Print this page
Saturday, 13 October 2018 11:01

መረገም የሚመስል መባረክ!

Written by  አብይ ተስፋዬ አሳልፍ (አተአ)
Rate this item
(11 votes)

 ስለታመሙ፣ ስለደከሙ፣  ሞተው ስለተቀበሩ
አገር ጥለው ስለጠፉ፣ በየበረሃውም ነፍሳቸውን
ስለገበሩ፡፡
(ብቻም ሳይሆን፣ ስለ ራሳችሁም ጸልዩ!)
*   *   *
አዲስ አበባ … /እኛ ሰፈር/
ከስድስት አመት በፊት፣ አንድ ዕለት እንደተለመደው ሲኒማ ገብቼ ስመለስ  አንደኛው ጓደኛዬ ድንገት ጠራኝና እንዲህ አለኝ፤ ‹‹…እኛ ብሩን አግኝተናል አንተ ብቻ ነህ የቀረኸው፡፡ ታውቆሃል አልዓዛር! … ወደ ኋላ እየመለስከን ነው፡፡ ደላላው እያዋከበን ነው፣ ካልሄድክ ንገረንና…›› አቋርጦ በሚቅለበለቡ ዓይኖቹ መሬት መሬት እየቃበዘ፣ ፀጉሩን ያክ ጀመር፡፡
ለሰከንዶች ተከዝኩና የጀመረውን አረፍተ ነገር ጨረስኩለት … ‹‹እኛ እንሂድ ነው?››  በቀስታ ራሱን በአዎንታ አነቃነቀ፡፡ አዎ እኛ እንሒድ! መሆኑ ነው። በተስፋ መቁረጥ እየተናጥኩ በቀስታ ወደ ቤቴ አዘገምኩ፡፡
ለነገሩማ መጀመሪያ አብረን ነበር ልንጠፋ የተነጋገርነው፡፡ አራት የሰፈራችን ስራ አጥ ጎረምሶች፤ ጥቂት ብሮችን አጠረቃቅመን በሊቢያ አድርገን  አውሮፓ ለመግባት ነበር ዕቅዱ፡፡  ለጉብኝት ያይደለ፣ ህይወት ለማሻሻል መሰደድ! ነበር ንግግሩ፡፡
ሁላችንም ቆራጦች ነበርን፣ እኔ ዱዲ አልነበረኝም፣ ለነገሩማ እነርሱም አልነበራቸውም፡፡ እነርሱ (ሶስቱ) ጥቂት ማምታት አድርገው አሁን የሚፈልጉትን ገንዘብ አግኝተዋል፡፡  … እኔ ብወጣ ብወርድ፣  … ባስብ ባስብ፣ … ምንም ማግኘት አቃተኝ፡፡ በነዚያ ቀናት ጭንቀት ይዞኝ ነበር፣ እህል መብላት ቀነስኩ፣ ቀስ እያለ ወዜ ከፊቴ ላይ ተነነ፡፡ ምንም ነገር ማድረግ ባለመቻሌ፣ ጥለውኝ እንደሚሄዱ አወቅሁ፡፡ ከእናቴ እንኳ የሚሰረቅ ጌጣጌጥ አጣሁ፡፡ የቀሯትን ጥቂት የጆሮ ላይ ተለጣፊ ወርቆች እኔ የተመረቅሁ ግዜ ሸጣ ጨርሳ ነበርና የገንዘብ ምንጮቼን ሁሉ ነጥፈዋል፡፡
ጓደኞቼ ገንዘቡን እንዴት አገኙ! …
