድበል)

     ተወልዶ ያደገው በአዳማ ከተማ ነው፡፡ ለግጥምና ውዝዋዜ የተለየ ፍቅር ያለው ሲሆን በሥዕል ችሎታውም አይታማም፡፡ ከ80 በላይ ኬሮግራፊዎችንና የሙዚቃ ቪዲዮ ክሊፖችን እንደሰራ ይናገራል፡፡ ገጣሚ ኤፍሬም መኮንን (ኤፊ ማክ) ከሳምንት በፊት “የወፍ ጐጆ ምህላ” የተሰኘ ሁለተኛ የግጥም መፅሐፉን፣ በአዳማ ተስፋዬ ኦሎምፒክ ሆቴል አስመርቋል፡፡ በምረቃ ሥነ ስርዓቱ ላይ የተገኘችው የአዲስ አድማስ ጋዜጠኛ ናፍቆት ዮሴፍ፣ የ27 ዓመቱን ወጣት ከያኔ አነጋግራዋለች፡፡ በጥበብ አጀማመሩና ህይወቱ፣ በኪነ ጥበብ እንቅስቃሴውና በወደፊት ህልሙ ዙሪያ እንዲህ አውግቷታል፡፡

   ለግጥምና ለውዝዋዜ ፍላጐትና ዝንባሌ እንዳለህ ያወቅኸው መቼ እና እንዴት ነበር?
እንደምታውቂው የሁለት ሙያ ባለቤት ነኝ። የሁለቱም ሙያ አጋጣሚ የሚገርም ነው፡፡ የግጥም አጀማመሬን ብነግርሽ፣ በአፍሪካ ደረጃ ሰኔ 9 ቀን የሚከበረው የህፃናት ቀን መሰረቴ ነው ማለት እችላለሁ፡፡ በየዓመቱ በዚህ እለት ህፃናት ተኮር የሆኑ ግጥሞች  ውድድር ይካሄድ ነበር፡፡ እኔም ለረጅም ጊዜ፣ 18 ዓመት ሞልቶኝ ህፃን ከሚለው የእድሜ ምድብ እስክወጣ እየተወዳደርኩኝ አንደኛ ነበር የምወጣው፡፡
ስታሸንፍ ምን ነበር የምትሸለመው?
መዝገበ-ቃላትና የተለያዩ ሊያግዙኝ የሚችሉ መፅሐፍትን እሸለም ነበር፡፡ መፅሐፍቱ አሁንም አሉ፡፡ የመጀመሪያው እንደውም ዲክሽነሪና አሁን የማላስታውሳትና የማላውቃት ገጣሚ በእጇ የሰራችውን ሹራብ ነበር የተሸለምኩት። በኦሮሚያም በአገር አቀፍ ደረጃም አሸንፌ፣ ሒልተን ሆቴል ውስጥ ተሸልሜ  አውቃለሁ፡፡ ያው ይሄ ሁሉ 18 ዓመት ሳይሞላኝ ነበር፡፡
የውዝዋዜ ጅማሮህስ ምን ይመስላል?
