Saturday, 06 October 2018 10:44

ነጋሪ: MANIFESTO

Written by  ሚፍታ ዘለቀ (የሥነ-ጥበብ አጋፋሪ
Rate this item
(4 votes)

“ጥበበኛ ነጋሪን ለማድመጥ፤ መጪውን ጊዜ ለመገንባት ወሳኝ ምዕራፍ ላይ ነን!”


    በጉራምዓይኔ የሥነ-ጥበብ ማዕከል በሰዓሊ ዳሪዎስ ኃ/ሚካኤል፣ ደምሴ ጉርሙ፣ ኪሩቤል መልኬ፣ ሮቤል ተመስገን፣ ሱራፌል አማረ፣ ታምራት ገዛኧኝና የሮ አዱኛ የቀረበና በዚህ ጽሁፍ አዘጋጅ አጋፋሪነት(Curation) የተሰናዳው ነጋሪ: MANIFESTO የሥነ-ጥበብ ትርዒት፣ ከትላንት መስከረም 25 ጀምሮ  ለዕይታ ክፍት ሆኗል፡፡
ትርዒቱ በሃገራችን ከቅርብ ጊዜ ወዲህ እየተከሰቱ ባሉ ፖለቲካዊ፣ ኢኮኖሚያዊ፣ ማሕበራዊና ሰብአዊ ቀውሶችና ትርምሶች ላይ የተመሰረተና  ረዥም  ጊዜ ከፈጁ ውይይቶች የተወለደ ነው፡፡ በተለይ ባለፉት ስድስት ወራት የኢትዮጵያውያን ሃሳብና የመወያያ አጀንዳ ሆነው የከረሙ ጉዳዮች ምን እንደነበሩ ማስታወስ አያሻም፡፡ ማንኛውም ዜጋ እንደ ግለሰብም ሆነ እንደ ማኅበረሰብ የሚወያይባቸውና የሚያስጨንቁ ጉዳዮች፣ የሥነ-ጥበብ ሰው ራስ ምታትና የቤት ስራ እንደሆኑ ይታወቃል፡፡ የቤት ስራውን የፖለቲከኞች ስራ ብቻ አድርጎ የመውሰድ አባዜ በተለይ በሃገራችን ፖለቲከኞች ዘንድ የተለመደ ነው፡፡ ክቡር ጠ/ሚኒስትር ዶ/ር ዐቢይ አህመድ፣ በሰኔ መጀመሪያ ላይ ለኪነ-ጥበብ ባለሙያዎች የሰጡት “ስልጠና”፤ ይህን ልማድ ለመስበር የታለመ ይመስላል፡፡ ስልጠናው እንደኔ ምልከታ፣ እንደ ዶሮ ወጥ የተቀመመ፣ የበሰለና በወግ የቀረበ ገበታ ሳይሆን እንደ ፈጣን-ምግብ (fast food) ሜኑ ሊወሰድ የሚችል ቢሆንም ውጤት አላመጣም ማለት ግን አይቻልም፡፡ (“ስልጠና”ውን በተመለከተ በሌላ ጽሁፍ እመለስበታለሁ፡፡)
ወደ ጉዳዬ ስመለስ፤ሠዓሊያንን ጨምሮ የሃገራችን የፊልም፣ የቴአትርና የሥነ-ግጥም ባለሙያዎች ተሰባስበው ለሁለት ወራት ያደረጓቸው ውይይቶችና ክርክሮች የዚህ ነጋሪ: MANIFESTO ትርዒት መነሻና መመንደጊያ ነው ማለት ይቻላል፡፡ የሥነ-ጥበብ ትርዒቱ፤ በሰብአዊነትም ሆነ በኢትዮጵያዊነት ልንመለከታቸው፣ ልንመረምራቸውና ልናሰምርባቸው የሚገቡ ወቅታዊ፣ ሃገራዊ ጉዳዮችን ነጋሪ ነው። ነጋሪ: MANIFESTO መጪውን ጊዜ ለመገንባት ወሳኝ ምዕራፍ ላይ እንደመገኘታችን፤ ነጋሪነት ተናጋሪነት ሳይሆን ጥበብ የተሞላ አመላካችነት መሆኑን በመረዳት፣ ጥበበኛ ነጋሪን ለማድመጥ አፍታ እንድንወስድ ይጣራል፡፡
