Sunday, 07 October 2018 00:00

የትምህርት ማሻሻያ ሳይሆን ማባባሻ “ፍኖተካርታ”

Written by  ዮሃስ ሰ
Rate this item
(2 votes)

      - ከእውነት ጋር በመጣላት የሚነሳ!


    “የትምህርትና ሥልጠና ችግሮቻችን እና የመፍትሔ አቅጣጫዎች” በሚል ርዕስ፣ በትምህርት ሚኒስቴር የተዘጋጀው ሰነድ፣ በአንድ በኩል እጅግ ከፍተኛ ሰነድ እንደሆነ አያጠራጥርም። ምክንያቱም፣ ለሚቀጥሉት 20 ዓመታት የአገሪቱን ትምህርት የሚመራ “ፍኖተካርታ” ይሆናል ተብሎ የተዘጋጀ ነው።
በሌላ በኩል ግን፣ እጅግ የወረደ ሰነድ ነው። እውነተኛ መረጃዎችን በመካድ ነው የሚነሳው። ከደርግ ዘመን እስከ ዛሬ ድረስ ሲናፈሱ የቆዩ የሐሰት መረጃዎችን በጭፍን ተቀብሎ፣ ያንኑን አሉባልታ እንደበቀቀን በማራገብና ነባሩን የጥላቻ ፕሮፓጋንዳ እንደአዲስ በማናፈስ ይጀምራል - ሰነዱ። ምን ይሄ ብቻ!
የሰነዱ መነሻ፣ “ከእውነት ጋር የተጣላ ጭፍን ትረካ” መሆኑ ብቻ አይደለም ችግሩ። መድረሻው ደግሞ፣ የባሰ ነው። ከእውቀት ጋር የተጣላ አላማ፣ ለሚቀጥሉት ሃያ ዓመታት፣ የአገሪቱ ዋነኛ የትምህርት መመሪያ መሆን እንዳለበት የሚገልፅ ነው - የሰነዱ መድረሻ ግብ።
ባለፈው ሳምንት፣ ሰነዱን በማጣቀስ እንደገለፅኩት፣ “የአገሪቱ ትምህርት፣ ከእውቀትና ከንድፈሃሳብ እየራቀ መሄድ አለበት” የሚል አጥፊ ሃሳብ፣ እንደዋና የመፍትሄ ሃሳብ በሰነዱ ቀርቧል። እስቲ ዛሬ ደግሞ፣ “ከእውነት ጋር የተራራቀው የሰነዱ መነሻ” ላይ ላተኩር።
በአፄ ኃይለሥላሴ ዘመን ስለነበረው የትምህርት ሥርዓት፣ ሰነዱ እንዲህ ይላል።
“...ሥርዓተ ትምህርቶቹ በሀገር ውስጥ እንዲቀረጹ ቢደረግም፣... ከውጭ ተጽእኖ ሙሉ በሙሉ ተላቀው፣ የሀገሪቱን ችግር የሚፈታ ተደራሽነት፣ ተገቢነት፣ ፍትሐዊነትና ጥራት ያለው የትምህርት ሥርዓት ሊዘረጋ አልተቻለም። የነበረው የትምህርት ተደራሽነት ውስን ሲሆን፤ ትምህርት ቤቶችም በዋና ዋና ከተማ ብቻ  ነበር የሚገኙት፡፡ የትምህርት እድል ሴቶች፣ ልዩ ፍላጎት ያላቸውና አርብቶ አደር ዜጎች ጨርሶ የእድሉ ተቋዳሽ አልነበሩም። ...በወቅቱ  ከ85%  በላይ  የነበረውና  በግብርና የሚተዳደረውን ሕዝብ ግብርናውን በማዘመን የኑሮ ደረጃውን አላሻሻለም”...(ገፅ 4)።
እስቲ በዚህ አንቀፅ ውስጥ የተጠቀሱ የሐሰት መረጃዎችንና የተሳከሩ ሃሳቦችን፣ ለመፈተሽ እንሞክር።

