Saturday, 12 May 2012 11:57

ከአራት ኪሎ ዳግም ልማት ሌላው ምን ይማራል?

Written by  ብርሃኑ ሰሙ
Rate this item
(0 votes)

ሰሞኑን በየአደባባዩ እየተጮኸባቸው በመሸጥ ላይ ካሉ መፃሕፍት አንዱ “PROCEEDINGS OF THE INTERNATIONAL SYMPOSIUM ON THE CENTNARY OF ADDIS ABABA” የሚል ርዕስ አለው፡፡ መጽሐፉ የአዲስ አበባ ከተማ ምሥረታ መቶኛ ዓመት በዓልን ምክንያት በማድረግ በሲምፖዚየም የቀረቡ የተለያዩ ጥናታዊ ጽሑፎችን ሰብስቦ ይዟል፡፡ በርካታ ፎቶግራፎችን፣ ካርታዎችንና ሠንጠረዦችን ያካተተውና 270 ገፆች ያሉት መጽሐፍ በህዳር ወር 1987 እ.ኤ.አ ነው የታተመው፡፡  አዲስ አበባ 125ኛ የምሥረታ ዓመቷን የምታከብርበት ወቅትን ጠብቆ መደበኛ ባልሆነ መልኩ ለሽያጭ የቀረበው ጥራዝ፤ ከተማዋ የመንግሥት መቀመጫ ለመሆን የበቃችበትን ሂደቶች እንዴት እንዳለፈች፤ ጥንታዊ ታሪኮችን ፈትሾ፣ አሸዋው ንጉሥ ሣህለሥላሴ ጋር የተያያዙ መነሻዎችን አመላክቶ፣ ዝርዝር ጉዞዎችን አስቃኝቶ፤ የደርግ መንግሥት በአዲስ አበባ የሰራቸውን ሕንፃዎች ጭምር ያስተዋውቃል፡፡

የመቅደላ፣ የመቀሌ፣ የአንኮበር … ጥንታዊ ቦታዎችን ፎቶግራፍ የያዘው መጽሐፍ፤ አዲስ አበባ ከተማ በተመሠረተችበት ዘመን የነበራት ገጽታ ምን ይመስል እንደነበር ከቀረቡት የፎቶ ማሳያዎች መካከል በቀሳውስት የተሞላው የ4 ኪሎ ቤተ መንግሥት (ግቢ)፤ የሕዝቡ ብዛትና የሜዳ ላይ መገበያያው ስፋት የሚያስደምመው አራዳ ገበያ፤ በገበያው አንድ ጥግ የዳኝነት አገልግሎት ይሰጥ የነበረው ሸንጐ፤ የአራዳ ገበያ ቆዳ ተራና የተገበያዩ ብዛት፤ መርካቶ በገበያነት ከመከተሟ በፊት ፊታውራሪ ሀብተጊዮርጊስ ዲነግዴ ይኖሩበት የነበረው እልፍኝና በዙሪያው የነበሩ የሣር ጎጆ ቤቶች .. ሲታዩ ታሪክን በጽሑፍ፣ በፎቶግራፍና በመሳሰለው ዘዴ ሁሉ መዝግቦ የማቆየት ጠቀሜታን ያመለክታል፡፡

በመጽሐፉ በገጽ 111 እና 112 የሚገኙት ሁለት ፎቶግራፎች ደግሞ ጥንትም ዛሬም ያለ ተመሳሳይ ታሪክ ያሳያሉ፡፡ አንደኛው ፎቶግራፍ የተነሳው ባሻ ወልዴ ችሎት ወይም ከእሪ በከንቱ ወንዝ አካባቢ በቆመ ፎቶ አንሺ ሲሆን ሁለተኛው ምስል የተወሰደው ከዋናው ፖስታ ቤት አካባቢ ወደፊት በር ባነጣጠረ ፎቶ አንሺ ነው፡፡

በሁለቱም ጥንታዊ ፎቶግራፎች እንደሚታየው ዳገቱ ላይ ባለው የ4 ኪሎ ቤተ መንግሥት ዙሪያ ያለው ቦታ የሚበዛው ባዶ ሆኖ፣ ጥቂት የሣር ጎጆ ቤቶች ብቅ ብቅ እያሉ መሆኑን ነው የሚያመለክቱት፡፡

