Print this page
Sunday, 14 October 2018 00:00

ዶ/ር ቆስጠንጢኖስ ስለ ሜካናይዝድ ግብርና፣ ነጻ ገበያ፣ ሙስና፣ ቢሮክራሲ---

Written by  አለማየሁ አንበሴ
Rate this item
(3 votes)


  • መንግስት በየቦታው ጣልቃ እየገባ፣ ነፃ ገበያውን እያበላሸ ነው የቆየው
  • ከውጭ የሚመጣው የፓልም ዘይት በዓመት 450 ሚሊዮን ዶላር ያስወጣል
  • እነ ኤፈርት፣ ጥረት- -- ኢንዶውመንት ሳይሆኑ የንግድ ድርጅቶች ናቸው
  • ከሚኒስትሩ በታች ያለ ሰራተኛ ሁሉ ተወዳድሮ ነው መቀጠር ያለበት
  • ትልቁ ጥፋት መንግስት ብቻውን ሁሉንም ነገር ልቆጣጠር ማለቱ ነው

    ፕሬዚዳንት ሙላቱ ተሾመ (ዶ/ር) መስከረም 28 ቀን 2011 ዓ.ም የህዝብ ተወካዮች እና የፌዴሬሽን ም/ቤትን በንግግር በከፈቱበት ወቅት መንግስት በዓመቱ ትኩረት ሊያደርግባቸው ያቀዳቸውን ተግባራት ጠቁመዋል፡፡ በፕሬዚዳንቱ ንግግርም የኢኮኖሚ ጉዳይ ድርሻ  ተሰጥቶታል፡፡ የንግድ ህግ ማሻሻል፣ የነፃ ገበያ ስርአትን ሙሉ ለሙሉ መተግበር፣ ግብርናን በሰፋፊ የመስኖ ሜካናይዝድ ማልማት--በዋናነት ይጠቀሳሉ። በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ የኢኮኖሚክስ መምህርና የኢኮኖሚ ጉዳዮች ተንታኝ የሆኑት ዶ/ር ቆስጠንጢኖስ በርሄ፤ በፕሬዚዳንቱ ንግግር ላይ ሰፊ ግምገማና ትንተና ለአዲስ አድማስ ሰጥተዋል፡፡ በዚህም ብቻ ሳይወሰኑ መንግስት በንግድ ሥራ ውስጥ ስላለው ሰፊ ድርሻና አሉታዊ ተጽዕኖው፣ ስለ ኢንዶውመንት፣ ስለ ሙስና፣ ስለ ፓርቲና መንግስት ሚና መደባለቅ ወዘተ-- በስፋት ያብራራሉ፡፡ መንግስት የዚህ ዓመት ዋነኛው ሥራው ማድረግ ያለበት ምን እንደሆነም ይጠቁማሉ። የአዲስ አድማስ ጋዜጠኛ አለማየሁ አንበሴ እንዲህ አነጋግሯቸዋል፡፡


    የ2011 የመንግሥት የትኩረት አቅጣጫ ተብለው በተለይ በኢኮኖሚው በኩል የተጠቀሱትን እንዴት አገኟቸው --?