ከሶስቱ ወዳጆች መሃል አንዱ በሰፈር ውስጥ ይበልጥ ታማኝ ነበር፡፡ ቤተሰቦቹም የተከበሩ ናቸው። ከእኔ ጋር አብረን ከዩንቨርሲቲ ሲቪል ምህንድስና ተመርቀናል፡፡ ታዲያ ይህ የመጥፋት ሃሳብ ከመጣ በኋላ (*) … አንድ ዕለት ቢራና ለስላሳ መጠጥ ወደሚያከፋፍለው የሰፈራችን ሀብታም ነጋዴ መጋዘን ብቅ አለና የማከፋፈል ስራ በትንሽ በትንሹ ለመጀመር እንደሚፈልግ፣ ነገር ግን ገንዘብ እንደሌለውና ጥቂት ጥቂት ዱቤ እንዲፈቅድለት ጠየቀው፡፡ እናም ልጁንና ቤተሰቡን በደንብ ስለሚያውቅ ፈቀደለት። የመጀመሪያው የገንዘብ ማግኛ ስልት የተጀመረው እንዲህ ነበር፡፡
(*) … (የመሰደድ ሃሳቡን ያመጣው አንደኛው ጓደኛችን ነው፡፡ ከሰፈራችን ድድ ማስጫ አንድ ማታ ተሰብስበን ሁለቱ ኒያላቸውን እየፈገሙ እያለ … ድንገት ከመሃላችን ቆመና እንዲህ አለ ‹‹...ለምን ጣልያን አንሔድም! የሚሸኘን ደላላ አግኝቻለሁ፡፡ እስኪ እነ ሮቤልን ተመልከቷቸው! በወራት እዚያ ደርሰው አመት ሳይሞላቸው አሳይለም ጠይቀው አሁን ጭራሽ ቤተሰብ ሁሉ መርዳት ጀምረዋል፣ እኛ ግን ከየዩንቨርሲቲው ወጥተን ተመልሰን ሰፈር ውስጥ ስኳርና ቡና ለእናቶቻችን መላላክ ጀምረናል፣ የሚያስፈልገንኮ ጥቂት መላ ብቻ ነው … እንዲያው እዚያ ሄደን በርትተን ከሰራን አገራችን ተመልሰን የመስራት ዕድል ይኖረናል፣ በዚሁ ከቀጠልን ግን ለአመታት ከሰፈራችን ድንጋይ ላይ ከመቀመጥ ውጪ ምንም አንቀጥልም … (ምናምን ምናምን … ሁለት ሰዓት የፈጀ ክርክርና በመጨረሻም መስማማት ተደረገ!) …  (ጥቂት የተባለው  ገንዘብ በኋላ ሲታይ እጅግ ብዙ ነበር!) ››)
*   *   *
አንድ ዕለት ስራ ፈትቼ እያዛጋሁ ኢንተርኔት ቤት ገባሁና የሆነ አነቃቂና አበረታች ታሪኮች እያሰስኩ ሳነብ እንዲህ የሚል ታሪክ አገኘሁ፡፡
ጋሽ ክላርክ ቤተሰብ ውስጥ እንዲህ ሆኖ ነበር …
ከአመታት በፊት፡፡ የአባባ ክላርክ ቤተሰብ ከቀናት በኋላ ከሳውዝሃምፕተን ወደ ኒውዮርክ ለሚያደርገው ጉዞ በጉጉት ተሞልቷል፡፡ አቶ ክላርክና ባለቤቱ ለብዙ ጊዜ ሰርተውና ቆጥበው እንዲሁም ጥቂት ብድር አክለውበት የሚፈልጉት የገንዘብ መጠን ላይ ደርሰው ነበር፡፡ ከዘጠኝ ልጆቻቸው ጋር ታላቅና የህይወት ዘመን ጉዞ ሊያደርጉ አስበው ሲያቅዱ የነበረው ለአመታት ነበር፡፡ ገንዘቡን ቆጥበው፣ ከዚያ ፓስፖርትና ፈቃድ አግኝተው፣በተቀናጣችው መርከብ አሜሪካ ለመግባት ሲዘጋጁ አመታት ወስዶባቸው ነበር፡፡
