Saturday, 06 October 2018 10:34

በሀሳብ መንገድ ላይ

Written by  ተመስገን
Rate this item
(0 votes)

“የእግርህን ሸፋፋነት በጫማዎችህ አታላክክ!!”
              ተመስገን

     “አፍንጫው ባይረዝም ግሩም ሃውልት ነበር!” … አለ ሰውየው፤ ሚካኤል አንጀሎ ሲሰራ የነበረውን ትልቅ የሰው ቅርጽ (statue) አንጋጦ እየተመለከተ፡፡
ቀራፂው፤ “እርግጠኛ ነህ?” ብሎ ጠየቀው፡፡
“በደንብ እንጂ!” በማለት አረጋገጠለት፡፡
አንጀሎ ከመሰላሉ ወረደ፡፡ ከሰውየው አጠገብ ቆሞ ስራውን አስተዋለና፤  “ልክ ነህ” በሚል ስሜት እራሱን እየነቀነቀ፣ መሰላሉ ላይ ተንጠለጠለ፡፡ ስራውን ሲጨርስ ተመልሶ ወረደና …
“አሁንስ?” … አለው ወዳጁን፡፡
“Perfecto! (አሪፍ ሆነ!)” ሲል መለሰ፡፡       
ቀራፂው ምክሩን ተቀብሎ፣ ስህተቱን አርሞ፣ ሃውልቱን በማስዋቡ እየተደሰተ፣ ወደ ጉዳዩ አቀና፤ ሰውየው፡፡
*   *   *
ከሌሎች መማር ጥሩ ነው፡፡ ተገቢ ነው፡፡ ትምህርት ቤት ስንሄድ፣ ሌሎች ሰዎች ያስተምሩናል። የምናነባቸው መጽሐፍትም ሌሎች ሰዎች የፃፏቸው ናቸው፡፡ አንዳንድ ጊዜ ግን ‹ሌሎች› ከምንላቸው ሰዎች የምንማረው እንዳለ ሆኖ፣ የሌሎችን ስራና ሃሳብ ከራሳችን ስራና ሃሳብ ጋር ስናነፃፅረው፣ ‹የኛ› የተሻለ ሊሆን ይችላል፡፡ ምክንያቱ ደግሞ ‹ሌሎች› የምንላቸው ሰዎች ሊሆን ይችላል፡፡ በአንድ የጥበብ፣ የፍልስፍና፣ የእምነት ወይም የፖለቲካ ርዕስ ላይ ድንገትና ለየብቻ ተጠይቀው የሚሰጡት ሃሳብና አስተያየት እንኳንስ ለአገርና ለህዝብ፣ ለዕውቀትና ለስልጣኔ ጥቅም ግብዓት ሊሆን ቀርቶ፣ እርስ በርሳቸው እንኳ የሚያግባባቸው አይደለም፡፡ በአብዛኛው የግል ስሜትን ማዕከል ያደረገና “እኔ እበልጣለሁ” በሚል ቃና የተከሸነ ነው የሚመስለው፡፡  
ወዳጄ፡- ለህመሙ መፍትሄ ያጣ በሽተኛ፤ ከአንድ ሀኪም ወደ ሌላው እየተንከራተተ የሚሰማውና የሚታዘዝለት መድኃኒት፣ አንዱ የሌላውን ምክርና ትዕዛዝ የሚቃረን ሲሆን አዕምሮው ይጨነቃል። አዕምሮው ሲጨነቅና ግራ ሲገባው ህመሙ ይባባሳል። እየተጠራጠረ የሚወስዳቸው መድኃኒቶች አይጠቅሙትም፡፡ … ህመም እንዳይሰማን ለማድረግ አዕምሯችን ትኩረቱ እንዲቀየር ወይም ሰመመን ውስጥ እንድንገባ አንስቴዢያ እንደምንወስድ ሁሉ ጉዳት ሲደርስብንም የህመም ስሜት እንደሚሰማን የምናውቀው በአዕምሯችን በኩል ነው - ይላሉ ባለሙያዎቹ፡፡ ለዚህ ነው … በማንኛውም ዓይነት ህመም የታወከ በሽተኛ ህክምና ሲጀምር፣ በህክምና ላይ እያለና ከህክምናው በኋላ፣ ከሚደረግለት በትህትና የታጀበ መልካም አቀባበል ጎን ለጎን፣ አዕምሮው ካልታከመ (Psychological Treatment ካልተሰጠው) ጥሩ ውጤት ማግኘት አዳጋች  የሚሆነው፡፡
ወዳጄ፡- ሌላውን መምከር ስትፈልግ ወይም ምክር ስትጠየቅ፤ የምትመክረው ግለሰብ፣ ድርጅት ወይም ህዝብ ታሪኩን፣ ኑሮውንና ፍላጎቱን በቅድሚያ ማጥናት ይኖርብሃል፡፡ “Know your audience” እንደሚሉት፡፡ ልትጭናት ለፈለግሃት አህያ፤ የወርቅ ሃብል፣ የአልማዝ ማበጠሪያ ወይም ዕቅፍ ጭድ ብታስቀምጥላት፣ የምትፈልገውን የምትመርጠው እሷ ናት፡፡ … ለራስህ አስበህ፣ ለራስህ አውርተህ፣ ለራስህ አጨብጭበህ፣ ‹ልክ› ነው ያልከውም ነገር፤ ሌሎች ሰዎችን ላያስደስት ይችላል፡፡ አዕምሯቸውን ሳይመጥን ሲቀር አሊያም የኑሮ ዘይቤአቸውን የሚያናጋ ሲሆን ይቆጣሉ። ከሀሳብ ባለፈ በምርጫቸው ጣልቃ አለመግባት ብልህነት ነው።
ወዳጄ፡- ትልልቅ ሃሳቦችን መሸከም ለማይችሉ አዕምሮዎች፣ ከአቅም በላይ የሚሆንባቸውን ዕውቀትና የአስተሳሰብ መርህ ያለ ስነ ልቦናዊ ዝግጅት መጫን፣ ለችግራቸው ፈውስ መሆኑ ቀርቶ ህመማቸውን የሚያባብስ ይሆናል፡፡ … የዚያኑ ያህል ትንንሽ ሃሳቦችን ትልልቅ አዕምሮዎች እንዲቀበሏቸው ማባበል ወይም ማስገደድ በራስ ላይ መቀለድ ነው፡፡ … አንድ በርሜል ውሃን ወደ አንድ ብርጭቆ ለመገልበጥ መሞከር ወይም አንድ ብርጭቆ ውሃን በትልቅ በርሜል ማስቀመጥ  በራስ ላይ መቀለድ ካልሆነ በቀር ምን ሊባል ይችላል? … የማይሆን እንዲሆን መታገል፣ ሊሆን ከሚችለውና ሊሆን ከሚገባው ጉዳይ ያዘናጋል፡፡ ጊዜ፣ ጉልበትና ንብረትም ይባክናል፡፡
ወዳጄ፡- ነገሮች የሚለወጡበትን መሰረታዊ ምክንያት፣ ህግና መንገድ ማወቅ ቅድሚያ ሊሰጠው የሚገባ ጉዳይ ነው፡፡ ውስጣዊና ውጫዊ ቅራኔዎች፣ የሳይንስና የቴክኖሎጂ ግብዓቶች፣ ዓለም አቀፋዊና አገራዊ ተፅዕኖዎች እንዲሁም ሌሎች ቋሚና ተለዋዋጭ ሁኔታዎችን ማገናዘብም ከስህተት ይቆጥባል፡፡ … በሰለጠኑ ሀገራት ውሻን አሰልጥኖ መኪና እንዲነዳ ማድረግ ተችሏል፡፡ ወደ በግነት መቀየር ተችሏል ሲባል ግን አልሰማንም፡፡ … ጥቅም ሊያስገኝ የሚችለው ቁም ነገር፤ መለወጥ ወይም ማስተካከል የፈለግኸውን ነገር ተፈጥሯዊ ባህሪ መረዳት ነው፡፡ … ምናልባት’ኮ መለወጥ፣ መስተካከል ወይም መታረም ያለብህ አንተው ራስህ ትሆናለህ፡፡ … መንገድህ ላይ ተደንቅሮ የሚያደናቅፍህን ጉቶ መንቀል ከአቅም በላይ ሆኖብህ፣ በሂደት እስኪበሰብስና ባህሪውን እስኪቀይር የምትጠብቅ ከሆነ ተሞኝተሃል፡፡ ተፈጥሮው በአጭር ጊዜ የሚለወጥ አይደለምና፡፡ … መንገድህን መቀየርና ባህሪህን ማረቅ ያለብህ አንተ ነህ፡፡ አለበለዚያ ቀድመህ ትበሰብሳለህ፡፡
ወዳጄ ሆይ፡- የአስተሳሰብ ድክመትህን በተፈጥሮ፣ በሌሎች ሰዎችና በጊዜ የምታላክክ ከሆነ … “የእግርህን ሸፋፋነት በጫማዎችህ አታሳብብ” የሚለውን ብሂል ዘንግተኸዋል ማለት ነው፡፡ … የራስህን እውነትማ ተጋፈጣት፡፡ በነገራችን ላይ … “One is a coward, if not face every natural happenings that comes in life, with all strength and dignity” በማለት የፃፈልን ማን ነበር?
*   *   *
ወደ ሚካኤል አንጀሎ እንመለስ፡፡ ሰውየው የሃውልቱ አፍንጫ እንደረዘመ ሲነግረው፣ ቀራፂው ምክሩን ተቀብሎ ስራውን እንዳስተካከለ፣ ሰውየውም በደስታ እየፈነደቀ ወደ ጉዳዩ እንደሄደ አውግተን ነበር፡፡ የሆነው ግን እንደሱ አልነበረም፡፡ ቀራፂው የሰውየውን ባህሪ አውቆታል፡፡ … “ለማለት ብቻ” መናገሩን፡፡ ምክሩን የተቀበለ መስሎ ሃውልቱ ላይ ከወጣ በኋላ መዶሻና ማንኪያውን ከሃውልቱ ድንጋይ ጋር እያጋጨና እያንኳኳ፣ በሽርጡ ኪስ ይዞት የነበረውን የእምነበረድ ዱቄት ነበር የሚያቦነው፡፡ አፍንጫውን ንክች አላደረገም፡፡ ይህን ያስነበበን ደራሲ አቤ ጉበኛ ነው፤
ሰማዩን ባንካሴ ቆፍሬ ቆፍሬ
ለወሬ ሱሰኞች አገኘሁኝ ወሬ! …. ብሎ  በሚጀምረው መጣጥፉ፡፡
ወዳጄ፡- ዝባዝንኬ ከሚያበዙ በርካታ ሰዎች ይልቅ ለስልጣኔ ግብዓት የሚሆን ቁምነገር የሚያፈልቁ ጥቂት ሰዎችን ማዳመጥ አይሻልም? “Best minorities are better than dull majorites” በሚለው አባባልስ አትስማማም? ከተስማማህ “አትላስ ሽረግድ”ን (Atlas Shurgged) አንብብ፡፡ አንጀትህን ታርስሃለች፤ ደራሲዋ!!... ካልተስማማህ “ብዙኃን ይመውዑ” የሚለውን ዘፈን መርጬልሃለሁ!!
ሠላም!!


Read 1484 times