Sunday, 07 October 2018 00:00

የያሬድ ጥበቡ “ወጥቼ አልወጣሁም” በወፍ በረር

Written by  ደረጀ በላይነህ
Rate this item
(0 votes)

• እነ አቶ መለስ ዜናዊን፣ በረከት ስምኦን፣ አዲሱ ለገሰን እንዴት ይገልጻቸዋል?
  • በ”ያ ትውልድ ፖለቲከኞች” ያልተለመደ ሚዛናዊነትና ቀናነት ይታይባቸዋል

    ሔነሪ ዴቪድ ቶሮው ልቡ ውስጥ በዋልደን ጫካ የተፀነሰው ሃሳብ፣ ቶልስቶይንና ጋንዲን ከዚያም ማርቲን ሉተር ኪንግን አነሁልሎ አልተቀበረም፤ ይልቅስ በአዳዲስ ልቦች በቅሎ ዓለምን አዳርሷል፡፡ ለብዙ ሕዝቦችም የነፃነት መድህን ሆኗል፡፡ እኔም ዛሬ በርካታ ታሪካዊ እውነታዎችን ገላልጦ የሚያሳየውን የፖለቲከኛ ያሬድ ጥበቡን “ወጥቼ አልወጣሁም” መጽሐፍ ሳነብ፣ የልቤ ጆሮ ውስጥ የገባው ይኸው ሀቅ ነው፡፡
መጽሐፉ የተለያዩ ፖለቲካዊ መጣጥፎች የተካተቱበት ቢሆንም፣ የዘመን አንጓውና የታሪክ ፍሰቱ ተሰናስሎ በመቅረቡ የኢትዮጵያን 40 ዓመታት ድፍን ታሪክ እንዲሁም የመሪዎችዋን ህልምና ገመና ቁልጭ አድርጐ ያሳያል፡፡ ለ27 ዓመታት በኢትዮጵያ ላይ የነገሰው ኢሕአዴግ፤ ሲጠፈጠፍ ድክድክ ሲል፣ ጐርምሶና ጐልምሶ አደባባይ ሲሞላ---ምን ይመስል እንደነበር በዝርዝር እናነባለን፡፡
ኢህአዴግን ከእግር ጥፍሩ እስከ ራስ ጸጉሩ አብጠርጥሮ የሚያውቀው የኢሕአፓ አባልና ታጋይ የነበረው፣ በኋላም የኢሕዴን መሥራች የሆነው ያሬድ ጥበቡ፤ህወሓትን ጨምሮ በዘመኑ ስለነበሩት የፖለቲካ ድርጅቶች ማንነትና ምንነት በስፋት ያወጋናል፡፡  
አቶ ያሬድ፤ ከሟቹ ጠቅላይ ሚኒስትር መለስ ዜናዊ ጀምሮ፣ ታምራት ላይኔን፣ አዲሱ ለገሠን፣ በረከት ስምኦንና ሌሎች የትግል ጓዶችን ባህርይ፣ ችሎታ፣ ጠንካራና ደካማ ጎን ወዘተ ---- በቅርበት ያየውን፣ አብሮ ታግሎ  የታዘበውን፣ የተገነዘበውን ያጋራናል፡፡ እኔ እንደ አንባቢ በእጅጉ የገረመኝና ልቤን ያነጠፍኩለት ጉዳይ፣ የደራሲው ቀናነትና ሚዛናዊነት ነው፡፡ በእኛ ሀገር የፖለቲካ ባህል ጨርሶ ባልተለመደ ሁኔታ፣ ከሱ ፍላጐትና አቋም የተለዩ፣ አንዳንዴም በጠላትነት የቆሙ ፓርቲዎችና ፖለቲከኞችን ጠንካራ ጐን እያደነቀ መፃፉ፣ ለአቶ ያሬድ ያለኝን አክብሮት የላቀ አድርጎታል። ምናልባትም ለኢትዮጵያውያን ሥነ-ልቡና በእጅጉ የራቀውን ጸጋ ተጎናጽፎ  በማግኘቴም ይሆናል የተደመምኩበት፡፡ በተለይ መበላላትና መጠፋፋትን ባህል ላደረጉት ለ”ያ ትውልድ” ፖለቲከኞች፤ በ11ኛው ሰዓት ላይም ቢሆን ዓይን ገላጭ ነው - የያሬድ ጥበቡ “ወጥቼ አልወጣሁም”፡፡ እንኳንም ጻፈልን ብያለሁ፡፡     
