Saturday, 20 October 2018 14:03

የብሔረሰብ መብት እና የዴሞክራሲ ፍጥጫ

Written by  ተፈሪ መኮንን
Rate this item
(11 votes)

  ‹‹አፍሪካ ራስን የማጥፋት ዓመል የተጠናወታት አህጉር ናት››
           
    ልቤ ያለው በኪነ ጥበብና በባህል ገደማ ነው፡፡ ግን ‹‹የጠሉት ይወርሳል፤ የፈሩት ይደርሳል›› እንዲሉ ሆኖ፤ የኪነ ጥበብና የባህል ጉዳዮችን ትቼ፤ በፖለቲካ ጉዳዮች ላይ ለማትኮር እገደዳለሁ፡፡ የመኖሬ ግብ አድርጌ የምመለከታቸውን ኪነ ጥበባዊና ባህላዊ ሥራዎችን ለመሥራት፤ ሰላማዊ - ማህበራዊ ህይወትን ለማረጋገጥ የሚያስችል የፖለቲካ ስርዓት የሰፈነበት ሐገር ለመፍጠር እኔም የበኩሌን ማድረግ ግድ ይሆንብኛል፡፡ ስለዚህ ስለ ፖለቲካ ጉዳዮች እጽፋለሁ፡፡ ምን ማድረግ እችላለሁ፡፡
አሁን የምንገኝበት ሁኔታ ጠ/ሚ ዶ/ር ዐቢይ አህመድ ከትናንት በስቲያ በፓርላማ ተገኝተው እንደተናገሩት እና ባለፈው ዓመት መጨረሻ ግድም ከወታደራዊ መኮንኖች ጋር በተወያዩ ጊዜ እንዳሉት፤ ‹‹ሐገራችን ተወንጭፋ ለመሄድ እና ዘጭ ብላ ለመውደቅ›› በምትችልበት ሁኔታ ውስጥ ትገኛለች፡፡ ሐገራችን በእንዲህ ያለ አሳሳቢ ነገር ተከብባ ባለችበት ሁኔታ ስለ ፖለቲካዊ ችግሮቻችን መነጋገር ይኖርብናል። በእንዲህ ዓይነት ሁኔታ ዝምታ ከድርጊት ይቆጠራል፡፡ የእኛ ዝምታ የምንጠላው ነገር እንዲመጣ የሚያደርግ ከሆነ፤ ዝምታችን የምንጠላው ነገር እንዲፈጠር ከመተባበር የተለየ ትርጉም አይኖረውም፡፡ አንዳንዶች የምንጠላው መጥፎ ነገር እንዲፈጠር ሲሰሩ እያየን እኛ ዝም ካልን፤ ዝምታችን የምንጣላው ነገር እንዲፈጠር ከመተባበር አይለይም፡፡ መጥፎ ነገርን ከመደገፍ የተለየ ተግባር አይሆንም፡፡ እንዲያውም በአንዳንድ ሁኔታ ዝምታው የሞራል ጉዳይ ብቻ ሳይሆን ከወንጀል የሚታሰብም ነገር ሊሆን ይችላል፡፡
የህግ ሰዎች እንደሚሉት የወንጀል ድርጊት የሚፈጸመው፤ በማድረግ (Commission) ወይም ባለማድረግ (Omission) ነው፡፡ በህግ፣ በሞራል ወይም በሥነ ምግባር ደንብ እንዲደረግ የሚጠበቀውን ነገር ባለማድረግ (በኦሚሽን) ወይም እንዳይደረግ የተከለከለውን ነገር በማድረግ (በኮሚሽን) ወንጀል ሊፈጸም ይቻላል፡፡ አንድ ነገር ማድረግን በሚጠይቅ ሁኔታ ውስጥ ሆነን፤ ያም ሁኔታ ሐገርን የሚያክል ትልቅ ነገርን የሚመለከት ነገር ሆኖ ሳለ፤ ህዝብን ያክል ክቡር አካል የሚጎዳ ችግር ሆኖ ሳለ፤ ዝምታን መምረጥ ወንጀል ነው፡፡ ስለዚህ ስለ የሐገራችን ፖለቲካ መነጋገር አለብን፡፡
