Saturday, 20 October 2018 14:01

የኩባ ሪፐብሊክ እና ኢትዮጵያ፤ በደም የተሳሰረ ወዳጅነት

Written by  በድሉ ዋቅጅራ
Rate this item
(1 Vote)


   • ኩባውያን ከየትኛውም ወዳጅ ሀገር በላይ ኢትዮጵያን ደግፈዋል፤ድጋፋቸው በደም የተሳሰረ ነው
   • የኩባ አብዮትና አብዮታዊ መሪዎቿ፣ የኢትዮጵያ ተማሪዎች እንቅስቃሴ ማዳወሪያ ነበሩ
         

    በኩባና በኢትዮጵያ ወዳጅነት ከተከናወኑ ተግባራት መካከል ከፍተኛውን ቦታ የሚወስዱት የካራ ማራ ድል እና የመጀመሪያዎቹ የነጻ ትምህርት እድል ተሳታፊ ኢትዮጵያዊ ህጻናትና ወጣቶች ወደ ኩባ የተጓዙበት 40ኛ አመት፣ ባለፈው ሳምንት በተለያዩ ዝግጅቶች ተከብሯል፡፡ እኔም ይህንኑ ምክንያት በማድረግ የሁለቱን ሀገሮች ወዳጅነት በወፍ በረር ቃኝቸዋለሁ፡፡
የኩባ ሪፐብሊክ በእኩልነትና በጋራ መረዳዳት ላይ ያተኮረ የውጭ ግንኙነት ፖሊሲ ትከተላለች፤ ዓለምአቀፋዊነት (internationalism) እና በሌሎች ሀገሮች አስተዳደርና የውስጥ ጉዳይ ጣልቃ ያለመግባት የውጭ ግንኙነቷ ካስማ ነው፡፡ በኩባ የውጭ ግንኙነት ፖሊሲ፣ ከሀገሮች ጋር በፈቃደኝነት ላይ የተመሰረተ አብሮ የመሥራትና የመረዳዳት ግንኙነት ለመመስረት አብሮ ከመሥራት በቀር፣ በሌሎች ሀገሮች አስተዳደር ውስጥ ጣልቃ በመግባት፣ በማንኛውም መንገድ ተፅዕኖ መፍጠር የተኮነነ ነው፡፡ የኩባ የውጭ ግንኙነት ፖሊሲ የተመሠረተው ከጋራ መረዳዳትና ትብብር መርህ አንፃር እንጂ፣ ከሀገራት በምታገኘው ፖለቲካዊና ምጣኔ ሀብታዊ ትርፍ ስሌት አይደለም፡፡ በዚህም የተነሳ ኩባ ለሌሎች ሀገሮች ያደረገችው እርዳታ፣ በሀገራቱ ከተደረገላት ወይም ከተቀበለችው እጅግ የላቀ ነው፡፡
የኩባ ሪፐብሊክ በአፍሪካ አህጉር ከሚገኙ ሀገራት ጋር ሰፊና ጠንካራ ግንኙነት የጀመረችው በ1975 እ.ኤ.አ (በዚህ ጽሁፍ ውስጥ የተጠቀሱት አመታት በሙሉ እንደ አውሮፓ አቆጣጠር ናቸው) ከአንጎላ ጋር ቢሆንም፣ ከ1950ዎቹ መጨረሻ ጀምሮ ከሌሎች የአፍሪካ ሀገራት ጋር ግንኙነት መስርታለች፡፡ የኩባ ሪፐብሊክ በአፍሪካም ሆነ፣ በሌሎች የሶስተኛው ዓለም ሀገራት የተከተለችው ፖሊሲ አዎንታዊ ከመሆኑም በላይ ተቀባይነቱ ከፍተኛ ነበር፡፡