በቤተመንግሥቱ ዙሪያ በሣር ጎጆ መሰራት የጀመሩት ቤቶች ሣሩ በቆርቆሮ፣ ጭቃው በድንጋይና በሸክላ እየተተካ ችምችም ብሎ በቤቶች የተሞላው የሥላሴ ገበያ፣ የእሪ በከንቱና የባሻ ወልዴ ችሎት መንደሮች ለሸራተንና ለፓርላማ ማስፋፊያ በሚል ለዳግም ልማት ነዋሪዎችን የማንሳቱ ሥራ ከተጀመረ ሰንበትበት ብሏል፡፡

ልማቱ፤ ከለመዱት አካባቢና ማሕበራዊ ትስስር ስለሚነጥል ሁሉንም ሰው ያስደስታል ተብሎ አይታሰብም፡፡ እየሆነ ባለው ነገር እየተደሰቱ ያሉት ምን ያህል ይሆናሉ? የተከፉትስ ቁጥራቸው ስንት ይደርሳል? ለሚለው ጥያቄ እቅጩን ቁጥር በግምትም ቢሆን መግለጽ ያስቸግራል፡፡ ከግል ፍላጎትና ጥቅም አንፃር ከሚታየው ማስደሰትና ማስከፋት ይልቅ ልማቱ ከአገራዊና ሕዝባዊ ጠቀሜታው፣ ከማህበራዊና ባህላዊ ፋይዳው፣ ከታሪክና ኢኮኖሚያዊ ዋጋው አንፃር ታይቶ፤ እየተሰራ ያለው ነገር ምን ያስገኛል? የሚለው በይበልጥ ቢያነጋግር፣ ቢያወያይ፣ ቢያከራክር ይጠቅማል፡፡

የሸራተንና የፓርላማ ማስፋፊያ በሚል ዓላማ ነባሩን ነዋሪ ከአካባቢው በማስነሳቱ ሂደት የታዩ ሳንካዎችና ሊከሰቱ የሚችሉ ችግሮችን ለማመልከት የሞከሩ አሉ፡፡ የካቲት 19 ቀን 2003 ዓ.ም ታዘበው ዘለላ የተባሉ ፀሐፊ በአዲስ አድማስ ጋዜጣ “የአዲስ አበባ ታሪካዊ ቤቶች የተጋረጠባቸው አደጋ” በሚል ርዕስ የችግሩን አንድ መልክ፣ በ4 ኪሎ የተፈጠረን ጥፋት በምሳሌነት በማቅረብ አመልክተዋል፡፡

በፍቃዱ አባይ የተባሉ ፀሐፊም ጥቅምት 4 ቀን 2004 ዓ.ም “የአዱ ገነት ልማት ተጠቃሚው ማን ነው?” በሚል ርዕስ በ4 ኪሎ መልሶ ማልማት ሂደት ውስጥ ያስተዋሉትን ታዝበው አስተያየታቸውን አቅርበዋል፡፡

ለዳግም ልማት ፈርሰው ሊጠናቀቁ ጥቂት በቀራቸው የሸራተንና የፓርላማ መንደር ቤቶች ማዕከል አድርጎ፣ በዚህ ወቅት ይህ ጽሑፍ መቅረቡ ምን ፋይዳ አለው? የሚል ጥያቄ ሊነሳ ይችላል፡፡ አንደኛው እየተሰራ ባለው ነገር ውስጥ የተከሰቱ ጥፋቶችን በጋዜጦች በኩል ለሕዝብና ለመንግሥትም ማመልከት የቻሉት ፀሐፍት፤ በአደባባይ ባይመሰገኑበትም ያቀረቡት ሐሳብ በመንግሥት ቢሮዎችም ድጋፍ ያለው መሆኑን መስማቴ ነው፡፡ ለዚህ ጽሑፍ መጀመር ምክንያቱም ይኸው ነው፡፡ ዝርዝሩን እመለስበታለሁ፡፡