የሐገራችን ፖለቲካ፣ የ60ዎቹ ትውልድ በፈጠረው የፖለቲካ አጀንዳና ባህል ተቀርቅሮ ቀርቷል፡፡ የሐገሪቱን ህዝብ ለድህነትና ለኋላ ቀርነት የዳረጉትን ፖለቲካዊና ኢኮኖሚያዊ ችግሮች ለመገንዘብ ጥረት አድርጎ በቅድሚያ ለትግል የተነሳው ‹‹ያ ትውልድ››፤ የሐገሪቱንና የህዝቦችዋን ችግር ለመፍታት ያስችላል ብሎ ያስቀመጠውን መሥመር ይዞ የታገለ ቢሆንም፤ ለዴሞክራሲያዊ ስርዓት ግንባታ የነበረው አስተዋፅዖ ግን ውስን ነው፡፡ በተሳሳተ የትግል መስመር ከተጓዙት የዚያ ትውልድ አካል የሆኑ ቅን ወጣቶች ብዙዎቹ እሳት ውስጥ የገባ ቅቤ ሆነው ጠፍተዋል፡፡ ህዝቡንም ለከፋ ጨፍጫፊ ስርዓት ጥለውት ተበታትነዋል፡፡
ነገር ግን ከዚያ ‹‹ትውልድ›› የትግል ስልት አንዳንድ ስህተቶችንና የአመለካከት ችግሮችን በማረም፤ ከረጅም የትጥቅ ትግል በኋላ ለዴሞክራሲ ስርዓት መሰረት የጣለውና የፌዴራላዊት ኢትዮጵያ መስራች የሆነው ትውልድ፤ ለምስጋና እና ለውግዘት የሚያበቁ ሥራዎችን ሰርቶ፤ አሁንም ለስርዓቱ መጠናከር እየተጋ ላለው ባለወርተራ ትውልድ መንገድ የለቀቀ ይመስላል።
በርግጥ ሥራው ከወቀሳ ባያድነውም አምባገነኑን ስርዓት በመገርሰስ፤ ህገ መንግስታዊ ስርዓትን ለመለማመድ የምንችልበትን ዕድል ፈጥሯል። ስለዚህ በአሁኑ ሰዓት በኢህአዴግ ጥላ ሥር የተሰባሰበው የለውጥ ኃይል በአባላቱ፣ በደጋፊዎቹና በአጋሮቹ ድጋፍ አዲስ ገዳና ለመተለም፤ በወረሳቸው መጥፎ ዕዳዎች ሸክም ትከሻው እንደ ጎበጠ፣ ሐገሪቱን ወደ አዲስ ምዕራፍ ለመውሰድ እየተጣጣረ ይገኛል፡፡ ግን ‹‹ሚዳቋ ዘላ ዘላ ከምድር›› ሆኖበት ተቸግሯል፡፡
ዛሬ በፖለቲካ መድረኩ ግንባር ቀደም ተዋናይ የሆኑት የዚያ ትውልድ አባላት፤ በኢህአዴግ ዙሪያ እና በተቃዋሚ የፖለቲካ ፓርቲዎች ዙሪያ ተሰልፈው፤ ከቀደመው ዘመን በተለየ መንፈስ ለመስራት ጥረት እያደረጉ ቢሆንም፤ ‹‹ራስ ከዋለበት እግር ይሰበሰባል›› እንዲሉ፤ በሁለቱም ጎራ ካሉት ፖለቲከኞች ብዙዎቹ፣ በአፈና ስርዓት ባህል ትውፊት ውስጥ ያደጉ በመሆናቸው፤ ፖለቲካችን ብዙ ፈተና ውስጥ ገብቷል። የዚያ ትውልድ አባላት፤ በአፈና ስርዓት አድገው፤ የስርዓቱን ችግር ተገንዝበው፣ በፖለቲካውና በትጥቅ ትግሉ ውስጥ በመሳተፍ፣ የአፈና ስርዓቱን ቢጥሉም፤ አሁንም ከአፈና ባህል ውርስ ራሳቸውን በመነጠል፣ የገዛ አስተሳሰባቸውን በመታገል፣ አዲስ ባህል በመገንባት፤ ዴሞክራሲያዊ ስርዓት ለመመስረትና ስርዓቱን ለማጠናከር የረባ ሥራ መስራት አልቻሉም፡፡
