Monday, 15 October 2018 00:00

ከኢትዮጵያ የሠላም ሀሳብ በስተጀርባ

Written by  ባየህ ኃይሉ ተሠማ bayehhailu@gmail.com
Rate this item
(1 Vote)

                    (የእንግሊዙ ሚኒስትር፤ በኤርትራና በኢትዮጵያ)
                  
    በአፍሪካ ለረጅም ጊዜ የቆየ ነው የሚባልለት በኢትዮጵያ መንግስትና በኤርትራ አማጽያን መካከል ሲደረግ የነበረው ጦርነት፣ በግንቦት ወር 1983 ዓ.ም በኤርትራ ነጻ መውጣት ሲደመደም፣ የሁለቱ አገራት ሕዝቦች መከራ ያበቃ መስሎ ታይቶ ነበር፡፡ ይሁንና በአካባቢው ሠላም ከሰፈነ ገና አሥር ዓመት እንኳ ሳይሞላ፣ ሁለቱ አገሮች በመሬት ይገባኛል ጥያቄ ሳቢያ ሌላ ዙር አዲስ ጦርነት ውስጥ ገቡ፡፡ ይህ ጦርነት በሁለቱም ወገን በአስር ሺዎች የሚቆጠሩ ወጣቶች ክቡር ሕይወት የተገበረለት ከመሆኑም ሌላ ለነዋሪዎች መፈናቀልና ለመሠረተ ልማት መውደም ምክንያት ሆኗል። በወንድማማቾች ሕዝቦች መካከል በተደረገው በዚህ አስከፊ ውጊያ ማግሥት፣ ጦርነትን በዘላቂነት እንደሚያስቆም ተስፋ የተጣለበትን የአልጄርስ የሠላም ስምምነት የሁለቱ አገራት መሪዎች ፈረሙ፡፡
ከአልጄርስ የሠላም ስምምነት ዋንኛ ዓላማዎች አንዱ፣ ለግጭት መንስዔ የሆነውን የሁለቱን አገሮች የመሬት ይገባኛል ጥያቄ በዓለም ዓቀፍ ሕጎች መሠረት መርምሮ፣ የፍርድ ውሣኔ የሚሰጥ የድንበር ኮሚሽን ማቋቋም ነበር፡፡ በዚህም መሠረት የተቋቋመው የኢትዮጵያና ኤርትራ የድንበር ኮሚሽን፣ ከሁለቱም አገሮች የቀረቡለትን ማስረጃዎች ሲመረምር ከቆየ በኋላ በሚያዝያ ወር 1994 ዓ.ም የመጨረሻ ውሳኔውን አሳወቀ። ውሣኔውን የኤርትራ መንግሥት የተቀበለው መሆኑን ገልጾ፣ በአፋጣኝ ተግባራዊ እንዲሆን ሲጠይቅ፣ የኢትዮጵያ መንግሥት በበኩሉ፤ ውሣኔው በመሬት ላይ ያለውን ሁኔታ ያላገናዘበና ኢ-ፍትሃዊ ስለሆነ በሁለቱ አገሮች መካከል ዘላቂ ሰላም የማያመጣ ነው በማለት ሳይቀበለው ቀረ፡፡
ይህን በኢትዮጵያ በአድሎአዊነት የተከሰሰውን የድንበር ኮሚሽን ውሣኔ ለማስፈጸም ባለመቻሉ፣ የሁለቱ አገሮች ድንበር ላይ እንደገና ጦርነት አገርሽቶ የወንድማማች ሕዝቦችን ለእልቂት ሊዳርግ ይችላል የሚል ስጋት እንዲፈጠር ምክንያት ሆኗል፡፡ ኢትዮጵያ የድንበር ኮሚሽኑን ውሣኔ ብትቀበል፣ ለሁለቱ አገሮችና ለቀጣናው ሠላም ጠቀሜታ ያበረክታል ያሉ የውጭ ኃይሎች፣ የኢትዮጵያ መንግሥት ሀሳቡን እንዲቀይር ለማግባባት ጥረት ሲያደርጉ ቆይተዋል፡፡ ከነዚህ ተጠቃሽ ጥረቶች ዋንኛው በእንግሊዝ መንግሥት በኩል የተደረገው ነው፡፡