ሁለተኛው ጠቀሜታ አዲስ አበባ ከተማ ከነባር ሠፈሮቿ የሚበዙት ለዳግም ልማት የመፍረስ ዕጣ የሚጠብቃቸው በመሆኑ፤ ቀድመው ከፈረሱት መንደሮች የሚወሰደው ልምድ ጥፋት እንዲቀንስ፣ በኋላ የሚያስቆጭ ነገር እንዳይሰራ፣ ከመፍረስ መጠበቅ ያለባቸውን ቤቶች በቅድሚያ ለይቶ መወሰንን የመሳሰሉት ጠቀሜታዎችን ስለሚያስገኝ ነው፡፡

ለዚህ ጽሑፍ መነሻ የሆነኝና “ቅርስ የነበሩት ቤቶች መፍረስ እንዳልነበረባቸው ሁሉም የመንግሥት ቢሮዎች መግባባት ላይ ደርሰውበታል” የሚለውን መግለጫ በሰማሁበት መድረክ ላይ በተሰራጨ በራሪ ወረቀት ላይ “ቅርስ” ለሚለው ቃል “በአንድ ወቅት የነበረን የአንድን ማህበረሰብ ማንነት፣ የአንድ አገር ስልጣኔ፣ ባህልና የአኗኗር ሁኔታን ቁልጭ አድርጎ የሚያሳይ ቁሳዊ ትውፊት ነው” የሚል ትርጉም ይሰጣል፡፡ ለአንድ አገር የቱሪዝም ኢንዱስትሪ ቅርስ ዋናውን ቦታ ይይዛል፡፡

ባለፈው ሳምንት የአራዳ ክፍለ ከተማ ባህልና ቱሪዝም ቢሮ፤ ለ3ኛ ጊዜ ያዘጋጀው የባህል ሳምንትን መነሻ አድርጎ ባዛርና የፎቶግራፍ ኤግዚቢሽን 4ኪሎ በሚገኘው በክፍለ ከተማው ደጅ አቅርቦ ነበር፡፡የ ኦርቶዶክስ፣ የካቶሊክ፣ የእስልምና 12 ቤተ እምነቶች፤ 4 ኪሎ፣ 6ኪሎ፣ አራዳ ጊዮርጊስና አርመን ሰፈር የሚገኙባቸውን አራት አደባባዮች፤ 7 ሐውልቶች፤ 71 ቤቶችን በቅርስነት መያዙን የሚገልጽ ማሳያ ፎቶግራፎችንና የጽሑፍ መግለጫዎች በኤግዚቢሽኑ አቅርቦ አሳይቷል፡፡

የክፍለ ከተማው ባህልና ቱሪዝም ቢሮ አሁን ከመዘገባቸውም በተጨማሪ ሌሎች ቅርሶችን ለይቶ ጥበቃ እንዲደረግላቸው እየተጋ ያለ ቢሆንም ከቢሮው አቅም በላይ በሆነ ምክንያት በቅርስነት መዝግቧቸው የነበሩ ታሪካዊ ቤቶች ፈርሰውበታል፡፡ የካቲት 19 ቀን 2003 ዓ.ም ታዘበው ዘለለ በአዲስ አድማስ ጋዜጣ ባቀረቡት ጽሑፍ እንዳመለከቱት፤ በልደታም፣ በ4ኪሎም በቅርስነት ተመዝግበው የነበሩ ቤቶች የዳግም ልማቱ ሰለባ ሆነዋል፡፡

