Print this page
Saturday, 06 October 2018 10:00

ይመኑኝ ጠቅላይ ሚኒስትር፤ ክልላዊ አስተዳደርን ከብሔር ጋር የደባለቀው ህገመንግስቱ እንጂ ዜጎች አይደሉም

Written by  ቴዎድሮስ ጸጋዬ (Silver Spring Marylan
Rate this item
(5 votes)

ክቡር ጠቅላይ ሚኒስትር፣ የኢህአዴግን ጉባኤ ሲከፍቱ ያደረጉትን ንግግር ሰማሁ፡፡ በመልካም ቃላትና አረፍተነገሮች በጎ መንፈስ በሀገራችን ለማስፈን ያደረጉትን ሙከራ ተመልክቻለሁ፡፡ እሰየው! ነገር ግን፣ “ክልላዊ አስተዳደርን ከብሔር ጋር አናምታታ” ብለው ማለትዎን አየሁና ድምጼን ላሰማ ተነሳሁ፡፡
እውነት እውነት እልዎታለሁ፤ ይህንን ክልላዊ አስተዳደርን ከብሄር የመቀላቀል ቅሌት የሰራው የድርጅትዎ ግራ ርዕዮትና ከዚያ የተወለደው ህገ መንግስት ነው፡፡
 1 - ገና ሲጀምር የህገመንግስቱ ተዋዋዮችና ቃልኪዳን አሳሪዎች አድርጎ የጠቀሳቸው ብሄሮች፣ ብሄረሰቦችንና ህዝቦችን ብቻ አይደለምን? እነኚህ አካላት ስንት ህዝብ ሲያካትቱ፣ ምን አይነት ስነልቡና ሲኖራቸውና እንዴት ሲሰፍሩ ይህን “ብሄር ብሄረሰብ” ወይም “ህዝብ” የሚል ስያሜ እንደሚያገኙ እራሱ ህገመንግስቱ ባያውቀውም። ነገር ግን ስላቁ ይገባናል። ህገ መንግስቱ ብሄር፣ ብሄረሰብ ወይም ህዝብ ሲል፤ የህገመንግስቱ ፈጣሪ የሆነው ኢህአዴግ እራሱን፣ ብሄራዊ ድርጅቶቹንና አጋር አሻንጉሊቶቹን እንዲሁም በኋላ ለስልጣኑ ሲያሰጉት ከአገር ያባረራቸውን ጽንፈኛ ተገንጣይ ቡድኖችን መሆኑ አይጠፋንም፡፡
2 - ይህ ህገ መንግስት ከብሄር በቀርስ ሌላ ማንነት ያውቃልን? አንድ ዜጋ በአፍ መፍቻ ቋንቋው መማር መዳኘቱ ሰብአዊ መብቱ እንጂ ከመንግስት የሚሰጠው ልዩ ስጦታ እንዳይደለ አምናለሁ፡፡ ነገር ግን በኢትዮጵያችን ያለው ማንነት የብሄር ብቻ ይመስል ህገ መንግስቱን፣ አስተዳደራዊ መዋቅሩን፣ ፖለቲካውን፣ የትምህርት ስርዐቱን ወዘተ በብሄርና ብሄር ብቻ እንዲቃኝ መደረጉ የህወሀትና የኦነግ ይቅር የማይባል ጥፋት ነው፡፡ ጠቤ ከቶም ከፌደራሊዝም ጋር አይደለም፡፡ እውነተኛ የፌደራሊዝም ጠባይ ከሌለው ከዘውግ ፌደራሊዝሙ ጋር እንጂ፡፡ ብዙ ጊዜ ህገመንግስቱ እንዲሻሻል የሚጠይቁ ዜጎችን አተያይ፣ አሃዳዊ መንግስት ለማምጣት የሚቀርብ እይታ አድርጎ መሳል ቅንነት የጎደለው ነው፡፡ እውነትም አይደለም። እኔ እስከማውቀው ድረስ ክቡር ጠቅላይ ሚኒስትር፤ በኢትዮጵያ የዚህን ህገ መንግስት ከመሰረቱ መሻሻል የሚጠይቁና የዜግነት ፖለቲካን Civic nationalism እውን ሆኖ  ማየት የሚሹ አገር አቀፍ ፓርቲዎች፣ ድርጅቶችና ተጽእኖ አሳዳሪ  ግለሰቦች አቋም ፌደራሊዝም እንደ አስተዳደር ፍልስፍና አያስፈልግም የሚል ፈጽሞ አይደለም፡፡ ይልቅስ፣ ይህን በዘውግ ብቻ የሚያስብና፣ ፌደራላዊ ነኝ ባይ አሃዳዊ ስርአት፣ በሌላ ዜጎችን በሚያዋህድና ለአገራዊ አንድነትና ህልውና ዋስትና በሚሰጥ እውነተኛ የዘውግ ያልሆነ ፌደራሊዝም ይተካ ዘንድ ነው ትግላቸው፡፡
3 - በዚሁ የመከራ ህገመንግስት  አንቀጽ 8 ላይ፤ ሉአላውያን ወይም የራሳቸው ሉአላዊነት ያላቸው ስለመሆናቸው የተደነገገው ካለ እነኚህ ብሄር፣ ብሄረሰብና ህዝብ በቀር ሌላ ስለማን ነው? ታድያ ከዚህ ህገ መንግስት በላይ አገራዊ አንድነትን የሚያፈርስና ኢትዮጵያን ከአንዲት የተዋሃደች አገርነት ወደ ጥቃቅን “አገራት ክምችት” የቀየረ ተወቃሽ ከየት ይመጣል?
