Sunday, 07 October 2018 00:00

ነገ… ያስፈራል!! - (መጣጥፍ)

Written by  አብይ ተስፋዬ አሳልፍ (አተአ)
Rate this item
(1 Vote)

 እዚሁ በፈራረሰ የልጅነት ሰፈሬ ተከራይቼ እኖራለሁ፡፡ ከልጅነታችን ቅርሶች አብዛኞቹን ስለደመሰስን ቅርሶችን ቀንሰናል፡፡ በዚህም እንኮራለን፡፡ እዚህ አጠገባችን የነበረው የመፅሐፍት ቤት፣ ተጠቃሚ በማጣት ይሁን ለልማት ተፈልጎ አልገባኝም እንጂ ከተዘጋና የሸረሪትና የአይጥ መጫወቻ ከሆነ ሰነባበተ። (ድሮ ድሮ ለማ በገበያና ተንኮለኛዋ አይጥ … ምናምን የሚባሉትን ተረቶች ያነበብኩት እዚያ ነበር፡፡) አሁን ቦታው ፈራርሶ በመታጠሩ ምክንያት እንደ ቆሻሻ ማጠራቀሚያ እያገለገለን ነው፤ ይመስገነው፡፡
የዱሮው ኳስ ሜዳችን ተወስዷል፤ አሁን በእኛ ቀበሌ የመጫወቻ ሜዳዎች የሉንም! (በድጋሚ ተመስገን ነው!) ሁሉም ክፍት ቦታዎች ተይዘዋል መሰለኝ፣ ክፍት ቦታና ትልቅ ዛፎች ለማየት ወይ ደግሞ ለታታናሾች እንደ ምሳሌ ለማስረዳት የምንጠቀመው፣ ቤተ ክርስቲያን ግቢ በመግባት ነው፡፡ ከክፍት ቦታዎች ውስጥ ያልተያዘና ለአልሚ ያልተመራ፣ ቀና ብዬ የማየው ሰማይ ብቻ ነው፡፡ ብዙ ቤተሰቦች ይኖሩበት የነበረው የእነ እትዬ ጥሩ መንደርም ከፈራረሰ አራት ዓመት አልፎታል፡፡ (እትዬ ጥሩ የጓደኛዬ እናት ሲሆኑ … ወያኔ ሲቀናብንና ቡና እያፈላን ብናማው ጊዜ አፈራርሶ በተነን ሲሉ ሰምቻለሁ … በርግጥ ማመን ከበደኝ እንጂ!…) አሁን ቦታው ቆሻሻ ይደፋበታል፤ ከዚያ ይኖሩ የነበሩት ቤተሰቦች ሁሉ ደግሞ በየላስቲክ ቤቱ ተደፍተዋል፡፡
ህፃን ሆኜ እናቴ የማላውቀውና ከቤታችን ራቅ ያለ ሱቅ ስትልከኝ እንዲህ ነበር የምትለኝ… ‹‹… ይቺን መንገድ ጨርሰህ እንደወጣህ፣ ከኳስ ሜዳው አጠገብ ካለው የበለጠ ሱቅ ባለ 10 ሳንቲሟን ሻይ ቅጠልና የ50 ሳንቲም ስኳር በለው! ብርር ብለህ ቶሎ ተመለስ፡፡ አደራ! … አደራ! ወንድሜ! እሁድ ሳንቲም ስለማገኝ እከፍላለሁ በላቸው፡፡›› እናም ወጥቼ በሩጫ አቀጥነዋለሁ፡፡ በነፋሻማው የሰፈራችን ዛፎች ጥላ ስር እየተዝናናሁ ሱቅ ደርሼ ስመለስ፣ ካለ ወጪ ቀሪ፣ ምርጥ ምርቃት እቀበላለሁ፡፡
*   *   *
አሁን ከተከራየሁት ቤቴ በር ላይ እግሮቼን እየታጠብኩ፣ የአከራዬ ጎረምሳ ልጅ ታናሽ ወንድሙን ሊልክ ሲለማመጠው ቁጭ ብዬ እታዘባለሁ፡፡ ‹‹ናቲ! እስኪ ሱቅ ልላክህ?!›› ይለዋል፤ ሁለት የመቶ ብር ኖቶች ይዞ በፈገግታ እየጠራው፡፡ ይህ ጎረምሳ ጫት በመቃም ጉንጮቹ ተሰርጉደው፣ የአሮጊት ጉንጭ መስሏል፤ ጥርሶቹ በልዘው ግማሾቹ በራሳቸው መቆም ስላቃታቸው መውደቅ ጀምረዋል፡፡