ለመልሶ ማልማት ነባር ቤቶች እንዲፈርሱ ሲደረግ፣ ከታሪካዊ መገኛ ስፍራቸው እንዲወገዱ ከተደረጉት ከአራት ኪሎ ታሪካዊ ቤቶች አንዱ “አሜሪካን ስኩል”፣ “ሊየን ቱሪዝም ቤቶች”፣ “ዶርዜ አይዞ” እየተባለ የተለያዩ አገልግሎት የሰጠው ቤት ባለቤት አርመናዊ ደሜጥርስ ጴጥሮስ ሲሆኑ ቤቱ በቅርስነት የተመዘገበበት ዋነኛው መሥፈርት የሥነ ሕንፃ አሰራሩ ነበር፡፡ ከአርመናዊ ቤት በስተጀርባ ይገኝ የነበረው የእንድሪያስ አባዲያስ ቤትም ኢትዮጵያዊ የቤት አሰራርንና ጥበብ የተከተለ በመሆኑና የቤቱም ባለቤት የ“አዕምሮ” ጋዜጣ አዘጋጅ ሆነው ከማገልገላቸው ታሪካዊነት ጋር ቤታቸው በቅርስነት ተመዝግቦ የነበረ ሲሆን አሁን በ”ነበር” ቀርተዋል፡፡ በቅርስነት የተመዘገቡት ቤቶች በምን ምክንያት እንዲፈርሱ ተደረገ? የክፍለ ከተማው ባህልና ቱሪዝም ቢሮ፤ ቤቶቹን ለማዳን ከከተማው ዋና ቢሮ ጀምሮ ባህልና ቱሪዝም ሚኒስቴር ድረስ ከማሳወቁም ባሻገር እስከ ፍርድ ቤት ድረስ ሄዷል፡፡

ክርክሮቹ ይግባኝ እየተጠየቀባቸው በመጨረሻ ቤቶች እንዲፈርሱ ሆኗል፡፡ እርምጃው በአንድ አስተዳደር ስር ያሉ ሁለት መንግሥታዊ ቢሮዎች የማይግባቡ መሆኑ የታየበት ብቻ ሳይሆን ለአንድ ዓላማና ግቡ የማይሰሩ አስመስሏቸዋል ተብሏል፡፡

“ከዚያ ስህተት በመማር መልሶ በማልማቱ ሂደት ለቅርስ ትኩረት እንዲሰጥ መግባባት ላይ ተደርሷል” የሚሉት አቶ ፍሬው ለማ፤ በአራዳ ክፍለ ከተማ ቱሪዝም ጽሕፈት ቤት የቱሪዝም ልማትና ዋና ቅርስ አስተዳደር ሂደት ውስጥ የቅርስና ቱሪዝም ኦፊሰር ናቸው፡፡ መግባባት ላይ ከተደረሰ በኋላ በልማት ምክንያት ከመፍረስ ከዳኑት ቤቶች አንዱ ቸርችል ጎዳና ላይ የሚገኘው የሐኪም ወርቅነህ ቤት አንዱ ነው ይላሉ፡፡

ቅርስን በተመለከተ በመንግሥት ቢሮዎች አካባቢ ብቻ ሳይሆን ሕብረተሰቡ ውስጥም የግንዛቤ ችግር እንዳለ የሚናገሩት አቶ ፍሬው ለማ፤ የባህልና ቱሪዝም ቢሮ በቅርስነት መያዝ የሚኖርባቸውን ቤቶች ለማጥናት ከሕብረተሰቡ መረጃ ሲጠይቅ፣ ሰዎች ጉዳዩን ከውርስ ጋር እያያያዙት እንደማይተባበሩና ለዳግም ልማት ቤቶችን የማፍረስ ሥራ ሲጀመር ግን ቤታቸው በቅርስነት እንዲመዘገብ የሚጠይቁ አሉ ብለዋል፡፡

ችግሩ ሰፊ ሥራ የሚጠይቅ መሆኑን ባለፈው ሳምንት በ4 ኪሎ አካባቢ የታየው ክስተት ጥሩ ማሳያ ነው፡፡ የአራዳ ክፍለ ከተማ ባህልና ቱሪዝም ቢሮ መዝግቦ ስለያዛቸው ቅርሶች የፎቶግራፍ ኤግዚቢሽን አቅርቦ ከሚያሳይበት ቦታ በቅርብ ርቀት በቅርስነት ተመዝግቧል የሚባለው የተስፋ ገ/ሥላሴ ማተሚያ ቤትን ከፊል ይዞታ ለማፍረስ፣ አፍራሽ ግብረ ኃይል ወደ ቦታው ተልኳል፡፡

የቀኛዝማች ተስፋ ገ/ሥላሴ ቤተሰቦችም አቤቱታቸውን ለመንግሥትና ለሕዝብ እያሰሙ መሆኑን ሚዲያዎች ዘግበውታል፡፡ መንግሥት በመጪው ትውልድ የማይከሰስበትን የልማት ሥራ መስራት አለበት የሚያስብለው እንዲህ ዓይነት የማይግባቡ አሰራሮች ስለሚታዩ ነው፡፡  ሰሞኑን በየአደባባዩ እየተጮኸባቸው በመሸጥ ላይ ካሉ መፃሕፍት አንዱ “PROCEEDINGS OF THE INTERNATIONAL SYMPOSIUM ON THE CENTNARY OF ADDIS ABABA” የሚል ርዕስ አለው፡፡ መጽሐፉ የአዲስ አበባ ከተማ ምሥረታ መቶኛ ዓመት በዓልን ምክንያት በማድረግ በሲምፖዚየም የቀረቡ የተለያዩ ጥናታዊ ጽሑፎችን ሰብስቦ ይዟል፡፡ በርካታ ፎቶግራፎችን፣ ካርታዎችንና ሠንጠረዦችን ያካተተውና 270 ገፆች ያሉት መጽሐፍ በህዳር ወር 1987 እ.ኤ.አ ነው የታተመው፡፡

አዲስ አበባ 125ኛ የምሥረታ ዓመቷን የምታከብርበት ወቅትን ጠብቆ መደበኛ ባልሆነ መልኩ ለሽያጭ የቀረበው ጥራዝ፤ ከተማዋ የመንግሥት መቀመጫ ለመሆን የበቃችበትን ሂደቶች እንዴት እንዳለፈች፤ ጥንታዊ ታሪኮችን ፈትሾ፣ አሸዋው ንጉሥ ሣህለሥላሴ ጋር የተያያዙ መነሻዎችን አመላክቶ፣ ዝርዝር ጉዞዎችን አስቃኝቶ፤ የደርግ መንግሥት በአዲስ አበባ የሰራቸውን ሕንፃዎች ጭምር ያስተዋውቃል፡፡

የመቅደላ፣ የመቀሌ፣ የአንኮበር … ጥንታዊ ቦታዎችን ፎቶግራፍ የያዘው መጽሐፍ፤ አዲስ አበባ ከተማ በተመሠረተችበት ዘመን የነበራት ገጽታ ምን ይመስል እንደነበር ከቀረቡት የፎቶ ማሳያዎች መካከል በቀሳውስት የተሞላው የ4 ኪሎ ቤተ መንግሥት (ግቢ)፤ የሕዝቡ ብዛትና የሜዳ ላይ መገበያያው ስፋት የሚያስደምመው አራዳ ገበያ፤ በገበያው አንድ ጥግ የዳኝነት አገልግሎት ይሰጥ የነበረው ሸንጐ፤ የአራዳ ገበያ ቆዳ ተራና የተገበያዩ ብዛት፤ መርካቶ በገበያነት ከመከተሟ በፊት ፊታውራሪ ሀብተጊዮርጊስ ዲነግዴ ይኖሩበት የነበረው እልፍኝና በዙሪያው የነበሩ የሣር ጎጆ ቤቶች .. ሲታዩ ታሪክን በጽሑፍ፣ በፎቶግራፍና በመሳሰለው ዘዴ ሁሉ መዝግቦ የማቆየት ጠቀሜታን ያመለክታል፡፡

በመጽሐፉ በገጽ 111 እና 112 የሚገኙት ሁለት ፎቶግራፎች ደግሞ ጥንትም ዛሬም ያለ ተመሳሳይ ታሪክ ያሳያሉ፡፡ አንደኛው ፎቶግራፍ የተነሳው ባሻ ወልዴ ችሎት ወይም ከእሪ በከንቱ ወንዝ አካባቢ በቆመ ፎቶ አንሺ ሲሆን ሁለተኛው ምስል የተወሰደው ከዋናው ፖስታ ቤት አካባቢ ወደፊት በር ባነጣጠረ ፎቶ አንሺ ነው፡፡

በሁለቱም ጥንታዊ ፎቶግራፎች እንደሚታየው ዳገቱ ላይ ባለው የ4 ኪሎ ቤተ መንግሥት ዙሪያ ያለው ቦታ የሚበዛው ባዶ ሆኖ፣ ጥቂት የሣር ጎጆ ቤቶች ብቅ ብቅ እያሉ መሆኑን ነው የሚያመለክቱት፡፡

