Saturday, 13 October 2018 10:53

የአእምሮ ጤና ችግር በከፍተኛ መጠን እየጨመረ ነው

Written by  መታሰቢያ ካሳዬ
Rate this item
(10 votes)

· በየዓመቱ ከ3ሺ700 በላይ ሰዎች ራሳቸውን ያጠፋሉ
   · ከፍተኛውን ቁጥር የሚይዙት ከ15-19 ዓመት ታዳጊዎች ናቸው
   · 22 ሚ. የዓለም ህዝብ፣ ድባቴ በተባለው የአእምሮ ጤና ችግር ይሰቃያል
        

    በአገራችን የአዕምሮ ጤና ችግር በከፍተኛ መጠን እየጨመረ መሄዱንና በችግሩ እየተሰቃዩ ከሚገኙ ሰዎች መካከል ዕድሜያቸው ከ15 ዓመት እስከ 19 ዓመት የሚሆናቸው ታዳጊዎች ከፍተኛውን ቁጥር እንደሚይዙ ተገለፀ፡፡
የዓለም የአዕምሮ ጤና ቀን ለ10ኛ ጊዜ በአማኑኤል የአእምሮ ህክምና ስፔሻላይዝድ ሆስፒታል ውስጥ ባለፈው ሳምንት በተከበረበት ወቅት እንደተገለፀው፤ በአገራችን በየዓመቱ ከ8 ሺ 700 በላይ ሰዎች ከአዕምሮ ጤና ችግር ጋር በተያያዘ ራሳቸውን ያጠፋሉ። ከእነዚህም መካከል ዕድሜያቸው ከ15-19 ዓመት የሚሆናቸው ታዳጊ ወጣቶች ከፍተኛውን ቁጥር ይይዛሉ ተብሏል፡፡
በሆስፒታሉ የአዕምሮ ጤና ሃኪም የሆኑት ዶ/ር መሃመድ ንጉስ እንደገለፁት፤ በዓለማችን 322 ሚሊዮን የሚሆኑ ህዝቦች ድባቴ በተባለው የአዕምሮ ጤና ችግር የሚሰቃዩ ሲሆን በየአራት ሰከንዱም አንድ ሰው ከአዕምሮ ጤና ችግር ጋር በተያያዘ ራሱን ያጠፋል፡፡
በአገራችን ከሚከሰተው የአዕምሮ ጤና ችግር የአብዛኞቹ መነሻ ምክንያቶች የአደንዛዝ እፅ ሱሰኝነት፣ ለተለያዩ አበረታች መድኃኒቶች የመጋለጥ ሁኔታና ከልክ ያለፈ የኢንተርኔት አጠቃቀም እንደሚጠቀሱ ተገልጿል፡፡
የወጣቶች የአዕምሮ ጤና በተለዋዋጭ ዓለም በሚል መርህ፣ ዘንድሮ ለ10ኛ ጊዜ በተከበረው የዓለም የአዕምሮ ጤና ቀን በተለይም በታዳጊ ወጣቶች የአዕምሮ ጤና ላይ ትኩረት በማድረግ፣ ጤናማ ትውልድ ለማፍራት በሚቻልበት ጉዳይ ላይ ትኩረት ተሰጥቶ ሊሰራ እንደሚገባ ተገልጿል፡፡
ህብረተሰቡ በአዕምሮ ጤና ችግሮች ላይ ያለውን ግንዛቤ በማሳደግ፣ በሽታው እንደ ማንኛውም በሽታ ታክሞ ሊድን እንደሚችልና ህክምናውም በአገራችን በብቁ ባለሙያዎች እየተሰጠ እንደሆነ በማወቅ፣ ህሙማኑን ወደ ህክምናው ይዞ መምጣት ይገባዋል ብለዋል- ባለሙያዎቹ፡፡
ወጣቱን ለሴሰኝነትና ለአጉል ባህርያት የሚገፋፉ ነገሮች ላይ መንግስት ትኩረት በማድረግ የወጣቱን ሰብዕናና ስነ ምግባር በተሻለ መንገድ ሊቀርፁ በሚችሉ ስራዎች እንዲተኩ ማድረግ እንደሚገባም ባለሙያዎቹ ጨምረው ገልፀዋል፡፡

Read 5212 times