Print this page
Saturday, 06 October 2018 09:41

ዶ/ር ዐቢይ አህመድ በ176 ድምፅ ተመረጡ

Written by  አለማየሁ አንበሴ
Rate this item
(15 votes)

“በዶ/ር ዐቢይ አመራር አለምን ያስደነቀ ለውጥ መጥቷል” - ዶ/ር ደብረፅዮን ገ/ሚካኤል

    በሐዋሳ ከተማ ላለፉት ሦስት ቀናት ጉባኤውን ሲያካሂድ የቆየው ኢህአዴግ፤ ዶ/ር ዐቢይ አህመድንና አቶ ደመቀ መኮንንን በሊቀ መንበርነትና በም/ሊቀመንበርነታቸው እንዲቀጥሉ የመረጠ ሲሆን ኢህአዴግ የርዕዮተ ዓለም ለውጥ አለማድረጉ ታውቋል፡፡ በጉባኤው በዋናነት ባለፉት 6 ወራት በዶ/ር ዐቢይ አህመድ አመራርነት የመጡ ፖለቲካዊ ለውጦች የውይይት አጀንዳ እንደነበሩ የጠቆሙት የስብሰባው ተሳታፊዎች፤ ጠ/ሚኒስትሩ የሰጧቸው አመራሮች ውጤታማና ስኬታማ ነበሩ በሚል መገምገሙን ጠቁመዋል፡፡ የህውሓት ሊቀ መንበር ዶ/ር ደብረፅዮን ገ/ሚካኤል በጉባኤው ላይ በሰጡት አስተያየት፤ በጠ/ሚ ዶ/ር ዐቢይ አህመድ አመራርነት ባለፉት 6 ወራት በሀገሪቱ የመጣው አዎንታዊ ፖለቲካዊ ለውጥ እውቅና ሊሰጠው ይገባል ብለዋል፡፡ “ባለፉት ስድስት ወራት የተመዘገቡት አለምን ያስደነቁ ለውጦች ዶ/ር ዐቢይ እንደ መንግሥት መሪ የራሱን ፈጠራ፣ ድፍረት፣ ጥበብና ሁለንተናዊ የአመራር ብቃት ተጠቅሞ ያመጣው ለውጥ ነው፣ ለዚህም ተገቢውን እውቅናና ክብር መስጠት ያስፈልጋል” ማለታቸውን አንድ በስብሰባው የተሳተፉ ከፍተኛ ባለስልጣን ተናግረዋል፡፡ በጉባኤው ሌላው ትኩረት የተሰጠው ጉዳይ የዲሞክራሲ ስርዓት ግንባታና የህግ የበላይነት ጉዳይ ሲሆን ከዚህ በኋላ የህግ የበላይነት እና የዲሞክራሲያዊ ስርአት ግንባታ ጉዳይ ለድርድር እንደማይቀርብ በጉባኤው ተወስኗል፡፡ ሙስናና የሰብአዊ መብት ጥሰት የሚፈፅሙ አካላት ከእንግዲህ በትዕግስት እንደማይታለፉም በጉባኤው ተወስኗል፡፡  ለውጡን እንደግለሰብም ሆነ እንደ ኢህአዴግ አባል ድርጅት የማይቀበሉና እንቅፋት ለመፍጠር የሚሞክሩ ወገኖች ላይ ቆራጥ እርምጃ እንዲወሰድ ከስምምነት ላይ መደረሱም ታውቋል፡፡
ከ6 ወራት በፊት ሀገሪቱም ኢህአዴግም በመስቀለኛ መንገድ ላይ እንደነበሩ ያስታወሰው ጉባኤው፤ ሀገሪቱ የመበተን አደጋ ተጋርጦባት እንደነበርም ገምግሟል፡፡ የአመራር ለውጥ ተደርጎ
ዶ/ር ዐቢይ ወደ ስልጣን ከመጡ በኋላ ኢትዮጵያውያን በለውጥ ተስፋ መሞላታቸውን፣ ይህም በሀገሪቱ የፖለቲካ መረጋጋት መፍጠሩ በጉባኤው ተወስቷል፡፡ በኢህአዴግ 11ኛ ጉባኤው ላይ የርዕዮተ ዓለም ጉዳይ የተነሳ ቢሆንም ከውሳኔ ሳይደርስ በይደር መታለፉንም ምንጮች ጠቁመዋል፡፡ በጉባኤው ማጠናቀቂያ የድርጅቱን ሊቀመንበርና ም/ሊቀመንበር ለመምረጥ 177 ሰዎች የተሳተፉበት ምርጫ ተካሂዶ፣ ዶ/ር ዐቢይ በ176 ድምፅ፣ ሊቀመንበር ሆነው ተመርጠዋል። አቶ ደመቀ መኮንን እና ዶ/ር ደብረፅዮን ገ/ሚካኤል ለም/ሊቀመንበርነት ተወዳድረው፣ አቶ ደመቀ 149 ድምፅ በማምጣት የምክትልነቱን ቦታ ይዘው ሲቀጥሉ ዶ/ር ደብረፅዮን 15 ድምፅ ማግኘታቸው ታውቋል፡፡



Read 9018 times