እንግዲህ ፕሬዚዳንቱ የ2011 የመንግሥትን የትኩረት አቅጣጫ ከገለጹበት ንግግራቸው አንዱ፣ በኢኮኖሚው መስክ ስለሚኖረው ስራ ነው፡፡ በዋናነት ወደ ሜካናይዝድ ግብርና የሚገባ መሆኑን ጠቁመዋል። ከዚህ በፊት የግብርና ሚኒስቴር ባወጣው ሪፖርት ላይ፣ ሀገሪቱ 72 ሚሊዮን ሄክታር የሚታረስ መሬት አላት ይላል፡፡ ይሄ መሬት ገና ያልተጠቀምንበት ነው። በዘመናዊ መንገድ ሳይሆን በልማድ ግብርና ነው ስንጠቀምበት የኖርነው፡፡ አሁን ደግሞ አለም በሙሉ በአረንጓዴ አብዮትና በሰፋፊ ሜካናይዝድ ግብርና ነው እየተዳደረ ያለው፡፡ በተለይ የቻይና እና የህንድ ህዝብ እያደገ፣ ኢኮኖሚውም እየበለፀገ ሲመጣ፣ ከፍተኛ የምግብ እጥረት ሊያጋጥማቸው ይችላል የሚል ትንበያ ነው ያለው፡፡ ከዚህ አንፃር ያለንን የተፈጥሮ ሀብት በዘመናዊ መንገድ አልምተን፣ ከራሳችን አልፈን፣ ይህን የዓለም ገበያ መያዝ የምንችልበት እድል አለ፡፡ ይሄን ለማድረግ የሶማሌ ክልልን መሬት ማልማት በቂ ሊሆን ይችላል፡፡ በነገራችን ላይ የሶማሌ ክልል ውስጥ ያለው ሰፊ መሬት፣ በዓለም ላይ በከፍተኛ ደረጃ ሊለሙ ከሚችሉ አራት ቦታዎች አንዱ ነው፡፡ አራት ወንዞች በመሬቱ ላይ ይፈሳሉ፡፡ ግን አልተጠቀምንባቸውም፡፡ መሬት የመንግስት ነው በተባለበት ሃገር፣ ብዙ ምክንያት ማቅረብ ሳያስፈልግ፣ ፕሬዚዳንቱ ባመላከቱት መሰረት፣ ይሄን መሬት ማልማት ያስፈልጋል፡፡ የማህበረሰቡ መሬት ነው የሚባል ነገር አለ፡፡ ይሄ ግን እስከ መጨረሻው አያስኬድም፡፡ ማህበረሰቡ፤ ከተረጂነት ወደ አምራችነት የሚቀየርበት መሆኑን ማስረዳትና መተማመን ፈጥሮ ወደ ስራ መግባት ያስፈልጋል፡፡ ሃገርን የተቆጣጠረና መሬት የመንግስት መሆኑን በህጉ ለደነገገ መንግስት፤”መሬቱ በጎሳ የተያዘ ነው፣ማልማት አልችልም” የሚለው ምክንያት ከእንግዲህ አይሰራም። የግል ዘርፉን በአግሮ ፕሮሰሲንግ ለማሳተፍ መታቀዱ ተገልጿል፡፡ ይሄ መልካም ነው፡፡ ለዚህ የአግሮ ፕሮሰሲንግ ተቋማት ጥሬ እቃ ከግብርናው ነው ሊመጣ የሚችለው፡፡ አሁን ባለው ሁኔታ ግን ይሄን ጥሬ እቃ በሚገባ አላዘጋጀንም፡፡
ሰፋፊ እርሻዎችን ለመስራት የሚያስችል ልምድ ባለፉት 27 ዓመታት የለንም፡፡ በንጉሱ ዘመን ተጀምሮ ልምድ አካብተን  ነበር፡፡ አሁን ግን የለም፡፡ ስለዚህ ሃገር ውስጥ ይሄን ለማድረግ ልምዱ የለንም፡፡ ከውጭ ልምድ ማግኘት አለብን፡፡ ይሄን ለማድረግ ደግሞ በሰፋፊ የመስኖ እርሻ ልምዱ ያላቸው እንደ ስፔን፣ ጣሊያን ከመሳሰሉት ሃገራት ባለሙያዎች ማምጣት ያስፈልጋል። እነዚህ ሃገሮች በመስኖ ሰፋፊ ግብርና የዳበረ ልምድ ያላቸው ናቸው፡፡ ለዚህ ደግሞ ሰዎቹ ብር ስለሚፈልጉ የባንኮች አሰራር መዘመን፣ አቅማቸው መገንባት አለበት፡፡ ስራው በባለሙያዎች መሰራት አለበት፡፡ በነገራችን ላይ ዘመናዊ ግብርናን መከተል የሚለው ፖሊሲ ከዚህ በፊት በወረቀት ደረጃ የተቀመጠ ነው፡፡ በተግባር አልተሰራበትም፡፡ የተሰራው መሰረተ ልማቱ ነው፡፡ መንገድ የመሳሰለው፡፡ አሁን በሙሉ አቅም ሰፋፊ የመስኖ እርሻ ልማትን መስራት ይቻላል። ከዚህ አንፃር ፕሬዚዳንቱ በንግግራቸው ያመላከቱት ጉዳይ ተገቢው ትኩረት ከተደረገበትና በባለሙያዎች ከታገዘ ሊተገበር የሚችል ነው፡፡
የውጭ ሃገር ባለሀብቶች ግብርና ውስጥ መግባታቸው ከልምድ ባሻገር ምን ያህል ጠቃሚ ነው? የሀገር ውስጥ ባለሀብቶችን ድርሻስ አይገዳደርም?