‹‹ስንት ትበጥሳለህ?!›› ጉቦ መሆኑ ነው፡፡ ገና ነፍስ ሳያውቅ፣ ትንሹ ጉቦና መማለጃ ለምዷል፡፡
‹‹ዱዲ አልሰጥህም!››
‹‹እንግዲያው አልሔድም!›› ግምጭጭ ብሎ፡፡
ታላቅየውም ይስቅና፤ ‹‹ እሺ በቃ ዴች ይበጠስልሃል! ቀጥል!››
‹‹እሺ ከየት ነው የማመጣልህ?!››
‹‹ይቺን ኮብልስቶን መንገድ ጨርሰህ እንደወጣህ ፈራርሶ ከታጠረው ግቢ አጠገብ ካለው የቢላል ጫት ቤት ባለ 60 ብሯን በለጬ ሁለት እና የቢጫ (5 ብር) ለውዝ!››
ብሩን እየተቀበለው፤ ‹‹ባህርዳር አይሻልህም?!››
‹‹ሂድ ከዚህ! ፈልፈላ-- ደግሞ ዲላይት ሲጃራም 8 ፍሬ ጨምርበት!››
ቅድም የትምህርት ቤት ዩኒፎርም የለበሱ ሁለት ወጣት ሴት ልጆች ሲገቡ አይቻለሁ፡፡ ስለዚህ አብረው የሚቅሙትና የሚያጨሱት መሆን አለበት። (ልጆቻቸውን ምንም እንደማታውቅ/ቅ የሚቀበሉ ወላጆችን በአይነ ህሊናዬ አስባለሁ፡፡ በተለይ ለሴት ልጆች እቆጫለሁ፣ ማህበራዊ ፍርዱ በእነርሱ ላይ ይጨክንባቸዋልና፡፡ ከተለያየ ወንድ ጋር በታዩ ቁጥር ሰው ርካሽ ያደርጋቸዋል፣ ወንዶች ደግሞ ከተለያየች ቆንጆ ሴት ጋር በታዩ ቁጥር ንፋስ እንደገባበት ባሉን እየጨመሩ ይሄዳሉ … ነገሩ ያው ቢሆንም ብዙ ጊዜ ማህበረሰቡ የሚመለከተው የሳንቲሟን አንድ ገፅ ብቻ ነውና! )
ዛሬ እንደ ቀልድ ህጻናት ተጠርተው እንዲገዙ የሚላኩት ይህ ነገር፣ ድሮ የት እንደሚሸጥ እንኳ የማናየውና የማንሰማው ነበር፡፡ በሆቴል በር አጠገብ ማለፍ በራሱ የሚያሸማቅቅበት ወቅትም ነበር፡፡ ዛሬ ህፃናት ይጠጡበታል፡፡ አልኮልም የሀገሪቱ ነባር አካል ለመሆንና በታሪኮች መሃል ጣልቃ ለመግባት በሚያማምሩ ማስታወቂያዎች እየታገለ ይገኛል።  እንግዲህ ይህ ቃሚ የአከራዬ ልጅ፣ ብር ሲያገኝ በለጬ፣ ሲያጣ ደግሞ ባህር ዳር ጫት የሚቅም ነው ማለት ነው፡፡ ‹ትንሹ ልጅ እንኳ እንዴት ታዘበው!› ብዬ እገረማለሁ፡፡
*   *   *
እዚህ ቤት የገባሁ ሰሞን፣ ማታ ላይ ከስራ ወደ ቤት ስገባ፣ ሰፈሩን የሚያውደው ሽታ እጣንና ሰንደል ይመስለኝ ነበር፡፡ ነገሩ ለካ ሌላ ኖሯል፡፡ በመንደሩ የሚገኙ ትልልቅ ቪላ ቤቶች ለሺሻ ቤትነት ተከራይተዋል፡፡ የሚያውደኝ መዓዛም ሳልከፍል የማጨሰው ሺሻ ነበር፡፡ ስለዚህ እኔም ሱሰኛ እየሆንኩ ነው ፣ በነጻ!