ምስራቅ አፍሪካን በተመለከተ ኩባ ከ1976 በፊት የነበራት ተጽእኖ ፈጣሪነት አነስተኛ ነበር፡፡ የኩባ ወታደራዊ ኤክስፐርቶች በሶማሊያ ውስጥ በሚገኙ የሶቭየት ህብረት የጦር ማሰልጠኛ ጣቢዎች ውስጥ በአሰልጣኝነት ይሰሩ ነበር፡፡ ይሁንና ኩባ እንደ ሶቭየት ህብረት የራሷን የጦር ማሰልጠኛ ጣቢያዎች ሶማሊያ ውስጥ የመመስረት ፍላጎት አልነበራትም። በተጨማሪም ለሶማሊያ ከምታደርገው ድጋፍ፣ ኢኮኖሚያዊ ጥቅም ማግኘትም አላማዋ አልነበረም፡፡ ከዚህም በተጨማሪ በምትከተለው የነጻነት ትግሎችን የመደገፍ ፖሊሲ የተነሳ የኤርትራ ነጻ አውጪዎችንም ትደግፍ ነበር፡፡
‹‹ኩባ›› የሚለው ስም ለመጀመሪያ ጊዜ ከኢትዮጵያ ጋር ተጣምሮ እንዲነሳ ያደረገው ኩባዊው ዴል ባዬ ነው፡፡ በ1935 - 36 ጣሊያን ኢትዮጵያን በወረረችበት ወቅት፣ በእንግሊዝ ውስጥ በለንደን ነዋሪ የነበረ ኩባዊ ነው፡፡ በወቅቱ ከኢትዮጵያውያን ጎን ተሰልፈው የሚዋጉ በጎ ፈቃደኞችን ለማስተባበር ዓለምአቀፋዊ እንቅስቃሴ ተመስርቶ ነበር፡፡ በሰሜን አሜሪካ ኒውዮርክ፣ በአውሮፓ ደግሞ ለንደን የዚህ እንቅስቃሴ ዋና ዋና ቦታዎች ነበሩ፡፡ ዴን ባዬ በዚህ ዓለምአቀፋዊ እንቅስቃሴ አማካይነት ወደ ኢትዮጵያ መጥተው፣ ከኢትዮጵያ ተዋጊዎች ጎን ከተሰለፉ ጥቂት ዓለምአቀፋዊ ተዋጊዎች መካከል አንዱ ነው፡፡ በወቅቱ ከዴል በተጨማሪ የቼክ ተወላጅ የሆነው አልዶልፍ ፓርልሳክ (Adolf Parlesak) እና ስዊድናዊው የህክምና ባለሙያ ጄራልድ ኒስትሮም (Gerald Nystrom) ይገኙበታል፡፡
ዴል ባዬ የተመለመለው አየር ኃይልን እንዲደግፍ ቢሆንም፣ በወቅቱ ወራሪዋ ኢጣሊያ እንጂ፣ ኢትዮጵያ የአየር ሀይል ስላልነበራት፣ ከእግረኛው የኢትዮጵያ ሠራዊት ጎን ተሰልፎ ተዋግቷል፡፡ ድል ለኢትዮጵያ ሆኖ፣ ነፃነት ከተመለሰ በኋላ፣ ዴል ባዬ ከንጉሱ ከአፄ ኃይለስላሴ የኮሎኔልነት ማዕረግ ተሰጥቶታል። እንዲሁም በወቅቱ ለኢትዮጵያውያን ተዋጊዎች መጠሪያ ከነበረው ጥቁር አንበሳ፣ አቻ የሆነ ‹‹ቀይ አንበሳ›› የሚል የጀግና ቅጽል ስም በንጉሱ ተሰጥቶታል።
ዴል ባዬ በኢትዮጵያ ውስጥ ያሳለፈውን ህይወት የሚተርክ፣ ‹‹White man in Black Hell›› የሚል መጽሐፍ፣ በ1936 አርቱሮ አልፎንሶ ሮሴሎ (Artuno Altonso Rosello) የተባለ ሰው በስፓኒሽ ቋንቋ ጽፎ አሳትሟል፡፡ ይህንን በአሉታዊ ርዕስ የተፃፈ መጽሐፍ፣ ተስፋዬ መኮንን ባይለየኝ፣ ‹‹ቀይ አንበሳ›› በሚል ርዕስ፣ ወደ አማርኛ ተርጉሞታል፡፡ በስፓኒሽ ቋንቋ የተፃፈው መጽሐፍ ምንም እንኳን ዴል ባዬ በኢትዮጵያ ያሳለፈውን ህይወት በዝርዝር ቢያሳይም፣ ርዕሱ ግን በወቅቱ ዓለም ለአፍሪካ የነበረውን ጨለምተኛ አመለካከት የሚያንፀባርቅ ነው (የኮንራድን ‹‹Dark Continent›› የተባለ ጽሁፍ ልብ ይሏል)፡፡