ይኸውም በቶኒ ብሌር የስልጣን ዘመን፣ በእንግሊዝ የውጭ ጉዳይ መስሪያ ቤት የአፍሪካ ጉዳዮች ሚኒስትር የነበሩት ክሪስ ማሊን፣ ከኤርትራና ከኢትዮጵያ መሪዎች ጋር ያደረጉት ንግግር ከጥረቶቹ አንዱ ነበር። ክሪስ ማሊን የዲፕሎማሲያዊ ተልዕኳቸውን ዓላማ ባሳተሙት ግለ-ማስታወሻ (Diary) ላይ ሲያትቱ፤ ኤርትራና ኢትዮጵያ ወደ ሌላ ዙር የወንድማማች ጦርነት እንዳይገቡ ለመከላከልና ወደ ውይይት ጠረጴዛ ለማምጣት ያለመ እንደ ነበር ጠቁመዋል፡፡ ከዚህ በተጨማሪም በአሥር ሺዎች የሚቆጠሩ ሰዎች ያለቁበት ጦርነት በቆመ ማግሥት፣ የመሬት ይገባኛል ጥያቄው፣ በኢትዮጵያና የኤርትራ የድንበር ኮሚሽን ሲታይ ቆይቶ እንደነበር አስታውሰው፣ የኮሚሽኑ ውሣኔ ግን የተፈለገውን ሠላም አላመጣም ብለዋል፡፡
በሁለቱ አገሮች መካከል ጦርነትም ሆነ ሠላም የሌለበት ሁኔታ ሊፈጠር የቻለው፣ የድንበር ኮሚሽኑ በፈጸመው ስህተት መሆኑን እንደሚያምኑ ክሪስ ማሊን በማስታወሻቸው አስፍረዋል። ይህንንም ሲያስረዱ፤ ‹‹በቅኝ ግዛት ዘመን ውሎች ላይ ተመስርቶ የሁለቱን አገሮች ድንበር በገለልተኝነት እንዲያሰምር ተስፋ የተጣለበት የድንበር ኮሚሽን፤ በመሬት ላይ ያለውን ሐቅ ከግምት ውስጥ ሳያስገባ፤ ለኤርትራ ያደላ ውሳኔ አሳለፈ፡፡ ጦርነቱን የቀሰቀሰችውና ኋላም ሽንፈት የተከናነበችው ኤርትራ፣ በዚህ የድንበር ኮሚሽን ውሳኔ በቀላሉ የሞራል የበላይነትን ለመጎናጸፍ ቻለች›› ብለዋል፡፡
ክሪስ ማሊን ወደ ጠበኞቹ የምሥራቅ አፍሪካ አገሮች የሚያደርጉትን ዲፕሎማሲያዊ ጉዞ የጀመሩት ከኤርትራ ነበር፡፡ አንድ ፓርቲ ብቻ የገነነባት፣ በሕዝቧ ላይ ብርቱ ቁጥጥር የምታደርገውና በቀድሞ ማርክሲስቶች የምትመራው ኤርትራ፣ በአልባኒያ ዓይነት ራስ የመቻል ፍልስፍና የምትመራ በመሆኗ፣ ከማንም የውጭ ኃይል ምክር እንደማትቀበል ክሪስ ሙሊን ገልጸው፣ የኤርትራው መሪ ከአሜሪካ መከላከያ ሚኒስትር ኮሊን ፓውል የተደወለላቸውን ስልክ እንኳን እንዳልተቀበሉት ጠቅሰዋል፡፡ ‹‹ከአሥር ዓመት ወዲህ ኤርትራን ለመጎብኘት የመጀመሪያው የእንግሊዝ ሚኒስትር እንደመሆኔ፣ ፕሬዚዳንት ኢሳያስን ለማነጋገር ስለተፈቀደልኝ ራሴን እንደ እድለኛ እቆጥረዋለሁ›› በማለት አስተያየታቸውን ሰጥተዋል፡፡
