Print this page
Saturday, 06 October 2018 10:24

ልጆች የሚያድጉበት ሐገር አልሆን አለ?!

Written by  አብዱልመሊክ ሁሴን
Rate this item
(4 votes)

ባለፉት አራት ዓመታት የተጓዝንበት ጎዳና በጣም አስጨናቂ ነበር፡፡ ፖለቲካዊ ብቻ ሣይሆን ማህበራዊ መሠረታችንም ተነቃንቋል፡፡ ነፍስ ያወቀውና ኃላፊነት የሚሰማው ሙሉ ሰው የሆነው ብቻ ሣይሆን ህጻናትም ብዙ ተጎድተዋል፡፡ ምናልባት ከሁለት ዓመት በፊት ይሆናል፡፡ ሁከቱ በተባባሰበት ወቅት ከልጄ ጋር የሁለት ሰዓት ዜና እያዳመጥን ነበር፡፡ በዜናው አንድ ከፍተኛ የአሜሪካ ባለሥልጣን (የውጭ ጉዳይ ሚኒስትሩ መሰሉኝ) ወደ ኢትዮጵያ ለጉብኝት መምጣታቸውን ከዜናው ስትሰማ፤ ‹‹ምን ይኼ ደግሞ አሁን ይመጣል እንዴ?›› አለች፡፡
አስተያየቷ ከሁከቱ ጋር እንደተያዘዘ አልገባኝም ነበር፡፡ ምን ተሰምቷት እንዲያ እንዳለች ለማወቅ ጓጉቼ ጠየቅኳት፡፡ ‹‹ለምን እንደሱ አልሽ?›› አልኳት፡፡
‹‹እሱ ሰላም ሲሆን አይመጣም እንዴ?!›› ብላ መለሰችልኝ፡፡ በቅድሚያ ሰላም የማጣታችን ጉዳይ ያን ያህል ያሳስባታል ብዬ ባለመገመቴ፤ የእሷ ደህንነት ሳያስጨንቃት፤ ‹‹በእርሷ ሐገር›› በእንግድነት የመጣ ሰው “ችግር ደረሰበት” ቢባል፤ ለሐገሯ ውርደት እንደሚሆን ስላሰበች መሰለኝ መጨነቋ፡፡
ሁከቱ ህጻናቱን እንዳስጨነቃቸው ተረዳሁ፡፡ ይህን ነገር ለመምህሩ ጓደኛዬ ነገርኩት፡፡ እርሱ በሚያስተምርበት ክፍል የተከሰተ ሌላ አሳዛኝ ነገር ጨመረልኝ፡፡ ለብሔር ብሔረሰብ ክብረ በዐል ተማሪዎችን ሲያዘጋጅ፣ አንዲት ተማሪ የብሔር ማንነቷን ለመደበቅ ስትሞክር በማየቱ ለቅሶ ቀረሽ ሐዘን እንደተፈጠረበት አጫወተኝ፡፡ ‹‹ከዚህ ነሽ ካሉሽ አይደለሁም በዪ (በል)›› ብለው ለልጆቻቸው ትዕዛዝ የሰጡ አንዳንድ ወላጆች መኖራቸውን አረዳኝ፡፡ በእነዚህ ጨቅላ ህጻናት ህሊና፣ ምን ዓይነት ስሜት እየፈጠርን እንደሆነ ተረዳሁ፡፡
ከፍ ሲል የጻፍኳቸውን አንቀፆች ጽፌ ስጨርስ፤  ‹‹ከልቦለድ ይልቅ ህይወት ታስደንቃለች›› የሚያሰኝ አንድ ሌላ እንግዳ ነገር ተከሰተ፡፡ ፊልም እያየች የነበረችው ልጄ፤ የጆሮዋን ጉትቻ መዋያ በጣቷ መታ መታ እያደረገች፤ ‹‹ጆሮዬ ላይ ድምጽ ይረብሸኛል›› አለች፡፡ ‹‹ምን ሆንሽ?›› አልኳት፤ ትንሽ ደንገጥ ብዬ፡፡ ዓይኗን ከቴሌቭዥን መስኮት በማንሳት፣ ወደኔ ዞር በማለት ‹‹ፊልሙን እያየሁ የሰው ወሬ ይሰማኛል›› አለችኝ፡፡
በርግጥም ጎረቤቴ  ከአንድ የማላውቀው ሰው ጋር ከውጭ እያወራ ነበር፡፡ ከጽሕፈት ጠረጴዛዬ ተቀምጬ መጻፍ ከመጀመሬ ከደቂቃዎች በፊት ከደጅ ስንጎራደድ ሰምቼው ነበር፡፡ ወደ ቤት ከገባሁ በኋላም ፍሬ ነገሩን ለመለየት በሚያስቸግር ሁኔታ ከፊልሙ ድምጽ ጋር ተዛንቆ ወሬው ይሰማኝ ነበር፡፡ ‹‹ከውጭ እከሌ ከሰው ጋር እያወራ እኮ ነው፡፡ ድምጹ ይሰማኛል›› አልኳት፡፡ እርሷም መለሰች፤ ‹‹በቀደም አራት ኪሎ የነበረው ግርግር ዝም ብሎ ይመጣብኛል›› አለች፡፡ አራት ኪሎ አያቷ ቤት ሄዳ የተፈጠረውን ግርግር፣ ሰላማዊ ሰልፍና ተኩስ አይታለች፡፡
በቀድም ከት/ቤት እንደ መጣች ‹‹ዛሬ [ሐሙስ] ክፍል ውስጥ ሆነን፣ የሆነ ተኩስ ሰምተን ተረበሽን፡፡ አስተማሪያችን ተረጋጉ፤ ወደ መስኮቱ አትሂዱ አለን፡፡ በመጨረሻ ርችት ነው ብለውን ተረጋጋን›› አለችኝ፡፡
ልጆቻችን በየጊዜው ብሔር ተኮር ጥቃት ስለመፈፀሙ፤ ሰዎች ከመኖሪያ ቀያቸው ስለ መፈናቀላቸው፤ ኢትዮጵያውያን በሐገራቸው ልጆች ስለ መታረዳቸው ሲወራ ይሰማሉ፡፡ ምናልባትም የኢንተርኔት አገልግሎት ለማግኘት የሚችሉት ይህን አሰቃቂ ትዕይንት ያያሉ፡፡ በልጆቻችን ሥነ ልቦና ሊፈጠር የሚችለውን እክል መገመት ቀላል ነው፡፡ በሐዋሳ የሚካሄደው 11ኛው የኢህአዴግ ድርጅታዊ ጉባዔ ከዚህ ዓይነት ችግር የምንወጣበትን መላ ማበጀት ይኖርበታል፡፡  


Read 5682 times