ሥርዓተ ትምህርትና “የውጭ ተፅእኖ”
የሰነዱ አዘጋጆች፣... በአፄ ኃይለሥላሴ ዘመን ስለነበረው የትምህርት ሥርዓት ለመናገር፣ በቅድሚያ ትንሽ ማገናዘብ፣ ትንሽ ማመዛዘን አልነበረባቸውም? ማለቴ፣... ከዛሬ 60 ዓመት በፊት ስለነበረው ሁኔታ የሚያወሩ አይመስሉም።
ለማመዛዘን ያህል፣ “እስቲ፣... የያኔውን እንተወውና፣ ዛሬስ፣... ሥርዓተ ትምህርትን በቅጡ አጥርቶና ጠንቅቆ የማሰናዳት በቂ እውቀትና ችሎታ ይዘናል ነው ወይ?” ብለው ራሳቸውን መጠየቅ ይችሉ ነበር። ግን በእውቀትና በችሎታ ዙሪያ ለመናገር የፈለጉ አይመስልም። አለበለዚያማ፣... “ከውጭ ተጽእኖ መላቀቅ... አልተቻለም”... የሚለውን ነባር ባዶ መፈክር፣ እንደገና ዛሬም ማነብነብ ለምን አስፈለገ? እውነትንና እውቀትን የሚያከብር ሰው፣ “የውጭ... የአገር ውስጥ” ከሚል ባዶ መፈክር አይጀምርም። እውቀት፣... በየትኛውም አገር፣... ያው እውቀት ነዋ።    
“የኢትዮጵያ ልዩ ሳይንስ፣ የኬንያ ልዩ ሳይንስ”... “አፍሪካዊ ጂኦሜትሪና ካልኩለስ፣ ምዕራባዊ ጂኦሜትሪና ካልኩለስ፣... “ኢትዮጵያዊ የሰውነት የደም ዝውውርና የባዕድ የሰውነት የደም ዝውውር” እያልን... ከጥንቆላ ያልተሻለ ኋላቀርነትን መታቀፍ ካልፈለግን በቀር፣... እውነትና እውቀት... የትም ቢሆን፣ መቼም ቢሆን፣... ያው እውነትና እውቀት ናቸው። “ጠጣር፣ ፈሳሽ፣ አየር...” ፣ የእውን ነገሮች መሰረታዊ ገፅታዎች ናቸው - የትም አገር ቢሆን፣ የትኛውም ዘመን ላይ ቢሆን። ታዲያ፣... “የኃይለሥላሴ ዘመን ሥርዓተ ትምህርት በአገር ውስጥ ቢቀረፅም ከውጭ ተፅእኖ ሙሉ ለሙሉ አልተላቀቀም” በሚል ረብ የለሽ አባባል፣ የያኔውን ዘመን በከንቱ የማጥላላትና የማንቋሸሽ ጭፍን ስሜት፣ ሰነዱ ውስጥ ምን ሊያደርግ ገባ?
ለነገሩ፣ የተሳከረበት ሰነድ አይደል? “የውጭ ተጽእኖ” እያለ የድሮውን የሚያወግዝ ሰነድ፣... እዚያው በዚያው ራሱን ለማዳነቅ ምን ብሎ እንደሚተርክ ተመልከቱ።
የአገሪቱ የትምህርት መመሪያ ለማዘጋጀት፣... ከማሌዢያና ከቬትናም ልምድ ወስደናል በማለት ራሱን ያዳንቃል። በዚያ ላይ፣ ሰነዱን መልክ የሚያስይዙ የውጭ ሰዎች እንደሚቀጠሩ፣ ሰነዱ ይገልፃል - (በአድናቆት ስሜት ነው ይህንን የሚገልፀው። “ከውጭ ተጽእኖ ሙሉ ለሙሉ አልተላቀቅንም” በሚል ውግዘት አይደለም)።
ይልቅስ፣... የአገር ውስጥም ሆነ የውጭ አገር፣... እውነትን የሚክዱና እውቀትን የሚያንቋሽሹ ምሁራንን ትቶ፣... እውነትንና እውቀትን የሚያከብሩ ምሁራንን መቅጠርና፣... ሌላ አዲስ ጥናት ሀ ብሎ መጀመር ይሻላል።
ወደ ሌሎቹ ነጥቦች እንሸጋገር።  
በኃይለሥላሴ ዘመን ትምህርት አልተስፋፋም? ለዚያውም በላቀ ፍጥነት!
በኃይለሥላሴ ዘመን... “የትምህርት ተደራሽነት ውስን” እንደነበር ይገልፃል - ሰነዱ። ምን ለማለት ተፈልጎ እንደሆነ አስቡት።
“ወደፊት የምንመኘው አይነት፣... ግማሽ ያህሉ ተማሪ፣... ዩኒቨርስቲ ድረስ መማር የሚችልበት ሰፊ የትምህርት እድል፣ በኃይለሥላሴ ዘመን አልነበረም” የሚል ከንቱ የትችት አስተያየት ከማቅረብ አይለይም - ሰነዱ ውስጥ የሰፈረው ትችት። “ትምህርት ቤት ከሚገቡ 100 ተማሪዎች መካከል፣ ዩኒቨርስቲ የመግባት እድል የሚያገኙት 6ቱ ብቻ ናቸው” በማለት፣ የዛሬውን የትምህርት ሁኔታ በደፈናው ማንቋሸሽም፣ ያው ጭፍን ትችት ነው።
ይልቅስ፣... በአምስት ወይም በአስር ዓመታት ውስጥ ምን ያህል ተሻሻለ? ምን ያህል አደገ? ብሎ ማገናዘብና ማመዛዘን ያስፈልጋል።
እንደበቀቀን ነባር ፕሮፓጋንዳን ከማነብነብ ይልቅ፣ እውነተኛ መረጃዎችን ለማገናዘብና ለማመዛዘን ፍቃደኛ እስከሆንን ድረስ፣... ወይም ይችን ታክል ትንሽ ብቃት ካላጣን በስተቀር፣... ባለፉት 1000 ዓመታት፣ ከየትኛውም ዘመን በሚበልጥ የላቀ ፍጥነት ትምህርት የተሰፋፋው፣
በኃይለሥላሴ ዘመን እንደሆነ ለማወቅ አይከብድም። በተቃራኒው፣ “ያኔ ትምህርት አልተስፋፋም” ብሎ ማጥላላት፣... ከአላዋቂነትም የከፋ እጅግ የወረደ ጭፍንነት አይደለምን?
ካሁን በፊት እንዳደረግኩት፣ ለማሳያ ያህል ጥቂት መረጃዎችን ልጥቀስላችሁ። (ሴቶችስ ምን ያህል የመማር እድል ነበራቸው? “ጨርሶ የእድሉ ተቋዳሽ አልነበሩም።” ይላል - የትምህርት ሚኒስቴር ሰነድ። ይሄም አባባል፣ ከእውነት ጋር የተጣላ፣ “እጅግ የወረደ ጭፍንነት” እንደሆነ ተመልከቱ።
የተማሪዎች ቁጥር - ከስንት ወደ ስንት?
1940 ዓ.ም ዋዜማ ላይ፣ የአገሪቱ የተማሪዎች ቁጥር፣ 35,000 ነበር (ከነዚህ ውስጥ 3,400 ሴት ተማሪዎች ናቸው። ወደ 10% ገደማ ያህሉ ማለት ነው)።