የኢትዮጵያ ህዝብ  የሩቅ ትናንት ህይወቱን በሐዘን፤ የዛሬ ህይወቱን በጽናት እና የነገ ህይወቱን በተስፋ በመመልከት፤ ራሱን በራሱ የሚያርም ስርዓት ለማፅናት እየተጋ፣  ነገን በተስፋ በማየት ወደ ብሩህ ዘመን ለመጓዝ ጥረት እያደረገ ነው፡፡ ታዲያ አሁን አንድ ነገር ተረድተናል፡፡ ለበርካታ ዓመታት በተጓዝንበት መንገድ ሄደን፣ ለውጥ ማምጣት አለመቻላችንን ተገንዝበናል፡፡ ስለዚህ መንግስት ዝንባሌውን ቀይሯል። ‹‹እኔ ያልኩህን ካልፈፀምክ እና ጥያቄህን ለማስፈፀም ጠብመንጃ ካነሳህ፤ እንደ መንግስት አይቀጡ ቀጥቼ አንበረክክሃለሁ›› ከሚል የእልህ ስሜት ተላቆ፤ ‹‹ያነሳችሁን ጠብመንጃ አስቀምጣችሁ፤ ጠብመንጃ በማንሳት የአመጽ ጎዳናን መከተል ስህተት መሆኑን በይፋ ገልፃችሁ፤ በሰላማዊው የፖለቲካ መድረክ ለመታገል ከወሰናችሁ ወይም ወደ ሰላማዊ መድረክ ለመግባት ፈቃደኛ ከሆናችሁ፤ ክስና ቅጣት ሳልል የሰላም አማራጮችን ለመደገፍ ዝግጁ ነኝ›› በማለት፤ ጠብመንጃ ካነሱ የፖለቲካ ቡድኖች ጋር ድርድር ለማድረግ ሲሞክር፤ በዚህ ሀገር ታሪክ ታይቶ የማያውቅ ፍፁም አዲስና አብዮታዊ እርምጃ ነው፡፡
ይህ ብቻ በዚህ ሐገር አዲስ ነገር እየተፈጠረ መሆኑን አመላካች ነው፡፡ የፖለቲካ ጥያቄን በጠብመንጃና በኃይል የማወራረድ ፖለቲካዊ ባህል እየተቀየረና የፖለቲካ ጥያቄን በዴሞክራሲያዊ አግባብ በማወራረድ፣ አዲስ እሴት እየተተካ መምጣቱን የሚያስገነዝብም ነው፡፡ ነገር ግን መቀየር ያለበት መንግስት ብቻ አይደለም። ተቃዋሚ የፖለቲካ ፓርቲዎችም አስተሳሰባቸውን በዴሞክራሲያዊ እሴት ማረቅ ይገባቸዋል፡፡
በዚህ ረገድ አንድ ነገር ለማንሳት እወዳለሁ፡፡ ቀደም ሲል አንዳንድ የተቃዋሚ ፓርቲ አመራሮች፤ ‹‹ኢህአዴግ ጠብመንጃ አንስተው ከሚዋጉት ወገኖች ጋር እየተነጋገረ፤ ደረቅ ወንጀል ለሰሩ ወገኖች በየዓመቱ ምህረት እየሰጠ፤ እኛ በሰላማዊ መንገድ እየታገልን ከምንገኘው የፖለቲካ ኃይሎች ጋር ለመነጋገር አለመፍቀዱ ትክክል አይደለም›› የሚል ወቀሳ በመንግስት ላይ ይሰነዝሩ ነበር፡፡ ‹‹መንግስት በሰላማዊ መንገድ ከሚታገሉ ቡድኖች ጋር ብቻ ሳይሆን ጠብመንጃ አንስተው ከሚዋጉት ጋር እየተነጋገረ የእኛን የውይይት ጥያቄ አልቀበልም ይላል›› ሲሉ የሚወቅሱም ነበሩ፡፡ ዛሬ እንዲህ ያለ ሮሮ አይሰማም። መንግስት በብዙ ተቀይሯል፡፡ ተፎካካሪ ፓርቲዎችም መለወጥ አለባቸው፡፡