የውዝዋዜ  አጀማመሬ በዚያን ወቅት የቀበሌ የኪነት ቡድኖች ነበሩ፡፡ አንድ ጊዜ ከአንድ ጓደኛዬ ጋር ከት/ቤት እንያቸው ብለን ወደ ቀበሌ ሄድን። በዚያን ጊዜ አንድ ልጅ ሲወዛወዝ አየሁና ወደድኩት፡፡ በተፈጥሮዬ አንድን ነገር ከወደድኩ መሆን እፈልጋለሁ። እንሞክር ብለን ገባንና ስናናግራቸው፤ “ምን መሆን ትፈልጋለህ?” አሉኝ፡፡ ዘፋኝም ተወዛዋዥም አልኳቸው። አስገብተውኝ ለተወሰነ ጊዜ ዘመናዊ ዳንሰኛ አደረጉኝ። ዳንሱን እሰራዋለሁ ግን ውስጤ አልተቀበለውም፤ ደስተኛም አይደለሁም ነበር። ወደ ባህል ውዝዋዜው ስገባ በጣም ፈጠንኩኝ። እርግጠኛ ነኝ አራት ወር ያህል እንደሰራሁ፣ በ16 ዓመቴ ጀማሪ ተወዛዋዥ ሆኜ፣ እዚሁ አዳማ ውስጥ በምሽት ክበብ ተቀጥሬ መስራት ጀምሬያለሁ፡፡ ቦታው ኪዳነምህረት መናፈሻ ይባላል። ጊዜው 1999 ዓ.ም ክረምት ላይ ነበር፡፡ ከ20 በላይ ተወዛዋዦች ተፈትነን መጨረሻ ላይ ሁለት ወንድና ሁለት ሴቶች ሆነን መስራት ጀመርን፡፡ እዛ የጀመርነው አራታችን እንደ አንድ ቡድን ሆነን መስራት ቀጥለን፣ “ኢትዮጵያን አይዶል” ተወዳድረን እስከማሸነፍ ደርሰን ነበር፡፡ የኮካ ኮላው ላይም አንደኛ ወጥተን 120 ሺህ ብር ተሸልመናል፡፡ “ጐልደን ስቴት የባህል ቡድን” ነበር የምንባለው፡፡ የቡድኑ መሪም እኔ  ነበርኩኝ፡፡
የግጥም ውድድሩ 18 ዓመት ሲሞላህ ቆመ፤ ከዚያስ እንዴት ገፋህበት?
ከዚያ በኋላማ በራሴ ግጥም እየፃፍኩ ማስቀመጥና በየወሩ የሚዘጋጁ የግጥም ምሽቶች ላይ እየሄድኩ ማንበብ ጀመርኩኝ፡፡ እዚያ በማደርገው ጥሩ እንቅስቃሴ የተለያዩ ገጣሚያን ሥራዎች የተካተቱበት “ሰሚ ያጡ ብዕሮች” የተሰኘ የግጥም መፅሐፍ ሲታተም፣ የእኔም አንድ ግጥም ተካተተልኝ፡፡ በመቀጠል 2003 ዓ.ም 35  ገጣሚያን የተሳተፉበት “የግጥም ከተራ” የተሰኘ መፅሐፍ ሲታተም፣ ሦስት ግጥሞቼ ተካተቱና አብረው ታተሙ፡፡ የግጥሙም ፍቅር በዚህና መሰል ሂደቶች ለመጐልበት በቅቷል፡፡
“ለባለቅኔው ቅኔ አጣሁለት” የተሰኘ የግጥም መፅሐፍህ የታተመበት ሂደት አስገራሚ ነው፡፡ እስኪ አጠቃላይ ሂደቱን አጫውተኝ?
እውነት ነው፡፡ ግርምቱ እስካሁንም አለ፡፡ እንደነገርኩሽ ግጥም እየፃፍኩ አስቀምጣለሁ፡፡ አሁንም እፅፋለሁ አስቀምጣለሁ፡፡ የማስቀምጠው ለሕትመት ይበቃል፣ ይመጥናል ብዬ ሳይሆን በቃ ግጥም ስለምወድ ስሜቴን ለመግለፅ እጽፍና ይቀመጣል፡፡ በዚያን ጊዜ እንደ አሁኑ ግጥም በፌስቡክ ብዙም አልተለመደም ነበር፡፡ እነዚያን የማስቀምጣቸውን ግጥሞች ሰብስባ አሳትማ ሰርፕራይዝ ያደረገችኝ ፍቅረኛዬ ናት፡፡
መፅሐፉ መታተሙን ያወቅከው  እንዴት ነበር?
አንድ ቀን አደራ የሚባል ጓደኛዬ ከቤት እንውጣ፣ ልምምድ እንግባ ብሎ ይዞኝ ይወጣል። ሌላም አበባው የሚባል ጓደኛ ነበረኝ፤ እሱም እንደኛው ተወዛዋዥ ነው፡፡ ልምምድ ገብተን ስንጨርስ “ወደ ቤት ሄደን ምሳ እንብላ” ስላቸው፤ “አይ እዚሁ ብንቆይ ይሻላል” ይሉኛል፡፡ አደራ የሚባለው ጓደኛዬ፣ ካፌ ይዞኝ ረጅም ሰዓት ቆየን። እኔ ደግሞ ረጅም ሰዓት አንድ ቦታ መቀመጥ አልወድምና “በል ወደ ቤት እንሂድ” ብዬ ይዤው ልገባ ስል፣ የተከራየሁት ቤት በር ከውስጥ ተቀርቅሮ በተለመደው አከፋፈት አልከፈት አለኝ፡፡
ከዚያስ?
