Sunday, 14 October 2018 00:00

መንግሥት በጦር ሰራዊቱ ውስጥ ያለውን ችግር በጥልቀት ሊፈትሽ ይገባል ተባለ

Written by 
Rate this item
(6 votes)

የሠራዊት አባላቱ ጠ/ሚኒስትሩንና ህዝቡን ይቅርታ ጠይቀዋ

ባለፈው ረቡዕ መስከረም 30 ቀን 2011 ዓ.ም ተሲያት ላይ፣ 240 የመከላከያ ሰራዊት አባላት፣ ከእነ ሙሉ ትጥቃቸው ወደ ብሔራዊ ቤተ-መንግስት ያመሩት ለግዳጅ  አልነበረም። ይልቁንም ከጠ/ሚኒስትር ዐቢይ አህመድ ጋር ለመወያየት ፈልገው ነው፡፡ የሰራዊት አባላቱ ያልተለመደ አመጣጥ እንግዳ የሆነባቸው የቤተ መንግስት ጸጥታና ደህንነት ሃላፊዎች፤ ከሁሉ አስቀድመው አባላቱን ትጥቅ እንዳስፈቷቸው  ምንጮች ጠቁመዋል፡፡ ከዚያ በኋላ ነው ቤተ መንግስት እንዲገቡ የተፈቀደላቸው ተብሏል፡፡
ጠ/ሚኒስትር ዐቢይ አህመድ፣ የዚያኑ ዕለት ምሽት ለኢቴቪ በሰጡት መግለጫ፤ ነገሩን ቀላል አድርገው ነው የገለጹት፡፡ በወታደሮቹ ቤተ መንግስት መከሰት የደነገጡ ወይም የተበሳጩ አይመስሉም፡፡ እንደውም ከሰራዊቱ አባላት ወደ ቤተ መንግስት መግባት ጋር ተያይዞ፣ በፌስቡክ ላይ በተሰራጩ የ”መፈንቅለ መንግስት ሙከራ” እየተደረገ ነው ዓይነት አሸባሪ የፈጠራ ወሬዎች ሳይደነግጡ አልቀሩም፡፡ ለዚያም ሳይሆን አይቀርም ራሳቸው ለቲቪ መግለጫውን የሰጡት። “የውሸት ዘመቻ ተቀብለን ካስተናገድን ያው መበላላት ነው” ያሉት ጠ/ሚኒስትሩ፤ ”በሃይማኖት፣ በዘር፣ በሥልጣን---ክፉ ሰዎች እንዲህ እየፈጠሩ ነው የሚያሰራጩት--” በማለት ህብረተሰቡ፣ ከፌስቡክ ዘመቻ ራሱን እንዲያቅብ መክረዋል፡፡    
ጠ/ሚኒስትሩ ነገሩን ቀለል ያድርጉት እንጂ ፖለቲከኞችና ምሁራን ግን የወታደሮቹን ድርጊት እንደ አደገኛ አዝማሚያ በመቁጠር መንግስት ዳግም እንዳይከሰት ወሳኝ እርምጃ መውሰድ አለበት ይላሉ፡፡  
“የሠራዊት አባላቱ የትኛውም ዜጋ ደፍሮ የማያደርገውን አማራጭ በመውሰድ፣ ትጥቅ ይዘው በአስገዳጅ ሁኔታ ቤተ መንግስት መግባታቸው አደገኛ መልዕክት ያለው ነው” ያሉት የዩኒቨርሲተ መምህሩ አቶ ስዩም ተሾመ፤ ”የሠራዊቱ አባላት ይህን ድርጊት ለመፈፀም የደፈሩት ስለታጠቁ ብቻ ነው፤ ይሄ ለሌላውም የሰራዊት አባላት አርአያነቱ በጎ አይደለም” በማለት ያስጠነቅቃሉ፡፡  
ሁሉም የህብረተሰብ ክፍል የየራሱ ጥያቄ አለው፣ ነገር ግን በእንዲህ መልኩ ማቅረብ የሚችልበት ድፍረትም የህግ አግባብም የለም ያሉት መምህር ስዩም፤ያለ ብዙ ችግር ሁኔታው መጠናቀቁ መልካም ነው፤ ድርጊቱ ዳግም እንዳይሞከር ግን የማስተካከያ እርምጃዎች መውሰድ ያስፈልጋል ብለዋል፡፡
ድርጊቱ በድንገት የተካሄደ ነው ብለው እንደማያምኑ የጠቆሙት ምሁሩ፤ “በሚገባ ተመክሮበትና ታቅዶበት የተደረገ መሆኑ፣ ድርጊቱን አደገኛ አዝማሚያ ያለው ያደርገዋል” ሲሉ ግምታቸውን ሰጥተዋል፡፡ “ጉዳዩን በየደረጃው ያሉ የጦር አዛዦች ያውቃሉ ብዬ እገምታለሁ፤ ማወቅም አለባቸው፤ ለምን የሰራዊቱ አባላት ከቡራዩ ተነስተው 4 ኪሎ እስኪደርሱ በዝምታ ተመለከቱ?” ሲሉ ይጠይቃሉ፤ አቶ ስዩም፡፡  