በቤተመንግሥቱ ዙሪያ በሣር ጎጆ መሰራት የጀመሩት ቤቶች ሣሩ በቆርቆሮ፣ ጭቃው በድንጋይና በሸክላ እየተተካ ችምችም ብሎ በቤቶች የተሞላው የሥላሴ ገበያ፣ የእሪ በከንቱና የባሻ ወልዴ ችሎት መንደሮች ለሸራተንና ለፓርላማ ማስፋፊያ በሚል ለዳግም ልማት ነዋሪዎችን የማንሳቱ ሥራ ከተጀመረ ሰንበትበት ብሏል፡፡

ልማቱ፤ ከለመዱት አካባቢና ማሕበራዊ ትስስር ስለሚነጥል ሁሉንም ሰው ያስደስታል ተብሎ አይታሰብም፡፡ እየሆነ ባለው ነገር እየተደሰቱ ያሉት ምን ያህል ይሆናሉ? የተከፉትስ ቁጥራቸው ስንት ይደርሳል? ለሚለው ጥያቄ እቅጩን ቁጥር በግምትም ቢሆን መግለጽ ያስቸግራል፡፡ ከግል ፍላጎትና ጥቅም አንፃር ከሚታየው ማስደሰትና ማስከፋት ይልቅ ልማቱ ከአገራዊና ሕዝባዊ ጠቀሜታው፣ ከማህበራዊና ባህላዊ ፋይዳው፣ ከታሪክና ኢኮኖሚያዊ ዋጋው አንፃር ታይቶ፤ እየተሰራ ያለው ነገር ምን ያስገኛል? የሚለው በይበልጥ ቢያነጋግር፣ ቢያወያይ፣ ቢያከራክር ይጠቅማል፡፡

የሸራተንና የፓርላማ ማስፋፊያ በሚል ዓላማ ነባሩን ነዋሪ ከአካባቢው በማስነሳቱ ሂደት የታዩ ሳንካዎችና ሊከሰቱ የሚችሉ ችግሮችን ለማመልከት የሞከሩ አሉ፡፡ የካቲት 19 ቀን 2003 ዓ.ም ታዘበው ዘለላ የተባሉ ፀሐፊ በአዲስ አድማስ ጋዜጣ “የአዲስ አበባ ታሪካዊ ቤቶች የተጋረጠባቸው አደጋ” በሚል ርዕስ የችግሩን አንድ መልክ፣ በ4 ኪሎ የተፈጠረን ጥፋት በምሳሌነት በማቅረብ አመልክተዋል፡፡

በፍቃዱ አባይ የተባሉ ፀሐፊም ጥቅምት 4 ቀን 2004 ዓ.ም “የአዱ ገነት ልማት ተጠቃሚው ማን ነው?” በሚል ርዕስ በ4 ኪሎ መልሶ ማልማት ሂደት ውስጥ ያስተዋሉትን ታዝበው አስተያየታቸውን አቅርበዋል፡፡

ለዳግም ልማት ፈርሰው ሊጠናቀቁ ጥቂት በቀራቸው የሸራተንና የፓርላማ መንደር ቤቶች ማዕከል አድርጎ፣ በዚህ ወቅት ይህ ጽሑፍ መቅረቡ ምን ፋይዳ አለው? የሚል ጥያቄ ሊነሳ ይችላል፡፡ አንደኛው እየተሰራ ባለው ነገር ውስጥ የተከሰቱ ጥፋቶችን በጋዜጦች በኩል ለሕዝብና ለመንግሥትም ማመልከት የቻሉት ፀሐፍት፤ በአደባባይ ባይመሰገኑበትም ያቀረቡት ሐሳብ በመንግሥት ቢሮዎችም ድጋፍ ያለው መሆኑን መስማቴ ነው፡፡ ለዚህ ጽሑፍ መጀመር ምክንያቱም ይኸው ነው፡፡ ዝርዝሩን እመለስበታለሁ፡፡

