Saturday, 13 October 2018 10:40

በ‘ባዶ ሜዳ፣ ኒሻን ድርደራ’

Written by  ኤፍሬም እንዳለ
Rate this item
(3 votes)

 እንዴት ሰነበታችሁሳ!
ስሙኝማ… ይሄ የመካካብ ነገራችን…አለ አይደል…ወይ ‘ሆቢ’ ወይ ‘አጉል ልምድ’ ብቻ መሆኑ ቀረና በቃ ‘ስትራቴጂ’ ነገር ሆኖ ቀረ! ተኩሰን ባልጣልነው አንበሳ… “ለምንድነው ራስህ ላይ የአንበሳ ጎፈር የማታደርገው!” መባባሉ፣ ‘እነ እንትና’ ብቻ የሚያደርጉት ሳይሆን አብዛኞቻችን አኮ እየሠመጥንበት ነው!
ስብሰባ ላይ…
“በእውነቱ ሥራ አስኪያጃችን ድርጀቱን ለከፍተኛ ደረጃ ለማድረስ ደከመኝ፣ ሰለቸኝ ሳይሉ ቀን ከሌት መልፋታቸው በእጅጉ ሊያስመሰግናቸው ይገባል፡፡ በእሳቸው አመራር ድርጅታችኝ ለሌሎች ሁሉ ምሳሌ ሆኗል፡፡” አዳራሹ ከዳር ዳር በጭበጨባ ይናጋል፡፡ የሥራ አስኪያጁ የድል ፈገግታ የስታዲየምን ፓውዛ ሊመሰል ምንም አይቀረው፡፡ (ባህር ዳሮች፣ ተሸማቀን አንገታችንን የማንደፋበት ስታዲየም ስለሰጣችሁን አንድዬ የምትፈልጉትን አብዝቶ ይስጣችሁማ!)
እናላችሁ… ሚኒስትር ዴታው ምናምን… “ይሄን ሰውዬ ለእሱ የሚመጥነው አነስ ያለ ምን ቦታ ላይ እናስቀምጠው?” ብለው ምክር ይዘዋል… አጅሬ “በሁለተኛው የዓለም ጦርነት ጀርመኖችን  ከፖላንድ ለማስወጣት ለፈጸመው ጀብዱ” የሚል የሚሊዮን ዶላር ኒሻን የተሰጠው ይመስል በኩራት ልብሱን ቀዶ ሊወጣ ምንም አይቀረው፡፡
በቃ… እንኳን ቀድመን ልንገባ፣ ባልጨረስነው የመቶና የምናምን ሜትር ሩጫ አሸናፊነቱን ሜዳልያ አንገታችን ላይ ሲያጠልቁልን… “አይ ይሄ እንኳን ለእኔ አይገባም” ብሎ ነገር የለም። እንደውም… “የሽልማት ገንዘቡስ!” ባንል ነው!  እንወዳለና! ጭብጫቦ እንወዳለና!
ስሙኝማ… እንግዲህ ጨዋታም አይደል…እኔ የምለው፣ ብዙ ‘ቦተሊከኞቻችን’ ውዳሴ ምናምን ይወዳሉ ልበል! የምር…አንዳንዴ ንግግሮቻቸውን፣ ቃለመጠይቆቻቸውን ምናምን ስንሰማ… “እነኚህ ሰዎች ስለ ራሳቸው እንዴት ነው የሚያሰቡት?” የሚያስብሉ ነገሮች አየገጠሙን ስለተቸገርን ነው። በጥቅሉ ስናወራ የሰዋችን አስተሳሰብ ከትናንት ወዲያ ላይ አለመቆሙን ማወቁ ጥሩ ነው፡፡ እግረ መንገድ…‘ማመልከቻ በሁሉም ወገን ላላችሁ ቦተሊከኞቻችን’…እስከዚህም ድረስ ነገር የማይገባን አታድርጉንማ! አንዳንዴ በንግግሮቻችሁና በመሳሰሉት ነገሮቻችሁ፣ ለመዋእለ ህጻናት አስተማሪነት የተግባር ልምምድ ላይ ያላችሁ እየመሰለን ስለጨነቀን ነው፡፡ 
ስሙኝማ… እንግዲህ ጨዋታን ጨዋታ ያነሳው የለ…እኔ  የምለው… ኤ.ቲ.ኤም. የሚሉት ነገር ዋናው ጥቅሙ ለጥድፊያም፣ ከሰልፍ ለመዳን ምናምን አይደል እንዴ!… ምኑን ከሰልፍ ተረፍነው! እንደውም አንዳንዴ የሰልፉ እርዝመት እኮ ሰዉ የራሱን ገንዘብ ሊያወጣ ሳይሆን በነጻ የሚታደል ነገር ያለ ነው የሚመስለው፡፡ አሀ…መአት ኤ.ቲ.ኤም. ተደርድሮ የሚሠሩት አንዱ ወይ ሁለቱ ብቻ ናቸው፡፡ ሁለትም ይሁኑ ሦስትና ከዛም በላይ ሁሉም ሲሠሩ ማግኘቱ፣ የምናምን ሚሊዮን ሎተሪ እንደማግኘት አይነት ነው፡፡ ደግሞላችሁ… መሳሪያዎቹ ላይ “አይሠራም” ምናምን ብሎ ለመለጠፍ ልዩ በጀት ማስፈቀድ ያስፈልጋል እንዴ! “እኛ ዘመናዊ ብለን የሠራናቸውን መሳሪያዎች፣ ኋላቀር በማስመሰል ላደረሱብን የሞራል ጉዳት…” ምናምን ብለው ዘ ሄግ እንዳይገትሩን!