ለረጅም ጊዜ ቤቱ ውስጥ ስለኖርኩ በዛ መልኩ ተዘግቶ አጋጥሞኝ አያውቅምና በሩን አንኳኳሁት። መጥተው ሲከፍቱልኝና ወደ ውስጥ ስገባ በድንጋጤ ክው ነው ያልኩት፡፡ አዳማ ላይ በኪነ-ጥበብ ትልቅ ተሳትፎ ያላቸው ከወጣት እስከ አዋቂ ግጥም ብለዋል፤ ግቢው ውስጥ፡፡ በቃ ሞልተውታል ነው የምልሽ፡፡ ጉዳዩ ምንድነው ስል፣ የሚመልስልኝ የለም፡፡ ጭራሽ ካሜራ ይዘው መቅረፅ ሲጀምሩ፣ ድንጋጤዬ እየጨመረ ሄደ። የምናገረው ሁሉ አጣሁ፡፡ በሌላ ወገን፤ ፍየል አርደው በብረት ምጣድ ይጠብሳሉ፡፡ በሌላ በኩል ቢራው ተደርድሯል፡፡ ይበልጥ ግራ ያጋባል፡፡ ኧረ ይሄ ነገር ምንድን ነው ንገሩኝ? ስል፤ “እንዴ አንተ ጓደኛችን ቤት መዝናናት አንችልም እንዴ?!” አሉኝ። ትችላላችሁ ግን እኔ ሳልሰማና ሳላውቅ እንዴት ሆነ አልኳቸው። ዝም ብለው ይተራመሳሉ፡፡ ከዚያም ዝም ብዬ ጠበቅኳቸው፡፡
እንደው ምንም የጠረጠርከው ነገር የለም?
በፍፁም! እኔ የጻፍኳቸው ግጥሞች መፅሐፍ ይሆናሉ ብዬ እንዴት ልገምት? ከዚያ ቆዩ ቆዩና “ኤፊ፤ እስከ ዛሬ በውዝዋዜውም በግጥሙም በርካታ አስተዋፅኦ አድርገሃል፡፡ ለከተማችንም ትልቅ የኪነ-ጥበብ ሥራ እየሰራህ ነው፡፡ ይህንን አስተዋፅኦ ግምት ውስጥ በማስገባት ስጦታ እንሰጥሃለን” አሉኝ፡፡ እንዴ ገና ወጣት ነኝ፤ ጅምር  ላይ ያለሁና ብዙ የማልም ነኝ፤ ምን ሰርቼ ነው ስጦታው ብላቸውም፣ “አይ በቃ እንሰጥሃለን” አሉና በሆነች የሸሚዝ ካርቶን ውስጥ የተጠቀለለ ነገር አለ፤ ምንድን ነው ስል፣ ሸሚዝ ነው አሉኝ፡፡ ውስጡ ግን ጠንካራ ነገር ስለነበረው፣ ግራ ገብቶኝ ስፈታው መፅሐፍ ነው፡፡ ፍቅረኛዬ ምዕራፍ ፍስሐ (ማፊ) አንድ የምወደውን ግጥም ታውቃለች፤ “ለባለቅኔው ቅኔ አጣሁለት” ይሰኛል፡፡ ይህን ግጥም አካትታ፣ ርዕስ አድርጋ ነው ያሳተመችው፡፡ እኔ ማመን አልቻልኩም፡፡ ትልቁ ድንጋጤ የመጣው ይሄን ጊዜ ነው፤ መፅሐፉን በቁሜ ጣልኩት፡፡
ፍቅረኛህ ገንዘብ ከየት አምጥታ ነበር ያሳተመችው? ተማሪ እንደሆነች ሰምቻለሁ--
በየጊዜው ለዚህ ለዚህ ጉዳይ እያለች፣ አንድ ሺህ ሁለት ሺህ ብር--- ትጠይቀኛለች። የምትጠይቅበትም መንገድ አሳማኝ ስለነበር እሰጣት ነበር፡፡ ብቻ እንዲህ አድርጋ መፅሐፍ ማሳተም እንደምችል አበረታታችኝ። እኔም ከዚያ በኋላ ብዙ ማንበብ፣ ማሰብና ማሰላሰል ቀጠልኩኝ፡፡ የተሻለ የግጥም መፅሐፍ ማሳተም እንደምችል፣ ተስፋ እንድሰንቅ አድርጋኛለች። ፍቅረኛዬ ማፊን በጣም ነው የማመሰግናት፡፡ በጣም የሚያበረታታና ጥሩ ምላሽ ነው ያገኘሁት።
ወደ ውዝዋዜው እንመለስ፤ ኬሮግራፈርና ተወዛዋዥ ነህ፡፡ በውዝዋዜው ለምን ያህል ጊዜ ሰርተሃል?