ሁለተኛው ጠቀሜታ አዲስ አበባ ከተማ ከነባር ሠፈሮቿ የሚበዙት ለዳግም ልማት የመፍረስ ዕጣ የሚጠብቃቸው በመሆኑ፤ ቀድመው ከፈረሱት መንደሮች የሚወሰደው ልምድ ጥፋት እንዲቀንስ፣ በኋላ የሚያስቆጭ ነገር እንዳይሰራ፣ ከመፍረስ መጠበቅ ያለባቸውን ቤቶች በቅድሚያ ለይቶ መወሰንን የመሳሰሉት ጠቀሜታዎችን ስለሚያስገኝ ነው፡፡

ለዚህ ጽሑፍ መነሻ የሆነኝና “ቅርስ የነበሩት ቤቶች መፍረስ እንዳልነበረባቸው ሁሉም የመንግሥት ቢሮዎች መግባባት ላይ ደርሰውበታል” የሚለውን መግለጫ በሰማሁበት መድረክ ላይ በተሰራጨ በራሪ ወረቀት ላይ “ቅርስ” ለሚለው ቃል “በአንድ ወቅት የነበረን የአንድን ማህበረሰብ ማንነት፣ የአንድ አገር ስልጣኔ፣ ባህልና የአኗኗር ሁኔታን ቁልጭ አድርጎ የሚያሳይ ቁሳዊ ትውፊት ነው” የሚል ትርጉም ይሰጣል፡፡ ለአንድ አገር የቱሪዝም ኢንዱስትሪ ቅርስ ዋናውን ቦታ ይይዛል፡፡

ባለፈው ሳምንት የአራዳ ክፍለ ከተማ ባህልና ቱሪዝም ቢሮ፤ ለ3ኛ ጊዜ ያዘጋጀው የባህል ሳምንትን መነሻ አድርጎ ባዛርና የፎቶግራፍ ኤግዚቢሽን 4ኪሎ በሚገኘው በክፍለ ከተማው ደጅ አቅርቦ ነበር፡፡የ ኦርቶዶክስ፣ የካቶሊክ፣ የእስልምና 12 ቤተ እምነቶች፤ 4 ኪሎ፣ 6ኪሎ፣ አራዳ ጊዮርጊስና አርመን ሰፈር የሚገኙባቸውን አራት አደባባዮች፤ 7 ሐውልቶች፤ 71 ቤቶችን በቅርስነት መያዙን የሚገልጽ ማሳያ ፎቶግራፎችንና የጽሑፍ መግለጫዎች በኤግዚቢሽኑ አቅርቦ አሳይቷል፡፡

የክፍለ ከተማው ባህልና ቱሪዝም ቢሮ አሁን ከመዘገባቸውም በተጨማሪ ሌሎች ቅርሶችን ለይቶ ጥበቃ እንዲደረግላቸው እየተጋ ያለ ቢሆንም ከቢሮው አቅም በላይ በሆነ ምክንያት በቅርስነት መዝግቧቸው የነበሩ ታሪካዊ ቤቶች ፈርሰውበታል፡፡ የካቲት 19 ቀን 2003 ዓ.ም ታዘበው ዘለለ በአዲስ አድማስ ጋዜጣ ባቀረቡት ጽሑፍ እንዳመለከቱት፤ በልደታም፣ በ4ኪሎም በቅርስነት ተመዝግበው የነበሩ ቤቶች የዳግም ልማቱ ሰለባ ሆነዋል፡፡

ለመልሶ ማልማት ነባር ቤቶች እንዲፈርሱ ሲደረግ፣ ከታሪካዊ መገኛ ስፍራቸው እንዲወገዱ ከተደረጉት ከአራት ኪሎ ታሪካዊ ቤቶች አንዱ “አሜሪካን ስኩል”፣ “ሊየን ቱሪዝም ቤቶች”፣ “ዶርዜ አይዞ” እየተባለ የተለያዩ አገልግሎት የሰጠው ቤት ባለቤት አርመናዊ ደሜጥርስ ጴጥሮስ ሲሆኑ ቤቱ በቅርስነት የተመዘገበበት ዋነኛው መሥፈርት የሥነ ሕንፃ አሰራሩ ነበር፡፡ ከአርመናዊ ቤት በስተጀርባ ይገኝ የነበረው የእንድሪያስ አባዲያስ ቤትም ኢትዮጵያዊ የቤት አሰራርንና ጥበብ የተከተለ በመሆኑና የቤቱም ባለቤት የ“አዕምሮ” ጋዜጣ አዘጋጅ ሆነው ከማገልገላቸው ታሪካዊነት ጋር ቤታቸው በቅርስነት ተመዝግቦ የነበረ ሲሆን አሁን በ”ነበር” ቀርተዋል፡፡ በቅርስነት የተመዘገቡት ቤቶች በምን ምክንያት እንዲፈርሱ ተደረገ? የክፍለ ከተማው ባህልና ቱሪዝም ቢሮ፤ ቤቶቹን ለማዳን ከከተማው ዋና ቢሮ ጀምሮ ባህልና ቱሪዝም ሚኒስቴር ድረስ ከማሳወቁም ባሻገር እስከ ፍርድ ቤት ድረስ ሄዷል፡፡