የጫት ንግድ ለአገሪቱ ገቢ አንዱ ዋልታ ለመሆን በቅቷል ይላሉ፡፡ መንግስታችንም ለአረንጓዴው አደንዛዥ/አነቃቂ እፅ፣ አረንጓዴ መብራት ሰጥቶታል። በየገጠሩ እርሻዎች ሁሉ ወደ ጫት እርሻነት መቀየር ከጀመሩ ቆይተዋል፡፡ የጤፍና የስንዴ እርሻዎች እየጠፉ ስለሆነ የወደፊቱ ጤፍ ከወደ ቻይና የመምጣት ዕድል ይኖረዋል፡፡ ብዙ ወጣቶች በሱስ ተመርዘዋል፤ እንደ ጣዕረ ሞት አካላቸው የማይታይ ባለስልጣናት በንግዱ ውስጥ እየተሳተፉ እንደሆነ የአደባባይ ሚስጥር ነው፡፡ ፅድቁ ቀርቶ …. እንደሚባለው ከጫት የሚገኘው ታክስ እንኳ በስርዓት እንዳይሰበሰብ፣ መክፈል የማይፈልጉና የማይገደዱ አካላት፣ ኬላዎችን እንደ ግል ቪላ ቤት በራቸው ተንደላቀው በነፃ ያልፏቸዋል፡፡
ትምህርት ቤቶቻችን ዙሪያቸውን … ቀን ጭፈራ በሚያዘጋጁ ስውር ክለቦችና ግልጽ ቪላ ቤቶች ተከበዋል፤ በነዚያ ቤቶች ደግሞ የአደንዛዥ እፆች እንደ ልብ ይሸጣሉ፣ ይለወጣሉ፡፡ እንደ ፊዚዮቴራፒ የሚያገለግሉ ማሳጅ ቤቶች እንኳ ባለ ሁለት ስለት ሆነው ቀርበዋል፡፡ ጫትና ሺሻ ቤቶች ልክ እንደ ቤተ መፃህፍት በግልፅ በሮቻቸው ተከፍተዋል፡፡ ወሲብ ሲወራ የሚያስደነግጥበትና ሚስጥራዊ የሆነበት ዘመን አልፏል፡፡ አሁን ደግሞ ጭራሽ ስሙ የማይነሳና የማይወራው፣ መኖሩም ልብ የማይባለው የተመሳሳይ ፆታ ግንኙነትና የህፃናት መደፈር ዜና በየጓዳ ጎድጓዳው፣ እንደ ሰደድ እሳት ከእጃችን እያመለጠ ነው፡፡ (እግዚኦ ማህረነ …. እንዲሉ አበውና እመው!)
ታናናሽና ጨዋ የሚመስሉት ወንድሞቻችንና እህቶቻችን እንዲሁም የጎረቤት ልጆች በቤት ውስጥ በሚኖራቸው ፀባይና በሰፈር በሚያሳዩት ጨዋነት ከለካናቸው የምንሸወድበት ዘመን ላይ እንገኛለን። ሰፈር ወይም ከቤት ያየነውን ፀባይ እንደ እባብ ቆዳ አውልቀው የሚጥሉት ትንሽ ወጣ ሲሉ ሆኗል (አንድ ፌርማታ እንደተጓዙ ይላሉ አንዳንዶች…)፡፡ ልጆቻቸውን የት ማስተማር እንዳለባቸው የጨነቃቸው ወላጆችም በዝተዋል፡፡ ትምህርትና ውጤት ንግድ ሆኗል፡፡
ቦሌ አካባቢ ቀን ቀን በምውልበት ሰፈር የማያቸው አጫሽ ታናናሽ እህቶቻችንና ወንድሞቻችን ያስደነግጣሉ፡፡ ሃሺሾች እንደ ልቧንጃ ቦለል ብለው ቤት የሚያፍኑበት ቦታ፣ ሴቶች እርቃን የሚደንሱባቸው መድረኮች፣ ሴሰኞችን የሚያቀጣጥሩ ወፋፍራም ደላሎች … እንደ ጉድ ሞልተዋል፡፡ እንደ አገር እያጣነው ያለውን ነገር ካሰብነው ነገ ያስፈራል፡፡ (ኸረ ጭራሽ ነገ መኖሩም ያጠራጥራል! … በርግጥ አለ!)