ከዚያስ?
በ1948 ዓ.ም፣ የአንደኛና የሁለተኛ ደረጃ ተማሪዎች ቁጥር፣ 95,000 ገደማ እንደነበር ዶ/ር ተከስተ ነጋሽ ይገልፃሉ 1952 ዓ.ም፣ የተማሪዎች ቁጥር 225,000 ደርሷል (የሴት ተማሪዎች ብዛት ደግሞ፣ 51,400  ሆኗል። ወደ 23% ገደማ መሆኑ ነው።)
1966 ዓ.ም የተማሪዎች ቁጥር ወደ 1 ሚሊዮን ደርሷል (የሴት ተማሪዎች ብዛት፣ ወደ 310,000 ጨምሯል። ማለትም ከ30% በላይ። ታዲያ፣ የሴት ተማሪዎች ቁጥር የቱን ያህል በከፍተኛ ፍጥነት እንደጨመረ በግልፅ እየታየ፣ ሴቶች ቅንጣት የመማር እድል የማያገኙበት ዘመን የነበረ ለማስመሰል መሯሯጥ ለምን አስፈለገ? “ጨርሶ የእድሉ ተቋዳሽ አልነበሩም” የሚል ጭፍን ውግዘት የሚያራግብ ሰነድ፣... ያለጥርጥር እጅግ የወረደ ሰነድ ነው)።   
ነገሩን አገናዝበንና አመዛዝነን በአጭሩ ለመረዳት፣... የኃይለሥላሴ፣ የደርግና የኢህአዴግ ዘመናትን ለማነፃፀር እንሞክር። ፣... የታዩ የትምህርት ለምሳሌ፣ ከ1948 እስከ 1966 ዓ.ም ድረስ በነበሩት 18 ዓመታት ውስጥ፣ ትምህርት በምን ያህል ፍጥነት እንደተስፋፋ በንፅፅር ስንመለከት፣ ከሌሎቹ ጊዜያት የላቀ እንጂ ያነሰ አይደለም።
የአንደኛ ደረጃ ትምህርት፡
በ18 ዓመታት ምን ያህል ተስፋፋ?
በኃይለሥላሴ ዘመን..... 10 እጥፍ (1948-67)
በደርግ ዘመን..... 3 እጥፍ (1967-83)
በኢህአዴግ ዘመን..... 5 እጥፍ (1984-2004)
በአብዮቱ ዋዜማ፣ የአንደኛ ደረጃ ተማሪዎች ቁጥር 1.1 ሚሊዮን ደርሷል - በ18 አመታት ውስጥ ከ10 እጥፍ በላይ በማደግ። ከዘጠና ሺ ተነስቶ፣ ከአንድ ሚሊዮን በላይ ሆኗል።
በደርግ ዘመን፣ የአንደኛ ደረጃ ተማሪዎች ብዛት፣ 2.9 ሚሊዮን ገደማ ደርሷል - ሶስት እጥፍ አድጓል ማለት ነው፤ በ17 ዓመታት።
ኢህአዴግ ስልጣን ከያዘ በኋላ ባሉት 20 አመታት ውስጥስ? የተማሪዎቹ ቁጥር ወደ 15 ሚሊዮን ገደማ ነበር የደረሰው። በደርግ ዘመን ከነበረው ቁጥር ጋር ሲነፃፀር በአምስት እጥፍ ይበልጣል።