በርግጥም ዛሬ ጠብመንጃ አንስቶ ከሚወጋው ኃይል ጋር ለመወያየት የደፈረ፤ በኢትዮጵያ ታሪክ የነበረውን የፖለቲካ ባህልና ልምድ በመተውና ሥነ- ምግባራዊ የበላይነት በመያዝ፣ መንፈሳዊ ጀግንነት የተላበሰ እርምጃ ከመንግስት አይተናል። በዴሞክራሲያዊ ስርዓት ውስጥ በህጋዊ መንገድ ተመዝግቦ በፖለቲካው መድረክ ከሚፎካከረው የፖለቲካ ድርጅት ጋር ብቻ ሳይሆን ጠብመንጃ ካነሳ ኃይል ጋር ለመወያየት፣ አገር አቋርጦ የሚጓዝ መሪ አይተናል፡፡ እንዲህ ዓይነት መንፈሳዊ ጀግንነት ከተፎካካሪ ፓርቲ መሪዎች እንፈልጋለን፡፡
እንደሚታወቀው፤ ‹‹የፖለቲካ ፓርቲዎች የጋራ መድረክ›› በሚል የሚታወቅ እና በፓርቲዎች የጋራ ጉዳዮች ላይ ምክክር የሚደረግበት መድረክ አለ። በዚህ የጋራ መድረክ ለመሳተፍ ፈቃደኛ ያልሆነ አንድ የፖለቲካ ፓርቲም መኖሩን እናውቃለን፡፡ ይህ የፖለቲካ ፓርቲም፤ ‹‹አንድነት - መድረክ›› ነበር። እንደሚታወቀው፤ መድረክ ወደ ጋራ መድረኩ ለመምጣት ፈቃደኛ ያልነበረው ‹‹ኢዴፓ ከሚባል ፓርቲ ጋር ቁጭ ብዬ አልደራደርም›› በሚል ነበር፡፡ በወቅቱ ‹‹ኢህአዴግ በሰላማዊ መንገድ ከምንታገለው ከእኛ ጋር ለመወያየት ፈቃደኛ አይደለም›› እያለ የሚወቅስ ፓርቲ፤ እንዴት እንዲህ ይላል ብለን ነበር። ‹‹ኢህአዴግ እኛ በሰላማዊ መንገድ የምንታገለው ወገኖች የምናቀርብለትን የውይይት ጥያቄ ሳይቀበል፤ ጠብመንጃ ካነሳው ወገን ጋር ይነጋገራል›› የሚል ክስ እያቀረቡ፤ እንዴት ‹‹ኢዴፓ ከሚባል ፓርቲ ጋር ቁጭ ብዬ አልደራደርም ይላል›› አሰኝቶን ነበር፡፡ በዚህ ዓይነት አቋም ዴሞክራሲያዊ ስርዓት መገንባት አይቻልም፡፡ ‹‹እኔ ከማልወደው ፓርቲ ጋር በአንድ ጠረጴዛ ዙሪያ አልወያይም›› የሚል የዴሞክራሲ እሴትን የሚፃረር አቋም ነው፡፡ ትኩረት የሚሻ አንድ ቀሪ ሥራ መኖሩንም ያመለክታል፡፡
‹‹አማራጭ ሐሳብ የማቅረብና የመደመጥ ዕድል ልትነፍጉን አይገባም፡፡ የጋራ ለሆነችው ሀገራችን እኛም የምናበረክተው አስተዋፅዖ ተገቢ ግምት ሊሰጠው ይገባል›› የሚል የፖለቲካ ድርጅት፤ ‹‹እኔም አማራጭ አለኝ›› ብሎ የተቋቋመ ህጋዊና ሰላማዊ የፖለቲካ ፓርቲ በሚገኝበት የፖለቲካ ፓርቲዎች የጋራ መድረክ ለመገኘት አልፈልግም ማለት አይገባውም ነበር፡፡ በውስጣቸው የሚነሱ የአቋም ልዩነቶችን በምን መንገድ ነው የሚያስተናግዱት የሚል ጥያቄ የሚያስነሳም ይሆናል፡፡ ‹‹የኢዴፓ ሀሳብ እኔ ባለሁበት መድረክ እንዲሰማና በሀሳብ ትግል እንዲሞግተኝ አልፈልግም›› የሚል ዴሞክራሲያዊ እሴቶችን የሚጻረር መልዕክትም ያስተላልፋል፡፡