ታዋቂው የኢትዮጵያ ታሪክ፣ ባህልና ቋንቋ ተመራማሪ ሪቻርድ ፓንክረስት፣ ወደ ኢትዮጵያ መጥተው ታላቅ ተግባር አከናውነዋል ብለው ከሚጠቅሷቸው የውጭ ሀገር ተወላጆች መካከል አንዱ ዴል ባዬ ነው፡፡ ሪቻርድ ፓንክረስት ዴል ባዬን፣ ‹‹ከኢትዮጵያ ጋር ተሰልፎ የተዋጋ የኩባ አብዮታዊ›› (Cuban revolutionary who fought on the side of Ethiopian) ይሉታል፡፡ በርግጥ ዴል ባዬ ወደ ኢትዮጵያ በመጣበት ጊዜ የኩባ አብዮት አልተጀመረም፤ ይሁን እንጂ የኮሙኒስት ፓርቲው ቀደም ብሎ፣ በ1923 ተመስርቶ፣ የፖለቲካ ተቃውሞዎችን ያካሂድ ነበር፡፡ ከዚህ አንጻር ሲታይ በኢትዮጵያ የሚካሄደው ተጋድሎ ፀረ ቅኝ ገዢ አብዮት ነበር፡፡  
በኢትዮጵያ አብዮት ከመፈንዳቱና ኢትዮጵያና ኩባ ዲፕሎማሲያዊ ግንኙነት ከመመስረታቸው አስቀድሞ፣ በኩባ የተካሄደው አብዮት ለኢትዮጵያ ወጣቶች ታላቅ አብዮታዊ መቀስቀስ ሆኗል፡፡ ኩባ ያካሄደችው የተሳካ አብዮትና ከምዕራቡ ዓለም፣ በተለይ ደግሞ ከአሜሪካ ጋር ያሳየችው ጠንካራ ተገዳዳሪነት፣ ለኢትዮጵያ የተማሪዎች እንቅስቃሴና አብዮታዊ አመለካከት ለነበራቸው ቡድኖች አርአያና መቀስቀስ በመሆን የተጫወተው ሚና ቀላል አይደለም፡፡ የኩባው መሪ ፊደል ካስትሮ፣ ‹‹History will absolve me›› የሚለው መጽሐፍ በኢትዮጵያ ተማሪዎች ዘንድ እጅግ ተነባቢ ነበር፡፡ ከዚህም በላይ ቼ ጉቬራ የተራማጅ ሰብዕና ግብ ሆኖ በተማሪዎች፣ በየአደባባዩ ይዘመር ነበር፡፡
    ፋኖ ተሰማራ፣ፋኖ ተሰማራ፤
    እንደነ ሆቺሚን፣ እንደ ቼ ጉቬራ፡፡
ደሳለኝ ራህመቶ በ1970ዎቹ መጀመሪያ ላይ ስለነበረው የኢትዮጵያ ተማሪዎች እንቅስቃሴና የኩባ አብዮት ግንኙነት በተመለከተ እንደጠቀሰው፣ ለኢትዮጵያ ተማሪዎች እንቅስቃሴ የኩባ አብዮት ቅርጽ ከይዘቱ የበለጠ ጠቃሚ ነበር፡፡ ምክንያቱም ከቪየትናምና ከቻይና የአብዮት ልምድ በተለየ፣ ፊደል ካስትሮና ቼ ጉቬራ የተለየ አብዮታዊ ሰብዕና ያላቸውና የአብዮታዊና ተራማጅ ሰብእና ግብ ተደርገው ይወሰዱ ነበር፡፡ በዚህም የተነሳ የወጣቱ ግብ እንደ ኩባ አብዮት ያለ የተሳካ አብዮት ማቀጣጠል ብቻ ሳይሆን፣ እንደ ፊደል ካስትሮና ቼ ጉቬራ ያለ ተራማጅ ሆኖ ለመገኘትም ነበር፡፡