ግን ድርጀቶች ፈራንካቸውን እስካገኙ ድረስ… “የራሱ ጉዳይ!” አይነት ነገር ነው፡፡
እናማ… ጥቅሙ እስከተገኘ ድረስ… “እንደ ፍጥርጥራቸው!” ዓይነት ነገር ብልጥነት አይደለም።
ብዙ ቦታዎች የራሳቸው ጥቅም ከተሟላላቸው በኋላ ‘አስጥተዋችሁ’ ይሄዳሉ፡፡
“ምን መሰለሽ፣ ትናንትና ከሰዎች ጋር ምሳ እየበላሁ እያለ ትን ይለኛል፡፡”
“አፈር በበላሁ! ተረፍክ?”
“ይህን ያህል ከባድ አልነበረም፡፡ ግን ትን ሲለኝ ምን አልኩ መሰለሽ…
“ምን አልክ?”
“በቃ፣ እሷ ስሜን ስታነሳ ነው አልኩ፡፡”
“ታድዬ!”
እንኳን እንደዛ ሊል መንገድ ላይ እስከተገናኙ ድረስ ትዝም አላለችውም እኮ! ግን… አለ አይደል… በቃ የወቅቱ ስትራቴጂ እንዲህ ሆኗላ! ባልዋልንበት ሜዳ፣ ባልወጣነው ተራራ፣ ባልተሻገርነው ወንዝ-- የሜዳሊያ መአት ሲደረድሩልን ነገራችን… “ኩራት ኩራት አይልሽም ወይ!” አይነት ይሆናል! የአንገት ቁጥር አስራ ሦስት የሚሰፋበት ትከሻችን ጥግና ጥግ የሄደ መስሎን፣ ነገራችን “ይህ በር ሊጠበኝ ነው መሰለኝ!” አይነት ነገር ይመጣል፡፡
እኔ የምለው…በቃ ‘ፈረንጆቹ’ እንደፈለጋቸው ነው ስማችንን እዚህ፣ አዚያ የሚያላጉት! አለ አይደል…መቼም በዚህ በቴከኖሎጂ በተራቀቀ ዘመን መረጃ የላቸውም አይባልም፡፡ በእርግጥ አፍሪካ በዘርፈ ብዙ ችግር የተሞላች ነች፡፡ በተለይም ከፍተኛ የምግብ እጥረት አለ፡፡ ግን ድፍን አፍሪካ ተርቧል ማለት አይደለም፡፡ ረሀብ ምን እንደሆነ የማያውቁ በጣም ብዙ የአፍሪካ ማህበረሰቦች አሉ፡፡ ሁሉንም በአንድ ቅርጫት-- ቀሺም ፖለቲካ ነው፡፡ እናላችሁ…ለአንድ አስተያየት መሰብሰቢያ የቀረበው ብቸኛ ጥያቄ እንዲህ የሚል ነበር…“በተቀረው ዓለም ላይ ስላለው የምግብ እጥረት መፍትሄ እባካችሁ ሀቀኛ አስተያየታችሁን ስጡ፡፡” ተደረሰበት የተባለው ድምዳሜ  ምን መሰላችሁ…
በአፍሪካ “ምግብ” ማለት ምን ማለት እንደሆነ አያውቁም፡፡
በምስራቅ አወሮፓ “ሀቀኛ” ማለት ምን ማለት እንደሆነ አያውቁም፡፡
በምእራብ አውሮፓ “እጥረት” ማለት ምን ማለት እንደሆነ አያውቁም፡፡
በቻይና “የግል አስተያየት” ማለት ምን ማለት እንደሆነ አያውቁም፡፡
በመካከለኛው ምስራቅ “መፍትሄ” ማለት ምን ማለት እንደሆነ አያውቁም፡፡
በደቡብ አሜሪካ “እባካችሁ” ማለት ምን ማለት እንደሆነ አያውቁም፡፡
በአሜሪካ ደግሞ “የተቀረው ዓለም” ማለት ምን ማለት እንደሆነ አያውቁም፡፡