የሁለተኛ ደረጃ ትምህርት፡
በ18 ዓመታት ምን ያህል ተስፋፋ?
በኃይለሥላሴ ዘመን..... 20 እጥፍ (1948-67)
በደርግ ዘመን..... 5 እጥፍ (1967-83)
በኢህአዴግ ዘመን..... 6 እጥፍ (1984-2004)
በንጉሡ ዘመን ሃያ አመት በማይሞላ ጊዜ ውስጥ፣ ከ20 እጥፍ በላይ የጨመረው የሁለተኛ ደረጃ ተማሪዎች ቁጥር፣ በ1966 ዓ.ም 200ሺ ገደማ እንደደረሰ የአለም ባንክ የመረጃ ሰንጠረዥ ያሳያል።
በደርግ ዘመን፣ የተማሪዎች ቁጥር ወደ 900ሺ እንደተጠጋ መረጃው ያሳያል። የደርግ ዘመን የተመዘገበው፣ ወደ አምስት እጥፍ የተጠጋ እድገት፣ ከንጉሡ ዘመን ያነሰ ነው።
ኢህአዴግ ደግሞ በሃያ አመታት ውስጥ ወደ ስድስት እጥፍ ገደማ በማሳደግ 4.5 ሚሊዮን አድርሶታል።

ከፍተኛ ትምህርት
በኃይለሥላሴ ዘመን..... 15 እጥፍ (1948-67)
በደርግ ዘመን..... 3 እጥፍ (1967-83)
በኢህአዴግ ዘመን..... 15 እጥፍ (1984-2004)
የከፍተኛ ትምህርት ተቋማት ተማሪዎች ቁጥር፣ በንጉሡ ዘመን፣ በ18 ዓመታት ውስጥ፣ ከአራት መቶ ገደማ ወደ 6500 አካባቢ ጨምሯል -  በ15 እጥፍ።
በደርግ ዘመን፣ ወደ ሶስት እጥፍ ገደማ አድጎ፣ 18ሺ ደርሷል።
በኢህአዴግ የመጀመሪያዎቹ ሃያ አመታት ደግሞ፣ እንደ ንጉሡ ዘመን በአስራ አምስት እጥፍ በማደግ፣ የተማሪዎች ቁጥር ከ350ሺ በላይ ሆኗል።

ቴክኒክና ሙያ
በኃይለሥላሴ ዘመን.... 30 እጥፍ (1948-67)
በደርግ ዘመን..... እጥፍ አላደገም (1967-83)
በኢህአዴግ ዘመን..... 30 እጥፍ (1984-2004)
በንጉሡ ዘመን፣ በመጨረሻዎቹ ሃያ አመታት፣ የቴክኒክና ሙያ ትምህርት ከ30 እጥፍ በላይ ስለጨመረ፣ የተማሪዎቹ ቁጥር በአብዮቱ ዋዜማ 8700 ገደማ ደርሶ ነበር።
በደርግ ዘመን የታየው እድገት ኢምንት ነው። የተማሪዎች ቁጥር ከአስር ሺ ብዙም ፈቀቅ አላለም።
በመጀመሪያዎቹ የኢህአዴግ አስር አመታትም እንዲሁ፣ የእድገት ፍንጭ አልታየም። ከዚያ በኋላ ነው፣ በፍጥነት ማደግ የጀመረው። በኢህአዴግ ሃያኛ አመት ላይ፣ የቴክኒክና ሙያ ተማሪዎች ቁጥር፣ ከሰላሳ እጥፍ በላይ በማደግ ከ350ሺ በላይ ሆኗል። (በንጉሡ ዘመን ከታየው የለውጥ ፍጥነት ጋር ተቀራራቢ ነው)።

Read 450 times