Saturday, 06 October 2018 11:19

የቀድሞ የማሌዢያ ቀዳማዊት እመቤት 17 ክሶች ተመሰረቱባቸው

Written by 
Rate this item
(2 votes)

 ባለቤታቸው ጠ/ሚ ናጂብ ራዛቅ የተመሰረቱባቸው ክሶች 25 ደርሰዋል

   
   በስልጣን ዘመናቸው ፈጽመዋቸዋል በተባሉ የገንዘብ ማጭበርበርና በስልጣን የመባለግ ወንጀሎች 25 ክሶች የተመሰረቱባቸው የቀድሞው የማሌዢያ ጠቅላይ ሚኒስትር ናጂብ ራዛቅ ባለቤት ቀዳማዊት እመቤት ሮሳማህ ማንሶር፣ 17 የታክስና ገንዘብ ማጭበርበር ክሶች ተመስርቶባቸዋል፡፡
የቅንጦት ኑሮን በመውደድና በሚሊዮን ዶላሮችን እያወጡ በውድ ጌጣጌጥ በማሸብረቅ የሚታወቁት የቀድሞዋ ቀዳማዊት እመቤት ሮሳማህ ማንሶር፣ ረቡዕ በአገሪቱ የጸረ ሙስና ተቋም ሃላፊዎች በቁጥጥር ስር መዋላቸውንና ከትናንት በስቲያ በኳላላምፑር ፍርድ ቤት መቅረባቸውን ቢቢሲ ዘግቧል፡፡
የ66 አመቷ ሮሳማህ ማንሶር ፍርድ ቤት ቀርበው በሰጡት ምላሽ፣የተከሰሱባቸውን ሁሉንም የወንጀል ድርጊቶች አለመፈጸማቸውን ገልጸው፣ ክሶቹን መቃወማቸውንና የዋስ መብታቸው እንዲከበርላቸው መጠየቃቸውን የጠቆመው ዘገባው፤ ፍርድ ቤቱም በግማሽ ሚሊዮን ዶላር  ዋስትና ከእስር እንዲለቀቁ መፍቀዱን አመልክቷል፡፡
በብዙ ሚሊዮን ዶላሮች የሙስና ቅሌት 21 የወንጀል ክሶች ተመስርቶባቸው የነበሩት የቀድሞው የማሌዢያ ጠቅላይ ሚኒስትር ናጂብ ራዛቅ፤ ባለፈው ሳምንት 556 ሚሊዮን ዶላር የህዝብ ገንዘብ ያለ አግባብ ወደ ግል ካዝናቸው ከማስገባታቸውና በስልጣን ከመባለጋቸው ጋር በተያያዘ፣ አራት አዳዲስ ክሶች እንደተመሰረቱባቸው  ተዘግቧል፡፡  


Read 1752 times