ለዚህ ሁሉ ተወቃሹ መንግስት ብቻ ነው የሚል ሃሳብ በልቤ የለም፡፡ ቤተሰብስ፣ ትምህርት ቤትና መምህራኑስ፣ የህግ አካላትስ፣ ታላላቆችስ፣ ምሁራንስ፣ ጋዜጠኞችስ፣ ደራሲዎችስ …. ታናናሾች የቆሙበት መሰረት የሁሉም የጋራ ውጤት ነውና፣ የሚሆነው ነገር ሁሉ የጋራ ውጤታችን ነው፡፡
*   *   *
ከደቂቃዎች በኋላ ታላቅየው ጉንጩን በጫት እንደወጠረ ብቅ አለና፣ ታናሽየውን ጠራው፣ ሌላ ድፍን መቶ ብር እያቀበለው…
‹‹ከተዘጋው ላይብረሪ አጠገብ ካለው የመስፍን ሱቅ መዋስልና ኮንደም ግዛና በፍጥነት ና!›› አይኖቹ እንደ ከረንቡላ ድንጋይ ብቅ ብቅ ብለዋል፡፡ (እንዲህ የሆነ ሰው ሲያዩ የኛ ሰፈር አራዶች ‹እግሮቹን ይዘህ እንደ ኩሽኔት በሁለት አይኑ ብትነዳው ይፈጥናል!› ይላሉ፡፡) በፊት ጊዜ ይህ ልጅ ገቢውን ከየት ነው የሚያገኘው ብዬ እመራመር ነበር፡፡ ነገሩን ያወቅሁት በቅርቡ ነው፡፡ ፎርጅድ ዶክመንቶችን ያዘጋጃል፡፡ መቼም ምን ያህል የፎርጅድ ባለድግሪዎች በመንግስት ስራ ላይ ቁብ እንዳሉ መገመት ከባድ አይደለም ተብሏል (እጅ የሰጠውንም ያልሰጠውንም ብንቆጥር አወይ ልፋት መና! ማለታችን ስለማይቀር ከቁጥር ፊታችንን እንመልሳለን እንጂ!...)፡፡ በፎርጅድ ወረቀት የመንግስት ስራን አበስብሰውታል (ስራውን ራሱ ፎርጅድ አድርገውታላ!)፡፡ ሲስተሙ ሞቶ አብቅቶለት ትንሳኤውን እየጠበቀ ነው፡፡ የእውነቱን የዲግሪ ወረቀት የያዙት ወጣቶችማ ኮብልስቶን እየፈለጡ ነው፡፡
‹‹ስንት ታመጣለህ!?›› ህጻኑ ልጅ እንደ ጉቦኛ የመንግስት ስራ ፈጻሚ፣ አይኑን አፍጥጦ ሲጠይቅ ገረመኝ፡፡
‹‹በቃ አሁን ቢጫ ይበቃሻል!›› የተቀዳደ ጅንስ ሱሪው ከኋላው ዝቅ ብሎ ተንጠልጥሏል፡፡ ፀጉሩ ማግኔት እንደያዘው ሰው ዙሪያውን ተንጨፋሮ ያስፈራል፡፡
ታናሽየውም ሙስናውን ከጨበጠ በኋላ ከእንደገና በረረ፡፡ እናም ታናናሾቻችንም ባሳየናቸው መንገድ እየበረሩ ነው! ስል አስባለሁ፡፡ (እናም በሃሳቤ እላለሁ … ታላቅየው ያስፈራል! መጪው ጊዜም ያስፈራል! ….)
በድንገት ወደ እኔ መለስ ብሎ እንዲህ ሲለኝ ነበር የባነንኩት ‹‹… ብሮ! … ለደንብ ትለኩሻለሽ’ንዴ! ››
‹‹አልገባኝም !›› አልኩ እየተደነጋገርኩ፡፡
‹‹ከጅምሩ ጀምሩ ነገራችንን ጭማድ አርገሽ ተከታተልሽ!…››
‹‹ኦህ!  … ይቅርታ …›› አልኩና ባዶውን የውሃ ኮዳ አንጠልጥዬ ወደ ቤቴ ገባሁ፡፡ (ሆሆይ እያልኩ በሃሳቤ! … ሆሆይ! በድጋሚ!)
*   *   *
በፈረሰ መንደር፣ በፈረሰ ላይብረሪ፣ በደካማ ትምህርት፣ በደካማ የቤተሰብ ቁጥጥር፣ በለዘብተኛ ጎረቤትና ሃላፊነቱን በማይወጣ ታላቅ፣ በጉቦኛ ፍትህና ያለ ገንዘብ በማይንቀሳቀስ የፖሊስ ስርአት፣ አድሎአዊ በሆነና በጎሰኝነት በሚመራ የመንግስት ስርአት፣ በማያንጽና በማይገስፅ የሃይማኖት መሰረት  ወዘተ ….  ውስጥ እየተራመድን … ታዲያ መጨረሻው ምን ሊሆን ነው!
ሲጃራ፣ አልኮል፣ ጫት፣ ኮንደም፣ ሺሻ …. የመሳሰሉትን እንዲገዛ የምትልከው ወንድምህ፤ ነገ ምን ሊያደርግልህ ኖሯል! …. ሲጃራ፣ ሃሺሽ፣  አልኮል፣ ጫት፣ ኮንደም፣ ሺሻ፣ ወሲብ …. እንዲሸጥበት የከፈትነውን ሱቅስ ካልቀየርነው ምን ሊፈጠር ኖሯል! …. በእርግጥም ያስፈራል!!

Read 483 times