Print this page
Sunday, 07 October 2018 00:00

ወደ ሃገር ቤት የተመለሱ የፖለቲካ ድርጅቶች በምርጫ ቦርድ አልተመዘገቡም ተባለ

Written by 
Rate this item
(4 votes)

“ከዜግነት ጋር የተያያዘው ህግ እንቅፋት ሆኖብናል”
በመንግስት ጥሪ ተደርጎላቸው ከውጭ አገራት ወደ ሃገር ቤት የተመለሱ በርካታ የፖለቲካ ድርጅቶች እስካሁን በኢትዮጵያ ምርጫ ቦርድ ተመዝግበው ህጋዊነትን ያላገኙ ሲሆን የፖለቲካ
ድርጅቶቹ እንዲመዘገቡ ምርጫ ቦርድ ጥሪ አቅርቧል፡፡ የኢትዮጵያ ምርጫ ቦርድ የኮሚኒኬሽን ጉዳዮች ዳይሬክተር አቶ ተስፋለም አባይ ለአዲስ አድማስ በሰጡት ማብራሪያ፤ ቦርዱ ቀደም ሲል ለፖለቲካ ድርጅቶቹ ጥሪ በማድረግ፣ በአመዘጋገብ ስርአቱና ሂደቱ ላይ ገለፃ መስጠቱንና እንዲመዘገቡም ማስታወቁን ጠቁመው፤ እስካሁን ከ“አፋር ህዝብ ፓርቲ” በስተቀር ወደ ጽ/ቤቱ ቀርቦ አቅርቢ እውቅና ለማግኘት
ያመለከተ ፓርቲ የለም ብለዋል፡፡ የሀገሪቱ ህግ፤ “ማንኛውም የፖለቲካ ድርጅት በሃገር ውስጥ ህጋዊ ሆኖ ነው መንቀሳቀስ አለበት” ይላል ያሉት አቶ ተስፋለም፤ ድርጅቶቹ ወደ
ምዝገባ ስርአቱ እንዲገቡ ቦርዱ የተለያዩ ጥረቶችን እያደረገ መሆኑን ገልፀዋል፡፡ በአሁኑ ወቅት ምርጫ ቦርድ በህጋዊነት የመዘገባቸው 22 ሀገር አቀፍና 40 ክልላዊ፣ በድምሩ 62 ፓርቲዎች መሆናቸውንም ዳይሬክተሩ ጠቁመው፡፡ ቦርዱም በሀገሪቱ የፖለቲካ ፓርቲነት የሚያውቃቸው እነዚህኑ ድርጅቶች ብቻ ነው ብለዋል - አቶ ተስፋለም፡፡ ወደ ሀገር ቤት የተመለሱ የፖለቲካ ድርጅቶች፣ ወደ ቦርዱ ቀርበው ህጋዊ የሚያደርጋቸውን ምዝገባ እንዲያከናውኑም ቦርዱ ጥሪ አቅርቧል፡፡ ወደ ሀገር ውስጥ ከተመለሱት የፖለቲካ ድርጅቶች መካከል የኦሮሞ ነፃነት አንድነት ግንባር እና የትግራይ ዲሞክራሲያዊ ትብብር፤ ከዜግነት ጋር የተያያዙ የህግ ድንጋጌዎች ምዝገባ እንዳያደርጉ እንቅፋት እንደሆነባቸው አስታውቀዋል፡፡
የትግራይ ዲሞክራሲያዊ ትብብር አመራር አቶ ግደይ ዘርአፅዮን “ከዜግነት ጋር በተያያዘ ያለው ህገ ደንብ ላይ ማብራሪያ እየጠየቅን ነው፤ ህጉ ተስተካክሎ ምዝገባውን እናከናውናለን
ብለን ተስፋ እናደርጋለን” ብለዋል፡፡ የኦሮሞ ነፃነት አንድነት ግንባር አመራር አቶ አሚን ጁንደም በተመሳሳይ፤ ይህ ህግ እና ተያያዥ ጉዳዮች ምዝገባውን እንዳያደርጉ እንቅፋት እንደሆነባቸው ለአዲስ አድማስ
አስታውቀዋል፡፡ አንድ የፖለቲካ ድርጅት በኢትዮጵያውያን ተቋቁሞ ኢትዮጵያዊ ዜግነት ባላቸው አመራሮች ብቻ እንደሚመራ በህግ ተደንግጓል፡፡
የጠ/ሚኒስትር ዐቢይ አህመድ ጥሪን ተከትሎ የትጥቅ ትግል ሲያደርጉ የነበሩ የፖለቲካ ድርጅቶችን ጨምሮ ከ15 በላይ የሚሆኑ ፓርቲዎች ወደ ሀገር ቤት መመለሳቸው ይታወቃል፡፡

Read 7363 times
Administrator

Latest from Administrator