ክሪስ ማሊን ከፕሬዚዳንት ኢሳያስ አፈወርቂ ጋር ተገናኝተው የተወያዩት ጥር 6 ቀን 1996 ዓ.ም ምሽት ሲሆን ይህንን አስመልክተው በማስታወሻቸው ሲጽፉም፤ ‹‹ፕሬዚዳንት ኢሳያስ የተቀበሉን ጥርሳቸውን እንደነከሱ ነበር፡፡ የመክፈቻ ንግግራቸው ለድርድር ምንም የማይጋብዝ ሆነብን፡፡ ‹እኔ በኢትዮጵያውያን አልፈርድም፤ የማዝነው በዓለም ዓቀፉ ማህበረሰብ ነው› በማለት አማረሩ፡፡ ሁለት ሠዓት የቆየው ውይይታችን ቀስ በቀስ እየተዝናና የመጣ ቢሆንም፣ አጥጋቢ የሆነ መደምደሚያ ላይ ለመድረስ ግን አልቻልንም። በዚያ የተረገመ የድንበር ኮሚሽን ውሣኔ ሳቢያ ኢሳያስ የሞራል የበላይነት ተቀዳጅተዋል፡፡ ድንበሩን የተመለከተ ውይይት ሲነሳ ማድረግ የሚጠበቅባቸው የድንበር ኮሚሽኑ ውሣኔ ህጋዊና አስገዳጅ መሆኑን መደጋገም ብቻ ነው፡፡ እኛም ከመስማማት በስተቀር ምንም ምርጫ የለንም›› ብለዋል፡፡ ይህ ነው የሚባል የተጨበጠ የሠላም ተስፋ ሳይዙ የኤርትራ ጉብኝታቸውን ያጠናቀቁት ክሪስ ማሊን፤ ቀጣዩ ጉዞዋቸውን ያደረጉት ወደ ኢትዮጵያ ነው፡፡  
ክሪስ ማሊን ጉብኝታቸውን የመዘገቡበት ግለ-ማስታወሻ እንደሚጠቁመው፤ ወደ ኢትዮጵያ ያመሩት ጥር 7 ቀን 1996 ዓ.ም ነበር፡፡ ‹‹ዘጠኝ መቀመጫዎች ባላት ሴሴና አውሮፕላን ከጅቡቲ ተሳፍረን፣ ከሁለት ሠዓት በረራ በኋላ ማምሻውን አዲስ አበባ ገባን። ከአውሮፕላን ማረፊያው በቀጥታ የተጓዝነው ወደ መለስ ዜናዊ ቢሮ ነበር። በጠቅላይ ሚኒስትሩ ቢሮ የነበረው ሁኔታ ለውይይት አመቺ ነበር፡፡ ይሁንና ይዤ የቀረብኩት ሀሳብ፣ ኢትዮጵያ የድንበር ኮሚሽኑን ውሣኔ እንድትቀበል ለማግባባት እንደመሆኑ ሥራው ቀላል አልነበረም›› በማለት የኢትዮጵያ ጉዟቸውን ይዘረዝራሉ፡፡
‹‹ለሁለት ሠዓታት ያህል መለስ ዜናዊን ወጥሬ መያዝ ነበረብኝ፡፡ ለምሣሌ ከኤርትራ ጋር ከሚደረገው ውጊያ የበለጠ ከድህነት ጋር የሚደረገው ጦርነት እንደሚበልጥ ያቀረብኩትን አስተያየት ጠቅላይ ሚኒስትሩ በበጎ ተቀብለውታል፡፡ ‹አሁን የሚያስፈልገው ታላቅ የመሪነት ድርጊት ነው፤ እርስዎ ደግሞ ለዚህ ታላቅ ሥራ የሚያንሱ አይደሉም› ወዘተ እያልኩ የሙገሳ ብልሐትንም ተጠቅሜአለሁ፡፡ መለስ ግን ከአቋማቸው ፍንክችም አላሉ፡፡ እንደ እውነቱ ከሆነ አቋማቸውን የሚያስለውጥ ምን ምክንያት ይኖራል፡፡ አብዛኞቹ አወዛጋቢ የድንበር ቦታዎች በኢትዮጵያውያን ቁጥጥር ስር ናቸው፡፡ ኤርትራ ከጊዜ ወደ ጊዜ እየከሰረች ሲሆን ኢትዮጵያውያን የአሰብን ወደብ ሳይጠቀሙ ለመኖር የሚችሉ መሆናቸው የታወቀ ነው›› ብለዋል፡፡