ለማይወዱት ሐሳብ የመደመጥ ዕድል መስጠት የማይፈቅድ አቋም፣ ፀረ- ዴሞክራያዊ አቋም ነው፡፡ ሐገራችን ወደ ተሻለ የዴሞክራሲ ስርዓት እንድትሸጋገር፣ እንዲህ ዓይነት አስተሳሰቦች ከተፎካካሪ ፓርቲዎች ዘንድ መታረም አለባቸው፡፡ “መንግስት ከያዘው ፖሊስ የተለየ አማራጭ ፖሊሲ አለን ከሚሉ ወገኖች ጋር መነጋገርና መወያየት አለበት” ሲሉ ወቀሳ  የሚያቀርቡ ወገኖች፤ ከእነርሱ የተለየ ፕሮግራም የያዘው እና የተለየ ፖሊሲ ከሚያራምድ የፖለቲካ ድርጅት ጋር ለመነጋገር አልፈልግም  የሚል አቋም ሊወስድ አይገባም፡፡
ይሁንና ባለፉት ዓመታት የታዩ የዴሞክራሲያዊ ስርዓት ባህልን የሚያመለክቱ አበረታች አዝማሚያዎችም ነበሩ፡፡ የፖለቲካ ፓርቲዎች በጋራ ጉዳዮች ላይ ለመምከር መድረክ መፍጠራቸው፤ የተቃዋሚ ፓርቲዎች ብዙ በደል ቢደርስባቸውም በዚህ መድረክ ለመሳተፍ ፈቃደኛ መሆናቸው፤ የጋራ መድረኩ የሚገዛበትን የሥነ-ምግባር ደንብ ማጽደቃቸው፤ የጋራ መድረኩ አባላት የዴሞክራሲያዊ ስርዓት የደም ስር ለሆነው የመወያየትና የመደራደር እሴት አክብሮት ማሳየታቸው፤ እንደኛ ዓይነት የፖለቲካ ባህል ላለው ህዝብ የእድገት ምልክቶች ናቸው፡፡ ለመነጋገር አለመቻል፤ የጦርነት መቅድም ነው፡፡
ሙቱምዋ ማውሬ (Mutumwa Mawere) የተባለ አንድ የዝምባብዌ ጋዜጠኛ፤ ‹‹አፍሪካ ራስን የማጥፋት ዓመል የተጠናወታት አህጉር ናት›› ይላል፡፡ ‹‹አፍሪካ ድሃ አህጉር ነች፡፡ ነገር ግን አፍሪካውያን የድህነት ዘበኛ የሆነውን ጦርነትን በቀላሉ ይቀበሉታል›› ይላል፡፡ ከዚህ የሚያወጣን መመካከርና መወያየት ነው፡፡
አጥኚዎች እንደሚሉት፤ ከአፍሪካ አህጉር ህዝብ 45 በመቶ የሚሆነው በድህነት ይኖራል፡፡ የአፍሪካ ሐገራት ይህን አኃዝ በግማሽ ለመቀነስ፤ ለ15 ዓመታት 7 በመቶ እና ከዚያ በላይ የሆነ የኢኮኖሚ ዕድገት ማስመዝገብ ይኖርባቸዋል፡፡ ስለዚህ ይህን ግብ ለማሳካት ከጦርነት መውጣት ያስፈልገናል። በኢኮኖሚው መስክ የምናገኘው ውጤትም፣ በኢኮኖሚ አጥር ብቻ ተወስኖ የሚታይ ሳይሆን ከዛ ክበብ አልፎ የሚሄድ ፋይዳ ያለው ነው፡፡
‹‹እንደ ሪፐብሊክ የቆሙት የአፍሪካ ሐገራት፤ ለነጻነትና በህዝብ ፈቃድ ለመገዛት የተለየ ትኩረት በመስጠት ሪፐብሊካዊነትን የመንግስታቸው መመሪያ ርዕዮተ ዓለም ማድረግ ሲገባቸው፤ በተጨባጭ የሚታየው ነገር እንደሚያመለክተው፤ ለሪፐብሊካዊ እና ለዴሞክራሲያ እሴቶች በመጓጓት፣ ቅኝ ግዛትን እንዲያ አምርረው የሚጠሉት እነዚሁ ህዝቦች፤ በመጨረሻ የኦሊጋርካዊና የአምባገነናዊ አገዛዝ ሞግዚቶች ሆነው ይቀራሉ›› ይላል፤ የዚምባብዌው ጋዜጠኛ ሙቱምዋ ማውሬ፡፡ አብዛኛዎቹ የአፍሪካ ሐገራት ሪፐብሊካዊ ናቸው፡፡ ነገር ግን የሪፐብሊካዊ የአስተዳደር ዘይቤን እውነተኛ ትርጉም ምን እንደሆነ ለመወያየት የሚሞክሩ ሰዎች የምንመለከተው በዓመት አንዴ ነው፡፡