ትልቁ ነገር ከውጭ የሚመጡት ሰፊ አቅም አላቸው። በቀላሉ ማሳካት ይችላሉ፡፡ ይሄ ሲሆን አብዛኛው ህዝብ ተጠቃሚ ይሆናል፡፡ ለምሳሌ አንድ የጣሊያን ባለሀብት ሲመጣ፣ ከሃገሩ ባንክ ተበድሮ ነው ወደ ስራ የሚገባው። የሀገሩ ባንክ በቂ አቅም ስላለው ማበደር ይችላል፡፡ የኛ ሃገር ባንክ ደግሞ በአንፃሩ በዚያ መጠን የማበደር አቅም የላቸውም፡፡ ስለዚህ የሀገር ውስጥ ባለሀብቶች፣ ሰፋፊ የመስኖ ግብርና ፕሮጀክት የሚጠይቀውን ወጪ መሸፈን የሚያስችል ብድር ከባንክ ማግኘት አይችሉም፡፡ የኛ ባንኮች አቅማቸው ውስን ነው፡፡ በዚያ ደረጃ አልደረሱም፡፡ የመስኖ ግብርና ቀላል አይደለም። መዋቅሩ ሰፊ በመሆኑ ኢንቨስትመንቱ ትልቅ ነው፡፡ አቅም ይጠይቃል። በዚያው ልክ አንዴ ስራ ከጀመረ ደግሞ በሚገባ ገቢ ያስገኛል፡፡ ለምሳሌ ወንጂ ስኳር ፋብሪካ 60 ዓመት ሊሞላው ነው፡፡ የወጣበትን ወጪ ሸፍኖ ዛሬ በትርፋማነት ስራውን እየሰራ ነው፡፡ የመስኖ ግብርና ባህሪው እንደዚህ ነው፡፡ ከዚህ አንፃር ፕሬዚዳንቱ በንግግራቸው ጉዳዩን ማንሳታቸው ጥሩ ነው፤ ግን እንዴት ነው የሚተገበረው የሚለው ነው ዋናው ጉዳይ።
ሙሉ ለሙሉ የነፃ ገበያ ስርአትን እንተገብራለን የሚል አቅጣጫም ተቀምጧል፤ ይሄን እንዴት ይመለከቱታል?
ነፃ ገበያ ከበፊት ጀምሮ በወረቀት ተቀምጦ አለ ነው የሚባለው፡፡ ነገር ግን ዋናው ችግር መንግስት በየቦታው ጣልቃ እየገባ፣ ነፃ ገበያውን እያበላሸ መቆየቱ ነው፡፡ ከዚህ አንፃር ነፃ ገበያ እንከተላለን ማለት አስቸጋሪ ነው፡፡ ለምሳሌ የምግብ ዘይት ከውጪ የሚያስመጡት አምስት ያህል፣ ያውም መንግስት የመረጣቸው ነጋዴዎች ብቻ ነበሩ፡፡ እነዚህ ነጋዴዎች በብቸኝነት የፓልም ዘይትን ሲያስመጡ ነው የቆዩት፡፡ ይሄ የፓልም ዘይት ገበያውን በሞኖፖል ማጥለቅለቁን ተከትሎ ደግሞ ቀድሞ ጠንካራ የነበረው የሀገር ውስጥ የዘይት ኢንዱስትሪ ሙሉ ለሙሉ እንዲዳከም ነው የተደረገው። ይሄ ግልፅ የመንግስት ጣልቃ ገብነት ነው። ዘይት ወደ ሃገር ውስጥ የሚያስገቡ ሰዎች፣ ከቀረጥ ነፃ ነው የሚያስገቡት፡፡ ሀገር ውስጥ የሚያመርቱት ደግሞ በታክስ ላይ ታክስ እንዲከፍሉ እየተደረገ ነው የተዳከሙት፡፡ ከውጭ የሚመጣው