Saturday, 20 October 2018 13:49

ሥነምግባር ጠፍቶብን እንጠፋፋ?

Written by  ዮሃንስ ሰ
Rate this item
(7 votes)


 • የሥነምግባር ባዕድ እየሆንን ነው - ፖለቲካውም ምኑም ምኑም....
 • ጠ/ሚ ዐቢይ በፓርቲያቸው ጉባኤ ላይ እንደተናገሩት፣ ዋናው የአገራችን የችግሮች ምንጭ የስነ ምግባር ብልሽት ነው፡፡
 • ከእውነት ብርሃን፣ ከስኬት መንገድ፣ ከተከበረ ሕይወት መራራቅ ብቻ ሳይሆን መጣላት!
       

   እውነትንና እውቀትን የሚያከብር የአገራችን ጥንታዊ ትምህርት የት ቀረ?
ክብረነገሥት የተሰኘው መጽሐፍ ውስጥ በንግሥት ሣባ ሕይወት ላይ ያተኮረውን ትረካ በአጭሩ እንመልከት። ጽሑፉ ንግሥቲቱን ሲያደንቅ ሦስት ፍሬ ሃሳቦችን ይጠቅሳል።
በእውቀት የመጠቀች፣ በብሩህ የአእምሮ ብቃትዋም በጣሙን የላቀች ንግሥት ናት - የእውነትን ብርሃን የምትፈነጥቅ የእውቀት ፋና።   
ትጉህ ሙያተኞች በየመስኩ እጅጉን የበዛ ሃብት እንዲፈጥሩና ኑሮን እንዲያለመልሙ፣ … በባህርና በምድር፣ ሥራ ሁሉ እንዲያፈራ፣ ንግድም እንዲሳለጥ፣... በጥበቧ ትክክለኛውን ሥርዓት ያፀናች፣... መልካም ዓላማና እቅድም በብልህ ጥረት ለፍሬ እንዲበቃና ኢላማውን እንዲመታ፣... መነሻውና መድረሻው እንዲገናኝ አቅጣጫውን የምትቀይስ፣ ጉዞውንም የምታቃና፣ ፈር-ቀዳጅ ንግሥት ናት - የስኬት መንገድን ያሳየች የተባረከች ንግሥት።
በድንቅ ብቃቷ ግርማዊ ክብርን እና ቅድስናን የተቀዳጀች ንግሥትም ናት - ወደርየለሽ ውብ ገፅታዋና ማራኪ ቁመናዋ፣ ብሩህና ክቡር ማንነቷን የሚያንፀባርቁና የሚመሰክሩ ናቸው። ሕይወቷ በሙሉ፣ ሰው የመሆን ድንቅ ክብርን በአርያነት ያሳያል፡፡ መቀዳጀትንና ማድነቅን አሳይታለች። ብቃትን፣ ጀግንነትንና የላቀ ራዕይን የራሷ በማድረግ፣ ልዕልናን ተቀዳጅታለች። በዚያው ልክ፣ የሌሎችንም ብቃት በማድነቅ፣ ጀግንነትን በማሞገስ፣ የላቀ ራዕይንም ከልብ በማፍቀር ጭምር መርታለች። በአጭሩ፣... በህልውናዋ፣ የተቀደሰ ሕይወትን በእውን አሳይታለች።
እንዲያም ሆኖ፣ በጥበብ ተራቅቄ፣ በእውቀት መጥቄ ጨርሻለሁ አላለችም። የንጉሥ ሰለሞንን የጥበብ ዝና ሰምታ፣ በአድናቆትና በጉጉት ሄዳ ለማየት የወሰነችበትን ምክንያት ለአገሯ ሰዎች እንዲህ ስትል ታስረዳለች፡-
