Saturday, 13 October 2018 11:32

አደጋ የተጋረጠበት የላሊበላ አብያተ ክርስቲያናት?!

Written by  አለማየሁ አንበሴ
Rate this item
(2 votes)

• እንኳን ኢትዮጵያዊው ቀርቶ የዓለም ህዝብ ተባብሮ ቅርሱን ከጥፋት ይታደገዋል
 • ቤተ ክርስቲያን፤ እንደ ህዝቡ ሁሉ አቤቱታ ማቅረብ ነው የምትችለው
 • ለላሊበላ ህዝብ ቅርሱ እንጀራው ነው፤ ኑሮው ነው፤ እስትንፋሱ ነው


   ባለፈው ሳምንት የላሊበላ አብያተ ክርስቲያናት ቅርስ አደጋ ተጋርጦበታል፤ በአስቸኳይ መፍትሄ ያስፈልገዋል በሚል የከተማዋ ነዋሪዎች ሰላማዊ ሰልፍ አድርገዋል፡፡ የባህልና ቱሪዝም ሚ/ር በበኩሉ፤ የቅርሱ ጥገና በሦስት ዓመት ውስጥ ይካሄዳል ብሏል፡፡ ለእድሳቱ የሚያስፈልገው ወጪ ግን ቀላል አይደለም። 300 ሚሊዮን ብር እንደሚፈጅ ተጠቁሟል፡፡
ለጊዜው ሚኒስቴር መሥሪያ ቤቱም ገንዘቡን  ከየት ሊያሰባስብ እንደሚችል የሚያውቅ አይመስልም። በሌላ በኩል፤ የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተ ክርስቲያን የቅርስና ቤተ መዛግብት ጽ/ቤት፤ ”ቤተ ክርስቲያኒቱ፤ መጠለያው በቅርሱ ላይ እያደረሰ ያለውን ጉዳት ደጋግማ አሳውቃለች” ይላል፡፡ የእድሳቱን ወጪ በተመለከተም፤ “ቅርሱ የቤተ ክርስቲያን ብቻ አይደለም፤ የሀገር ነው፤ ሆቴሎች፣ የኢትዮጵያ አየር መንገድ-- ሁሉም ባለ ድርሻዎች ናቸው” የሚሉት የጽ/ቤቱ  ኃላፊ ቀሲስ ሰለሞን ቶልቻ፤ ቅርሱን ለመታደግ ሁሉም አካል የድርሻውን መወጣት እንዳለበት ይናገራሉ፡፡ የአዲስ አድማስ ጋዜጠኛ አለማየሁ አንበሴ፤ ቀሲስ ሰለሞን ቶልቻንና የባህልና ቱሪዝም ሚ/ር የህዝብ ግንኙነት ሃላፊን በጉዳዩ ዙሪያ  አነጋግሯቸዋል፡፡ ከቀሲስ ሰለሞን ይጀምራል፡-