የፓልም ዘይት በዓመት 450 ሚሊዮን ዶላር ነው የሚፈጀው፡፡ ይሄ ከፍተኛ የውጭ ምንዛሬ ነው፡፡ በአንፃሩ ሀገራችን ለቅባት እህል ምርት የሚሆን በቂ መሬት፣ በቂ የማምረት ልምድ፣ በቂ አቅም እያላት አቅሟን እንዳትጠቀም ነው የተደረገው፡፡ በኬንያ እኮ የንግድ ፈጠራ ባለሙያዎች፣ የየራሳቸውን የዘይት መጥመቂያ ሰርተው ነው ለገበያ የሚያቀርቡት፡፡ በኛ ሃገር ግን የፓልም ዘይት ከውጭ እያመጣን፣ (ያውም በጤና ባለሙያዎች የማይመከር) የኑግ ዘይት ምርቶች ኢንዱስትሪ እንዲዳከም ተደርጓል። መንግስት እንዲህ ያሉ ነገሮች ውስጥ እየገባ፣ ነፃ ገበያን ማካሄድ አይቻልም፡፡ ነፃ ገበያ የሚባለው ሰዎች ምርጫ ሲኖራቸው ነው፡፡ ለምሳሌ የገዥው ፓርቲ አባል ፓርቲዎች፣ የራሳቸው የንግድ ድርጅት አላቸው፡፡ በጠቅላላው የኢትዮጵያን ህዝብ ህይወት የሚቆጣጠሩ ድርጅቶች አደራጅተዋል፡፡ ታዲያ እንዴት ነው ነፃ ገበያ ሊተገበር የሚችለው? እነዚህ ተቋማት ከባንክ ለመበደር ሲሄዱ ኮላተራል አያስፈልጋቸውም፤ የውጭ ምንዛሬ ቅድሚያ ይሰጣቸዋል፡፡
እንደ ኤፈርት፣ ጥረት --የመሳሰሉትን ማለትዎ ነው? ኢንዶውመንት የሚሉት---
አዎ! እነዚህ ኢንዶውመንት አይደሉም፤ የንግድ ድርጅቶች አይደሉም ለማሰኘት ነው ኢንዶውመንት የተባሉት እንጂ በተግባር የንግድ ድርጅቶች ናቸው፡፡ ኢንዶውመንት ቢሆኑ ኖሮ፣ ሰብአዊ ስራ ላይ ይሰማሩ ነበር፡፡ አሁን ሶማሌ ክልል ሲራብ፣ ሰዎች በግጭት ሲፈናቀሉ----የትኛውን እርዳታ ነው የሰጡት? ኢንዶውመንት ማለት እኮ እርዳታ የሚሰጥ ትርፍን የማያሰላ ማለት ነው፡፡ እነ ኤፈርት ግን በተግባር ኢንዶውመንት አይደሉም፡፡
የእነዚህ ድርጅቶች እጣ ፈንታ ምን መሆን ነው ያለበት?
እነዚህ ተቋማት ሊበራላይዝ መደረግ አለባቸው። እንደ ማንኛውም የንግድ ድርጅት ነው መዋቀር ያለባቸው፡፡ ኤፈርት የትግራይ ህዝብ ድርጅት ነው ከተባለ፣ በንግድ ድርጅትነት ተመዝግቦ በአግባቡ መስራት አለበት፡፡ የህወሓት ነው ከተባለ ደግሞ እንደ ማንኛውም ድርጅት ግብር እየከፈለ፣ እያተረፈ እየከሰረ መኖር አለበት፡፡ በአጠቃላይ የህዝብ መሆን አለባቸው፡፡
መንግሥት በነፃ ገበያው ውስጥ ያለው ጣልቃ ገብነት ምን ድረስ ነው?