መላው ቤተሰብ ጉጉት ሰቅዞ ይዞታል፡፡ ለጉዞው መጀመር ጥቂት ቀናት ሲቀሩት ግን አዲስ ነገር ተፈጠረ። ትንሹ ልጃቸው ከመስኩ ላይ እየተጫወተ እያለ፣ በሰፈራቸው ድንገት የተከሰተ አንድ ወስላታ ውሻ ቂጡ ላይ ገመጠው፡፡ ቤተሰቡ ተደናግጠው ሃኪም ጠሩ፡፡ ሃኪሙ አየው፡፡ ቁስሉንም ጠራረገና ሰፋው፡፡ በርግጥ ቁስሉ ትንሽ ቢመስልም አሳሳቢ ነበር። እናም ስራውን አጠናቆ ሲወጣ የተለመደውን ቢጫ ካርድ ከቤታቸው በር ጉበን ላይ ሰቀለ፡፡ ይህ ቢጫ ካርድ ማለት ለኳረንቲን የተለየ ቤተሰብ ማለት ነበር፡፡ ምናልባት የእብድ ውሻ በሽታ ሊኖር ስለሚችል ለ14 ቀናት ከሃኪሙ በቀር ማንንም ሳይገናኙ ይከርማሉ ማለት ነው፡፡ ጠባቂም ይመደብባቸዋል፡፡ ጋሽ ክላርክ ይህንን ሲያዩ ከወለሉ ምንጣፍ ላይ እየተንከባለሉ ልክ እንደ ህጻን ያለቅሱ ጀመር፡፡
*   *   *
… እኛ ሰፈር …
የጉዞው ነገር ከወሬ አልፎ እዚህ ከመድረሱና ከመጠናቀቁ ከጥቂት ወራት በፊት፣ ጓደኛዬ አቢካ መጠጦቹን በዱቤ እየወሰደ ማዞር ጀመረ፣ የሚገርመው ያልታሰበ አዲስ ስራ ቢሆንም በሚገርም ሁኔታ አዋጭ ነበር፡፡ በጥቂት ሳምንታት ውስጥ ጎበዝ ነጋዴ ሆነ። መጀመሪያ በአንድና በሁለት ሺ ተጀመረ፤ ቀጥሎ የአምስት ሺ ወስዶ ሸጠና መለሰ፣ ቀጥሎ የአስር ሺ ወሰደ፣ ብድሩን መለሰ…፣ ሃያ ሺ፣ ሰላሳ ሺ …. ሃምሳ ሺ …. በሁለት ወር ውስጥ እጅግ ተሻሻለ፣ የሚያከፋፍለበት ስፍራ ሰፋ፣ የሚገፉ ጥቂት ጋሪዎችን ጨመረ፣ ሸቃዮች ቀጠረ፡፡ ታዲያ አንድ ቀን ቁጭ ብለን ስናወራ፤ ይህንን ስራ እኔም ልሳተፍበትና ከምራችን ብንቀጥለውስ ስል አወያየሁት፡፡
(ቆንጆ ስራ ከጀመርን ስደት ምን ያስፈልገናል ስል አስቤ ነበር፡፡ … ጨነቀው፡፡ ጓደኞቼስ! ሲል አሰበ፡፡ የተነጋገሩበትን ለመተውና ኢንጂነሪንግ ተመርቆ እያለ እንዲህ ዝቅ ያለ ስራ እየሰራ መቀጠሉ ከበደውና በጋራ በተስማሙበት መሰረት መቀጠሉን መረጠ፡፡ ይቅርብኝ! ሲል መለሰልኝ፡፡)
ሶስቱ የተስማሙበት ነገር ቀላል ነበር፡፡ እየተበደረ በመክፈል በእርሱና በሰውየው መሃል ለወራት ጠበቅ ያለ መተማመን መገንባት፡፡ በመቀጠል ያሰቡት ገንዘብ ላይ ሲደርሱ፣ የመጨረሻውን ገንዘብ ሰብስበው  መጥፋት፡፡  እናም አሁን ይኸው ስምንት ወራትን ከሰሩ በኋላ ከሚፈልጉት ገንዘብ ላይ ደርሰዋል ማለት ነው! ‹እኛ አግኝተናል!› ሲሉ አወጁልኝ፡፡  
*   *   *