በውዝዋዜ ወደ 11 ዓመት ሰርቻለሁ፡፡ ግን በዚህ ሙያ ጨርሻለሁ ብሎ ነገር አለ ብዬ አላስብም። ሁሌም ተማሪ ሆነሽ ነው የምትቀጥይው፡፡ ዛሬ አማርኛ፣ ነገ ትግርኛ፣ ከዚያ ኦሮሚኛ እየሰራሽ ባህል እያጠናሽ ነው የምትሄጂው፡፡ ከ80 በላይ ብሔር ብሔረሰቦች ባሏት አገር፤ ሁሉንም አጥንቶ ለመስራት እድሜ ልክ ላይበቃ ይችላል። ስለዚህ የምትችይውን ያህል ሰርተሽ እንኳን በፊት የሰራሽውን ማሻሻልና ማሳደግ የግድ አለብሽ። ስለዚህ በውዝዋዜ ውስጥ መቻል ስለሌለና ሁሌ ተማሪ ሆነሽ ስለምትቀጥይ፣ ለማወቅ እያጓጓሽ ነው የምትሄጂው፡፡ እስካሁን ከ80 በላይ ኬሮግራፊና ውዝዋዜ ሰርቻለሁ፡፡ በሁሉም ላይ ራሴ ኬሮግራፊ ሰርቼ ራሴም የተወዛወዝኩባቸው እንጂ ሌላ ቦታ ተጠርቼ ሰርቼ አላውቅም፡፡ በውዝዋዜው ብዙ መስራትና አሻራ ማስቀመጥ እፈልጋለሁ፡፡ እኔ የምፈልገው ኤፍሬም ተወዛዋዥ ነበር እንድባል ሳይሆን ኤፍሬም በነበረበት ዘመን ውዝዋዜ እንዲህ ነበር እንዲባል ነው፡፡ አሁን እዚያ ደረጃ ላይ አልደረስኩ ይሆናል፤ ግን እርግጠኛ ነኝ እደርሳለሁ፡፡ የውዝዋዜ ሙያን ወድጄው ስለምሰራው፣ ጥበቡንም የተሻለ ደረጃ ላይ አደርሰዋለሁ፡፡ ጥበቡም የተሻለ ደረጃ ላይ ያደርሰኛል ብዬ ነው የማምነው፡፡
በውጭም በአገር ውስጥም እየተዘዋወርክ እንደምትሰራ ሰምቻለሁ፡፡ እስኪ ስለሰራህባቸው ቦታዎች አጫውተኝ?