መንግሥት መሰረተ ልማት ነው መስራት ያለበት። ለምሳሌ የኃይል ማመንጫ ግድብ፤ ባቡር፣ መንገድ-- መንግስት ይሰራል፡፡ የግል ሴክተሩ ሊገባ የማይችልበት ቦታ መግባት አለበት፡፡ አሁን ግን በኛ ሁኔታ ኮንዶሚኒየም እንኳ የሚገነባው መንግስት ነው፡፡ በቂ ኮንትራክተሮች እያሉ ነው መንግስት ኮንዶሚኒየም የሚሰራው፡፡ አንዳንዴ እንደውም ኮንዶሚኒየም ጠፋ እየተባለ መንግስት መሳለቂያ ሲሆን አይተናል። በነፃ ገበያ መንግስት ያለበት ኃላፊነት፣ የተቆጣጣሪ ኤጀንሲ ማቋቋም ነው፡፡ ከፍተኛ ባለሙያዎች በኤጀንሲው ተቀምጠው ገበያውን የሚቆጣጠሩ (ሪጉላቶሪ) መሆን አለባቸው፡፡ ለምሳሌ ናይጄሪያ ውስጥ እኔ ነኝ ያቋቋምኩት፤ እስከ ዛሬ ይሰሩበታል። ጥሩ ሪጉላቶሪ ኤጀንሲ ካለ፣ የአለም ገበያ ቢዋዥቅ እንኳ ቀውስ ውስጥ ከመግባት ይታደጋል፡፡ በሁሉም ሴክተር ተቆጣጣሪ አካላት ያስፈልጋሉ፡፡ መንግስት ኮንዶሚኒየም ከመገንባት፣ ዘይት ከመቸርቸር ወጥቶ፣ መሰረተ ልማትና ቁጥጥር ላይ ማተኮር አለበት፡፡ እዚህ ሃገር እኮ መንግስት የናይት ክለብ ባለቤት ሁሉ ነበር። ሆቴሎች፣ ናይት ክለቦች ነበሩት፡፡ አሁንም ሂልተንና ጊዮን የመንግስት ናቸው፡፡ ይሄ ተገቢ አይደለም፡፡ አሁን ለሌብነት የተመቸ አሰራር ነው ያለው፡፡
የኢትዮጵያ ህዝብ አሁን ለስራ ተነሳስቷል፡፡ የአገልግሎት ዘርፉ የግብርና ዘርፉን በእጅጉ ጥሎት አድጓል፡፡ ይህ የሆነው ደግሞ መንግስት ሰውን ነፃ አድርጎ አላሰራ ስላለ ነው፡፡ አሁን ክፍለ ከተማ፣ ወረዳ የሚባሉት በጭራሽ የማይደረስባቸው፣ በመሳሪያ የሚጠበቁ ኃላፊዎች ያሉባቸው ቦታዎች ሆነዋል፡፡ በተለይ በመሬት አካባቢ ያለው ሙስና ደግሞ የትየለሌ ነው፡፡ ስለዚህ ይበልጥ ነፃ ገበያ ባመቻቸን ቁጥር ሙስናን እየቀነስን ነው የምንሄደው፡፡
ፕሬዚዳንቱ በንግግራቸው የጠቆሟቸው የኢኮኖሚ እድገት አቅጣጫዎች ምን ያህል የመተግበር እድል አላቸው?
ገዥው ፓርቲ ከዚህ በኋላ ምርጫ ያለው አይመስለኝም፡፡ ምክንያቱም እነዚህ ተወዳዳሪ ፓርቲዎች መግቢያ ቀዳዳ የሚያገኙት በኢኮኖሚና በንግድ፣ በኑሮ ውድነቱ ላይ ነው፡፡ በተለይ የግል ዘርፉ አለማደግ አጀንዳቸው ሊሆን ይችላል፡፡ ስለዚህ ገዥው ፓርቲ ምርጫ የለውም፡፡ በፍጥነት ማስተካከያ መውሰድ መቻል አለበት፡፡ እንደ ሜቴክ አይነት ድርጅቶች ላይ ውሳኔ ማሳለፍ አለበት፡፡ ስኳር ፋብሪካን መንግስት የሚገነባበት ምክንያት ለኔ አይገባኝም፡፡ ስኳር ፋብሪካ በግሉ ሴክተር መሥራት የሚቻል ነው። መንግስት የስኳር ልማትን በራሱ ይዞ አኮላሽቶታል፡፡ የሀገር ውስጥ ባይችሉ የውጪ ኢንቨስተሮች ጠንቅቀው ሊሰሩበት የሚችል ሴክተር ነው፡፡ ታዲያ የሚመጡ ኢንቨስተሮች ተጠንተው፣ አቅማቸው ተፈትሾ መሆን አለበት፡፡ ለምሳሌ ያገለገሉ ማሽኖችን እንደ ኮላተራል ማስያዣ የሚያቀርቡ የውጭ ባለሀብቶች አሉ፡፡ ይሄ መፈተሽ አለበት፡፡ ይሄን ለማድረግ ባንኮች መጠናከር አለባቸው፡፡ አሁን ልማት ባንክ ብቻ ስለሚሰራ በቀላሉ በዚህ በኩል ለመጭበርበር የተጋለጠ ነው፡፡