እናም የጋሽ ክላርክን ታሪክ የቀጠልኩ ዕለት እንዲህ ነበር የሆነው፡፡ … /ጋሽ ክላርክ ቤተሰብ ውስጥ…/
የመላው ቤተሰብ ህልም መርፌ እንደጠነቆለው ፊኛ ተንፍሶ ነበር፡፡ ልጆቹ አለቀሱ፣ ትልልቆቹ አማረሩ፣ እንደ ህጻን ተንሰቀሰቁ፡፡ የኒው ዮርክ! ጉብኝት ህልማቸውና የቅንጦት ጉዟቸው ተሰረዘ፡፡ ኪሳራቸውን እየቆጠሩ ተከዙ፡፡ ይህ በተከሰተ በቀናት ውስጥ አባትየው ከበረንዳ ላይ ተቀምጦ እያለ … ከሩቅ፣ ከወደቡ አጠገብ መርከቧ ጉዞዋን ስትጀምር ተመለከተ። በድጋሚ ቤተሰብ እንደሞተበት ሰው ተንሰቀሰቀ፡፡ የህይወት ዘመን መልካም ሽልማት ያለውን ጉብኝት አጣው:: ትንሹን ልጁንና አምላኩን ረገመ፡፡
በቤታቸው እንደታሰሩ መርከቢቱ የነሱን ወደብ ለቃ በሄደች በጥቂት ቀናት ግን ሌላ ዜና መላውን ዓለም አናወጠ፡፡ ግዙፏ፣ የማትሰጥምና የማትነቃነቅ የምትስለው ቅምጥሏ ታይታኒክ፤ ያንን ሁሉ ህይወት ተሸክማ ሰመጠች፡፡ የክላርክ ቤተሰብ በዚያ ልጅና በዚያ ምንዱብ ውሻ ንክሻ ባይሆን ኖሮ አሰቃቂ እልቂት ውስጥ ይደመሩ ነበር፡፡ ጋሽ ክላርክ ዜናውን እንደሰማ ደነዘዘ፡፡ መረገም የሚመስል መባረክ እንደሚኖር አልጠረጠረም ነበር፡፡ ተንደርድሮ ወደ ቤቱ ገባና ትንሹን ልጁን አቅፎ አለቀሰ፡፡
እናም ወደ ሰማያት አንጋጦ እንዲህ አለ! ‹‹አምላኬ … መረገም በሚመስል መባረክ ውስጥ ስላሳለፍከኝ አመሰግናለሁ!››
*   *   *
… እኛ ሰፈር …
ወዳጆቼ አንድ ማለዳ ጠፉ፡፡ ብቻዬን ቀረሁ፡፡ ገንዘቡን በማጣቴ ከስደተኞቹ ጓደኞቼ ጎድዬ ስለነበር አለቀስኩ፡፡ ቤተሰብ ሁሉ ሲተራመስና እኔን በጥያቄ ሲያዋክብ ሰነበተ፡፡ አላውቅም ስል ካድኩ፡፡ ከሳምንት በኋላ ከጠረፍ ላይ ደውለው መጥፋታቸውን አሳወቁና ገላገሉኝ፡፡ አላውቅም ብልም ያኮረፉኝ ቤተሰቦች አልጠፉም፡፡ አስታውሳለሁ … እኔ እድሌን፣ ድህነቴን፣ ሀሳብ ለመቀየርና ለመወሰን መቸገሬን እያማረርኩ፣ ከአልጋዬ ላይ ተጋድሜ ለቀናት አነባሁ፡፡
ቀናት ነጎዱ፣ እዚህ ህይወት ትንቅንቅ ሆነ፡፡ ይመስገነው ብለን ጥቂት እየሰራን መዋል ጀመርን፡፡ የጓደኞቼ ቤተሰቦች ግን ለሳምንታት፣ ለወራት፣ አሁን ደግሞ ለአመታት አንዲት ቃል ከልጆቻቸው አጡ፤ የመጨረሻ ድምፃቸው የተሰማው ከጠረፍ ነበር፡፡ እናም ስድስት አመት የስደተኛ ወዳጆቼ ድምፅ ጠፋ፡፡
ዛሬ ….