    ከዚህ ቀደም ቤተ ክርስቲያኒቱ፤ “የላሊበላ አብያተ ክርስቲያናት ጉዳይ ያሳስበኛል” በማለት መግለጫ መስጠቷ ይታወሳል፤ ከዚያ በኋላ ክትትል አድርጋችኋል?
በላሊበላ አብያተ ክርስቲያናት ዙሪያ ያሉ የመጠለያ ጉዳዮች አሳሳቢነታቸውን እኛም ለመንግስት አሳውቀናል፡፡ መጠለያውን የተከለው አካልና ባለድርሻ አካላት ማለትም ባህልና ቱሪዝም ሚኒስቴር፣ ቅርስ ጥናትና ጥበቃ እንዲሁም የአማራ ክልል ባህልና ቱሪዝም ቢሮ፣ የላሊበላ ገዳም አስተዳደር፣ ጠቅላይ ቤተ ክህነት በጋራ በአሳሳቢነቱ ላይ ተወያይተዋል፡፡ ቤተ ክርስቲያኒቱ መጠለያው እያደረሰ ያለውን ጉዳት ደጋግማ አሳውቃለች፡፡ በጊዜ ገደብ ነው መጠለያው የተተከለው፡፡ አሁን የጊዜ ገደቡ ካበቃ አመታት ተቆጥረዋል፡፡ በወቅቱ መጠለያው ጥሩ ጥቅም ሰጥቶ ሊሆን ይችላል፤ አሁን ግን ጉዳት ነው እየፈጠረ ያለው። በዚያው ልክ ቅርሱ ላይ አሁን የደረሰው ጉዳት ሳይጠገን ዝም ብሎ መጠለያው ይነሳ ቢባልም ጉዳቱ የባሰ ነው የሚሆነው፡፡ ቅርሱ ባለፉት 10 ዓመታት፣ ፀሐይና ዝናብ ሳያገኘው በመጠለያ የቆየ ነው፡፡ አሁን በድንገት መጠለያው ተነስቶ ለፀሐይና ለዝናብ ቢጋለጥ ጉዳት ማጋጠሙ አይቀርም፡፡ ስለዚህ ተገቢ ጥናት ያስፈልጋል፡፡
ዋነኛ ባለቤት የሆነችው ቤተ ክርስቲያኒቱ ቅርሱን ከጉዳት ለመታደግ ምን ጥረት እያደረገች ነው? በመንግስት ላይ የምታደርጉት ግፊት ምን ያህል ውጤት አስገኝቷል?
አሁን የፌደራል መንግስት ለቅርስ ጥበቃ የመደበው በጀት 32 ሚሊዮን ብር ገደማ ነው፡፡ ከዚያ ውስጥ 20 ሚሊዮን ብር ያህሉን ለላሊበላ እንደሚያውለው በባህልና ቱሪዝም ሚኒስቴር ተገልጿል፡፡ ላሊበላ ልዩ ቅርስ ነው፡፡ ዛሬም አገልግሎት ያልተቋረጠበት ህያው ቅርስ ነው፡፡ በሙዚየም የተቀመጠ አይደለም። በሮቹ ላለፉት 800 ዓመታት እየተከፈቱ እየተዘጉ ነው፡፡ ለ800 ዓመታት የሰው እጅ ነክቶታል፡፡ እንደ ሌሎች በክብር የተቀመጡ ቅርሶች አይደለም ላሊበላ፡፡ አንዴ ከእጅ ከወጣ አይገኝም፡፡ ህዝቡም ሰላማዊ ሰልፍ የወጣው ለዚህ ነው፡፡ ለላሊበላ ህዝብ ቅርሱ እንጀራው ነው፡፡ ኑሮው ነው፡፡ የላሊበላ ቅርስ ለላሊበላ ህዝብ እስትንፋሱ ነው፡፡ ከዚህ አንፃር ነው እኛ ትኩረት እንዲያገኝ ግፊት እያደረግን ያለነው፡፡ እርግጥ ባህልና ቱሪዝም ትኩረት አልሰጠውም ማለት አንችልም፡፡ ይሄ ቅርስ የሀገር ሀብት ነው፤ የቤተ ክርስቲያኒቱ ብቻ አይደለም፡፡ በንብረትነት ልታስተዳድረው ትችላለህ፤ ነገር ግን የበላይ ተቆጣጣሪ አካላት ዩኔስኮ፣ የባህልና ቱሪዝም ሚኒስቴር፣ ቅርስና ጥናት ባለስልጣን ናቸው፡፡
ቤተ ክርስቲያኒቱ፤ የድርሻዋን ተወጥታለች ማለት ይቻላል ---
ቤተ ክርስቲያኒቱ በባለቤትነት ታስተዳድረው እንጂ የጥገና፣ የቅርሱ አጠባበቅ ቴክኒካዊ ጉዳዮችን የሚከታተለው መንግስት ነው፡፡ ቤተ ክርስቲያኒቱ ከዚህ አንፃር በፓትርያርኩ ጽ/ቤት በኩል ለመንግስት አቤቱታ ስታቀርብ ቆይታለች፡፡ በቅዱስ ሲኖዶስ ጉባኤ ደረጃ ውይይት ተካሂዶ፣ መንግስት ተገቢውን ጥበቃ ለቅርሱ እንዲያደርግ፣ ጥገናውንም እንዲያከናውን ደብዳቤ ተጽፏል፡፡ ቤተ ክርስቲያኒቱ ከዩኔስኮ ጋር ቀጥታ ግንኙነት የላትም፤ ዩኔስኮ ግንኙነት ያለው ከመንግስት ጋር ነው፡፡ ማድረግ የምትችለው እንደ ህዝቡ ሁሉ አቤቱታ ማቅረብ ነው፡፡ ከዚህ በፊት መጠለያውን የሰሩት የዩኔስኮ ባለሙያዎች፣ ወደ ሀገር ቤት መጥተው፣ የላሊበላን ጉዳይ ለሚከታተለው የጥናት ቡድን ሪፖርት አቅርበው ነበር፡፡