“ነፍሴ ጥበብን ትሻለች። ልቤ እውቀትን ለመጨበጥ ታስሳለች። በጥበብ ፍቅር ተማርኬያለሁ፣ በእውቀት አውታሮች ተከብቤያለሁ። ጥበብ፣ … ከከበረ ወርቅና ብርም ይልቃልና። ጥበብ በምድር ላይ ከተፈጠሩት ነገሮች ሁሉ ይበልጣልና። ከሰማያት በታች፣ ከጥበብ ጋር የሚስተካከልስ ነገር ምን አለ?” ትላለች ንግሥቲቱ።
በመቀጠልም፣ ጥበብ፣ … መንፈስንና ውበትን፣ ሕይወትንና ሰብዕናን፣... ኑሮንና ደህንነትን፣ ሥራንና እንቅስቃሴን፣... ሃሳብንና ንግግርን ሁሉ የምታስተካክል፣ የምታቃናና የምታሳምር መሆኗንም ትገልጻለች።
ጥበብ፣... “ለልብ ደስታ፣ ለዓይን ፍንትው ያለ ደማቅ ብርሀን፣ ለእግር ግስጋሴ፣... ለደረትም ጋሻ፣ ለራስም መከታ፣ ለአንገትም ሃብል፣ ለወገብም ቀበቶ ናት” በማለትም ታወድሳለች። የመንፈስ ደስታና የሕይወት እርካታን፣ የኑሮ ስኬትና ጣዕምን፣ እውነትንም የምታሳይ ከፀሐይ የላቀች የአእምሮ ብርሃን እንደሆነች ትናገራለች - ንግሥቲቱ እውቀትን ስታወድስ።  
ያለ ጥበብ “አገርና መንግስት፣ ሕግና ሥርዓት፣ አይቃናም። ያለ ጥበብ ሃብትና ንብረት አይበረክትም። ያለ ጥበብ፣ እግር በተራመደበት መሬት ላይ ፀንቶ መቆየት አይችልም። ያለ ጥበብ፣ የአንደበት ንግግርም አይጨበጥም።” በማለት ታስተምራለች።
“ጥበብ ለኔ ... ስልጣኔና ኃይል ትሆንልኛለች። ጥበብ ለኔ፣ የተትረፈረፈ በረከት ትሆንልኛለች” በማለት፣ ጥበብንና እውቀትን ስለ መሻት፣... ጥበብን ስለ ማፍቀር፣... እውቀትን ስለ ማክበር... ከነጥቅሙ፣ ከነበረከቱ ምን እንደሚመስል ከተናገረች በኋላ ነው፣... ለጥበበኛና ለአዋቂ ሰው ያላትን አድናቆትና ክብር የምትገልፀው።
“ጥበብን ማክበር፣ ጥበበኛውን ማክበር ነው። ጥበብን ማፍቀር ጥበበኛውን ማፍቀር ነው።” ትላለች። ጥበብን መሻትም ጥበበኛውን መሻት ስለሆነ፣ ለረዥም ጉዞ መነሳቷን አስረዳች።
የአገሬው ሰዎችም እንዲህ ሲሉ መለሱ። “እመቤታችን ሆይ፣... ጥበብ እንኳ ሞልቶሻል። የጥበብ እመቤት በመሆንሽም ነው፣ ጥበብን ማፍቀርሽ” በማለት አድናቆታቸውን ገልጸዋል።
እንግዲህ ይታያችሁ። ከምዕተዓመታት በፊት በኢትዮጵያ የነበረ ይህን የመሰለ የስነምግባር ትምህርትንም እንኳ አጥተናል።

ከጥንቶቹም በታች ሆነናል? 4ሺ ዓመታት የኋሊት!
