Saturday, 20 October 2018 14:07

ፍርድና ፍቅር!

Written by  ደረጀ በላይነህ
Rate this item
(6 votes)

  ስንጋባ ከለምለም ከንፈሮችዋ የሚፈልቀው የፍቅር ቃል፣ ልብ የሚያስለመልመው ቅላፄዋ ሁሉ ማርኮኝ ነበር፡፡ በተለይ የሽፋሽፍቷ ግርማ፣ ያይኖችዋን ብርሃን እየከለለ ሲያቀብለኝ፣ የገነት በሮች ወለል ብለው የተከፈቱልኝን ያህል ተደንቄ ነበር፡፡
የሰርጋችንም ቀን ያ ውበትዋ፣ በቬሎ አሸብርቆ ብቅ ሲል፣ ነፍሴ ክንፎችዋን አራግፋ፣ በዝማሬ ዜማ ስትሰግድ አስታውሳለሁ፡፡ የማውቃቸው ሰዎች ሁሉ ስለ እኛ ፍቅርና ሕይወት የሚያሸበሽቡ እስኪመስለኝ ሰከርኩ፡፡ አቤት የቀናት ጣዕም ልዩነት! ጫጉላ ቤትም ሌላ ዓለም ውስጥ ነበርኩ፡፡
በኋላ በኋላ ግን የሳምራዊት ወሬ ሙዚቃው እየቀነሰ፣ ሀይሉ እየከረረ የመጣ መሰለኝ፡፡ ምናልባት እኔ መሀንዲስ መሆኔ ባይተዋር አድርጎኝ ይሆን? ብዬም እጠረጥራለሁ፡፡ ሙያችን የተራራቀ ሳይሆን አይቀርም። ምናልባት የሥነ ልቡና ወይም የስነ ጋብቻ ምሁራን አማክሬ ብንጋባ ይሻል ነበር ይሆን? ብዬ የኋሊት የማስብባቸው ጊዜያት ጥቂት አይደሉም፡፡ አንድ መሀንዲስና የሕግ ባለሙያ ተግባብተው ባንድ ጎጆ ውስጥ እንዲኖሩ ምን መደረግ ነበረበት ይሆን?
ባለቤቴ ክፋት ያለባት አይመስለኝም፡፡ ነገሩ ያለመግባባት ሳይሆን አይቀርም፡፡ ከሁሉ ከሁሉ የጠላሁት፣ የምናወራቸውን ነገሮች ሁሉ ከህግ ጋር ማያያዟ ነው፡፡ ይሄ በጣም ግራ ያጋባኛል፡፡ እኔ ስለ ህግ ብዙም ትኩረትና ስሜት የለኝም፡፡ በዚያ ላይ የቄስ ልጅ ስለሆንኩ፣ ብዙ ነገሮችን ከፈጣሪ ጋር ማያያዝ ይቀናኛል፡፡ እሷ ደግሞ ስለ ፖለቲካ ቢነሳ፣ ስለ ሃይማኖት-- ዘልላ ወንጀለኛ መቅጫ … የፍትሐ ብሄር ህግ እያለች … አንቀፅ ትጠቅሳለች፡፡
በቀደም አጎቴ በጠና መታመሙን ስነግራት፡-
“የህመማቸው መነሻ ምንድነው? የተጣሏቸው ሰዎች አሉ? ከባለቤታቸው ጋር ሰላም ናቸው?” ስትል ጠየቀችኝ፡፡ ይህ ራሱ ለኔ ግራ ነው፡፡ ሰው የእግዜር በሽታ አይታመምም ማለት ነው?
“ኧረ ከማንም ፀብ የለውም፤ የበላው ነገር አልተስማማውም መሰለኝ!” አልኳት፡፡
“ምሳ የተመገቡት የት ነበር? ምግቡ መመረዙን በሀኪም ማረጋገጥ ከተቻለ፣ ምግብ የተመገቡበትን ቤት በወንጀለኛ መቅጫ ህግ ቁጥር ምናምን …” አለችኝ፡፡
መንገድም ላይ ስንሄድ፣ ካፌ ጎራ ብለን ሻይ ቡና ስንል፣ ሕግ ሕግ ማለቷን አልወደድኩላትም። እኔ የማምነው በፍቅር ህግ ነው፡፡ በተለይ በእኔና በእርሷ ትዳር ውስጥ ዋናው ነገር መፈቃቀርና መቻቻል ነው። እርሷ ግን አንዳንዴ ከሀገርም አልፋ ትልልቆቹ ሀገራት ድረስ ትዘልቅና፤ “ያለፈቃዴ ገላዬን መንካት አትችልም። ግብረ ስጋም ቢሆን ሁለታችንም ስንፈላለግ ብቻ ነው፤ አለበለዚያ በህግ እንደሚያስቀጣ የምታጣው አይመስለኝም፡፡ አስገድዶ መድፈር ማለት ነው” ትለኛለች፡፡