ወደ ዋና ጉዳያችን ስመጣ፤መጽሐፉ እጅግ በጣም በርካታ ጉዳዮችን ይዳስሳል፡፡ የበረሃውን ኢሕአፓን፣ ህወሓትን፣ ኢዲዩን፣ ኢሕዴንን፣ ጀብሃን፣ ሻዕቢያንና ሌሎችን--- መልክና ገመና ያወጣል፡፡  የመሪዎቹን ህልምና ርዕይ፣ ክፋትና በጐነት፣ ሌላም ሌላም … በሚገባ ያስቃኘናል፡፡ አደባባይ መጥተው የምናውቃቸው እነ መለስ፣ እነ ታምራት ላይኔ፣እነ አዲሱ ለገሰ፣ እነ አቶ በረከት ስምኦን--- ሌሎችንም  ማንነትና ጉዞ በየቀለማቸው፣ በሚመች ፍሰት፣ በሚጥም ትረካ ይነግረናል፡፡ በቅጡ ያስተዋውቀናል፡፡
እንደ ደራሲው ገለፃ፤ ሕወሓት ሲጀመርም ብሔራዊ ቅራኔ ዋነኛው ችግር ነው ብሎ ነው የተነሳው፡፡ 4/5ኛው ሕዝብ በብሔራዊ ቅራኔ የታፈነ ነው ብሎ ያምናል። ስለዚህም ህብረ ብሔራዊ ፓርቲዎች፤ የሀገሪቱን የሰቆቃ ሕይወት ለመለወጥና በጊዜው የነበረውን የደርግን መንግሥት ለማስወገድ፣ ትክክለኛ አታጋዮችና መፍትሄ ይሆናሉ ብሎ አያምንም ነበር፡፡
አንድ አማራና ትግሬ ለማኝ አብረው መለመን የማይችሉበት ቅራኔ አላቸው ብሎ የሚያምነው ሕወሓት፤ የብሔር ታጋይነቱን ሰንደቅም መልሶ ሲያጥፈውና ሲቀረጥፈው እንደነበር ማሳያ አስቀምጦልናል፡፡ ለምሳሌ፤ ለትግራይ ህዝብ እታገላለሁ ብሎ የታጠቀውን “ትግራይ አርነት ግንባር”፤ በሚዘገንን ሁኔታ አስወግዷቸዋል፡፡ የልዑል ራስ መንገሻ ስዩምን ድርጅትም እንዲሁ በጥፋት እሳት አንድዶታል፡፡
ስለ ኢሕዴን ሲገልጽም፤ “ኢሕዴንንም ቢሆን በፈለገው አምሳል ጠፍጥፎ ያድበለበለው ተለጣፊ ባይሆንም፣ ከቁጥጥሩ የማያመልጥ ደካማ ድርጅት ሆኖ እንዲቀጥል ብዙ ጥረት አድርጓል” ይላል፡፡ የ“የካቲት ቡድን” አባላት ከኢሕዴን ጋር ለመቀላቀል ያደረጉትን ጥረት አክሽፏል፡፡ የህወሓትን ወላዋይና አድርባይ ባህርይ የሚያጋልጠው ያሬድ፤ጠንካራ ጎኑንም ያለ ስስት በአድናቆት ይገልጻል፡፡
