Sunday, 14 October 2018 00:00

ከመጠምጠም መማር ይቅደም

Written by 
Rate this item
(9 votes)

ከዕለታት አንድ ቀን ሁለት ባልንጀራዎች ነበሩ፡፡ ወደ አንድ ሩቅ አገር ለመሄድ አስበው መንገድ ጀመሩ፡፡ አንደኛው በሽተኛና ለቋሳ ነው፡፡ ሁለተኛው ብርቱና ጤናማ ሰው ነው። የሚሄዱት በረሀውን አቋርጠው ነው፡፡ ፀሐዩ ያነድዳል፡፡ አሸዋው ያቃጥላል፡፡ በረሀው ረዥምና ሰፊ ነው፤ አቅምና ወኔ ይፈታተናል፡፡ በዋዛ ማለፍ አልተቻለም፡፡
በሽተኛው ተዝለፍልፎ ወደቀ፡፡ ጤነኛውና ጠንካራው፤ በሽተኛውን ከወደቀበት አንስቶ ተሸክሞ፣ በረሀውን እስኪጨርሱ ድረስ ተጓዙ፡፡ አወረደውና ጥቂት አረፍ አሉ፡፡
አየሩ እየቀዘቀዘ፣ ጀንበሯ እያዘቀዘቀች መጣች፡፡ ጥቂት እንደሄዱ “እንተኛ?” አለ በሽተኛው፡፡
“እውነትክን ነው፡፡ በጊዜ መተኛት፣ በጠዋት መነሳት፣ የጤንነት ምንጭ ነው! የጠቢብነት መሰረት ነው፡፡ ሀብትም፡፡”
“Early to bed
and early to rise
makes a man, healthy, wealthy and wise. እንዲሉ ፈረንጆች፡፡” አለ ጤነኛውና በሳሉ ጓደኛው፡፡
ተኙ፡፡
ማታ ነው - የጅብ ሰዓት፡፡ ጅብ፤ ጓደኛሞቹ ወደተኙበት መጣ፡፡ በሽተኛው የጅቡን እንቅስቃሴ ሰምቶ፣ አወቀው፡፡ ስለዚህ ጎኑ ያለውን የበረሀ ጓደኛውን ትቶ ሮጠና ዛፍ ላይ ወጣ፡፡ ጅቡ ወደተኛው ሰው ተጠጋ፡፡ ጆሮው ዙሪያ ተጠግቶ አሸተተውና ምንም ሳያደርገው ሄደ፡፡ ጅብ የሞተ አይነካምና፡፡
 ይህ ሁሉ ሲሆን በሽተኛ ጓደኛው ዛፍ ላይ ሆኖ ቁልቁል ይመለከታል፡፡ ጅቡ ከራቀ በኋላ ከዛፉ ላይ ወረደና ወደ ጓደኛው ሄደ፡፡ ለካ ጓደኛው የጅብን ባህሪ ስለሚያውቅ ነው፣ ፀጥ እረጭ ብሎ የሞተ ያስመሰለው!!
በሽተኛው ጤነኛውን ጠየቀው፡- “ጅቡ አፉን በጣም ጆሮህ ላይ አቅርቦ ምን አለህ?”   
ጠንካራው ሰውም እንዲህ ሲል መለሰ፡-
“ሁለተኛ፤ በክፉ ቀን የሚከዳ ባልንጀራ አትያዝ ብሎኝ ነው ያለፈው!” አለው፡፡
*   *   *
ለካ የሞተ መምሰል አንዳንዴ አሪፍ እስትራቴጂ ነው! ጊዜን የማወቅ ጉዳይ ነው፡፡ መንጋትና መምሸቱን ከማያውቅ ትውልድ ይሰወረን! ከከሀዲም ያድነን!
“ትላንቱን የማያውቅ
ዛሬን የሚያሳስቅ
 ነገን የሚደብቅ
እንደኖረ ሳይሆን እንዳይኖረው ይወቅ” -- ብሏል ገጣሚው ፀጋዬ ገብረመድህን በ”ቴዎድሮስ ስንብት ከመቅደላ ላይ”-  ይህን መሳዩን ትውልድ፡፡
“ሽማግሌውን ባንቀልባ፣ ከምንሸከም እንኮኮ
ጎልማሳውን ከወኔ ጣር፣ ካልፈታን ከፍርሃት ምርኮ”  
እንደ ወዶ ገባ ኮርማ፣
መጠለሉን ከሴት ታኮ
ካቀቃተን ምንድን ነን እኮ?”
 ትውልድን ማዳን ፀጋ ነው፡፡ ጥረታችን እዚያ ዙሪያ ይሁን፡፡ “ወጣት የነብር ጣት” የሁሉም ዘመን ማተብ አይደለም! “የነብርን ጅራት አይዙም፤ ከያዙ ጭራሽ አይለቁም” የሚባለው ለለውጥም ይሰራል፡፡ (ለውጡ ጅራት ይኑረውም አይኑረውም) ለማናቸውም ዓይነት ለውጥ መዘጋጀት፡፡ ከማናቸውም ዓይነት ለውጥ መነሳትና ለማጥበቅ ሀሞትን መሰነቅ እንጂ እህህም እህህም የትም አያደርስምና፡፡ “እህህን ለፈረስ ያስተማርኩ እኔ ነኝ እሱንም ቢርበው እኔን ሲቸግረኝ” (ለመሆኑ እህህ … ምን ያህል ረጅም ነው? ሳንወለድ ጀምሮ ስንሞትም እሱ ቀጣይ ነው?!) Sustainable poverty /ዘላቂ ድህነት/ መኖር አለመኖሩን መንግስታዊ ያልሆኑ ድርጅቶች (NGOs) ይንገሩን፡፡
“ወጣቱማ ይማር! ቢፈልግ ደግሞ ይማረር
ሀሁውን በቅጡ ይቁጠር
ጥቁር መጋረጃ ይቅደድ
ፈተናን መሸሽ ያስወግድ
የልጅነቱን ያህል ይሂድ!
የወጣትነቱን ይንደድ
የጎልማሳነቱን ይውደድ
እንጂ በትኩሳት ብቻ፣ በጀማነትም አይንደድ!
በዚህም በዚያኛውም ስም፣
ትርፍ ፍለጋ አይሰደድ!
ለተሻለ ነገር ሁሉ፣ በራሱ መንገድ ይወደድ!”
ብቻ ለማናቸውም የተሻለች ኢትዮጵያን ለመፍጠር፤ “ከመጠምጠም መማር ይቅደም!!

Read 9018 times