ለሁሉም ሌላ ሌላው ድምዳሜ ሲሰጥ ለአፍሪካ ግን “ምግብ ማለት ምን ማለት እንደሆነ አያውቁም፣” አሉንና አረፉት! እናላችሁ… እንዲህ የመሳሰሉትን ነገሮች በአስተማማኝ ለመለወጥ በጋራ ከመጣርና ከመስራት ይልቅ በባዶ ቲሪሪም፣ ታራራም እየተካካብን፣ ችግራችንና መከራችን በካብ ላይ ካብ እየሆነ ነው፡፡
ይቺን ስሙኝማ…የወጣቱ እድሜ 24 ነበር። ከአባቱ ጋር በባቡር እየተጓዘም ነበር፡፡ መሀል ላይም…
“አባዬ አየሀቸው፣ ዛፎቹ ወደ ኋላ እየሄዱ ነው!” ሲል ጮኸ፡፡
አባትየው ፈገግ አለ፡፡ ከጎናቸው የተቀመጡት ባልና ሚስት በወጣቱ የህጻንነት ባህሪይ አዝነው ይመለከቱት ነበር፡፡ በድጋሚ ወጣቱ…
“አባዬ አየሀቸው፣ ደመናዎቹ ከእኛ ጋር እየሮጡ ነው!” ሲል ጮኸ፡፡
ባልና ሚስቱ ነገሩ ግራ ቢገባቸው አባትየውን ጠየቁት፡፡
“ልጅህን ለምን ጥሩ ዶክተር ዘንድ አትወስደውም?” አሉት፡፡
አባትየውም ፈገግ ብሎ እንዲህ አላቸው…
“ወስጄው ነበር፣ አሁን ከዛው እየተመለስን ነው። ልጄ ከውልደቱ ጀምሮ ዓይነ ስውር ነበር፡፡ ገና ዛሬ ነው ማየት የጀመረው” አላቸው፡፡
“በዚች ዓለም ላይ ያለ እያንዳንዱ ሰው የየራሱ ታሪክ አለው፡፡ ሰዎችን ጠንቅቀህ ካላወቅሀቸው በስተቀር ድምዳሜ ላይ አትድረስ፡፡ ምክንያቱም ስለ ሰዎቹ የምትሰማው እውነታ ሊያስገርምህ ይችላልና!” ነው ምክር ሰጪዎቹ የሚሉት፡፡ እናላችሁ…እኛም ዘንድ ብዙ ጊዜ ድምዳሜ ላይ የሚደረሰው በእውነተኛው ታሪክ ላይ ተመስርቶ ሳይሆን በልብ ወለዱ ላይ እየሆነ ሰዎች ባልዋሉበት ስም ይሰጣቸዋል…በበጎም፣ በመጥፎም፡፡
እኔ የምለው…እንግዲህ ጨዋታም አይደል፣ የምክር ነገር ከተነሳ ይቺን ስሙኝማ… ሰውየው በሆነ ነገር ይከሰስና መንግስት ጠበቃ ያቆምለታል።
ዳኛውም ለጠበቃው እንዲህ ይሉታል… “ለተከሳሹ ጠበቃው ስለሆንክ ለእሱ የሚያዋጣውን ነገር ምከረው፡፡”
ከዚያም እረፍት ይሆናል፡፡ ከእረፍት መልስም ችሎቱ ሲጀመር ተከሳሹ ተመልሶ አልመጣም፡፡ ዳኛውም ጠበቃውን “ተከሳሹ የታለ?” ይሉታል፡፡
ጠበቃውም… “ክቡር ዳኛ፤ ለእሱ የሚያዋጣውን ምከረው ባሉኝ መሰረት መክሬዋለሁ፡፡”
“እኔ የጠየቅሁህ ለምን እንዳልመጣ ነው፡፡”
“ክቡር ዳኛ፤ ሰውየው በተከሰሰበት ጥፋተኛ መሆኑን ስለደረስኩበት፣ ባዘዙኝ መሰረት የሚጠቅመውን መከርኩት፡፡”
“ምን መከርከው?”
“ተመልሶ ቢመጣ ተፈርዶበት መታሰሩ ስለማይቀር እንዲጠፋ መከርኩት፡፡”
“መታሰሩ ስለማይቀር እንዲጠፋ መከርኩት” አይነት ምክርና ‘መመካከር’ በዝቶ ሊሆን ስለሚችል ጥናት ይካሄድልንማ! እስከዛው ግን በ‘ባዶ ሜዳ ኒሻን ድርደራው’ ቢቀንስልን አሪፍ ነው፡፡
ደህና ሰንብቱልኝማ!

Read 2862 times