ኢትዮጵያ እንደ ሌሎቹ የአፍሪካ ሐገራት በቅኝ ባትገዛም፤ ነገር ግን እውነተኛ ሪፐብሊካዊ ባህል በመገንባት ረገድ እርሷም ከአብዛኛዎቹ የአፍሪካ ሐገራት ያልተለየ ተግዳሮት ገጥሟታል፡፡ ኢትዮጵያ ከ80 በላይ የሚደርሱ ብሔረ-ልሳናዊ ማንነት (ethno-linguistic) ያላቸው በበርካታ ህዝቦች ሐገር ነች፡፡ እንደ እብድ ከእኩለ ቀን በላይ መጨመት በማይችለው የአፍሪካ ቀንድ ግዛት የምትገኘው እና ለብሔረ-ልሳናዊ ማንነት እውቅና በመስጠት በልዩነት የምትጠቀሰው ኢትዮጵያ፤ ብሔረ-ልሳናዊ ማንነት፤ የድንበር፣ የትምህርት ፖሊሲ፣ የበጀት ድልድል፣ ‹‹የዜግነት›› ወዘተ ነገሮች  ሁሉ መወሰኛ ሚዛን ሆኗል፡፡  
በ1983 ዓ.ም ደርግን በመጣል ሥልጣን በያዘውና ‹‹የሙከራ›› የሚመስል አዲስ የአስተዳደር ዘይቤ በፈጠረው ኢህአዴግ አማካኝነት በተቋቋመው ‹‹የኢትዮጵያ ፌዴራላዊ ዴሞክራሲያዊ ሪፐብሊክ›› መንግስት ወስጥ ብሔረሰብ እና ዴሞክራሲ እንደ ተፋጠጡ አሉ፡፡ የብሔረሰብ ፌዴራሊዝም ለግጭት ይዳርገናል በሚል የሚሰጉ ወገኖች አሉ፡፡ በተለያዩ  የፌዴራል መንግስት  አባል ክልሎች መካከል ያለው ልዩነት በጣም ሰፊ ነው፡፡ በሰፊው የኦሮሚያ ክልል እና በአንድ ግንብ ዙሪያ ተወስና በምትገኘው ሐረሪ መካከል ያለው ልዩነት እጅግ ሰፊ ነው፡፡ እንዲህ ያሉ ልዩነቶች ፌዴሬሽኑ ሚዛን እንዲያጣ አድርገውታል። ብዙ የውጭ ሰዎች እንደ ሙከራ ፕሮጀክት የሚመለከቱትና አሳሳቢም ሆኖ የሚታየውን ፌዴሬሽን በተመለከተ የሚደረጉ  ምሁራዊ የፖሊሲ ጥናት እና የፖለቲካ ዳይናሚክስ ትንተናዎች በዘውግ ላይ ያተኮሩ ናቸው፡፡
‹‹የብሔር ፖለቲካው ምን ያህል ፋይዳ አስገኝቷል፤ ምን ያህል ወደ እኩልነት፣ ወደ ዴሞክራሲ ስርዓት ግንባታ እና ወደ ማህበረ-ኢኮኖሚያ ልማት መርቶናል›› የሚል ጥያቄ ተነስቶ መነጋገር አለብን። የኢትዮጵያ መንግስት መጠሪያ በሆነው ስያሜ ውስጥ ያለው (ዴሞክራሲያዊ -) ሪፐብሊካዊ ጉዳይ ብዙ ትኩረት የማይሰጠው ጉዳይ ሆኗል፡፡ ከስያሜው እንደሚታየው ኢትዮጵያ ሪፐብሊክ ነች፡፡ ሪፐብሊክ ብለን ከጠራናት፤ በዚህ ረገድ ምን ያህል የረባ ሥራ ሰርተናል ብለን መጠየቅ ተገቢ ይሆናል፡፡ ለዚህ መቼ ጊዜ አግኝተን፡፡ ለዚህ መቼ ልብ አግኝተን፡፡ ለዚህ ትዕግስት አግኝተን። ኢትዮጵያ በመጥፎ የፖለቲካ ባህል የታሰረች፤ የብሔረሰብ መብት እና ዴሞክራሲ የተፋጠጡባት ሐገር ናት፡፡


Read 5114 times