Sunday, 14 October 2018 00:00

ጠ/ሚኒስትሩ አዳዲስ የካቢኔ አባላትን ያሾማሉ ተብሎ ይጠበቃል

Written by  አለማየሁ አንበሴ
Rate this item
(12 votes)

· ሚኒስቴር መሥሪያ ቤቶች ይጣመራሉ፤የካቢኔ አባላት ከ28 ወደ 20 ዝቅ ይላሉ
· ሰላምና የህግ የበላይነት እንዲሰፍን የሚሰራ “የሰላም ሚኒስቴር” ሊቋቋም ነው

የጠቅላይ ሚኒስትሩ የካቢኔ አባላት ቁጥር ከ28 ወደ 20 ዝቅ የሚደረግ ሲሆን በርካታ ሚኒስቴር መሥሪያ ቤቶች ይጣመራሉ ተብሏል፡፡ አዲስ “የሰላም ሚኒስቴር” መስሪያ ቤትም ይቋቋማል፡፡
የፌደራል መንግስት አስፈፃሚ አካላትን ስልጣንና ተግባር ለመወሰን አዲስ ረቂቅ አዋጅ መዘጋጀቱን የጠቆሙት የጠቅላይ ሚኒስትሩ ጽ/ቤት ኃላፊ አቶ ፍፁም አረጋ፤ ስድስት ያህል ሚኒስቴር መስሪያ ቤቶች ይዋሃዳሉ ብለዋል፡፡
በረቂቅ አዋጁ መሰረት፤የንግድ ሚኒስቴር እና የኢንዱስትሪ ሚኒስቴር ተዋህደው፣ የንግድና ኢንዱስትሪ ሚኒስቴር እንዲሆን፤ የሳይንስና ቴክኖሎጂ ሚኒስቴር እና የመገናኛ ኢንፎርሜሽን ቴክኖሎጂ ሚኒስቴር ተዋህደው፣ የኢኖቬሽንና የቴክኖሎጂ ሚኒስቴር እንዲሆኑ ተወስኗል፡፡
በተጨማሪም የከተማ ልማት ሚኒስቴር እና የኮንስትራክሽን ሚኒስቴር ተዋህደው የከተማ ልማትና ኮንስትራክሽን ሚኒስቴር እንዲሆን የተወሰነ ሲሆን በየሚኒስቴር መስሪያ ቤቱ ስር ያሉ ተጠሪ ተቋማትም በተመሳሳይ ሁኔታ እንዲዋሃዱ ይደረጋል ተብሏል፡፡
በሀገር ውስጥ ሰላምና የህግ የበላይነት እንዲሰፍን፣ በህዝቡ ፈቃድ ላይ የተመሰረተ አንድ የፖለቲካ ማህበረሰብ በጋራ መገንባት ላይ ትኩረት ሰጥቶ የሚሰራ “የሰላም ሚኒስቴር” እንዲቋቋም ተወስኗል ብለዋል - አቶ ፍፁም፡፡
አዲስ የሚቋቋመው “የከፍተኛ ትምህርትና የሳይንስ ሚኒስቴር” ሁሉንም የሀገሪቱን የመንግስት ዩኒቨርሲቲዎችና የቴክኒክና ሙያ ተቋማትን የሚያስተዳድር ሲሆን ትምህርት ሚኒስቴር፤ከመዋዕለ ህፃናት እስከ 12ኛ ክፍል ያለውን የትምህርት ሂደት ያስተዳድራል ተብሏል።
የኢትዮጵያ ገቢዎችና ጉምሩክ ባለስልጣን “የገቢዎች ሚኒስቴር” ተብሎ እንዲጠራ የተወሰነ ሲሆን ለሚኒስቴር መስሪያ ቤቱ ተጠሪ የሆነ የጉምሩክ ኮሚሽን እንዲደራጅ መወሰኑም ታውቋል፡፡ የመንግሥት የልማት ድርጅቶች ሚኒስቴር የነበረው ፈርሶ፣ “የመንግስት የልማት ድርጅት ይዞታና አስተዳደር ኤጀንሲ” በገንዘብ ሚኒስቴር ስር ይቋቋማል ይላል - ረቂቅ አዋጁ፡፡  
ይህን የአደረጃጀት ለውጥ ለማድረግ ያስፈለገው፣ በዋናነት የ2ኛውን የእድገትና ትራንስፎሜሽን እቅድ በቀረው ጊዜ ለማጠናቀቅና የተጓተተውን አካክሶ ለመፈፀም መሆኑን የሚገልጸው ረቂቁ፤ የተጀመረውን የለውጥ ጉዞ የማይቀለበስበት ደረጃ ለማድረስም ያስችላል ብሏል፡፡ አዲሱ የመዋቅር ለውጥ፤ የአስፈፃሚ አካላት ቁጥር ቀልጣፋ፤ ወጪ ቆጣቢና ውጤታማ ለማድረግ ያግዛል፤ ተደራራቢና የድግግሞሽ ስልጣንንም ያስቀራል ተብሏል፡፡
ጠቅላይ ሚኒስትሩ አዲሱን የመንግስት አስፈፃሚ አካላት አደረጃጀት አዋጅን በመጪው ሳምንት ለፓርላማው አቅርበው የሚያስጸድቁ ሲሆን  አዳዲስ የካቢኔ አባላትንም ያሾማሉ ተብሎ ይጠበቃል፡፡

Read 9327 times