በ1974 የኢትዮጵያ አብዮት ከመፈንዳቱ አስቀድሞ፣ በ1970ዎቹ መጀመሪያ ኩባ የኢትዮጵያ አማጽያን (በተለይ የኤርትራ ነፃ አውጪ አማጽያንን) እና የሱማሊያን ናሽናሊስቶች ትደግፍ ነበር፡፡ ይህም በተማሪው እንቅስቃሴ ውስጥ የኩባ አብዮት ከተጨቆኑና ነፃነት ከተነፈጉ ህዝቦች ጎን የሚቆም ዓለምአቀፋዊ ሀይል ተደርጎ እንዲወሰድ አድርጓል። ምንም እንኳን በወቅቱ ኩባን የመጎብኘትና በኩባ በተዘጋጀ ጉባኤ ለመሳተፍ እድል የገጠመው ሀጎስ ገብረየሱስ የተባለ አንድ ተማሪ ብቻ ቢሆንም፣ የኩባ አብዮትና አብዮታዊ መሪዎቿ የኢትዮጵያ ተማሪዎች እንቅስቃሴ ማዳወሪያ ነበሩ፡፡
በ1928 በዴል ቦዬ ፀረ- ፋሺስት ግለሰባዊ ተጋድሎ ‹ሀ› ብሎ የጀመረው የኢትዮ-ኩባ ግንኙነት፣ በ1970ዎች መጀመሪያ የኩባ አብዮት፣ የኢትዮጵያ የተማሪዎች እንቅስቃሴ ፋና ወጊ በመሆኑ የተነሳ እየዳበረ መጥቶ፣ በኢትዮጵያ አብዮት ፍንዳታ ማግስት፣ በ1975 ኢትዮጵያና ኩባ ሪፐብሊክ ዲፕሎማሲያዊ ግንኙነት መሠረቱ፡፡ ይህንን ስምምነት ተከትሎ፣ ኩባ በ1976 በአዲስ አበባ፣ ኢትዮጵያ ደግሞ በ1977 በሀቫና ላይ ኤምባሲዎቻቸውን ከፈቱ፡፡ ወዛደራዊ አለማቀፋዊነትንና ከወገንተኝነት የፀዳ የውጭ ግንኙነት ፖሊሲን መከተል፣ የሚሉትን መርሆዎች ኢትዮጵያ ከኩባ የውጭ ግንኙነት ፖሊሲ መርሆዎች መካከል የተማረቻቸው ናቸው፡፡
በ1977 የሱማሊያ ጦር ኢትዮጵያን በመውረር፣ የሀገሪቱን በርካታ ግዛቶች ሲቆጣጠር፣ ሶቭየት ህብረት ያለማመንታት ለኢትዮጵያ ከፍተኛ ድጋፍ ማድረግ ጀመረች፡፡
ይሁንና ሶቭየት ህብረት በጊዜው የአፍሪካን ናሽናሊዝም የመረዳት ችግር ስለነበረባት፣ የኩባን ድጋፍ አብዝታ ትፈልግ ነበር፡፡ ኩባ ያለፈችበት ታሪካዊ ጉዞ የአፍሪካን ናሽናሊዝም ከሶቭየት የበለጠ እንድትረዳው አግዟታል፡፡ ይህን ደግሞ ሶቭየት ህብረት በኩባ የአንጎላ ቆይታ ተገንዝባለች። ሶቭየቶች ኩባ በኢትዮጵያ ያላት ተሳትፎና ድጋፍ በአፍሪካ ቀንድ ፖለቲካዊና ስትራቴጂያዊ ግባቸውን በማሳካት፣ በቀጠናው ተደላድለው በሁለት እግራቸው ለመቆም እንደሚያስችላቸው ጠንቅቀው ያውቁ ነበር፡፡ ምንም እንኳን ሶቭየት ህብረት የኩባን ድጋፍ አጥብቃ ብትፈልግም፣ የኩባን የውጭ ግንኙነት ፖሊሲ ልታስቀይራት አልቻለችም፡፡ በመሆኑም ኩባ የኢትዮጵያና የሶማሊያ ጦርነት የሀገራቱ ጉዳይ ስለሆነ ጣልቃ እንደማትገባ አስረግጣ ገለጸች፡፡
የኋላ ኋላ ግን ኩባ ከኢትዮጵያ ጋር ወግና እንድትቆም ያደረጋትን የውጭ ግንኙነት ፖሊሲ ውሳኔ የተቀበለችው፣ ኢትዮጵያን በተመለከተ የነደፈቻቸው ሁለት የውጭ ጉዳይ ስትራቴጂዎች በመክሸፋቸው ነው (S. Kessler, 1990)፡፡