ጥንታዊያኑ የግብፅ አዋቂዎች ያስተማሩት የስነምግባር መመርያ፣ “ሀሰት”ን ከመንቀፍ የሚነሳና “እውነት”ን በማክበር ላይ የተመሰረተ ነው። ግን፣ በዚያ ብቻ የታጠረ አይደለም። የእውነትን ብርሃን፣ የስኬትን መንገድና የተቀደሰ ሕይወትን ሁሉ ያካትታል።  
“እውነትም፣ መንገድም፣ ሕይወትም እኔ ነኝ” እንደተባለው ነው። ሀሳብንና ንግግርን፣ ተግባርንና ኑሮን፣ ባህርይንና ሰብዕናን እንዴት መምራት ይገባል? እውነትን በሚያፀድቅ የአእምሮ ብርሃን፣ መንገድን በሚያቃና፣ ሕይወትን በሚያለመልም ሥርዓት ሁለመናችንን መምራት እንደሚገባ ይጠቁማል - በግብፅ ከ4000 ዓመታት በፊት የነበረው የስነምግባር ትምህርት።
በጥቅሉ፣ መልካም ስነምግባር ማለት የ”ሥርዓት” ባለቤት መሆን ማለት ነው። ማለትም... - ብሩሁን እውነት የወደደና የጸደቀ አእምሮ፣ ቀናውን መንገድ የመረጠና የተባረከ ኑሮ፣ ድንቅ ብቃትን ያከበረና የተቀደሰ ሕይወት።
በሌላ አነጋገር፣ ብሩህ እውነትን፣ ቀና መንገድንና የተቀደሰ ሕይወትን ከሚቃረን ነገር ጋር መነካካት፣ መቀራረብና መቆራኘት አይገባም ማለት ነው። ይህንንም ነው፣ የጥንቱ ዘመን የግብፅ አዋቂዎች፣ ከሺ ዓመታት በፊት፣ በዝርዝር ሲያስተምሩ የነበሩት። የመደበኛ መመሪያ ያህል ሰፊ ተቀባይነት ያገኘውና 42 ነጥቦችን የያዘው የስነምግባርና የግብረገብነት ማስተማሪያና ማስመስከሪያ ፅሁፍን መመልከት ይቻላል። ከንጉሥ እስከ ገበሬ፣ ከቤተ መንግሥት እስከ መኖሪያ ቤት፣ … በሁሉም ስፍራ የማይጠፋ … ከሕይወት ከአጠገብ የማይለይ ማዕተብ እንዲሆንላቸው የሚመኙት ፅሁፍ ነው … አብዛኞቹ የጥንት ዘመን ግብፆች፡፡ እስቲ የሥነ ምግባር ነጥቦቹን አንድ በአንድ እንያቸው፡፡
• (ሀ) እውነትን እውቀትን የሚያስተምሩ፣ ከአላዋቂነት  የሚገስፁና ከሀሰት ከቅጥፈት ጋር አለመነካካትን የሚመሰክሩ (20 ነጥቦች)።  
1. አልዋሸሁም።
2. ለእውነት ጆሮዬን አልደፈንኩም።
3. በሀሰት ሰውን አላብጠለጠልኩም።
4. በሀሰት መንግስትን አላጥላላሁም።
5. በሀሰት ቅዱስን አላራከስኩም፡፡
6. አሳባቂ አልሆንኩም።
7. ሐሜተኛ አልሆንኩም።
8. ወሬ አነፍናፊ አልሆንኩም ።
9. አስመሳይ አልሆንኩም።
10. አጋናኝ ጉረኛ አልሆንኩም።
11. አላመነዘርኩም።
12. ዝሙት አልፈፀምኩም።
13. ራሴን ደብቄ አልባለግኩም።
14. የተፈጥሮ ማንነቴን አላዛባሁም።
15. ግልፍተኛ አልሆንኩም።
16. አኩራፊ ነጭናጫ አልሆንኩም።
17. ችኩል አልሆንኩም።
18. ቀባጣሪ አልሆንኩም።
19. በጩኸት አልተናገርኩም።
20. ያልተገባ ነገር አልበላሁም።
• (ለ) ቀና መንገድን የሚያስተምሩ፣ የሰው ንብረት አለመንካትን የሚመሰክሩ (15 ነጥቦች)።
21. አልሰረቅኩም፡፡
22. ራሴ ከማፈራው ንብረት ውጭ፣ ሌላ አላሻኝም።
23. የሰውን ንብረት አልከጀልኩም።
24. ንብረቴን አስከብራለሁ እንጂ በሌላ ንብረት ላይ ውዝግብ አላስነሳሁም።
25. አልዘረፍኩም።
26. ሸፍጥ አልፈፀምኩም።
27. ወሮበላ አልሆንኩም።
28. አልመዘበርኩም።
29. የእለት ጉርስ ቀማኛ አልሆንኩም።
30. ከድርሻዬ እላፊ ለራሴ አላዳላሁም።
31. ከመካነ እምነት  አልሰረቅኩም።
32. አላጭበረበርኩም።
33. ልክ አላጎደልኩም።
34. ወንዝ አላቆሸሽኩም።
35. አልበደልኩም።
• (ሐ) ሕይወትን ማክበር የሚያስተምሩ፣... ሰው አለመንካትን የሚመሰክሩ (6 ነጥቦች)።
36. አልገደልኩም።
37. ሰውን አልነካሁም።
38. ሽብር አልፈጠርኩም።
39. ረብሻ አልቀሰቀስኩም።
40. ተጋፊ እብሪተኛ አልሆንኩም።
41. ለጥፋተኞች ፊት የሚሰጥ ሾላካ አልሆንኩም።
• በአጠቃላይ፣...
