በየስፖንሰር እጥረት ሳቢያ ውድድሮችን በቀጥታ የቴሌቭዥን ስርጭት ለማስተላለፍ አልተቻለም ምናልባት ነገ የፍፃሜ ውድድሮች ስርጭት ይኖራቸዋል ተብሎ ይጠበቃል፡፡ በየውድድሮቹ ለሚያሸንፉ አትሌቶች የሚሰጠው ሽልማትም አንሷል፡፡ ይሁንና የአትሌቲክስ ፌደሬሽን ሃላፊዎች በሰጡት መግለጫ ሻምፒዮናው በ5ሺሜ፤ በ3ሺ መሰናክልና በሌሎች ውድድሮች እስክ 3 ማጣርያዎች ለማለፍ በብዛት አትሌቶች መኖራቸው፤ በሜዳ ላይ የተለያዩ ስፖርቶች በቴክኒክ የተሻለ ተሳትፎ ሊያሳዩ መጠበቁና የክልሎች ተሳትፎ መጠናከር አበረታች ሆኗል፡፡ አሸናፊ አትሌቶች በአህጉራዊና ዓለም አቀፍ ውድድሮች ላይ ለሚሳተፉ ቡድኖእች የመመረጥ እድላቸው ሰፊ መሆኑ ትልቁ ኽልማት ይሆናል፡፡ የኢትዮጵያ አትሌቲክስ ፌደሬሽን በቀጣይ ዓመት ብሄራዊ የአትሌቲክስ ሻምፒዮናው በስፖንሰሮች ድጋፍ ተጠናክሮ፣ በሽልማት አድጎ፤ የቀጥታ ቴሌቭዥን ስርጭት ኖሮትና ለመጀመርያ ግዜ የመስተንግዶ አቅም ባላቸው ክልሎች እንዲዘጋጅ ጥረት መደረጉ እንደሚቀጥል ይገልፃል፡፡የኢትዮጵያ አትሌቲክስ ፌዴሬሽን በሰጠው ጋዜጣዊ መግለጫ፣ የአዲስ አበባ አስተዳደር ለክልልና ለክለብ በሚሰለፉ ተጨዋቾች ውዝግብ ከተሳትፎ መቅረቱን ሲገልፅ ሁኔታው በቀጣይ እንዳይደገም ምክክር ላይ መሆኑን አሳውቋል፡፡ በሌላ በኩል የሱማሌ ክልል ባለው የአስተዳደር ግንኙነት አለመቀላጠፍ መሳተፍ አለመቻሉንም እየመረመረ ነው፡፡ ከዚያ ውጪ የድሬዳዋ አስተዳደርን ጨምሮ ከተቀሩት 8 ክልሎችና 19 ክለቦች ወንዶች 513፣ ሴቶች 483 በድምሩ 996 አትሌቶች በያዙባቸው ቡድኖች እየተሳተፉበት ናቸው፡፡ የአትሌቲክስ ሻምፒዮና፣ ውርወራና ዝላይን ጨምሮ ከአጭር ርቀት እስከ አሥር ሺሕ ሜትር ያሉትን ያጠቃልላል፡፡ ሻምፒዮናው ተተኪ አትሌቶች ለማፍራትና ዓለም አቀፍ የውድድር ዕድል የማያገኙ አትሌቶች ምቹ መድረክ መሆኑን የገለፁት የፌደሬሽኑ ሃላፊዎች በመጪው ክረምት በስፔን ባርሴሎና በሚካሄደው የመጀመርያው የዓለም ወጣቶች ሻምፒዮናና በቤኒን በሚስተናገደው 18ኛው የአፍሪካ አትሌቲክስ ሻምፒዮና ደረጃ ውስጥ የሚገቡ አትሌቶች የመጀመርያ ተመራጭ ይሆናሉ፡፡በሌላ በኩል ውርወራና ዝላይን ጨምሮ የአጭር ርቀት ተወዳዳሪዎች በዓለም አቀፍ ደረጃ ውጤት ባይኖራቸውም በቀጣይ ግን በዓለም አቀፍ ደረጃ ተወዳዳሪ የሚሆኑ አትሌቶችን ከምልመላ ጀምሮ ለይቶ በማውጣት ፌዴሬሽኑ በዕቅድ ይዞ እየሠራ መሆኑን ተናግረዋል፡፡