የመጀመሪያው ስትራቴጂ፤ ኢትዮጵያና ሶማሊያ፣ ‹‹ሶሻሊስታዊ ፌዴሬሽን›› እንዲመሰርቱ በፊደል ካስትሮ የቀረበው እቅድ ሲሆን በጉዳዩ ላይ በማርች ወር 1977፣ በየመንና በኩባ አደራዳሪነት፣ ኤደን ላይ በሱማሊያና በኢትዮጵያ መካከል ውይይት ተካሂዷል፡፡ በዚህ ‹‹የኤደን ስብሰባ›› ተብሎ በሚታወቀው ስብሰባ የቀረበው ‹‹ሶሻሊስታዊ ፌዴሬሽን›› የመመስረት ሃሳብ ተቀባይነት ሳያገኝ ቀርቷል፡፡
ሁለተኛው የኩባ ስትራቴጂ፤ የኢትዮጵያን አብዮት መሪነት ከወታደር ወደ ሲቪል ለማሸጋገር የነደፈችው ነው፡፡ ይህን ስትራቴጂ ተግባራዊ ለማድረግ በወቅቱ የነበረውን ጠንካራ የፖለቲካ ፓርቲ (መኢሶን) መሪ ነገደ ጎበዜን በስደት ከሚኖርበት ሀገር ወደ አዲስ አበባ በማስመጣት፣ በኢትዮጵያ አብዮት መሪነት ውስጥ ወሳኝ ሚና እንዲኖረው ለማድረግ የወሰደችው እርምጃ፣ ራሱን የአብዮቱ ቀኝ እጅና መሪ አድርጎ በሚቆጥረው ወታደራዊ ደርግ ተቀባይነት ካለማግኘቱም በላይ፣ ጉዳዩ ኩባ በኢትዮጵያ አብዮት ላይ የፈጠረችው ክህደት ተደርጎ በመታየቱ፣ የሁለቱ ሀገሮች ዲፕሎማሲያዊ ግንኙነት ላይ ትልቅ ችግር ፈጥሯል፡፡ ይሁን እንጂ በመጨረሻ ይህ ተግባር በኢትዮጵያ የሚገኙት የኩባ አምባሳደር ስህተት እንጂ፣ የኩባ የግንኙነት ፖሊሲ አካል አለመሆኑ ተገልጾ፣ በሁለቱ ሀገሮች ግንኙነት ላይ ያንዣበበው ደመና ሊገፈፍ ችሏል።
በነዚህ ሁለት ስትራቴጂዎች መክሸፍና በየጊዜው በፍጥነት በሚቀያየረው የአፍሪካ  ቀንድ የፖለቲካ ሁኔታ የተነሳ፣ ኩባ የውጭ ግንኙነት ፖሊሲዋን እንድትቀያይርና ከደርግ ጎን እንድትቆም የሚያስገድድ ሁኔታ ውስጥ ገባች፡፡ ሶማሊያ ሶቭየትንና ኩባን ከሀገሯ ባባረረች መንፈቅ ባልሞላ ጊዜ ውስጥ በኦጋዴን በኩል ኢትዮጵያን ወረረች፡፡ በጊዜው ኢትዮጵያ የነበራት የጦር ሀይል፣ ከአስር ዓመታ በላይ በሶቭየት ህብረትና በኩባ ወታደራዊ ኤክስፐርቶች የሰለጠነውንና ሶቭየት ሰራሽ ዘመናዊ መሳሪያ የታጠቀውን የሶማሊያ ጦር ሊመክት አልቻለም፡፡ ይህ ኩባን ከሶቭየት ሀሳብ ጋር በመስማማት፣ ከኢትዮጵያ ጋር ወግና በጦርነቱ እንድትሳተፍ አድርጓታል፡፡
በወቅቱ በኢትዮጵያ ላይ የተደረገውን ወረራ በመቃወም በርካታ ሀገሮች ለኢትዮጵያ ድጋፍ አድርገዋል፡፡ ከነዚህም መካከል ቻይና፣ ዩጎዝላቪያ፣ ምስራቅ ጀርመን፣ ሮማንያ፣ ቼኮዝሎቫኪያ፣ የመንና ቡልጋሪያ ይገኙበታል፡፡ በተለይ ግን ሶቭየት ህብረት በታሪክ ታይቶ የማይታወቅ የአየርና የባህር፣ የጦር መሳሪያ ማጓጓዝ በማድረግ (በመጀመሪያዎቹ ስድስት ቀናት ብቻ ሃምሳ በረራ አድርጋለች)፣ አንድ ቢሊየን ዶላር የሚያወጡ የጦር መሳሪያዎችን ወደ ኢትዮጵያ አድርሳለች (Bonner,1978)፡፡ የእነዚህን ዘመናዊ የጦር መሳሪያዎች አጠቃቀም ለኢትዮጵያውያን ኤክስፐርቶች ለማሰልጠን ደግሞ የኩባ ድጋፍ ወሳኝ ነበር፡፡
