Sunday, 14 October 2018 00:00

ስለ ጎሳ ፖለቲካ ሲወራ “ፌዴራሊዝሙን አደጋ ላይ ልትጥሉት ነው” አትበሉ!

Written by 
Rate this item
(0 votes)

   ኢትዮጵያ በቋንቋ፣ በኃይማኖት፣ በባህልና በሌሎች ማህበራዊ እሴቶች እጅግ የተሰበጣጠረ ሕዝብ ያለባት አገር እንደመሆኗ፣ ሁሉንም ሕዝብ እኩል አከባብሮና አቻችሎ ሊያኖር የሚችል መንግስታዊ አወቃቀር ያስፈልጋታል። ለዚህም ፌደራላዊ የመንግስት አወቃቀር ተመራጭና ምቹ ስለመሆኑ ምንም አያከራክርም፡፡  ጥያቄው ያለው የፌደራሊዝም ሥርዓቱ በምን መሰረት ላይ ይዋቀር በሚለው ላይ  ነው። ይህን ደግሞ በደመ ነፍስ እንዲህ ይሁን እንዲያ ከማለት፣ አገሪቱ ያለችበትን ወቅታዊና ተጨባጭ እውነታዎች በቅጡ ያገናዘበና  በባለሙያዎች የተጠና ፌደራላዊ አወቃቀር እንዲኖር ማድረግ ይቻላል። በዚህ ዘርፍ የተደረጉ በርካታ ጥናቶችም ስላሉ፣ እነሱንም በቅጡ መፈተሽ ጊዜና አቅምንም ይቆጥባል።
እኔን እያሳሰበኝ ያለው በአገሪቱ ውስጥ እየተንሰራፋ የመጣውና ለብዙ ዜጎች ህይወት ህልፈትና መፈናቀል ምክንያት የሆነው ቋንቋንና ጎሳን ያማከለው የመንግስት አወቃቀር ነው። ክልሎች በዚህ መልክ በመዋቀራቸው ብቻ ሳይሆን ላለፉት ሃያ ሰባት አመታትም በመንግስትና አክራሪ በሆኑ ብሔረተኞች ሲቀነቀንና ሲሰበክ የኖረው ዘር ተኮር ፖለቲካ፣ ዛሬ ፍሬው ጎምርቶ፣ በየክልሉ አደጋዎች እያስከተለ ነው። አንዱ ስፍራ ላይ አፈናቃይና ተሳዳጅ የሆነ የህብረተሰብ ክፍል፣ ሌላው ክልል ላይ ተፈናቃይ እየሆነ አገር እየታመሰች ነው።
በተለያዩ  ክልሎች የሚታዩት ዘር ተኮር ጥቃቶች ያልነኩት የህብረተሰብ ክፍል የለም። በግንባር ቀደምነት አማራው ከኖረበት ቀዬው ከወልቃይትና ራያ አንስቶ፣ በሁሉም ክልሎች ማለት ይቻላል የጥቃት ሰለባ ሆኗል። ኦሮሞውም እንዲሁ ከሶማሌ ክልልና ከቤኒሻንጉል ጉምዝ እየተሳደደ ነው። በደቡብ ክልል አንዱ ጎሳ ሌላውን እያፈናቀለ ነው። ሌሎቹም ጎሳዎች ተመሳሳይ እጣ ፈንታ እየገጠማቸው ነው። ማቆሚያው የቱ ጋ እንደሆነ አይታወቅም።
ይህን አደጋ ያስከተለው ደግሞ አገሪቱ ስትከተል የኖረችው የጎሳ ፌደራሊዝም እንደሆነ ማሳያው የሁሉም ጥቃቶች ምንጭ አሳዳጅ የሆነው አካል፤ «ክልሌ ነው፣ የእኔ መሬት ነው፣ እናንተ ባዳዎች ናችሁ፣ በዚህ ስፍራ የመኖር ዋስትናችሁ በእኔ ፈቃድ የተወሰነ ነው--» ከሚል ስሜት የመነጨ መሆኑ ነው። ይህ ስሜት ደግሞ ዝም ብሎ ከየትም የመነጨ ሳይሆን የሕግ ድጋፍም ጭምር ያለው  ነው። ከሕገ-መንግስቱ ጀምሮ የክልል ሕገ-መንግስቶች ለዜጎች እውቅና አይሰጡም። ዜጎች የአገራቸው ባለቤት አይደሉም። እያንዳንዱ ክልል ለብሔር፣ ብሔረሰቦች የተሰጠ ስለሆነ፣ ሁለት አይነት ዜግነት እንዲኖር አድርጓል።
በቤኒሻንጉል የሚኖር ኦሮሞ ወይም አማራ ወይም ትግሬ እዚያው ክልል እንኳን ቢወለድ፣ ከአንድ ጉሙዝ እኩል በክልሉ ውስጥ የዜግነት መብት የለውም። በተመሳሳይ ሁኔታ አንድ አንድ ጉራጌ ወይም ከንባታ ወይም ወላይታ፤ በኦሮሚያ ክልል ውስጥ ከአንድ ኦሮሞ እኩል የዜግነት መብት የለውም።