መጀመሪያ በአይዶል እንዳሸነፍኩኝ በነፃ አገልግሎት ብሔራዊ ቴአትር ሰርቻለሁ። ተወዳድሬ ሁለት ኮርስ ከወሰድን በኋላ ከተወዳደርነው ሰባት ሴትና ሰባት ወንድ ሆነን ተመርጠን፣ እንደ ቡድን “ለ” ሆነን፣ ከአንድ ዓመት በላይ ሰርቻለሁ፡፡ ከዚያ ወጥቼ በአየር ኃይል ኦርኬስትራ ባንድ ውስጥ የውዝዋዜ አሰልጣኝ ሆኜ ለአንድ ዓመት ከአምስት ወራት ያህል ሰርቻለሁ። ተወዛዋዥም ሆኜ ሰርቻለሁ፡፡ ከዚያ ወደ አቡዳቢ ሄጄ ለሁለት ወራት ሰርቻለሁ፡፡ በነገራችን ላይ በርካታ የውጭ እድሎች ነበሩኝ፤ ስጠራ ተነስቼ የምሄድ አይደለሁም፣ አልፈልገውም፡፡
ምክንያትህ ምንድን ነው?
ቀደም ብዬ እንደነገርኩሽ፣ እዚህ አገር ላይ የራሴን አሻራ ማስቀመጥ እፈልጋለሁ፡፡ አሻራ ማስቀመጥ የምችለው ደግሞ በዚህ የወጣትነት እድሜዬ፣ እዚሁ አገሬ ላይ በደንብ ስሰራና ስታወቅ ነው፡፡ በልጅነቴ ውጭ ሄጄ ከተቀበርኩና ሰው ከረሳኝ፣ ሙያውን የምሰራው ለገንዘብ ብዬ ነው ማለት ነው፡፡ ገንዘብ ሰብስቤ ከውጭ ስመጣ፣ ለሙያው ያለኝ ክብርና ፍቅር የሚቀንስ ይመስለኛል፡፡ ብዙ ጊዜ ሲጠይቁኝ አልሄደም ስለምል፣ “በቃ ኤፍሬም ወደ ውጭ አይሄድም” ነው የሚሉት፡፡ ባለፈው አቡዳቢ የሄድኩትም ጓደኛዬ ደውሎ፣ “ለሁለት ወር ተኩል ናት፤ መጥተህ ሰርተህ ተመለስ” ብሎኝ ነው፡፡ ወቅቱም ሁለተኛው የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ የታወጀበትና ሥራ የተቀዛቀዘበት ስለነበር፣ እሺ ብዬ ሄጄ ተመለስኩኝ ማለት ነው፡፡ “አሁንም ና” ስባል ግን ብድግ ብዬ አልሄድም፡፡
በአሁኑ ወቅት ምን እየሰራህ ነው?
በአሁኑ ወቅት ሶደሬ ሪዞርት በሳምንት አንድ ቀን ምሽት እሰራለሁ፡፡ እዚህ እኔ የማሰለጥናቸው “የኤፍሬም ልጆች” የሚል ስያሜ ያላቸው 15 ወንድና 15 ሴት፣ በድምሩ 30 ታዳጊዎች አሉ፡፡
እንደ ተመስገን ልጆች ማለት ነው--?