ኩባ ለኢትዮጵያ ያደረገችውን ድጋፍ፣ በሌሎች የሶሻሊስት ሀገሮች ከተደረገው ድጋፍና እርዳታ ሁሉ የላቀ የሚያደርገው፣ በህይወት መስዋእትነት ጭምር የተገለጠ መሆኑ ነው፡፡ የኩባ መንግስት ከህዳር 1977 እስከ የካቲት 1978 ድረስ፣ ባለው ጊዜ አስራ አምስት ሺህ ወታደሮችን ወደ ኢትዮጵያ በማምጣት፣ ከኢትዮጵያ ወታደሮች ጎን ተሰልፈው እንዲዋጉ አድርጓል፡፡ የሶማሊያን ወራሪ ለማስወጣት በተደረገው ታላቅ የማጥቃት ዘመቻ የተሳተፉትን የኩባ ወታደሮች የመሩት የሀገሪቱ ም/የመከላከያ ሚኒስትር የነበሩት ጀነራል ኦርናልዶ ኦቾዋ ሲሆኑ፣ የሶቭየት ህብረት ምክትል የምድር ጦር አዛዥ የነበሩት ሜጀር ጄነራል ቫስሊ ፔትሮቭን የጠቅላይን እዙን መርተዋል፡፡
ኢትዮጵያ ድንበሯን ዘልቆ በርካታ ቦታዎችን ተቆጣጥሮ በነበረው የሱማሌ ጦር ላይ በአጭር ጊዜ ውስጥ፣ ውጤታማ የመልሶ ማጥቃት ጦርነት አድርጋ በድል ለመወጣቷ፣ ኩባ ከተዋጊ ወታደሮች በተጨማሪ፣ የጦር አማካሪዎችን፣ የወታደራዊ ኤክስፐርቶችንና የህክምና ባለሙያዎችን ድጋፍ አድርጋለች፡፡ ኩባ ለኢትዮጵያ ያደረገችው እርዳታ እጅግ ከፍተኛ ወጪ ያስወጣት ሲሆን በምላሹ ከኢትዮጵያ ያገኘችው እጅግ ጥቂት ወይም ‹‹ምንም›› የሚባል ነበር፡፡ የኩባ እርዳታ ሶሻሊስታዊ አለማቀፋዊ ወንድማማችነትን ብቻ መሰረት ያደረገ ነበር፡፡
የሶማሊያን ወረራ እንደ ጥሩ አጋጣሚ በመጠቀም፣ በወቅቱ ኤርትራን ለመገንጠል ይዋጋ የነበረው የኤርትራ ነጻ አውጪ ግንባር (ሻዕቢያ) ጥቃቱን አጠናክሮ ቀጠለ። በመሆኑም መንግስቱ ሀይለማርያም ሶቭየትና ኩባ እርዳታቸውን እንዲጨምሩ ደጋግሞ ይጠይቅ ገባ፡፡ ሶቭየት ህብረት ጥሪውን ተቀብላ እርዳታዋን ለመጨመር ተስማማች፤ ይህ ስምምነቷ ግን ከኩባ ጋር ውጥረት ውስጥ ከተታት፡፡ ኩባ፤ ኢትዮጵያ ከሻዕቢያ ጋር ያላት ጉዳይ የኢትዮጵያ የውስጥ ጉዳይ በመሆኑ፣ ሶቭየትና ኩባ ጣልቃ መግባት እንደሌለባቸው አጥብቃ አሳሰበች፡፡ ፊደል ካስትሮ፤ የኩባ የውጭ ፖሊሲ በሌሎች ሀገር ጣልቃ መግባትን የማይፈቅድ መሆኑን አጽንኦት በመስጠት፣ ኢትዮጵያ የጠየቀችውን እርዳታ እንደማይሰጡ ገለጹ፡፡ ከዚህም በላይ ኩባ ለረዥም ዓመታት የኤርትራ አማጽያንን ስትደግፍ የነበረችና አሁንም ድጋፏን ሙሉ በሙሉ ያላቋረጠች ከመሆኗ አንጻር የደርግ ጥያቄ አጣብቂኝ ውስጥ ከተታት፡፡