ሌላው የሚታየኝ ችግር፤ አዳዲስ ሀሳብና ተሞክሮ ያላቸውን ሰዎች ወደ ፋይናንሱ አመራር ያለማምጣት ነገር  ነው፡፡ በውጭ ሃገር ብዙ ልምድ ያካበቱ፣ እዚህም ብዙ ልምድና እውቀት ያላቸው ሰዎች አሉ። ለምን በቦታው አይመደቡም? አንዱ ችግር ደሞዝ ይመስለኛል፡፡ አንድ ሚኒስትር 400 ዶላር በወር እየተከፈለው ትልቅ የፋይናንስ ተቋም እንዲመራ ሲደረግ፣ በስሩ ያሉት በትንሽ ደመወዝ ሲቀጠሩ ምን ታስቦ ነው? ሙስና እናላለን፤ነገር ግን ይሄስ መጤን የለበትም? አነስተኛ ደሞዝ እየተከፈሉ የሚሊዮን ዶላር ፕሮጀክት የሚፈቅዱ ባለሙያዎችን ነው በቦታው የምናስቀምጠው፡፡ የግል ባንኮች ዛሬ ለአመራሮቻቸው በወር የሚከፍሉት ከ100 ሺህ ብር በላይ ነው። የመንግስት መዋቅር ግን ይሄን አይፈቅድም፡፡ ጠቅላይ ሚኒስትር መለስ 6 ሺህ ብር ነበር ደመወዙ፤ እሱ በመንግስት ወጪ ነው የሚንቀሳቀሰው ብንል እንኳ ከሱ በታች ያሉ ሰዎች እንዴት ነበር የሚኖሩት? የደመወዝ ማነሱ ለሙስና ያጋልጣል፡፡ ባለሙያ ያሸሻል፣ ይህ ደግሞ የባለሙያ እጥረት ይፈጥራል። አማራጭ የሌላቸው ሰዎች ብቻ ናቸው ሳይወዱ በግድ ለመኖር ሲሉ በአነስተኛ ደመወዝ የሚቀጠሩት፡፡ አንዳንዴ ስለ ሙስና ሲያወሩ ከውጪ የመጣ ወረርሽኝ እንጂ ራሳቸው ጋ ያለ አይመስልም፡፡ እነዚህ ሰዎች ቢሮክራሲ ቢፈጥሩ ምን ይደንቃል፡፡ በአንድ ወቅት ግማሽ ሚሊዮን ሄክታር መሬት ተረክበው የነበሩ የውጪ ሃገር ባለሀብቶች፣ በመንግስት ቢሮክራሲ ተማረው ጥለው ወጥተዋል የሚል ዜና ተነግሮ ነበር። ግማሽ ሚሊዮን ሄክታር መሬት እኮ በአግባቡ ከለማ የኢትዮጵያን ህዝብ ይቀልባል፡፡ ግን ቢሮክራሲው ያንን እድል ይዞ ገደል ከተተው ማለት ነው፡፡ ስለዚህ መንግስት ብዙ ነገር ማስተካከል አለበት፡፡ ይህቺ ሃገር ባለሙያ አላጣችም፡፡ ወደ 3 ሚሊዮን ዜጎች ለባዕዳን ውድ ሙያቸውን ሸጠው ነው የሚያድሩት፡፡ ይሄን አቅማቸውን እውቀታቸውን ለሃገር ቢያውሉት ብሎ ማሰብ ያስፈልጋል፡፡ እንዲያውሉት ደግሞ ጥሩ ደመወዝ ያስፈልጋቸዋል፤ ስለዚህ መንግስት በዚህ በኩል አብዝቶ ማሰብ አለበት፡፡
ይህቺ ሀገር ማንኛውም ኢትዮጵያዊ ሊያገለግላት የሚችልባት መሆን አለባት፡፡ ዝም ብሎ 8 ሚሊዮን አባላት አሉን፤ እነሱ ይስሩ ማለት ሃገር መግደል ነው፡፡ ለዚህ ለዚህማ ደርግም 6 ሚሊዮን አባላት ነበሩኝ ይል ነበር፡፡ ነገር ግን በሽግግሩ ጊዜ አንድም አባል ነን የሚል አልተገኘም፡፡ ከሚኒስትሩ በታች ያለ ሰራተኛ ሁሉ ማስታወቂያ በጋዜጣ ወጥቶ፣ ተወዳድሮ ነው መቀጠር ያለበት፡፡ እኛ ሀገር እኮ ባለሙያ ሳይቀር በፓርቲ አባልነት ነው የሚሾመው እንጂ በሙያው አይደለም፡፡ አንድ ክፍለ ከተማ ውስጥ ሲኬድ የአራቱም የኢህአዴግ ግንባር ድርጅት አባላት በእኩል መገኘት አለባቸው ተብሎ፣ የባለሙያውን ቦታ በኮታ ተከፋፍለውት ነው የተቀመጡበት፡፡ ይሄ ለሀገሪቱ መጥፎ ነው፡፡ ሙሉ በሙሉ መቀየር አለበት፡፡ የዚህ ዓመት አንዱ ትኩረት፣ ይሄ መሆን አለበት፡፡ መንግስት ከንግድ መውጣት አለበት ሲባል ቤት ከማከራየትም መውጣት አለበት። በደርግ የተወረሱ ቤቶች ለባለቤቶቹ መመለስ አለባቸው፡፡ አሁን የኢትዮጵያ ህዝብ ብዙ ነገር ያውቃል፤ ስለዚህ ይሄ መንግስት ብልጥ መሆን አለበት። ብዙ ማሻሻያ ማድረግ ይጠበቅበታል፡፡
አንዱ የመንግስት የትኩረት አቅጣጫ ሙስናን መዋጋት የሚል ነው … ሙስናን ለመቀነስ ምንድን ነው መደረግ ያለበት?