ያቀረቡት ሪፖርት ምንድን ነው የሚለው?
እነሱ “ምንም ስጋት የለውም፤ ለቀጣይ ዓመታት ሊያገለግል ይችላል” የሚል ድምዳሜ ላይ ደርሰዋል። ማገልገል ይችላል የሚል ሪፖርታቸውን ካቀረቡ በኋላ በተደረገ የመስክ ምልከታ ግን በአካባቢው ያሉ ነዋሪዎችና ካህናቶች፤ ቅርሱ ጉዳት እየደረሰበት እንደሆነ ነግረውናል፡፡ እኛም ባደረግነው ምልከታ፣ ስጋቶች እንዳሉ ተረድተናል፡፡ በተለይ ቤተ አማኑኤል ላይ ያለው ስጋት ከፍተኛ ነው፡፡ የመሰንጠቅ ችግር አጋጥሟል፡፡ እንደ ጠቅላይ ቤተ ክህነት፤ ጉዳቱ ተጠግኖ መጠለያው መነሳት አለበት የሚል ፅኑ አቋም ነው ያለን። ከእንግዲህ በኋላ መጠለያው በቅርሱ ላይ መቆየት የለበትም፡፡
ቅርሱን ለመጠገን በአጠቃላይ የሚያስፈልገው በጀት ምን ያህል ነው?
300 ሚሊዮን ብር ያስፈልጋል የሚል ነው ባለሙያዎች ያቀረቡት ጥናት፡፡ ይሄን በጀት ለማግኘት እውነቱን ለመናገር ከባድ አይደለም፡፡ የኢትዮጵያ ህዝብ ተባብሮ የሚያዋጣው ገንዘብ ነው። ዳያስፖራውን ብናነቃንቀው ከዚህም በላይ ገንዘብ ይሰጣል፤ዋናው ኃላፊነቱን ወስዶ የቴሌቶን ፕሮግራም የሚያዘጋጅ አካል መኖሩ ነው፡፡ ይህን ለማድረግ ደግሞ የመንግሥት በጎ ፍቃድ ያስፈልጋል፡፡ ይሄ ከተደረገ እንኳን ኢትዮጵያዊው ቀርቶ የዓለም ህዝብ ተባብሮ ቅርሱን ከጥፋት ይታደገዋል፡፡ ወሳኙ የመንግስት ቁርጠኝነት ነው፡፡ ኢትዮጵያ ትልቅ ሀገር ናት፤ ህዝቧም ቀናኢ ነው፤ ይሄን ቅርስ ማዳን ይችላል፤ አቅጣጫ የሚሳየውን ነው የሚፈልገው፡፡
እዚህ ጋ አንድ ጉዳይ ላንሳ፡፡ ለምሳ አንድ ዩኒቨርሲቲ የአንድ የግንባታ ዓመት ወጪው 3 መቶ ሚሊዮን ብር ገደማ ነው፡፡ መንግስት ይሄን አስታግሶ ከጠፋ የማናገኘውን ቅርስ ለምን አያድንም? የተለየ ትኩረት ሊሰጠው ይገባል፡፡ ቤተ ክርስቲያኗ በየጊዜው ግፊት ታደርጋለች፡፡  
ቅርሱ አሳሳቢ ሁኔታ ውስጥ እንዳለ በፓትርያርኩ ደብዳቤ ተፅፏል፡፡ መንግስት ላሊበላን በተለየ አይን  ማየት ይገባዋል፡፡ በነገራችን ላይ ቅርሱ ሳይጠገን መጠለያው እንዲነሳ አንፈልግም፡፡ በመጀመሪያ ቅርሱ መጠገን አለበት፡፡ ሳይጠገን ከተነሳ በአንድ ክረምት ሊፈርስ ይችላል፡፡
ቤተ ክርስቲያኒቷ ቅርሱን ለመታደግ የሚያስችል በቂ ገንዘብ አላት የሚል ሙግትም ይቀርባል …
አዎ ገንዘብ አላት፤ ነገር ግን ቅርሱ የሷ ብቻ አይደለም፤ የሀገር ነው፡፡ ሆቴሎች፣ የኢትዮጵያ አየር መንገድ-- ሁሉም ባለድርሻ ነው፡፡ ቅርሱን ለመጎብኘት ከሚመጣው ቱሪስት እኮ ትልቁ ተጠቃሚዎች እነሱ ናቸው፡፡ የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ዶላር የሚመነዝረው እኮ ቅርሱ ስላለ ነው፡፡ ቤተ ክርስቲያኒቱ እኮ ዶላር አትመነዝርም፤ ቅርሱ የጋራ ከሆነ ሁሉም ወገን  ድርሻ አለው፡፡
ቤተ ክርስቲያኒቱ ድርሻዋ ምን ያህል  ነው?
መዋጮ ማቅረብ አለባት ከተባለ እንደ አንድ ባለድርሻ፣ ምዕመኖቿን አስተባብራ ገንዘብ ልታዋጣ ትችላለች፡፡ ግን ገንዘብ ለማሰባሰብ የመንግስት ውሳኔ ያስፈልጋል፡፡ የላሊበላ ነገር በማያዳግም መልኩ ነው መመለስ ያለበት፡፡  

Read 1051 times