Sunday, 14 October 2018 00:00

የአፍሪካ እንስሳት ሀብት ኤግዚቢሽን የኢትዮ ፓልተሪ ኤክስፖ በሚቀጥለው ሳምንት ይካሄዳል

Written by  መንግስቱ አበበ
Rate this item
(3 votes)

 4ኛው የአፍሪካ እንስሳት ሀብት አውደ ርዕይና ጉባኤ፣ እንዲሁም 8ኛው የኢትዮ ፖልተሪ ኤክስፖ በሚቀጥለው ሳምንት ከጥቅምት 8-10 ቀን 2011 በሚሊኒየም አዳራሽ ይካሄዳል፡፡
ኤግዚቢሽኑን አስመልክቶ ከትናንት በስቲያ በጁፒተር ሆቴል በተሰጠው ጋዜጣዊ መግለጫ፣ ከ13 ሀገራት የተውጣጡ ከ60 በላይ ኩባንያዎች ምርቶቻቸውንና ዘርፉ የደረሰበትን የቴክኖሎጂ ውጤቶች የሚያቀርቡ ሲሆን ከ5 ሺህ በሚበልጡ ባለድርሻ አካላት እንደሚጎበኝም ተገምቷል፡፡
የንግድ ትርዒቶችን በማዘጋጀት በሚታወቀው ፕራና ኤቨንትስና መቀመጫውን ሱዳን ባደረገው ኤክስፖ ቲም በጋራ ባዘጋጁትና ለ3 ቀናት በሚቆየው 4ኛው ዓለም አቀፍ የእንስሳት ሀብት ተዋጽኦና በ8ኛው የዶሮ አውደ ርዕይ ላይ፣ ከቤልጂየም፣ ቻይና፣ ኢትዮጵያ፣ ጀርመን፣ ሀንጋሪ፣ ሕንድ፣ ኢጣሊያ፣ ዮርዳኖስ፣ ኔዘርላንድስ፣ ፓኪስታን፣ ስፔይን፣ ሱዳንና አሜሪካ የሚመጡ ዓለም አቀፍ የዘርፉ መሪዎች የሚሳተፉ ሲሆን ዓላማውም በቴክኖሎጂ ሽግግር ላይ የተመሰረተ የእውቀት ሽግግር፣ የንግድ ልውውጥና የገበያ ትስስር መፍጠር ነው ተብሏል ፡፡
ይህ አውደ ርዕይ በግብርናና እንስሳት ሀብት ሚ/ር፣ በኢንዱስትሪ ሚ/ር፣ በኢትዮጵያ ሥጋና ወተት ኢንዱስትሪ ልማት ኢንስቲትዩት፣ በእንስሳት መድኃኒትና መኖ አስተዳደርና ቁጥጥር ባለስልጣን የሚደገፍ ሲሆን፣  የአሜሪካ ዕርዳታ ድርጅት ፊድ ዘ ፊውቸር ጋር የኢትዮጵያ ፕሮጀክት፣ የኢትዮጵያ ኔዘርላንድስ ንግድ ለግብርና ዕድገት ፕሮግራምና የኔዘርንድስ የአፍሪካ ንግድ ካውንስል እውቅና እንደተቸረው ተገልጿል፡፡
በመግለጫው ወቅት በኢትዮጵያ የእንስሳት ውጤቶች ፍላጎት በከፍተኛ ፍጥነት እያደገ ቢመጣም የምርት መጠኑ ይህንን ፍላጎት ማሟላት የሚያስችል ዕድገት እንዳልታየበት የተገለፀ ሲሆን፣ ኢትዮጵያ፣ በቁም እንስሳት ሀብት ብዛት ከአፍሪካ አንደኛ፣ ለዶሮ እርባታ ተስማሚ የአየር ንብረት ቢኖራትም፣ የዜጎችዋ ነፍስ ወከፍ የእንስሳት ተዋጽኦ ተጠቃሚነት እጅግ ዝቅተኛ ነው ተብላል፡፡
በዚህና በሌሎች ምክንያቶች፣ በዘርፉ ላይ ከፍተኛ መዋዕለ ንዋይ ቢፈስ የተሻለ ዕድገት መኖሩን በመገንዘብ፣ መንግሥት፣ የድህነት ቅነሳን፣ የምግብ ዋስትናን ማረጋገጥ፣ ለኢኮኖሚያዊ ዕድገት አስተዋጽኦ ያለውን ፋይዳ በመገንዘብ፣ ከዘርፉ የሚገኘውን የውጭ ምንዛሪን ከፍ ለማድረግ፣ የአካባቢ ብክለትን ለመቀነስ ግብ አድርጎ፣ ለቁም እንስሳትና ለዶሮ እርባታ፣ እንዲሁም ለእንስሳት ተዋጽኦ ዘርፍ ልማት ትልቅ ትኩረት ሰጥቶ እየሰራ መሆኑ ተመልክቷል፡፡
ከአገራችን ወጣ ብለን የአፍሪካን ገበያ ስንቃኝ፣ እኤአ በ2050 የአፍሪካውያን ዓመታዊ የወተት ፍጆታ 83 ሚሊዮን ቶን፣ የሥጋ ፍጆታ 13.5 ሚሊዮን ቶን፣ የዶሮ ሥጋ ፍላጎት 11.8 ሚሊዮን ቶን እንደሚደርስ የተገመተ ሲሆን፣ የእንቁላል ፍጆታ 6.1፣ የፍየል 3.5 የበግ 5.9 ሚሊዮን ቶን እንደሚደርስ የተለያዩ ጥናቶች እንደሚያመለክቱ ተገልጿል፡፡
በመጪዎቹ 10 ዓመታት የእንስሳት ተዋጽኦ ፍላጎት ፈጣን ዕድገት እንደሚታይበት የተጠቀሰ ሲሆን የወተት ፍላጎት ዓመታዊ ዕድገት 2.2 በመቶ፣ የዶሮና የፍየል ስጋ ፍላጎት ደግሞ 3.3 በመቶ እንደሚጨምር መረጃዎች ያመለክታሉ ተብሏል፡፡

Read 1975 times