Saturday, 20 October 2018 13:28

“የአዲስ አበባ ወጣቶች እስር ህጋዊ መሰረት የሌለው ነው” - የህግ ባለሙያዎች

Written by  አለማየሁ አንበሴ
Rate this item
(2 votes)

“ያለአግባብ የታሰሩና የተቀጡ ካሉ፣ ለለውጡ እንደከፈሉት ዋጋ ሊያዩት ይገባል” - ጠ/ሚኒስትር ዐቢይ


    ለአንድ ወር ያህል በጦላይ ወታደራዊ ማሰልጠኛ ታስረው ሲሰለጥኑ ነበር የተባሉ 1ሺ174 የአዲስ አበባ ወጣቶች፤ ከትላንት በስቲያ ከእስር የተለቀቁ ሲሆን የወጣቶቹ እስርም ሆነ የግዳጅ ስልጠና ህጋዊ መሰረት የሌለው ነው ሲሉ የህግ ባለሙያዎች ተችተዋል፡፡  
ወጣቶቹ በጦላይ ወታደራዊ ማሰልጠኛ በቆዩባቸው ጊዜያት በህገ መንግስት፣ በሰላም አስፈላጊነት፣ እራስን ከወንጀል ስለ ማራቅና ተያያዥ ስልጠናዎች ወስደው ማጠናቀቃቸው የተገለፀ ሲሆን ከማሰልጠኛው ሲወጡም፤ “ሰላም ለሁላችንም ስለሆነች እንጠብቃለን” የሚል ቲ-ሸርት ለብሰው ታይተዋል፡፡
የወጣቶቹ እስርና ስልጠና የህግ አግባብነት ያለው መሆኑን የተጠየቁ የህግ ባለሙያዎች በሰጡት አስተያየት፤ የመንግስት ድርጊት የሀገሪቱን ህገ መንግስትም ሆነ የወንጀለኛ መቅጫ ህጉን የተፃረረ ነው ብለዋል፡፡  መንግስት በወንጀል የጠረጠረውን ግለሰብ፣ በ48 ሰዓት ውስጥ ለፍ/ቤት የማቅረብና በማስረጃ ከስሶ የማስቀጣት መብት እንጂ ሰዎች በኃይል ሰብስቦ፣ ወታደራዊ ማሰልጠኛ ውስጥ በማስገባት የግዳጅ ስልጠና የመስጠት ህጋዊ መብት እንደሌለው ባለሙያዎቹ ገልጸዋል፡፡ መንግስት ለዚህ የህግ ጥሰት ወጣቶቹንና የኢትዮጵያን ህዝብ ይቅርታ መጠየቅ እንዳለበትና ወጣቶቹ ላባከኑት ጊዜና የሞራል ጉዳት ካሳ መክፈል እንደሚገባውም አስረድተዋል።   
ጠ/ሚኒስትር ዶ/ር ዐቢይ አህመድ ሰሞኑን ለፓርላማ በሰጡት ማብራሪያ፤ በወቅቱ በከተማዋ የተፈጠረው ችግር አደገኛ አዝማሚያ የነበረው በመሆኑ ተገቢው ማጣራት ሳይካሄድ የታሰሩ ወጣቶች መኖራቸውን ጠቁመው፤በእስሩ ማግስት በደረሳቸው መረጃም የተወሰኑ ወጣቶችን አጣርቶ ለመፍታት መቻሉን ተናግረዋል፡፡ “ወጣቱን ሰብስቦ የማሰርም ሆነ የማንገላታት ፍላጎት የለንም” ሲሉም አስረድተዋል፡፡
ለውጡን እየመራን ያለነው በየቀኑ በህይወታችን ተወራርደን ነው ያሉት ጠ/ሚኒስትሩ፤”ከአዲስ አበባ ወጣቶች መካከል ያለ አግባብ ለእስር የተዳረጉና የተቀጡ ወጣቶች ካሉ፣ የተቀበሉትን መከራ ለለውጡ እንደከፈሉት ዋጋ ሊያዩት ይገባል” ብለዋል፡፡   

Read 3259 times