ስድስት አመት አለፈ … ወዳጆቼ የት እንደገቡ አልተሰማም፡፡ መረገምም ይሁን መባረክም አልታወቀም፡፡ ማን እንደተረገመና ማን እንደተባረከ አልተለየም፡፡
ከቀናት በፊት በህይወቴ በጣም በመማረሬ የተነሳ በተበሳጨሁበት እለት፣ ከእናቴ ጋር ቁጭ ብዬ ቡና እየጠጣሁ ከአንድ መፅሃፍ ውስጥ የሚገኝ የአለም ካርታ አጠናለሁ፡፡ በስድስት አመታት ዱብዱብ ውስጥ ጥቂት ጥሪት ስላጠራቀምኩ ልቤ ተነሳስቶ ነበር፡፡ በተለይ የጓደኞቼ ድምፅ ከተሰማ፣ ለእኔ የመጨረሻው ፊሽካ ይሆናል ብዬ ወስኜ ነበር፡፡ እናም ካርታውን እያጠናሁ ነበር … ጠረፉ እዚ ጋ! (…ወታደሮችና ጠባቂዎች ይኖራሉ!)  ከዚያ ሱዳን፣ ደግሞ በዚህ በኩል ከሆነ በርሃ አለ (ቆዳን እንደ ደራጎን ምላስ የሚልስ እሳት የሆነ ንዳድ … ቃጠሎ … ሃሩር … አሸዋ … ይኖራል)፣ ደግሞ ግብፅ ምናምን ወይ ደግሞ በዚያ በኩል ሊቢያ (እንደ እንሰሳ የሚቆጥሩን ሰዎች እዚያ አሉ!)፣ ከዚያ ውቅያኖስ … (እጅግ ቀዝቃዛና ጨዋማ ውሃ! ስንት ወገኖቻችንን የበላ!) … ከዚያ አውሮፓ …. ከዚያ …. እያልኩ በሃሳቤ እስላለሁ፡፡
እናቴ ቡናዋን ስኒዋ ላይ እያንቆረቆረች እንዲህ አለችኝ … ‹‹ጌታ! … እንዲያው አንድ የሚገርመኝ ነገር ሁልጊዜ እጠይቅሃለሁ እያልኩ ስተወው አመታት ነጎዱ … ልጠይቅህ እስቲ፡፡ ከሶስቱ ጓደኞችህ ጋር ሚስጥረኞችና በጣም ቅርብ እንደሆናችሁ አውቃለሁ፣ ታዲያ እንዴት ከጓደኞችህ ተለይተህ ቀረህ! … እኔ መቼም ሁሌም አስበዋለሁ፡፡ ገርሞኛል! … የኔ መድሃኒያዓለም እኔን ብቻ የፈጠረ ያህል ይሰማኛል። እዚህ ብቻዬን በዚህ እድሜዬ ጥለኸኝ ብትሄድ፣ ይሄኔ ማን ጎንበስ ቀና እያደረገ ያስታምመኝ ነበር። ማንስ ይንከባከበኝና ይጦረኝ ነበር፡፡ አቤት ጌታዬ! ይወደኛልኮ… !››
ሳቅ ብዬ ነገሩን ጥቂት አሰብኩትና እንዲህ አልኳት፤ ‹‹…የመድሐኒዓለም ስራ ነው!…›› ሁለታችንም ሳቅን፡፡ (…የምደብቀው ነገር እንዳለ ይገባታልና ነው…)
እኔ ግን ልቤ ግማሽ መንገዱን (እዚሁ የመቆየትና ያለመቆየት ቀዩን መስመር!) አልፎ ነበር፡፡ ያንን የመረገም /የመባረክ/ መንገድ ሊጀምር ተነሳስቶም ነበር፡፡ አሮጊት እናቴን ሳስባት፣ ያለውንና የምሰራውን ነገር የምወደው ቢሆንም (ገቢ ስለሚያስገኝ!…) እርካታና ደስታ የሚባል ነገር ከልቤ ውስጥ ተነቅሎ ከጠፋ አመታት አልፈዋል፡፡ የሲቪል መሃንዲስ ሆኜ ስጨርስ አገሬ ሺዎችን በሚይዝ አዳራሽ ውስጥ፣ ትላልቅ ባለስልጣን አምጥታ ያስመረቀችኝ ቢሆንም … አሁን ግን ላዳ ታክሲ በጨረቃ መንዳት ከጀመርኩ ሁለት አመት አልፎኛል፡፡ እናም እናቴንና እኔን ማኖር ችያለሁና ተመስገን ነው፡፡
ሁልጊዜ በእረፍት ቀኔ ከአምልኮ ቦታ ቆሜ ፈጣሪዬን ሳመሰግን እንዲህ እላለሁ፤ … ‹አምላክ ግን ይወደኛል! … መረገም በሚመስል መባረክ ውስጥም ያሳልፈኛል፤ ያኖረኛል!›


Read 3296 times