ሙስና የሚባለው ትርጓሜው፣ የመንግስትና የህዝብ ገንዘብ ያለ አግባብ መባከን ነው፡፡ የመንግስትን ስራ በአግባቡ አለመስራት ሙስና ነው፡፡ በኛ ሃገር ያለው ግልፅ የቀን ዘረፋ ነው፡፡ የስኳር ፋብሪካዎች ዘረፋ ተብሎ የሚወራው በቢሊዮን የሚቆጠር ነው፡፡ ስለዚህ ግልፅ የቀን ዘረፋ ነው፤ ሙስና፡፡ ተቆጣጣሪውና መሪው በእኩል ስልጣን ነው እየተንቀሳቀሱ ያሉት። ተቆጣጣሪው ሰሪውን ለመንካት የፈራበት ዘመን ነው፡፡ ተቆጣጣሪውና ሰሪው ተመሳጥረው ነው አብረው የሚሰሩት፡፡ በየመስሪያ ቤቱ ያለው የውስጥ ኦዲተር ተመሳጥሮ ነው የሚሰራው፡፡ በየመስሪያ ቤቱ በኦዲተርነት መመደብ ያለባቸው ሃይማኖት ያላቸው፣ በስነምግባር የታነጹ፣ የህዝብ ሃብት ግድ የሚላቸው መሆን አለባቸው፡፡ ደሞዛቸው በበቂ እነሱንና ቤተሰባቸውን የሚያኖራቸው መሆን አለበት፡፡ ይሄ ሁሉ ህንፃ አዲስ አበባ ውስጥ ከየት በመጣ ብር ነው የሚሰራው? ተብሎ ቢጠየቅ እኮ ብዙ ጉድ ይወጣል። አሁን የምናወራው ስለ ጉቦ አይደለም፤ ስለ ዘረፋ ነው፡፡ ለዚህ ነው የበለጠ መንግስት ከንግድ ውስጥ ራሱን ማውጣት አለበት፡፡ የማይነኩ ሰዎች መነካት አለባቸው፤ የፖለቲካ ፍራቻ መቅረት አለበት። ሙስናን ለመዋጋት የሲቪክ ማህበረሰብ መደራጀት አለበት፡፡ ሚዲያዎች አቅማቸው ተጠናክሮ ወደ ምርመራ ዘገባ ማተኮር አለባቸው፡፡ ሚዲያዎች ይሄን ሚናቸውን እንዲወጡ ማጠናከር ያስፈልጋል፡፡ ዛሬ በኛ ሃገር ያሉ ሚዲያዎች ስለ ሙስና ቢያጋልጡ ከለላ የላቸውም። ጡንቻ ያለው አካል አንጠልጥሎ እስር ቤት ነው የሚከታቸው፡፡ ስለዚህ ሚዲያዎች አስተማማኝ ዋስትና ያስፈልጋቸዋል፡፡ በየትኛውም ዓለም ትልቁ የሙስና አጋላጭ መዋቅር ሚዲያው ነው፡፡ አሁን በዋናነት ጥፋት እየሆነ ያለው፣ መንግስት ብቻውን ሁሉንም ነገር ልቆጣጠር ማለቱ ነው፡፡     

Read 2985 times