ትክክል፡፡ ተመስገን ታላቅ የሙያ ጓደኛዬ ነው። እዚህ ናዝሬት ሲመጣም ብዙ እንወያያለን፣ እንመካከራለን፡፡ ልምድም እንለዋወጣለን፡፡ ወደ ስራዬ ስመጣ፣ አሁን ከዚህ ወር በኋላ አየር ኃይል ኦርኬስትራ ተመልሼ፣ በአሰልጣኝነቱም በተወዛዋዥነቱም ሥራ እጀምራለሁ ብያለሁ። በፋና ቴሌቪዥን የሚተላለፈው የ”ሀገርኛ” ፕሮግራም የውዝዋዜ አሰልጣኝም ሆኜ እየሰራሁ ነው፡፡
እዚህ ናዝሬት ውስጥ በየወሩ የሚካሄድ “ሮሃ ሙዚቃል” የተሰኘ የሥነ-ጽሁፍ ምሽት ከጓደኞችህ ጋር መሥርተሃል---
አዎ፡፡ “ሮሃ ሙዚቃል”ን አራት ሆነን ነው የመሰረትነው፡፡ አንዱ እኔ ነኝ፡፡ ሀሳቡንም እንደ ሀሳብ ያመጣሁት እኔ ነበርኩኝ፡፡ እዚህ ናዝሬት ላይ ወርሃዊ የኪነ-ጥበብ ምሽት እንዲኖር ከፍተኛ ፍላጐት ነበረኝ። በወር አንድ ጊዜ ምሽቱን ማዘጋጀት ብቻ ሳይሆን በይዘትም ሆነ በአቀራረብ የተለየ ቅርፅ እንዲኖረው እፈልግ ነበር፡፡ አዳማ ለመመስረቷ ምክንያት የሆናት የባቡር መስመር መዘርጋቱ ነው፡፡ እናም ተበላሽቶ የቆመ ባቡር አለ። መስራቾቹን ማለትም ተስፋሁን ከበደ (“ፍራሽ አዳሹ” በተሰኘው በባለ አንድ ሰው ተውኔቱ ይበልጥ ይታወቃል) እንደውም “ፍራሹ እያዩ ፈንገስ” ነው የሚባለው፡፡ እሱን ፍቅረኛዬን ምዕራፍ ፍስሃ፣ መለሰ አውራሪስ የተሰኘ ፎቶግራፈር (የካዮን ፒክቸርስ ባለቤት ነው)፣ እኔም በነገራችን ላይ ቪዲዮግራፊ ተምሬ ተመርቄያለሁ፤ ማፊ ተዋናይት ናት፡፡ ብቻ የተለያየ ሙያ ባለቤቶች ነን፡፡ እናም ጠርቻቸው፣ እዚያ እንደ ዋዛ ቆሞ የቀረ ባቡር አለ፤ ለምን አፅድተነው የግጥም ምሽታችንን በዚህ ባቡር ውስጥ አናቀርብም ብዬ ነገርኳቸው፡፡ ይህ ባቡር ታሪካዊና ትልቅ ሜዳ መሃል ያለ ነው፡፡ ግን ዝጓል፡፡ በሆነ መልኩ አፅደተን ልንጠቀምበት ፈልገን በጣም አስቸጋሪ ነገሮች ገጠሙን። የፅዳቱ ሁኔታ አስቸገረንና በአዳራሽ ማቅረብ ጀመርን፡፡ “ሮሃ ሙዚቃል” በአድዋ በዓል ማግስት ተመስርቶ አድዋ ላይ ትኩረት ያደረገ የሥነጽሁፍ ምሽት አሳለፍን፡፡ በዚያን ጊዜ መግቢያው ነፃ ነበር፡፡ ጥሩ ተቀባይነት አገኘ፡፡ ይሄው ከሁለት ዓመት በላይ ሆኖታል፡፡ በዚህ አጋጣሚ የከተማ መስተዳድሩ፣ ያንን ባቡር የሚያፀዳበት መንገድ ፈልጐ፣ ታሪካዊና የተለየ ስራ የምንሰራበትን እድል ቢፈጥርልን ደስ ይለኛል፡፡
በወቅቱ እኔ ባንድ መስርቼ ባህል ምሽት እሰራ ስለነበር የስነ-ጽሁፍ ምሽታችንን የኔ በሆነው “ግዕዝ” ባንድ ታጅበን ነበር የምንሰራው፡፡ በባህላዊ ባንድ ታጅቦ ግጥም ማንበብም አልተለመደም ነበር፤ እስካሁን ከእኔ ባንድ ጋር ነው የምንሰራው። ትልልቅ ገጣሚዎችን ከአዲስ አበባና ከተለያዩ ቦታዎች እናመጣለን፡፡ ከዚያ ቀስ እያልን 10 ብር፣ ከዚያም 20 ብር መግቢያ መጠየቅ ጀመርን፡፡ አሁንም በጥሩ ሁኔታ ምሽታችን ቀጥሏል፡፡ አንደኛ ዓመታችንን በቲታስ ሆቴል  ስናከብር ደፍረን 50 ብር አደረግነው፡፡ ደራሲ ዘነበ ወላ፣ ገጣሚ ምልዕቲ ኪሮስ፣ በላይ በቀለ ወያና ሌሎችም ተገኝተዋል። በትንሹ ከአንድ ሺህ ሰው በላይ የታደመበት ደማቅ ምሽት ነበር፡፡
ግጥም በውዝዋዜን ለመጀመሪያ ጊዜ አስተዋውቀሃል፡፡ እስኪ ስለዚህ ጉዳይ አብራራልኝ?