ክሪስ ማሊን ከአቶ መለስ ዜናዊ ጋር ባደረጉት ውይይት፣ አጥጋቢ መልስ ስለ ማግኘታቸው በማስታወሻቸው የጠቆሙት ነገር የለም። ምናልባት ለአዲሱ የሠላም ጥረት ምላሽ ለመስጠት ጠቅላይ ሚኒስትሩ ጊዜ አስፈልጓቸው ሊሆን ይችላል፡፡ ክሪስ ማሊን ግን ከዚህ ውይይት በኋላ ወደ ሰሜኑ የኢትዮጵያ ክፍል በማቅናት፣ በአዲግራትና በዛላንበሳ ጉብኝት አድርገዋል፡፡ በተለይ በመንግሥታቱ ድርጅት የሠላም አስከባሪ ሕንዳውያን ወታደራዊ መኮንኖች ታጅበው፣ የዛላንበሳን ከተማ በጎበኙበት ወቅት የታዘቡትን በማስታወሻቸው እንዲህ አስፍረውታል፡-
‹‹ኢትዮጵያውያንን ያስገረመ ድንገተኛ ወረራ ያካሄዱት የኤርትራ ወታደሮች የዛላንበሳ ከተማን የተቆጣጠሩት ያለ ምንም ውጊያ ነው፡፡ ከተማዋን የሚለቁበት የቁርጥ ቀን ሲመጣ በከተማዋ የሚገኙ ህንጻዎችን - ትምህርት ቤትና ቤተ ክርስቲያን እንኳ ሳይቀር - በፈንጂ አወደሙ፡፡ ዛሬ ነዋሪዎቹ ሕይወታቸውን የሚገፉት በፈራረሱት ሕንጻዎች ውስጥ ነው፡፡ ልብ የሚሰብር ትዕይንት ነው። ኢትዮጵያውያን ጉዳዩን በእርቅ ለመፍታት አለመፍቀዳቸው የሚያስገርም አይደለም፡፡ ኢሳያስን ወይም ባለሥልጣኖቻቸውን እንደገና ባገኛቸው ከተማዋ እንድትወድም ማን ትዕዛዝ እንደሰጠ እና ለምን ትዕዛዝ እንደሰጠ እጠይቅ ነበር›› ብለዋል፡፡
ክሪስ ማሊን በኢትዮጵያ ያደረጉትን የሶስት ቀናት ጉብኝት አጠናቀው ወደ ብሪታንያ የተመለሱት ጥር 10 ቀን 1996 ዓ.ም ነበር፡፡ ከዚህ ጊዜ በኋላ ግለ-ማስታወሻቸው ኢትዮጵያና ኤርትራን ለቀጣዮቹ አሥር ወራት ሳይጠቅስ ይቆያል፡፡ የኢትዮጵያ ስም በማስታወሻቸው ገጽ ላይ ለሁለተኛ ጊዜ የሚታየው ጥቅምት 18 ቀን 1997 ዓ.ም ነው፡፡ በዚህ እለት አቶ መለስ ዜናዊ ባደረጉላቸው ጥሪ ወደ አዲስ አበባ እንደሄዱ፤ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትሩ አቶ ሥዩም መሥፍን በተገኙበት ከጠቅላይ ሚኒስትሩ ጋር የተወያዩ መሆኑን ማስታወሻቸው ይጠቁማል፡፡
‹‹መለስ ከወራት በፊት እንዲቀበሉት ስገፋፋቸው የነበረውን የኢትዮ-ኤርትራ የድንበር ኮሚሽን ውሣኔ ለመቀበል መዘጋጀታቸውን በመግለጽ አስደነቁኝ፡፡ ‹‹ግሩም ነው፤ ግን ውሣኔውን እንዲቀበሉ የሚያሳምን ምን ነገር አገኙ ?›› ስል ጠየቅኳቸው፤ ‹እርስዎ ነዎት› አሉኝ። በበኩሌ ይህ አነጋገራቸው እውነት መሆኑ ያጠራጥረኛል፡፡ ተመሳሳይ ጫና በአስተዳደራቸው ላይ ያሳረፉ ሌሎች ኃይሎች ይኖሩ ይሆናል። ምናልባት በኮሚሽኑ ውሣኔ የተነሳ በኤርትራ የተያዘውን የሞራል የበላይነት ኢትዮጵያ የራሷ ለማድረግ መጣጣር አለባት በማለት በተደጋጋሚ ያደረግኩት ውትወታ የራሱን አስተዋጽኦ አድርጎም ሊሆን ይችላል፡፡