42. ክፋት አልሰራሁም።
(ትርጉሙ፣... በሃሳብ፣ በተግባርና በባሕርይ፣...  አልሰነፍኩም፣ አልሸፈጥኩም፣ አልሸፈትኩም። እውነትንና እውቀትን አልተውኩም። ቀና መንገድን፣ ሰርቶ መኖርን አልጣስኩም። ቅድስናንና ብቃትን አላፈረስኩም።)
“የእውነት ባለቤት የሆንከው የእውነት ጌታ ሆይ፣ ባንተ ስም ሐሰትን አስወግጄ፣ እውነትን ይዤ፣ እነሆ አንተ ዘንድ መጥቼ ከፊትህ ቀርቤያለሁ” በማለት ነው፣ 42ቱን የስነምግባር ነጥቦችና ምስክርነቶችን የሚዘረዝረው። (Lord} of Truth is your name. Behold, I have come before you bringing to you Truth, having repelled for you falsehood.)
ሲጨርስም፣ በሃሳብና በንግግር ፅዱ መሆኑን፣ በተግባርና በኑሮ ንፁህ መሆኑን፣ በባህርይና በሰብእናም ስመጥር መሆኑንም ይናገራል። እንዲህ ይላል፤...
“ከፊታችሁ መጥቼ የቀረብኩት፣ ያለ ሃሰት፣ ያለ በደል፣ ያለ ክፋት ነው። በእውነት ነው የምኖረው፤ እናም እውነት ይገባኛል። አፈ ፅዱ፣ እጀ ንፁህ፣ ስመ ጥሩ ነኝ።”
ይሄ፣ 4000 ዓመታትን ያስቆጠረ የስነ ምግባር ትምህርትና መመሪያ ነው። ይህንን እንኳ መማር ያቅተናል?
ካሁን በፊትም እንደጠቀስኩት፣ የእስራኤል የጥንት የስነምግባር ትምህርቶችንም ማየት ይቻላል።

ሺ ዓመታት ያስቆጠረ ስነምግባር ጠፍቶብን እንጠፋፋ?
እውነትን ያዝ፣ በእውነት ተመራ ለማለት አይደለም እንዴ፣ “አትዋሽ፣ በሃሰት አትመስክር” የተባለው?
የኑሮ አላማህን በራስህ ጥረት ተግተህ አሳካ፣ የግል ንብረትን አክብር ለማለት አይደለም እንዴ፣… በሌሎች ንብረት ላይ አታሰፍስፍ፣ የሌሎችን “አትመኝ”፤ “አትስረቅ” የተባለው?
ባልንጀራህን እንደ ራስህ መዝን፣ መልካምን ሰው ውደድ፣ አንዱ የሌላውን ሕይወት አይድፈር ለማለት አይደለም እንዴ፣ “ባልንጀራህን እንደ ራስህ ውደድ። አትግደል” የተባለው?
አርአያዎችን፣ የበቁ ሰዎችን፣ ቅዱስን አድንቅ፣ አክብር፣ አወድስ፤… አታርክስ፣… ለማለት አይደለም እንዴ፤… ራስህንና ፍቅርን አክብር፣ አታርክስ ለማለት አይደለም እንዴ፣ “አታመንዝር” የተባለው። ሌሎችን አታርክስ - ይህን ሁሉ የሚያስተምሩህን አክብር ለማለት አይደለም እንዴ፣ “ወላጆችህን አክብር” የተባለው? ቅዱስን አክብር የተባለው?