“ስለ ራሳቸው ያላቸው ግምት መሬት የለቀቀ ባዶ ፊኛ አይደለም፤ መሪዎቹ ማንነታቸውን ያውቃሉ። ችሎታቸውንና ድክመታቸውን ይረዳሉ። ችሎታቸውን ለማሳደግ ይጥራሉ፡፡ ድክመታቸውን ለማረም ፍቃደኞች ናቸው፡፡ ከገባሩ መካከል ጥሩ ጄኔራሎች፣ ድንቅ የቀዶ ጥገና ሐኪሞች ሊወጡ እንደሚችሉ ያምናሉ፡፡ እምነታቸውንም በተግባር ያውሉታል። አንድ የሶስተኛ ክፍል ትምህርት ደረጃ ያደረሱትን ብልህ የገባር ልጅ፤ የቀዶ ጥገና ሐኪማቸው ረዳት ሆኖ ለዓመት ሁለት ዓመት ከሰራ በኋላ ጋንግሪን የወረሰውን ቁስለኛ እጅ እግር ቆርጦ አሽጐ፣ እንዲያድን ዕድሉን ይሰጡታል፤ እምነት ያሳድሩበታል--”
የኢሕአፓ አባል የነበረው አቶ ያሬድ፤ በትጥቅ ትግሉ ውስጥ ያደረጋቸውን እልህ አስጨራሽ ፍልሚያ ይተርክ እንጂ የራሱን ፓርቲ ከፍ አድርጎ፣ የታሪክ ማማ ላይ ለመስቀል አልጣረም፡፡ እንደ ፓርቲ፣ የጦር ሜዳ ውሎ ባደረጉባቸው ስፍራዎች የገጠማቸውን ሽንፈትም ሳይደብቅና ሳያዳላ ይነግረናል፡፡
የቀድሞው ጠ/ሚኒስትር አቶ መለስ ዜናዊ የግድ ካልሆነባቸው በቀር ፤”ኢትዮጵያ” ብሎ መጥራት ብዙም አይመቻቸውም ነበር ይላል - ያሬድ፡፡
 “አቶ መለስ የአብዮታዊ ዴሞክራሲ ማራቸውን በየትኛው ቀፎ ላይ ለመጋገር እንደሚፈልጉ ግልፅ አይደለም፡፡ በየገፁ የቦናፓርቲዝም አደጋ የሚል ሐረግ የተደነቀረ ከመሆኑ ጋር፣ ለእርም እንኳ “ኢትዮጵያ፣ የኢትዮጵያ ህዝብ” ብሎ ከመጠቀም በጣም የተቆጠቡ በመሆናቸው፣ ስለ ፈረንሳይ ነው የሚያወሩት? ብሎ ግር ለመሰኘት የሚያስችል አቀራረብ ነው የመረጡት። አቶ መለስ ቢሆንላቸው ሶማሊያን፣ ሱዳንና ጅቡቲን ጨምረው የአፍሪካ ቀንድ ፌዴራላዊ ሪፐብሊክ የሚል አዲስ አገር መመስረት ቢችሉ አልዋጥ ብሎ ከሚተናነቃቸው ኢትዮጵያዊ ስም ይገላገሉ ነበር…”
አቶ መለስ፤ በአንድ ወገን ለእነ አይኤምኤፍ ማጐብደድን እየሸሹ፣ በሌላ ወገን ደግሞ እጅ እየሰጡ፣ የሀገራቸውን ነጋዴ፣ ሠራተኛና ወዘተ… ከኢሕአዴጐች ውጭ ያሉትን በማጣጣል ለውጥ ለማምጣት መሞከራቸውና መፎከራቸውን እንደማይቀበሉት አቶ ያሬድ ይገልጻል፡፡ “ግሎባላይዜሽን ተቆጣጣሪ የሌለው አንዳች ኃይል መሆኑን መገንዘብዎን አስተውለናል፤ ግን ከዚህ ኃይል ጋር በ“አብዮታዊ ዴሞክራሲ” ወኔ በመጋፈጥና በመጋጨት ሳይሆን በስልት ነው “ነፃ አገር” መገንባት የሚቻለው…” ይላል፡፡