4 - ከዚህ ለዜጎች ሳይሆን ለብሄሮች… ሉአላዊነት ከሚያጎናጽፍ ግራ ህገ መንግስትና አንቀጽ ማህጸንም፣ ለየብሄሩ መገንጠልን የሚፈቅድ አንቀጽ ተወልዶ፣ በህገ መንግስቱ ሰፍሮ እንደሚገኝ መቼም ይዘነጋዎታል ተብሎ ሊታመን አይችልም፡፡ ይህም፣ የአገር ህልውና ስግብግብና ጽንፈኛ በሆኑ እኩይ ተጽእኖ አሳዳሪ፣ የዘውግ ፖለቲከኞች እጅ የወደቀ እንዲመስል አድርጎታል፡፡ ሀገር፣ እንዳትነጣጠል ሆና የተዋሃደች ሳትሆን ማንም “ደበረኝ” ሲል ጥሏት የሚወጣ፣ ገርበብ ተደርጋ የተተወች ደሳሳ ቤት እንድትሆን የተደረገው በዚህ ህገ መንግስት ነው፡፡ ታድያ የአገርን ህልውና ቅድመሁኔታዊ የሚያደርገውን  ይህንን ገንጣይ አንቀጽ፤ በአሁን ወቅት እግርዎ እስኪቀጥን አለምን ቢዞሩ  ከፈረደባት አገራችን በቀር የትም አያገኙትም።  ስለዚህም ክልላዊ አስተዳደርን ከብሄር ማንነት እንዳይለይ አድርጎ የዘረጋውና  ከብሄር ማንነት በላይ ለሌሎች ማንነቶች አይኑ የታወረው፣ ይህ ህገ መንግስት ነውና፣ ጣትዎን እዚህ አሜሪካ መጥተው በጎበኙን ጊዜ “ባይሻሻል እመርጣለሁ” ባሉት ህገ መንግስት ላይ ብቻ ይቀስሩ፡፡
5- ክቡር ጠቅላይ ሚኒስትር፣ ብዙ ጊዜ ስለ ዜጎች በአገራቸው ያሻቸው ቦታ ተንቀሳቅሶ፣ ሰርቶና ሀብት አፍርቶ የመኖር መብት ሲናገሩ እሰማለሁ። ይገርምዎታል፤ እኔ በዚህ ሃሳብዎ አልስማማም። ምክንያቱም፣ ተንቀሳቅሶና ሰርቶ፣ ሀብት አፍርቶ የመኖር መብትማ የማናቸውም የመኖርያ ፈቃድ ያገኙ ስደተኞች እንጂ የዜጎች መብት አይደለም፡፡ የዜጎች መብት ከዚህ በእጅጉ ይልቃል፡፡ የዜጎች መብትማ የአገር ባለቤትነት መብት ነው፡፡ አንድ ኢትዮጵያዊ ከአንዱ ወደ ሌላው የአገሩ ግዛት ሲንቀሳቀስ እየተሰደደ አይደለምና ያለው፣ መብቱ ተንቀሳቅሶ ሰርቶና ሀብት አፍርቶ በመኖር ብቻ መገለጡ ዜግነትን ያሳንሳል። ይህም በአንድ ኢትዮጵያዊና ከደቡብ ሱዳን ወይም ከኤርትራ ወይም ከሌላ ስፍራ በመጣ ስደተኛ ተጠላይ መሀል ያለውን የመብት ልዩነት  የሚያጠፋ ነው፡፡ ታድያ በተለያየ ጊዜ ዜጎችን ማፈናቀል እንደማይገባ ሲናገሩ፤ “የጎረቤት አገራትን ስደተኞች እንኳ እንቀበል የለ” አይነት ንግግር ሲያደርጉ ልቤን ቅር ይለዋል፡፡ የዜጎች መብት ከዜግነታቸው እንጂ እዚያ በተሳሳተ ርዕዮትና ትርክት ቀድመው እንደሰፈሩ ከሚያምኑ ቡድኖች ቸርነት ሊመነጭ አይችልምና፡፡ ዜግነት ከገዛ አገር ጋ ያለ ልዩ ቃልኪዳንና ውድ ቁርኝት ነውና፣ እንደ አንድ ኢትዮጵያዊ በገዛ አገሬ ያለኝ መብት ከስደተኞች ጋር መነጻጸሩን ወይም መስተካከሉን ልቤ አይፈቅደውም። በሰው አገርም በእኔው አገርም ስደተኛ ሆኜ እንዴት እችለዋለሁ? ሆኖም፣ ይህም ጠማማ እይታ ከምን እንደመነጨ ያውቃሉ? ከዚሁ አገር አፍራሽ  ህገ መንግስት! የዚህ ህገ መንግስት ውላጆች የሆኑት የየክልሎቹ ህገ መንግስቶችም፤ በየክልሉ ያሉ ህዝቦችን ነባርና መጤ ብለው የሚከፍሉ፣ ነባር ለሚሏቸው ደግሞ በዚያ ክልል መሬትም ሆነ ሀብት ላይ ሌላው ዜጋ የሌለውን የልዩ ባለቤትነት መብት የሚሰጡ ሆኑ። ይኼ፣ ሰሞኑን ያየነው “አዲስ አበባ የእኔ ብቻ ናት፤ ሌሎቻችሁ ነዋሪዎች እንጂ ዜጎች አይደላችሁም” የሚል የኦሮሞ ድርጅቶች “ዳንኪራም” አንዱ ምንጭ  የዚህ ህገ መንግስት ነጣጣይ መንፈስ ነው፡፡ ልብ ይበሉ ጠቅላይ ሚኒስትር፣ የእነኚህ ድርጅቶች አዋጅ ህገ መንግስታዊ ነው አላልኩም፡፡ የማወራው ግን ህገ መንግስቱ በሀገሪቱ ስላረበበው የ“እኔ ብቻ” መንፈስ ነው፡፡
ፈጣሪ ያሳይዎ፤ መላ ሀገሪቱን የወረሰውን የግጭት ካርታ ቢመለከቱ የግጭቱ ወላፈን ያልደረሰበትን የኢትዮጵያ ክፍል አያገኙም፡፡ ትግራይ ክልል ከአማራ ክልል፣ አማራ ክልል ከኦሮሚያ ክልል፣ አማራ ክልል ከቤኒሻንጉል ክልል፣ ጋምቤላ ክልል ከደቡብ ክልል፣ ኦሮሚያ ክልል ከደቡብ ክልል፣ ኦሮምያ ክልል ከሶማሌ ክልል ጋር፣ በአዲስ አበባ ምክንያት ደግሞ ኦሮሚያ ክልልን ከተቀሩት የኢትዮጵያ ክልሎች በሙሉ ጋር… እነኚህ ሁሉ በዚህ ህገ መንግስት ምክንያት የተፈለፈሉ አልያም የተባባሱ የመሬትና የድንበር ይገባኛል እንዲሁም የተፈጥሮ ሀብት አጠቃቀምን ሰበብ ያደረጉ ግጭቶች ናቸው፡፡ ይህ እንግዲህ በየክልሎቹ ውስጥ በየብሄሮች መሀል የሚካሄደውን ስፍር ቁጥር   የሌለው አፈናቃይና ደም አፋሳሽ ግጭት ሳይጨምር ነው፡፡ እናም፣ ግጭቱ ሰርክ የሚከሰት፣ ሰላም ደግሞ በእነኚህ ግጭቶች መሀል ያለች አጭር አፍታ መሆኗ ነው፡፡ ስለዚህም ባለፉት ሦስት አስርት አመታት ገደማ በመላ አገሪቱ በዜጎች ላይ የሚደርሰው መፈናቀልና የአገር ውስጥ ስደት እዚህም እዚያም ባሉ ግለሰቦች ስህተት ተፈጠረ ሳይሆን፣ ህገ መንግስት ሰራሽ፣ መዋቅር ሰራሽና ስርአት ወለድ ነው፡፡ መፍትሄውም የህገ መንግስት፣ የመዋቅርና የስርአት ለውጥ ነው፡፡