እነዚህ ነገሮች ከጥላቻ ፖለቲካ ጋር ተቀላቅለው የፈጠሩት ነገር፣ ይሄው ዛሬ የምናየው እርስ በእርስ መጠፋፋትና አንዱ ሌላውን ማሳደድ ነው። ይህ አይነቱ ጎሳን ያማከለ፣ ዜጎችን ያበላለጠ፣ አንዱን ተሳዳጅ ሌላውን አሳዳጅ ያደረገ ዘር ተኮር የመንግስት ፖሊሲ ሊቀየር ይገባል።
የሚያሳዝነው ይህ ሁሉ አደጋ እየታየና ህዝብ በገዛ አገሩ እየተፈናቀለም፣ ፌደራሊዝሙ የተዋቀረበት መንገድ ይፈተሽና ይስተካከል ሲባል፣ አክራሪ ጎሰኞቹ ብቻ ሳይሆኑ በዘር ፖለቲካ የቆረቡ ሰዎችም፣ «ፌደራሊዝሙን ልታጠፉብን ነው የተነሳችሁት» እያሉ ሲያላዝኑና እንቧ ከረዩ ሲሉ መስማታችን ነው። ፌደራሊዝሙን ከጎሰኝነት አጽዱት ሲባል፣ «በአንድነት ስም ልትውጡን ነው» የሚል ስጋትም ነው ደጋግሞ ሲገለጽ የሚሰማው።
በአገሪቱ ውስጥ ጎጠኝነት ተንሰራፍቶ ከቁጥጥር ውጭ እየወጣ ነው። ሰዎች በጎጥ ከረጢት ውስጥ ሆነው ነው አገራቸውን የሚያስቡት። ያ ደግሞ የጋራ አገራዊ ራዕይም ሆነ እንደ አንድ አገር ሕዝብ በጋራ እንዳንቆም ብቻ ሳይሆን አብረን እንዳንኖርም እያደረገ ነው። ችግሩ የዘር ፖለቲካውን የሚያጦዙት ልሂቃኑ የጥቃሉ ሰለባ አይደሉም። በዘር ግጭት የሚሞተው ያው በየመንደሩ ያለው ደሃና  የዚህ መሰሪ ፖለቲካ ግራ ቀኙ ያልገባው ምስኪን ሕዝብ ነው። ፖለቲከኛው ገሚሱ አዲስ አበባ፤ ቀሪውም አውሮፓና አሜሪካ ተቀምጦ ነው እሳትና ነዳጅ ወደ ድሃው መንደር የሚወረውረው። በጎሳ ፖለቲካ መዘዝ ሟቹና ተፈናቃዩ ግን ደሃው ሕዝብ ነው። በእኛ ዝቅጠት ይህ ድሃ ህዝብ እስከ መቼ ነው ባገሩ ተሳዳጅ የሚሆነው?
ጉዳዩ  በጊዜ ተመክሮበት እልባት ያግኝ የሚል ጥሪ ከመብት ተሟጋቾች ሲቀርብ፣ ፌደራሊዝሙን ልታፈርሱ ነው እያሉ የሚያንቧርቁ ጎሰኞች ቆመው ሊያስቡ ይገባል። አሁንም በግልጽ ቋንቋ ለማስቀመጥ «አዎ! ኢትዮጵያ ፌደራላዊ የመንግስት አወቃቀር ነው የሚበጃት» እዚህ ላይ ጥያቄም ሆነ ጥርጥር የለም። ጥያቄው ዘርን ያማከለ አይሁን ነው። የዘር ፖለቲካው እያስከተለ ያለው አደጋ ባሳሰብን ቁጥር ጸረ ፌደራሊዝም አድርጎ ማቅረብ፣ አንድም ዝም ለማሰኘት አለያም «በዘር ፖለቲካው እያተረፍን ስለሆነ ለእኛ ተመችቶናልና ማንም ቢሞትና ቢፈናቀል አይመለከተንም» ነው የሚሆነው።
ለማንኛውም ለለውጥ ኃይሉ መልካሙን ሁሉ እየተመኘን፣ የአገር ግንባታውም (nation building) ሆነ የመንግስት ግንባታው (state building) ትግል ከወዲሁ አሳታፊ፣ በጥናት ላይ የተመሰረተ፣ ግልጽነት የተሞላውና ተጠያቂነት የሰፈነበት  መሆኑን ማረጋገጥ ያስፈልጋል። መሰረቱ ያልጸና የአገርም ሆነ የመንግስት ግንባታ አሸዋ ላይ እንደ ተጣለ ድንኳን ነውና በነፈሰ ቁጥር መንገዳገድ ብቻ ሳይሆን ከስር መመንገልም ይኖራል። ቸር ያሰማን!
(ከስዩም ተሾመ ፌስቡክ ጥቅምት 3, 2018)

Read 2312 times