ደራሲው አቶ መለስን በብዙ ጉዳዮች ይተቻል - በመጽሐፉ፡፡ ለምሳሌ በአቶ ታምራት የጠቅላይ ሚኒስትርነት ዘመን፣ በተደጋጋሚ ጣልቃ መግባታቸውን ያነሳል፡፡ በኒያላ ኢንሹራንስና በዳሸን ባንክ ጉዳይ ለውጭ ሀገር ዜጋ የማይፈቀደውን ሥራ፣ “ከህግ ውጭ ነው” በማለት የወቅቱ ጠቅላይ ሚኒስትር ታምራት ላይኔ ያገዱትን፣ አቶ መለስ ስልጣን ተላልፈው መፍቀዳቸውን ይጠቅሳል፡፡ በተመሳሳይ፣ በዚሁ ወቅት የአቶ መለስ ዘመድ የወሰዱትን ቪላ ቤት፣ በፍርድ ቤት ውሳኔ ለባለቤቱ ተመልሶ ይሰጥ ሲባል፣ አቶ ታምራት የወሰኑትን ውሳኔ ከማፍረስ ጀምሮ በርካታ አምባገነናዊና የሕግ የበላይነትን የሚጻረሩ ስራዎች መስራታቸውን ያስታውሳል፡፡   
አቶ መለስ ካነበቡዋቸው መጻሕፍት በጥልቀት የገባቸውና የተዋሃዳቸው የስታሊን “ኦን ዘ ኦፖዚሽን” የሚለው ነው ይላል፡፡ እንዲያውም የቱ የራሳቸው፣ የትኛው የስታሊን መሆኑ እስኪጠፋቸው ድረስ የሰውየው ሀሳቦች ውስጣቸው ዘልቋል በማለት ይገረምባቸዋል፡፡ በሌላ በኩል ደራሲው፣ ከአቶ መለስ ጋር የሚስማማባቸው ጉዳዮች እንዳሉም ከመግለፅ ወደ ኋላ አላለም፡፡ በተለይ የሊብራል ዴሞክራሲን ጽንሰ ሀሳብን በሚመለከት ከመለስም አልፎ እንደሚሄድ  ይገልጻል፡፡
“ከአቶ መለስ ጋር በትግል ሜዳ ከተገናኘን ባለፉት ሃያ አንድ ዓመታት ውስጥ እንደዚህ በአንድ መሠረታዊ ጉዳይ ላይ ተስማምተን የምናውቅ አይመስለኝም።” ለዚህም ምክንያቱ፤ ሊብራል ዴሞክራሲ ለሀገራችን ባዕድ ስለሆነ ነው ባይ ነው፡፡
እንግዲህ የአቶ ያሬድ ትልቁ በጐ ነገር፤ በሚስማማበት መስማማትና በሚለያይበት መለያየትን መቀበል ነው፡፡ በሚዛናዊነቱ የተነሳ የሚተቹት  ወገኖች እንደሚኖሩም  ያውቃል፡፡
“ለኢሕአዴግ መሪዎች ማን መካሪ አደረገህ የሚሉ ሃያስያን፣ ደስተኛ እንደማይሆኑ አውቃለሁ፡፡ እኔ ግን በሰው ልጆች ላይ ተስፋ አልቆርጥም፡፡ ቀናውን መንገድ ካሳየናቸው ለመከተል ይከጅላሉ የሚል እምነት አለኝ።” (ገፅ 129) ባይ ነው - ደራሲው፡፡
የቀድሞው ጠ/ሚኒስትር በሞት ከተለዩም በኋላ ጥንካሬያቸውን አፈር አላለበሰውም፡፡ “በተፈሪነታቸው ብቻ ሳይሆን በብሩህ አዕምሯቸው ትጋት አቶ መለስ አራቱን የኢሕአዴግ ድርጅቶች አስተባብረው ለመሄድ ችለው ነበር፡፡” በማለት ጥንካሬያቸውን በድፍረት ይገልፃል - በመጽሐፉ፡፡

Read 396 times