ኩባ በኤርትራ አማጽያንና በደርግ መንግስት መካከል ያለውን ችግር በተመለከተ አቋሟን ሳትቀይር 1970ዎቹን ዘለቀች፡፡ ይሁን እንጂ በ1980ዎቹ ሁኔታዎች ኩባ ወታደሮቿን ሙሉ በሙሉ ከኢትዮጵያ እንድታስወጣ ባለመፍቀዳቸው፣ በ1986 አጋማሽ ላይ አምስት ሺህ ወታደሮቿ ኦጋዴን ላይ ነበሩ፡፡ ይህ ደግሞ ኩባ በቀጥታም ባይሆን፣ ገለልተኛ ሆና በቆየችበት የሻዕቢያና የኢትዮጵያ መንግስት ጉዳይ ተሳታፊ እንድትሆን አድርጓታል፡፡ የኩባ ወታደሮች ኤርትራ ሄደው ባይዋጉም ኦጋዴንን በመጠበቅ፣ ኦጋዴንን መጠበቅ የነበረበት የኢትዮጵያ ሰራዊት በሰሜን ግንባር ከኤርትራ ነፃ አውጪዎች ጋር እንዲዋጋ አግዘዋል፡፡ ይህም ቀስ በቀስ ሻዕቢያ፤ ኩባን የነፃነት ትግላቸውን ለማኮላሸት ከኢትዮጵያ መንግስት ጋር የተሰለፈች ሀገር አድርጎ እንዲወስዳት ምክንያት ሆኗል፡፡
ኩባ ከኢትዮጵያ ጋር ተሰልፋ በተዋጋችበት የሶማሊያ የመስፋፋት ወረራ ከተሰለፉት መታደሮች መካከል 163ቱ መስዋእትነት ከፍለዋል፡፡ የእነዚህ ጀግኖች ፎቶ ግራፍ፣ ከጥቁር አንበሳ ሆስፒታል ግርጌ በሚገኘው የኢትዮ ኩባ ወንድማማችነት አደባባይ (ትግላችን ሀውልት) ለመታሰቢያ ተቀምጧል፡፡ በሶማሊያ ወረራ ወቅት በርካታ ኢትዮጵያዊ ወታደሮችና ሲቪሎች በምርኮ ወደ ሶማሊያ ተወስደው፣ ለአስራ አንድ አመታት በእስር ቤት ውስጥ በሰቆቃ አሳልፈዋል፡፡ ኮሎኔል ኦርላንዶ ካርዶሶ ቪላቪሶነሶ የተባለው ኩባዊ ወታደርም በውጊያ ላይ ተማርኮ፣ ከኢትዮጵያውያኑ ጋር አስራ አንድ አመት በእስር ቤት አሳልፏል፡፡ ኮሎኔል ኦርላንዶ ለዚህ ተግባሩ ‹‹ብሄራዊ ጀግና›› ተብሎ የኩባን ከፍተኛ ሽልማትና ክብር ተቀዳጅቷል፡፡ በወቅቱ የኩባን ጦር መርተው ወደ ኢትዮጵያ የመጡት ሌተናል ጀነራል ራሞን ኢስፒኖዛም ብሄራዊ ጀግና ሲሆኑ፣ የሀገሪቱ ምክትል መከላከያ ሚንስትር ሆነው እያገለገሉ ነው፡፡ ከነዚህ በተጨማሪም አባቶቻቸው በኢትዮጵያ የተሰዉባቸው ሁለት ሰዎች (አንድ ሴትና አንድ ወንድ) በበአሉ ላይ ታድመዋል፡፡
ኩባ ብሄራዊ ጀግና ያለቻቸው የኢትዮጵያን ጀግኖች ነው፤ እኛ ረስተናቸዋል፡፡ ኩባና ኩባውያን ከየትኛውም ወዳጅ ሀገር በላይ ኢትዮጵያን ደግፈዋል፤ ድጋፍና እርዳታቸው በደም የተሳሰረ ነው፡፡ እኛ ኢትዮጵያውያን እነዚህን ጀግኖች ዘወትር ልናስባቸውና ልናከብራቸው ይገባል፡፡

Read 2340 times