ያው የሁለት ሙያ ባለቤት መሆኔን ደጋግሜ እየነገርኩሽ ነው፡፡ ሁለቱን ነገሮች ደግሞ አጣጥሜ መስራት እፈልግ ነበር፡፡ የምወደውን ግጥም፣ በጣም በምወደው ውዝዋዜ ማለት ነው፡፡ ይህንን ነገር ይበልጥ እንዳስብበትና እንድተገብረው ያደረገኝ የከተማችን አንጋፋው ገጣሚ አዳም ሁሴን ነው፡፡ “ሮሃ ሙዚቃል”ን እኛ እንመስርተው እንጂ አዘጋጁ ታላቅ ወንድማችን አዳም ሁሴን ነው፡፡ እሱ እንግዳ በመጋበዝና በማዘጋጀት ዋነኛ ሚና ያለው ነው፡፡ በጣም መመስገን አለበት። እነዚህን ሙያዎች አዋህደህ ተጠቀምበት አለኝ። እናም ለአዲስ አመት መድረክ ላይ ሰራሁት፡፡ መድረኩ ጄቲቪ ላይ የሚተላለፍ ነበር፡፡ ግጥም በውዝዋዜ ጥሩ ተቀባይነትን አገኘ፡፡ የግጥምን ሀሳብ በውዝዋዜ ማንፀባረቅ ነው፡፡ ውዝዋዜ ማለት ባህላችንን፣ አለባበሳችንን፣ ማንነታችንን የያዘ ሲሆን ከግጥም ጋር ሲዋሃድ በጣም አስደሳች ነውና ጀመርኩት። በጣም ጥሩ ሆነ፡፡ በ”የወፍ ጐጆ ምህላ” መጽሐፍ ምርቃቴም ላይ እንዳየሽው፣ሥነሥርዓቱን ካደመቁት ፕሮግራሞች አንዱ በተስፋሁን ከበደ ግጥም ታጅቤ ያቀረብኩት ግጥም በውዝዋዜ ነው፡፡ ወደፊት ይበልጥ አዳብረዋለሁ፡፡
በግጥሞችህ የልማት ጥያቄን፣ የአገር ነፃነትንና ፖለቲካዊ ጭብጦችን አንስተሃል፡፡ አቀራረብህም  ማራኪ ነው፡፡ ለምሳሌ፤
ለተወለደ ልጅ እስኪ ስም ለማውጣት
አትሽቀዳደሙ
ነፃ ባልሆነ አገር የተወለደ ልጅ ነፃነት ነው ስሙ
ትላለህ፡፡ ይሄ የሚገርም እይታ ነው፤ ለእኔ---
እውነት ነው፡፡ አንዳንዴ መልከ ጥፉን በስም ይደግፉ ይሆንብሻል፡፡ ነገሩ ብዙ ነፃነት በሌለበት አገር የልጅን ስም ነፃነት ብሎ መጥራት፣ ለመፅናናት ካልሆነና ነፃነትን ለመናፈቅ ካልሆነ፣ ስሜት የሚሰጥ ስም አይደለም፡፡ እውነተኛውን ነፃነት ለማግኘት መስራትና ልጅን ነፃነት ብሎ መጥራት ለየቅል ናቸው። ለምሳሌ አንድ አንቺም እንደወደድሽው የነገርሽኝ፣ እኔም የምወደው ግጥም አለ፤
ሀገር ከተራበ ወገን ከተጠማ
ሊጡ ኩፍ ብሎ ምጣዱ ካልሰማ
ማገዶ አትጨርስ በዋዛ ፈዛዛ
ይሄን ስበርና አዲስ ምጣድ ግዛ፡፡--- ይላል፡፡
እዚህ ላይ መግለፅ የተፈለገው ስለ ምጣድም ስለ ሊጥም ስለ ማገዶም እንዳልሆነ ግልፅ ነው፡፡ ግን በወካይ ቁሶች የመግለፅ አቅሜን ተጠቅሜ፣ ትልቅ መልዕክት ማስተላለፍ ነው የምፈልገው፡፡
ሥዕልም ትሞክራለህ መሰለኝ?