ክርክሮቹ ይግባኝ እየተጠየቀባቸው በመጨረሻ ቤቶች እንዲፈርሱ ሆኗል፡፡ እርምጃው በአንድ አስተዳደር ስር ያሉ ሁለት መንግሥታዊ ቢሮዎች የማይግባቡ መሆኑ የታየበት ብቻ ሳይሆን ለአንድ ዓላማና ግቡ የማይሰሩ አስመስሏቸዋል ተብሏል፡፡

“ከዚያ ስህተት በመማር መልሶ በማልማቱ ሂደት ለቅርስ ትኩረት እንዲሰጥ መግባባት ላይ ተደርሷል” የሚሉት አቶ ፍሬው ለማ፤ በአራዳ ክፍለ ከተማ ቱሪዝም ጽሕፈት ቤት የቱሪዝም ልማትና ዋና ቅርስ አስተዳደር ሂደት ውስጥ የቅርስና ቱሪዝም ኦፊሰር ናቸው፡፡ መግባባት ላይ ከተደረሰ በኋላ በልማት ምክንያት ከመፍረስ ከዳኑት ቤቶች አንዱ ቸርችል ጎዳና ላይ የሚገኘው የሐኪም ወርቅነህ ቤት አንዱ ነው ይላሉ፡፡

ቅርስን በተመለከተ በመንግሥት ቢሮዎች አካባቢ ብቻ ሳይሆን ሕብረተሰቡ ውስጥም የግንዛቤ ችግር እንዳለ የሚናገሩት አቶ ፍሬው ለማ፤ የባህልና ቱሪዝም ቢሮ በቅርስነት መያዝ የሚኖርባቸውን ቤቶች ለማጥናት ከሕብረተሰቡ መረጃ ሲጠይቅ፣ ሰዎች ጉዳዩን ከውርስ ጋር እያያያዙት እንደማይተባበሩና ለዳግም ልማት ቤቶችን የማፍረስ ሥራ ሲጀመር ግን ቤታቸው በቅርስነት እንዲመዘገብ የሚጠይቁ አሉ ብለዋል፡፡

ችግሩ ሰፊ ሥራ የሚጠይቅ መሆኑን ባለፈው ሳምንት በ4 ኪሎ አካባቢ የታየው ክስተት ጥሩ ማሳያ ነው፡፡ የአራዳ ክፍለ ከተማ ባህልና ቱሪዝም ቢሮ መዝግቦ ስለያዛቸው ቅርሶች የፎቶግራፍ ኤግዚቢሽን አቅርቦ ከሚያሳይበት ቦታ በቅርብ ርቀት በቅርስነት ተመዝግቧል የሚባለው የተስፋ ገ/ሥላሴ ማተሚያ ቤትን ከፊል ይዞታ ለማፍረስ፣ አፍራሽ ግብረ ኃይል ወደ ቦታው ተልኳል፡፡

የቀኛዝማች ተስፋ ገ/ሥላሴ ቤተሰቦችም አቤቱታቸውን ለመንግሥትና ለሕዝብ እያሰሙ መሆኑን ሚዲያዎች ዘግበውታል፡፡ መንግሥት በመጪው ትውልድ የማይከሰስበትን የልማት ሥራ መስራት አለበት የሚያስብለው እንዲህ ዓይነት የማይግባቡ አሰራሮች ስለሚታዩ ነው፡፡

Read 3752 times Last modified on Saturday, 12 May 2012 12:02