6  - እስኪ ያስቡት ክቡር ጠቅላይ ሚኒስትር፣ በአንድ “የራሴን ቋንቋ ብቻ እናገራለሁ” በሚልና ከሌሎች ኢትዮጵያውያን ወገኖቹ ጋር የሚግባባበትን አማርኛ ቋንቋን ባለመማር ለብሄሩ መብት አስተዋጽኦ የሚያደርግ የሚመስለውን ምስኪን ወጣት ያስቡት። ይህ ወጣት፣ ሌሎች ወገኖቹን እንዳይገነዘብና ወገኖቹም እርሱን እንዳይገነዘቡት በቋንቋ ግድግዳ ተለይቶ፣ ብሄር ባለው ቢሮክራሲ ተነጥሎ፣ ብሄር ባለው ባንዲራ ተከልሎ፣ በከፋፋይ ትምህርት ተጋርዶ በየት በኩል  ኢትዮጵያ በልቡ ሰሌዳ ትጻፍ? ይህንን የቋንቋ፣ የመዋቅር፣ የቢሮክራሲ፣ የትምህርት ስርአት፣ የባንዲራ፣ የፕሮፖጋንዳና የህግ አጥር ተሻግሮ በምን አቅሙ ወደ ኢትዮጵያዊነት ይደግ? እንዴት ብሎ ኢትዮጵያ ሰገነት ላይ ይውጣ? ይህ ወጣት፣ የሰው ልጅ ታሪክ በአጼ ምኒሊክ የተጀመረ ይመስል፣ ዳግማዊ አጼ ምኒሊክና አባታችን አዳም ቢምታቱበት እንዴት እንፍረድበት? ይህ ስርአታዊና መዋቅራዊ ህመም ነውና በባህል ትውውቅ መድረኮችና በአገርህን እወቅ ክበባት  አይፈወስም፡፡
ክቡር ጠቅላይ ሚኒስትር፣ ሀገራችንን በውስጥ መፈናቀል ባለፉት አመታት በጦርነት አፈር ድሜ ከምትበላው ከሶርያ እንኳ እንድትበልጥ ምክንያት የሆነው፣ የአንድ አገር ዜጎችን በማያቋርጥ የእለት ተእለት ሽኩቻ ውስጥ የዘፈቀን፣ ህይወቱን በእኛ ልዩነት ላይ የመሰረተውና የጋራ የኖሩ ኢትዮጵያዊ እሴቶቻችንን ይበልጥ እንዳናበለጽግ ገደል ሆኖ የነጣጠለን ይኸው ህገ መንግስትና አስተዳደራዊ መዋቅር ነው፡፡ እመሀላችን ሆኖ ግጭት የሚያቀጣጥለው፣ ልዩነት የሚያባብሰው፣ የአገርን ተስፋ የሚያጨልመው፣ አንድነታችንን ቀስ በቀስ በልቶ እዚህ ያደረሰን የታቀፍነው እሳት … ይኸው በንግግርዎ ያልጠቀሱት፣  በለውጥ አጀንዳዎም ስፍራ ያልሰጡት የዘር መዋቅርና ህገ መንግስት ተብዬ ነው፡፡ ዙርያ ዙርያውን አይሂዱ፡፡ ሸረሪቷ ሳለች እለት ተእለት ድሩን መጥረግ ምን ይረባል ብለው? ዝሆኑ ችግር ሊድጠን በደረስንበት፣ ስለዚህ ዋና ጭብጥ ሳያነሱ፣ እኛን ዜጎችዎን ስለ ግብረገብና ሞራል ሲሰብኩን ቢውሉ ምን ይፈይዳል? ያጣነው ስር ተከል መሰረታዊ ለውጥ እንጂ የግለሰቦች በጎ ፈቃድ አይደለም፡፡ ግለሰብ በስልጣኑ ሲባልግ ወይም በስነምግባር ሲጎድፍ፣ በስርአትና በተቋም ያርቁታል። ስርአትና መዋቅር ሲጎድፍስ?
እውነት እውነት እልዎታለሁ፤ ይህንን ግልጽ ችግር የማያምንና ለዚህ መፍትሄ የማይሻ፣ ስለዚህም የመከራ ሰነድ “ህገመንግስት” እና ይኸው ስለወለደው የዘር  መዋቅር መለወጥ የማይወያይ ጉባኤ፤ ለኢትዮጵያ መዳንን ሊያስገኝ ከቶ አይችልም፡፡

Read 3447 times