ምንም አልልም፡፡ ሳልማር በፊትም በቀለም ፔይንቲንግ እሰራ ነበር፡፡ “ሶፊ አርት ስቱዲዮ” ነው የተማርኩት፡፡ የስቱዲዮው ባለቤት የሆነ ሥዕሌን አሳየሁትና ገርሞት፤ ”እኔ ጋ ና አስተካክልሃለሁ” አለኝ - ተማርኩኝ፡፡ ነገር ግን ግጥሙም ውዝዋዜውም ጊዜ ስላልሰጠኝ ለሥዕሉ ብዙ ቦታ አልሰጠሁትም፡፡ ሁሉንም አድምቼ ሳልሰራ እዛም እዚህም መርገጥ ጥሩ አይሆንም፡፡ ውዝዋዜን አጥብቄ ያዝኩ፡፡ ፍቅረኛዬ ማፊ የመጀመሪያ መፅሐፌን ሰርፕራይዝ ስታደርገኝ ግጥምን እንደ ሁለተኛ ሥራዬ አጥብቄ ያዝኩኝ፡፡ ሁለቱን በምን ላቀናጅ ስል “ግጥም በውዝዋዜ” መጣ፡፡ ሥዕሉን ደግሞ ወደፊት እንደ ሁኔታው አመቺነት አየዋለሁ።
ወደፊት ምን አቅደሃል?
ወደፊት የግጥም ብቻ ሳይሆን የወግም ብዙ መጽሐፍትን መፃፍ እፈልጋለሁ፡፡ እድሜዬም ብስለቴም እየጨመረ ሲሄድ፣ በደንብ ማንበብ ስችል ማለቴ ነው፡፡ በውዝዋዜው በኩል አሁን ካለሁበት አንድ ምዕራፍ ከፍ ማለት እፈልጋለሁ። ለምሳሌ እኔ ራሴን ፕሮፌሽናል ተወዛዋዥ ብዬ እጠራ ይሆናል፤ ነገር ግን ፕሮፌሽናል ነህ ብሎ እውቅና የሰጠኝ አካል የለም። ይሄ የሆነው በአገሪቱ ላይ ለዚህ ሙያ እውቅና ለመስጠት የተቋቋመ ተቋም ስለሌለ ነው፡፡ ነገር ግን ባህል ተበላሸ፣ ተበረዘ ይባላል፡፡ መንግስት በዚህ በኩል እየሰራ አይደለም፡፡ ክልሎችም ባህል ተበላሸ ይላሉ፤ ግን ባህሉን ለመጠበቅ የሚያደርጉት ጥረት አይታይም። ቴአትር ቤቶች የሚያቀርቡትም ቢፈተሽ ብዙ ችግር ያለበት ነው፡፡ ውዝዋዜ ጥበብም ነው ባህልም ነው፡፡ በጥበብነቱ ማደግ አለበት፡፡ እንደ ባህልነቱ መጠበቅ አለበት የሚል እምነት አለኝ፡፡ ስለዚህ ስለ ውዝዋዜ መሰረታዊ ነገሮችን የያዘ መጽሐፍ በቅርቡ አሳትማለሁ። ተወዛዋዥ ማለት ምን ማለት ነው ሲባል፤ “እኔ እንጃ” የሚል ተወዛዋዥ እንዲኖረን አልፈልግም። ስለዚህ በዚህ ዙሪያ ብዙ መስራት እፈልጋለሁ። እዚህ እስክደርስ ድጋፍና እንክብካቤያቸው ያልተለየኝን እናቴንና በዙሪያዬ ያሉትን ሁሉ ከልብ አመሰግናለሁ። አንዱን ጠርቼ ሌላውን እንዳልዘነጋ በማሰብ ነው ስም ያልጠቀስኩት፡፡     

Read 487 times