‹‹በአዲሱ የመለስ የሠላም ሀሳብ መሰረት፣ ኢትዮጵያ፣ የኢትዮ-ኤርትራ የድንበር ኮሚሽን ውሳኔን በመርህ ደረጃ ትቀበላለች፣ ያለባትን ውዝፍ ዕዳ ለኮሚሽኑ ትከፍላለች እንዲሁም ድንበሩን በመሬት ላይ ለሚያሰምረው ኮሚሽን አገናኝ መኮንኖችን ትመድባለች››
‹‹መለስ የሠላም ሀሳቡን ይፋ ከማድረጋቸው በፊት የፓርቲያቸውን ሥራ አስፈጻሚ ኮሚቴ እና ፓርላማውን ማሳመን እንደሚገባ ገልጸውልኛል። የሠላም ሀሳቡ ተወዳጅ እንደማይሆን አውቀዋል፤ ሆኖም ተቀባይነት እንዲያገኝ ማድረግ እንደሚችሉ እርግጠኛ ናቸው። የሠላም ሀሳቡን በሚቀጥለው ወር አጋማሽ ለሕዝብ ለመግለጽ ተስፋ አድርገዋል፡፡ እስከዚያው ድረስ ግን ጉዳዩን በምሥጢር እንድንይዘው ጠይቀውናል። የሠላም ሀሳቡን ኢሳያስ እንደማይቀበሉት መለስ ቅንጣት ታክል ጥርጣሬ አልነበራቸውም፡፡ ይሁንና ሠላም የናፈቀው የኤርትራ ሕዝብ የተለየ አስተያየት ሊኖረው እንደሚችል ያምናሉ››
አቶ መለስ ዜናዊ የሠላም ሀሳቡን ከፓርቲዬ ስራ አስፈጻሚ ኮሚቴ ጋር እወያይበታለሁ ባሉት መሰረት፣ ጉዳዩ ለውይይት መቅረቡን ሕዳር 5 ቀን 1997 ዓ.ም ታትሞ የወጣው አዲስ ዘመን ሲያትት፤ ‹‹የኢህአዴግ ሥራ አስፈጻሚ ኮሚቴ በቀረበለት ሪፖርት ላይ በመመስረት የኢትዮ-ኤርትራ ጉዳይ ላይ የተወያየ ሲሆን፤ በዚህም መንግሥት ሰላምን ለማረጋገጥ እያደረገ ያለውን ጥረት ወደፊትም በይበልጥ እንዲያጠናክር ወስኗል›› በማለት ገልጾ ነበር፡፡
የሚኒስትሮች ምክር ቤት በበኩሉ ሕዳር 15 ቀን 1997 ዓ.ም ባደረገው ስብሰባ፤ በኢትዮጵያና በኤርትራ መካከል ያለውን አለመግባባት ለመፍታት የሚያስችል ‹‹አዲስ ዘላቂ የሠላም ሀሳብ›› ማጽደቁን ለአዲስ ዘመን ጋዜጣ በላከው መግለጫ አስታውቆ፣ ውሣኔው ጠቅላይ ሚኒስትሩ በተገኙበት ለሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት እንደሚቀርብ ጠቁሟል፡፡
የክሪስ ማሊን ጉብኝት ከተገባደደ ልክ ከአንድ ወር በኋላ፤ አቶ መለስ ዜናዊ ‹‹ባለ አምስት ነጥብ የሠላም ሀሳብ›› የተባለውን አዲስ ውሳኔ ለሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አቀረቡ፡፡ ምክር ቤቱ በሠላም ሀሳቡ ላይ በተወያየበት ወቅት ጠቅላይ ሚኒስትሩ የኮሚሽኑ ውሣኔ ኢ-ፍትሐዊ እና ፍርደ ገምድል መሆኑን መንግሥት እንደሚያምን ጠቁመው፤ ለሁለቱ አገሮች ሠላምን ከማስፈን የሚበልጥ ነገር እንደሌለ በመገንዘብ ውሣኔውን ለመቀበል እንደተቻለ ገልጸው ነበር፡፡