በትርዒቱ ስራውን ያቀረበው አንጋፋው ሠዓሊ ደምሴ ጉርሙ “የተበላሸ” የሚል ስያሜ ከሰጠውና ቀይና አረንጓዴ የትራፊክ መብራት በአንድነት ከበሩበት ስራ ብንጀምር፣ እርምጃዎቻችን ምንም ያህል በተስፋ የተሞሉ ቢሆኑም ለመቆም የሚያስገድዱን የአስተሳሰብና የአመለካከት አደጋዎችን እስካላጠራን ድረስ ወደ ኋላ እንኳን ለመመለስ እድል የማይሰጥ መቆም፣ ለመቆም ብንገደድ፣ የሚገርም እንዳልሆነ የሚያሳስብ ነው፡፡
ማጉያ ሌንስ፣ የውሃ ልክ፣ ሰፌድ፣ ሚዛን፣ ወንፊት፣ መስታወት፣ ማይክሮስኮፕና ሉል በግድግዳ ላይ በቅንብር ተሰቅለዋል (ሁሉም ቁሶች በሸራ ላይ የተሳሉና የተለምዶ ግልጋሎታቸውን የሚሰጡ ሳይሆኑ የሥነ-ጥበብ ቁሶች መሆናቸውን ልብ ይሏል)፡፡ ሠዓሊ ታምራት ገዛኧኝ፤ ”ነኝ፣ ነው፣ ናት፣ ነንነት የቱ ጋ ነው?” የሚል ስያሜ በሰጠው ስራው፤ የሆንነውን ለመሆን፣ ያልሆንነውን መሆን ብዙ ድካምና ብክነት እንደሚያመጣ ይሰብካል፡፡ በሆንንባቸው ማንነቶች ውስጥ ወዳሉ መገለጦች ለመጥለቅ በተሳነን ቁጥርም፣ ነን ያልነው (ነገር ግን) ያልሆንነውን መሆን እንደምንጀምር፤ ይህ ሲሆን ደግሞ ምናልባትም ለትውልድ የሚተርፍ ድካምና ኪሳራ እንደምንሸምት እያሳሰበ፣ አቤቱ ወደ ጉድ አታግባን ከማለት ጎን ለጎን፣ የሆንነውን ለመፈተሽ  ወደ ምርምር እንድንገባ ይወተውተናል፡፡ እኔ ከዚህ ሃገር ነኝ... እኔ ከዚህ ብሔር ነኝ...እኔ ከዚህ ጎሳ ነኝ... እኔ ከዚህ ዘር ነኝ... እኛ ከዚህ ሙያ፣ ጥበብ፣ ሳይንስ፣ ኃይማኖት፣ ፖለቲካ፣ እምነት...  ተከታይ ነን የሚሉ ስያሜዎች፤ የስይማቱን ጥልቅነት እስክንገነዘብ ድረስ እየገደሉን፣ እያዳኑን፣ እያስተማሩን እየቀጡን----እንደሚቀጥሉ በማስታወስ እነዚህ ስያሜዎች ወደፊት ግን በጥረት እንደሚሰጡ/እንዲሰጡ፣ በዚህም መንገድ አንድነት፣ ቅድስና፣ ፍቅር፣ ሰላም፣ ይቅርታ፣ ክብር... በዓለም ማስፈን እንደሚቻል ሰዓሊ ታምራት ይነግረናል፡፡
ባሕልና ልማድ ጊዜን ይመስላሉ፡፡ ሙዚየም መቀመጥ በሚገባው ቀንበር፣ በሬዎችን ጥምድ አድርገን እያረስን፣ ስለ ምቾት ማሰብና ስለ ፍትሐዊ የሃብት ክፍፍል መነታረክ ምን ይባላል? ሠዓሊ ሱራፌል አማረ፤ በሬዎች በሚጠመዱበት ቦታ እውነተኛ የበሬ አጽሞችን በሰቀለበትና የፍራሽ ልባስ በተጠመጠመበት ቀንበር እንዲሁም የፍራሽ ልባስ የተጠመጠመባቸውና እንዲሁ የተተዉ ድንጋዮች በአፈር ላይ ያስቀመጠበት ስራውን ሲያስረዳ፤ “ዘመኔ ይህ ነው፡፡ እኔም አሁን እዚህ ጋ ነኝ፤ ከዘመኔ ጋር፡፡ እንደ ፍጥርጥሩም ቢሆን ሲንከባለል ያገኘሁት አውድ ውስጥ እገኛለሁ፡፡ ለዚሁ እውነት እጅ የሰጠሁ ጊዜ ዓይኔ መገለጡን ይጀምራል። ያለፉትም የሚመጡትም፣ የትም ያሉትም ሁሉ እጣ ፈንታቸው ይሄው ነበር ለካ እላለሁ፡፡ የዘላለሙ ዑደት አካል የሆንኩ ሰው ነኝ፡፡ ተራ ሰው ልክ እንደ ሁላችሁም፡፡ ሳር ቅጠሉን ፖለቲካ ቢሸፍነው እንኳ ሳርና ቅጠልነቱን ለዘላለም እንደማይቀይር የማውቅ - ተራ ሰው...“ እያለ ባሕል፣ ዘልማድ፣ ፖለቲካ፣ ዘመንን ይሞግታል፡፡
የመረረውን እውነት በጥሬው እየፈጩ ከመዳከም፣ ዘላቂ የማሰላሰያ እጥፋቶች እያበጁ አሰልቺ ድግግሞሾችን በለበጣ እያዳከሙ መኳተን፣ ለሚጠብቀን ሩቅና ረዥም ጉዞ የሚያዋጣ አማራጭ ይሆን? ቢሆንም ባይሆንም “አዲስ ጋዜጣ” የሚል ስያሜ ያለውና ባለ ሃያ አራት ገጾች በእጅ የተጻፈ ጋዜጣ እንዲሁም  አራት ኪሎ ጆሊ ባር አጥር ስር ያለችውን የማንበቢያ አደባባይ፣ አራት ሜትር በሁለት ሜትር መጠን ባለው ግዙፍ ፎቶግራፍ ያቀረበው ሠዓሊ ሮቤል ተመስገን፤ የአዲስ ጋዜጣ ፕሮጀክትን ለመጀመር ብሎም ይህንን ቅርጽ ለመያዝ ያበቃው፣ በ2006 ዓ.ም መንግስት 6 ጋዜጦችን፣ መጽሄቶችን፣ አዘጋጆችንና ጦማርያንን በመክሰስ፣ ህትመታቸው መቋረጡን ተከትሎ፣ የሃገሪቱ የመጻፍና የማሰብ ነጻነት አፈና መባባስ እንደሆነ ይናገራል፡፡ ሰዓሊው ይህንን ጋዜጣ ሲጀምረው፣ መደበኛ ባልሆነ መንገድ የተቃውሞ ድምጹን የማሰሚያ መድረኩም ነበር። እንደ ሰዐሊው አረዳድ፣ አራት ኪሎም ሆነ ሌሎች  ቦታዎች የሚገኙ የጋዜጣ ማንበቢያ ስፍራዎች፣ ሰዎች መረጃን ለመስጫና ለመቀበያነት በማሰብ በሂደት የገነቧቸው ተለዋዋጭ፣ ተንቀሳቃሽና ታዳጊ አደባባዮች ናቸው። ከተለመዱት መደበኛ አደባባዮች ለየት የሚያደርጋቸው ታዲያ፣ የጋዜጦቹ አደባባይ ሰዎች ሲኖሩት ብቻ አደባባይ የሚሆን የፍላጎት መድረክ መሆናቸው ነው። የሰዐሊው ጋዜጣም በነዚህ የመሰባሰብ ሃውልቶች መካከል በአቀራረቡ ዘዋራነት፣ መንገጫገጭን ይፈጥር ዘንድ አዘጋጅቶታል። በነጋሪ: MANIFESTO በቀረበው “አዲስ ጋዜጣ” ’ የተካተቱት ርዕሰ ጉዳዮች፣ ከቀድሞው የሃገሪቱ ጠ/ሚ ኃይለማርያም ደሳለኝ ስልጣን መልቀቅ እስከ ኢትዮጵያና ኤርትራ የሰላም ስምምነት----ይዳስሳሉ። በጋዜጣው የተዳሰሱት የአምስት ወራት ቆይታ ውስጥ በርካታ የፖለቲካ ለውጦች የተስተናገዱበት ወቅት በመሆኑ ከተለያዩ ምንጮች የተሰባሰቡትን ‘መረጃዎች’፤ ሰዐሊው በስላቅ አሽቶ አዋቅሯቸዋል። ይህ የሰዐሊው የጋዜጣ ስራ በተለያዩ ሃገራት የተለመደ ቢሆንም፣ በኢትዮጵያ ግን ለመጀመሪያ ጊዜ መቅረቡ ነው።