ምሁሩ እንዲህ ይበሉ እንጂ የሰራዊቱ አባላት በእርግጥም ከቡራዩ ወደ 4 ኪሎ ቤተ መንግስት በቀጥታ መምጣታቸውን  ማረጋገጥ  አልተቻለም።  
በዚህ ጉዳይ ላይ ጥልቅ ምርመራና ፍተሻ ተካሂዶ የማስተካከያ እርምጃ መወሰድ እንዳለበት በአፅንኦት የተናገሩት አቶ ስዩም፤ ብሶታቸውን ለማሰማት በዚህ መንገድ ወደ ቤተ መንግስት ያመሩትን የሰራዊት አባላት በህግ ተጠያቂ ለማድረግ መሞከር ግን ተገቢነት የለውም የሚል አቋም ያንጸባርቃሉ;፡፡
ጠ/ሚኒስትሩ፤ ብሶታቸውን ሊተነፍሱ ወደ ቤተ መንግስት ያመሩትን የሰራዊት አባላት በተመለከተ በኢቴቪ ብቅ ብለው የተናገሩትን የሰማ ሰው ሁሉ፣ የቱንም ያህል ህገ ወጥ ድርጊት ፈጽመው ቢሆን እንኳን ከፑሽ አፕ የዘለለ፣ ጨከን ያለ እርምጃ ይወሰድባቸው የሚል ሃሳብ ላይሰነዝር ይችላል፡፡ በእርግጥ ትንሽ ተሃድሶ ቢጤ ያስፈልጋቸው ይሆናል፡፡ በድጋሚ ከጠ/ሚኒስትሩ ጋር ለመወያየት ወደ ቤተ መንግስት ጎራ እንዳይሉ።   
የፖለቲካ ተንታኙ ዶ/ር መንግስቱ አሰፋ በበኩላቸው፤ ውትድርና ከሌላው ሙያ በተለየ መልኩ ጥብቅ የስራ፣ የኑሮና የተልዕኮ ዲሲፕሊን ያለው ነው ይላሉ፡፡ “ወታደር ጥያቄ ሲኖረው በየደረጃው ላሉ አመራሮች  ማቅረብ ነው የሚጠበቅበት፤ ድርጊቱ ጥሩ አዝማሚያን አያሳይም” ብለዋል፡፡
“መንግስት በወታደር ዘንድ የሚከበር እንጂ በቀላሉ የሚደፈር መሆን የለበትም” ያሉት አንጋፋው ፖለቲከኛ አቶ ያሬድ ጥበቡ በበኩላቸው፤ የሰራዊት አባላቱ ድርጊት የሚያመላክተው በሰራዊቱ ለቀናት ወይም ለሳምንታት የተካሄደ ምክክር መኖሩን ነው ይላሉ፡፡  
ውይይቱ የተካሄደውም በወታደሮቹ አስገዳጅነት ነው ብለው እንደሚያምኑ የተናገሩት አቶ ያሬድ፤ ወታደሮች ጥያቄ ሲኖራቸው መስመራቸውን ይዘው ባሉበት ይጠይቃሉ እንጂ በምንም አይነት ሁኔታ ወኪል መርጠው፣ ቤተ መንግስት ገብተው፣ ጥያቄ ማቅረብ ሊፈቀድላቸው አይገባም ነበር ብለዋል፡፡
“ከአሁን በኋላ በፈለጋቸው ሰአት እየመጡ ተመሳሳይ ትዕይንት እንደማያደርጉ ምን መተማመኛ አለ?” ሲሉ የሚጠይቁት አቶ ያሬድ፤ “ጠ/ሚኒስትሩና አመራሮቻቸው ሁኔታዎች እንዴት እዚህ ደረጃ እንደደረሱና መፍትሄ መሻት እንዴት እንዳልቻሉ፣ ራሳቸውን መፈተሽ አለባቸው ብለዋል፡፡
የወታደሮቹ ድርጊት በፑሽ አፕ የፎቶ ምስሎች የሚደበቅ ተራ ነገር ሳይሆን ኢትዮጵያ በየቀኑ እየተላመደች የመጣችው ስርአት አልበኝነት አንድ አካል ነው የሚል እምነት እንዳላቸው የገለፁት አቶ ያሬድ፤ የዶ/ር ዐቢይ አህመድ መንግስት፣ ሁለንተናዊ ጥንቃቄ ማድረግ አለበት ብለዋል፡፡
በእርግጥም ብሶታቸውን ለመናገር ቤተ መንግስት የገቡት የሰራዊቱ አባላት፤ ከጠ/ሚኒስትር ዐቢይ ጋር ውይይታቸውን ሲጨርሱ ፑሽ አፕ እንዲሰሩ ተደርገዋል፤ ከዶ/ር ዐቢይ ጋር። ጠ/ሚኒስትሩ የዩኒቨርሲቲ ምሁራንን ባወያዩበት ወቅትም፣ ከጥቂት ወጣት ምሁራን ጋር ፑሽ አፕ መሥራታቸው አይዘነጋም፡፡ በመጨረሻም የሠራዊቱ አባላት፣ ከዶ/ር ዐቢይ ጋር ፎቶ ተነስተው ነው የተለያዩት፡፡
ይህ በእንዲህ እንዳለ፤ የሰራዊት አባላቱ ለፈጸሙት ድርጊት፣ በትላንትናው ዕለት፣ ህዝቡንና ጠ/ሚኒስትር ዐቢይ አህመድን ይቅርታ መጠየቃቸውን ለማወቅ ተችሏል፡፡  
Read 8336 times