በተጨማሪም ጠቅላይ ሚኒስትሩ፤ ኢትዮጵያ የድንበር ኮሚሽኑን ውሣኔ እንድትቀበል እሳቸው ‹‹ወዳጆች›› ካሏቸው ወገኖች የቀረበ ጫና መኖሩን አልሸሸጉም፡፡ ‹‹ከአንዳንድ ወዳጆች ጋር በዚህ ጉዳይ ላይ ውይይት ተደርጓል፡፡ እነዚህ ወዳጆች ኢትዮጵያ የፍርድ ቤቱን ውሳኔ በመርህ ደረጃም ቢሆን የተቃወመች መስላ መታየቷ ለሠላም እንቅፋት ነው። ቢያንስ ይህ ቢስተካከል ለሰላም የተመቸ ሁኔታ ሊፈጥር ይችላል የሚል አስተያየት በተደጋጋሚ ብዙ ወዳጆች ሲገልጹልን ቆይተዋል። በኛ ግምት አሁን የወሰድነው የአቋም ማስተካከያ የነዚህ ወዳጆቻችንን ጥያቄና አስተያየት በአግባቡ እንደሚያስተናግድ ይገነዘባሉ ብለን እንገምታለን›› በማለት ለምክር ቤቱ ተናግረው ነበር፡፡
በኢትዮጵያና በኤርትራ መካከል ያለውን አለመግባባት ለመፍታት ይረዳል ተብሎ በጠቅላይ ሚኒስትር መለስ ዜናዊ የቀረበውን ይህን ባለ አምስት ነጥብ የሠላም ሀሳብ፤ የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አባላት በ10 ተቃውሞና በሶስት ድምጸ ተዐቅቦ አጽድቆት ነበር፡፡
ይህ የክሪስ ማሊን ማስታወሻ እንደ ልብ የማይገኘውን ከአገር መሪዎች ጋር የሚደረግ ምሥጢራዊ ዲፕሎማሲያዊ ንግግር ምን እንደሚመስል በመጠኑ ያሳየን ከመሆኑም በላይ የኢትዮጵያ መሪዎችም ከአገሪቱ ዘላቂ ጥቅምና ጎረቤታዊ ወንድማማችነት ይበልጥ የኃያላን መንግሥታት ጫና ይበልጥ ያሳስባቸው እንደነበረ የሚያሳይ ነው፡፡ ከዚህም ሌላ የሠላም ሀሳቡ አገር በቀል ሳይሆን የራሳቸውን ብሔራዊ ጥቅም አስልተው ከሚንቀሳቀሱ የውጭ ኃይሎች ዲፕሎማሲያዊ ጫና የመጣ በመሆኑ ለስኬታማነቱ በኢትዮጵያ መሪዎች በኩል ከልብ የተሰራበት አይመስልም፡፡ በመጨረሻም ይህ ከአንገት በላይ የሆነ የሠላም ውሳኔ፣ የሀሳቡን የውጭ መሀንዲሶች ለጊዜው ከማስደሰት ያለፈ እውነተኛ ዘላቂ ሠላም ለማምጣት ምንም ፋይዳ እንደሌለው ታይቷል፡፡
ከኤርትራ ጋር ለሃያ አመታት ተበላሽቶ የቆየው ግንኙነት በአጭር ጊዜ ውስጥ ሊሻሻል የቻለው፣ በአንድ በኩል፤ በኢትዮጵያ ወገን ከቂም በቀል ርቆ፣ በሀገር ፍቅር ታጅቦና በቅን ልቦና ተመርቶ በእውነተኛ የወንድማማችነት መንፈስ የሚሰራ መሪ ወደ ሥልጣን በመምጣቱ ሲሆን፣ በሌላ በኩል ደግሞ የእርቅ ጥረቱ ተነሳሽነት የውጭ ኃይሎች ጫና የወለደው ሳይሆን ከቅን የወንድማማችነት ስሜት የመነጨና ቤት ያፈራው እውነተኛ ጥረት በመሆኑ፣ በኤርትራ በኩል አዎንታዊ ምላሽ ለማስገኘት እንደቻለ ይታመናል፡፡


Read 5265 times Last modified on Saturday, 13 October 2018 11:47