በየዘመናቱ እየተለማመድነው የመጣነው የሰዎችን  ሞት የመርሳት አባዜ፣ የታሪካችን ሃፍረት የሚገለጥበት ከባድ ጢሻ ነው፡፡ ሠዓሊ ዳሪዎስ ኃይለሚካኤል፤ “የአንድ ሰው ሕይወት ዋጋ ስንት ነው?” በሚል ስያሜ፣ አራት ሜትር በሁለት ሜትር ጥቁር ላስቲክ ላይ የአበባ ጉንጉን ውክልና ያላቸው ቢጫ ወረቀቶችን ወርድ ባግድመት በኮን ቅርጽ፣ ዝንፍ በማይል ድርድሮሽ በማቅረብ፣ ኮምጨጭ ያለ እውነት ይነግረናል። “የሃገራችንን የመጨረሻው ግማሽ ምዕተ ዓመት ሂሳብ ብናወራርድ፣ በአማካይ በየአስራ አምስት አመቱ ብቅ የሚል ምስል አለ፡፡ መገለጫውን ሃገራዊ ቀውስ፤ መደምደሚያውን ነፍስ በሊታና ደም ምሱ የሆነ። የዚህ አዙሪት ድግግሞሽ በሰብአዊ ኅላዌነታችን ለመፈጸም ቀርቶ ለማሰብ የሚያስደነግጡ ድርጊቶችን እንደ ዘበት ተለምዶአዊ ሁነቶች እየቆጠርን መጓዝ ከጀመርን ሰነባበትን፡፡ እናስ?... አሁንም ያለፈ አዙሪት ልምምዳችንን ለመድገም እያኮበኮብን ነው ወይስ...? መቼ ነው ከዚህ አዙሪት ቅንብብ የምንወጣው? ጊዜው የዘመናት ሂሳባችንን ኪሳራና ትርፍ ውጤት አጢነን፣ የጋራ አዋጭ የጉዞ መንገድ መምረጫ ምዕራፍ ላይ ነን። ወርድ ባግድመት ሒሳባዊ ቋንቋ ነው፡፡ የተመሳሳይ ነገር ልኬት ውጤቱም ሃገር፣ ክልል፣ ብሔር፣ ጥቁር፣ ነጭ፣ አጭር፣ ረጅም፣ እኛና እነሱ ሳይል የትም ጊዜና ቦታ ላይ ውጤቱ ተመሳሳይ ነው፡፡ ወርድ ባግድመት ስሌት ሉላዊ ሕግ ነው፡፡ አጭሩና ቀላሉ ውጤታማ መንገድ ነው፡፡ እንደ ሃገር እና እንደ ሰው የሉላዊነት አካል አንዱ አባል ነን፡፡ አብረን እየተጓዝን ነው ብለን የምናስብ ከሆነ፣ ካለንበት አዙሪት ማጥ መውጣትና የተሻለ ነገ ምርጫችን ከሆነ፣ ትክክለኛውን የስሌት ቀመር መተግበር ግዴታችን ይሆናል፡፡ ሃገር የሚቆመው በግለሰብ ጫንቃ ላይ ሳይሆን በተቋም ማማ ላይ ነው። የተቋም መገለጫው ደግሞ የወርድ ባግድመት ስሌት ቀመሩ መርሁ...“ በማለት ወደ ኋላ እንዳንመለስ፣ ወደፊት በጥንቃቄ እንድንደረደር ይመክረናል፡፡
በትርዒቱ የቀረበው ሌላኛው ግዙፍ ስራ፣ በጨርቅ ላይ የተሰፋው ባለ አራት ሜትር ገደማ ወርድና ሁለት ሜትር ከፍታ ያለው የሠዐሊ ኪሩቤል መልኬ “ዳግም ሞት” ሲሆን በዚህ ሥራው፤”ያለፈ ታሪካችን መታሰቢያዎች ዳግም እንዳንሞት ካልረዱን፣ ልምምዳችን ችግር የመፍታት ችሎታ ሳይሆን ሁሌም አዳዲስ ችግሮችን የመላመድ ችሎታ እያሳደግን መሆናችንን ያጋልጣል” የሚል ሃሳብ ያስተጋባል። “በባሕላዊ ወይም መንፈሳዊ ረገድ የምንጋራቸው እሴቶች ስለሌሉን ሳይሆን፤ ያሉንን በጎ ጉዳዮች ከየዘመኑ መንፈስ ጋር ማግባባት ተስኖን በረጅም ዘመናት ውስጥ የአንድነታችን መሰረት ሆኖ የቆየውን ታሪካዊ የባሕል ቅርሳችንን እንድናጣ ሆነናል፡፡ እንደ ሃገር “ዘመናዊነትን” ብቻ ሳይሆን ሃጢያትንም እየኮረጅን እዚህ ደረስን፡፡ ዓለም ሞቶ በተነሳበት ጉዳይ እኛ አሁን እየሞትን ነው፡፡ አይቶ ሰምቶ መርምሮ ከመምረጥ ይልቅ ሁሉን እየሞከርን ማለፍን መረጥን። ይህም አያሌ መስዋዕትነትን አስከፈለን፡፡ የቁስ ኋላ ቀርነትን ብቻ ሳይሆን ከዓለም ጋር እኩል የምንጋራው ጊዜ እንኳ ብዙ አመት ወደ ኋላ ጥሎን ሄደ፡፡ ሌላው ዓለም የደረሰበትን እውቀትና ሰብዓዊ ምልከታ በጊዜአችን እንዳናገኝ አደረገን፡፡ የብዙ እናቶቻችን ነጠላ ውሃ ብቻ ሳይሆን እንባም እያጠበው፣ ሃገር ልጆቿን ይዛ አሁን ያለንበት ላይ ደረሰች፤ በምንም ነገር ውስጥ ተስፋ አይሞትምና። ..... እነሆ አሁን ሃገር እውነትን በእውቀት የሚኖሩ ልጆቿን ትፈልጋለች...“ እንግዲህ ጥበበኛ ሲናገር፣ ልቦና ያለው አድማጭ አያሳጣን እንጂ ምን ይባላል፡፡
“የሮ ኬኛ” ወይም “የኛ ጊዜ” የሚል ስያሜ ያላቸው አንድ የሶስት ደቂቃ ቪዲዮ እንዲሁም አንድ ሌላ ፎቶግራፍ ያቀረበው ነዋሪነቱን ጀርመን ሃገር በርሊን ከተማ ያደረገው ፎቶግራፈር የሮ አዱኛ፤ ሌላኛው የትርዒቱ ተሳታፊ ነው፡፡ የሮ ባለፉት ጥቂት ወራት በተጓዘባቸው ቦታዎች ካጋጠሙት አያሌ አስደንጋጭ የመንጋ (mob) ድርጊቶች መሃከል በሻሸመኔ የተከሰተ አንድ አጋጣሚን በቪዲዮ ያሳየናል፤ ፎቶግራፉ ደግሞ በድንጋይ ከተሰበረ አውቶብስ ውስጥ የተነሳ ሲሆን ከተሰበረው አውቶብስ ውጭ በርቀት የሚታይ ቀልብ የሚገዛ መልክዓ-ምድርን ያሳየናል፡፡ እናም “የሮ ኬኛ” ወይም “የኛ ጊዜ” እያለ በዘይቤ ይናገራል፡፡ ይህም ሰነድ፣ መረጃን ይፋ ማውጣት፣ ማሳየትና ማስቀመጥ ቢያንስ ለመመራመር ጊዜ ስናገኝ ልንጠቀምበት እንደምንችል  ነጋሪ ነው፡፡ ገና ስንትና ስንት ያልወጣ ጉድ አለ!
ነጋሪ: MANIFESTO ለጀመርነው አዲስ ዓመት እንዲሁም ለኢትዮጵያችን መጪ ጊዜ ስንቅ የሚሆኑ ሃሳቦችን ለመንገር፣ በቀናኢነት የቆመ ልዩ ትርዒት በመሆኑ እንዳያመልጣችሁ ስጋብዝ፣ የሥነ-ጥበብን ከልብ የመነጨ አበርክቶትና ትሩፋት እንደምታጣጥሙበት ያለኝን ሙሉ እምነት በመግለጽ ነው፡፡ በመጨረሻም  ከማንኛውም ቁስ ሆነ ቁስ-ጥበብ የሚመነዘር ነቢብም ሆነ ገቢር ሃሳብ፣ በጥልቀትና በስፋት ለመወያየት የሚቻለው ባለን ዝግጁነት መሆኑን ለማስታወስ እወዳለሁ፡፡ ቸር እንሰንብት!!!

Read 714 times