Sunday, 07 October 2018 00:00

የኤርትራ መንግሥት የፖለቲካ እስረኞችን እንዲፈታ ተጠየቀ

Written by  አለማየሁ አንበሴ
Rate this item
(4 votes)

    የኢትዮጵያና የኤርትራ እርቅን ተከትሎ ፖለቲካዊና ዲፕሎማሲያዊ ማሻሻያ እያደረገች ነው የተባለችው ኤርትራ፤ የፖለቲካ እስረኞችን እንድትፈታ ሂውማን ራይትስ ዎች ጠይቋል፡፡ የሁለቱ ሀገራት ግንኙነት ዳግም ከተጀመረ በኋላ የኤርትራ መንግሥት በተለይ በዲፕሎማሲው ረገድ ከፍተኛ ማሻሻያ ማድረጉን፣ የህገ መንግስት ረቂቅ ማዘጋጀት መጀመሩን፣ በሃሳብ ልዩነትና በፖለቲካ አመለካከት የተሰደዱ ኤርትራውያን ወደ ሀገራቸው እንዲመለሱ ጥሪ ማቅረቡን የገለፀው የሰብአዊ መብት ተሟጋች ድርጅቱ፤ ከእነዚህ ማሻሻያዎች ጎን ለጎን የፖለቲካ እስረኞችን መፍታት አለበት ብሏል፡፡
በ2001 (እኤአ) 21 ከፍተኛ የመንግሥት ባለስልጣናትና ጋዜጠኞች በግፍ መታሰራቸውንና በእስር ላይ የተለያዩ ኢ - ሰብአዊ ተግባር እየተፈፀመባቸው መሆኑን የጠቆመው ድርጅቱ፤ እነዚህን ጨምሮ በመቶዎች የሚቆጠሩ እስረኞች በአስቸኳይ እንዲፈቱ ጠይቋል፡፡ የሀገሪቱ መንግስት በህግ የበላይነትና በእስረኞች ጉዳይ ማሻሻያ ያደርጋል ተብሎ ሲጠበቅ በቅርቡ ግልፅ ባልሆነ ምክንያት የሀገሪቱን የገንዘብ ሚኒስትር ዘብጥያ መወርወሩ “ተገቢነት የጎደለው ኢ-ፍትሃዊ ድርጊት” ነው ሂውማን ራይትስ ዎች ሲል በፅኑ ኮንኗል፡፡የኤርትራ መንግስትና የኢትዮጵያ መንግስት፤ የተባበሩት መንግስታት በኤርትራ ላይ የጣለውን ማዕቀብ እንዲያነሳ መጠየቃቸው የሚታወቅ ሲሆን ሂውማን ራይትስ ዎች በበኩሉ፤ የመንግስታቱ ድርጅት የሃገሪቱን ሰብአዊ መብት አጠባበቅና አያያዝ እንዲያጤን ጠይቋል፡፡



Read 7255 times