እነዚህ መርሆችኮ፣ ድሮ ጥንት፣… ከአራት ሺህና ከሁለት ሺህ አመታት በፊት በኢትዮጵያና በግብፅ ስልጣኔ፣ በሜሶፖታሚያ በባቢሎን ስልጣኔ… መልክ ይዘው የሰፈሩና እጅጉን የሚከበሩ ቀዳሚ መርሆች ነበሩ።
በዛሬ ዘመን፣ ይህንንም አጥተን፣ እንጠፋፋ?
ኦሪት ዘጸአት ምዕራፍ 20 ላይ፣ እንዲህ ይዘረዝራል። አባትህንና እናትህን አክብር፤... በሐሰት አትመስክር።... አታመንዝር።... አትግደል።...  የባልንጀራህን ቤት አትመኝ... ከባልንጀራህ ገንዘብ ሁሉ ማናቸውንም አትመኝ።... አትስረቅ።...
ቀጣዮቹ ሦስት ምዕራፎች እነዚህን ነው የሚዘረዝሩት።
ምዕራፍ 21፣ በአብዛኛው ከስድብ እስከ ድብደባና ግድያ ድረስ፣ ሰውን የመንካት ጥፋቶችን ይዘረዝራል።
ምዕራፍ 22፣ በአብዛኛው ስርቆትን፣ የንብረት ድርሻንና ውሎችን የሚመለከቱ በደሎችን ይዘረዝራል።
ምዕራፍ 23 ደግሞ እንዲህ ሲል ይጀምራል።... “1፤ ሐሰተኛ ወሬ አትቀበል፤ ሐሰተኛ ምስክርም ትሆን ዘንድ ከኃጢአተኛ ጋር እጅህን አታንሣ።... 2፤ ክፉውን ለማድረግ ብዙ ሰዎችን አትከተል፤ ፍርድንም ለማጥመም ከብዙ ሰዎች ጋር ተስማምተህ አትመስክር።” በማለት ይቀጥላል።

በአጭሩ ምን ለማለት ፈልጌ ነው?
ዋና ዋናዎቹ የስነምግባር መርሆች በጣም ጥቂትና ግልፅ ናቸው።
ለእውነታ በታመነ የአእምሮ ንቃት አማካኝነት፣ እውቀትን ማዳበር መልካም የስነምግባር መርህ ነው። ከእውነት ብርሃን መሸሸግና ከእውነት መራቅ... ከዚያም አልፎ መጥላት ደግሞ፣ የመልካም ስነምግባር ፀር ነው።
ሙያን በወደደ ፍሬያማ ትጋት አማካኝነት ስኬትን በሚያቀናጅ ቀና መንገድ መጓዝ፣ መልካም የስነምግባር መርህ ነው። ከዚህ መስነፍና መዛነፍ፣ አፈንግጦ በጠላትነት ማመፅ ደግሞ ፀረ ስነምግባር ነው።
የግል ብቃትን ከልብ በሚያደንቅ፣ ራስን የመቻልና ራስን የማሻሻል ራዕይን በፅናት በመያዝ የምንገነባው ጠንካራ የእኔነት ሰብዕና … እጅግ የተቀደሰ ሕይወት ነው - ይሄ ነው የመልካም ስነምግባር ጉልላት። ከዚህ መርህ ውጭ መንሻፈፍ፣ መንሸራተትና አምፆ መሸፈት ደግሞ ፀረ ስነምግባር ነው።
እነዚህ ሦስት መሰረታዊ የስነምግባር መርሆዎች፣ ከላይ በጠቀስኳቸው የጥንት የስነምግባር ትምህርቶች ውስጥ ሳይቀር እናገኛቸዋለን። በዛሬው ዘመናችንና በዚህችው አገራችን ውስጥ ግን ለመሰረታዊዎቹ የስነምግባር መርሆች ባዕድ እየሆንን ነው።

Read 5473 times