ይሄ ያበሳጨኛል፡፡ እኔ እንዳልኳችሁ … የቄስ ልጅ ነኝ፡፡ ቤተ ክርስቲያን አካባቢ ማደጌን ነግሬያታለሁ። በእርግጥ የእርሷ አባት የፖሊስ መኮንን እንደነበሩ ሁሌ ታስታውሰኛለች፡፡ ስታወራልኝ ቁመታቸው ጭምር አይቀራትም፡፡ ‹ባንዲራ መስቀያ› የመሰሉ እያለች ብትተርክልኝም እሷ ግን በአባቷ አልወጣችም፤ አጭር ናት፡፡ በዚያ አጭር ቁመቷ ታዲያ ያመቀቻቸው የሕግና የፍርድ ብዛትና ዓይነቶች፣ ሳስበው ግርም ይለኛል፡፡
እውነት ለመናገር … የኔ አባት እናቴን ሲናገሯት የሰማሁት፤ ሃዋርያው ጳውሎስ ለፆምና ለፀሎት ተስማምታችሁ ካልሆነ አትከላከሉ የሚለውን ነው። “በዚያ ሁለቱ አንድ ይሆናሉ” ብሏል መፅሐፉ፡፡ ታዲያ መጽሐፍ ቅዱስ፤ ከሷ የህግ መጽሐፍ አንሶ ነው፤ አሥሬ “አንቀጽ ቁጥር” እየጠቀሰች የምታስጨንቀኝ? ለነገሩ ጥፋቱ የኔ ነው፡፡ ሰው ለመክሰስ የህግ መጽሐፍ የምትበረብር ሴት ማግባት አልነበረብኝም፡፡ ቅን ሀሳብ የምታስብ፣ “ህንፃው ተንጋደደ! ተወላገደ!” ብላ ለግዑዝ ነገር የምትጨነቀውን መሀንዲስ ማግባት ነበረብኝ! … የእጄን ነው ያገኘሁት!
ግን ደግሞ በዚህ ነገረኛና ከሀዲ በበዛበት ዘመን፣ ለተቋራጭ ሥራ የርሷ ዓይነት ሳተና ጠበቃ ያስፈልጋል። ስንት አጭበርባሪና ከሃዲ ሰው አለ? ግን ትንሽ ቀነስ ብታደርገው ጥሩ ነበር፡፡ አሁን በቀደም ዕለት “ሰራተኞቼ ልግምተኛ ሆነዋል” ብዬ እንደ ቀልድ ባወራት፣ ያወረደችው መዐት፣ የጠቀሰችው ሕግና አንቀፅ እኔኑ አስፈራኝ፡፡ ለሁሉ ነገር ህግ ተጠቅሶ ይቻላል እንዴ? በመነጋገር ብንፈታው ምናለበት?
አሁን ከጎረቤቶቻችን ጋር ቡና አንጠራራም፣ ሰላምታውም የለበጣ ሆኗል፡፡ አንድ ቀን ድመቷ ጓዳ ገብታ ወተት ደፋች ብላ፣ የወንጀለኛ መቅጫ ህግ ጠቅሳ፣ ወደ ፍርድ ቤት እንሄዳለን ስትል፣ እዚያው እግሯ ሥር ወድቄ ለመንኳትና ተወችው፡፡ በስንተኛው ቀን ደግሞ ያ ሾላካ የወይዘሮ ደብሬ ውሻ ሳታስበው ሾልኮ እግሯን ቢያሸት፤ “ሀገር ይያዝልኝ!” አለች። ጎረቤቱ ሁሉ ተሰብስቦ ፍርድ ቤት ይመስል የሕግ አንቀጽና ቁጥር፣ ህዝባር ሲባል አመሸ፡፡ የት እንደምሄድ ግራ ገባኝ፡፡ ሕንፃ ሥራ ላይ ውዬ፣ አዳር ደግሞ ፍርድ ቤት ሆነብኝ፡፡
ያንን ሁሉ ውበት ተሸክማ የዚህ ዓይነት ነገር መተብተብ ቢቀርባት ምናለ? በዚህ በሚያምር ድምጿ ወይ ለፈጣሪ፣ ካልሆነም ለፍቅራችን ብታዜምበትስ? የሰው ልብ ፈንክታበት ምን ትጠቀማለች? አሁንማ ሥጋት እየሆነብኝ የመጣው እርሷ ከሳሽ፣ እኔ ተከሳሽ መሆኔ ብቻ አይደለም፡፡ ልጃችን ሲወለድ ምስክር ወይ ጠበቃ ማድረጓ አይቀርም የሚል ስጋቴ ነው፡፡  
እስቲ ሰው ከወያላ ጋር ይጣላል? በዚያ ላይ ህፃን ልጅ ነው፡፡ ሃምሳ ሳንቲም መልስ አዘገየ ብላ ስትወርድበት፣ ሽምቅቅ ነው ያልኩት፡፡ “የሰው ንብረት ያለአግባብ መዝረፍ፣ የሰዎችን ተገቢ ጥቅም ነጥቆ ለራስ ማዋል፣” ካለች በኋላ ሕገ መንግሥቱ ላይ ዘልላ፤ “የሰዎችን ሰብዐዊ መብት መጣስ፣ መገለማመጥና እየሰሙ እንዳልሰሙ መሆን …” እያለች ቀጠለች፡፡
ወያላው ድምፁን ቀንሶ፤ “ይቺ ዘፋኝ ነጠላ ዜማዋን - አታቆምም!” እያለ ተላጠባት፡፡ እንዴት ያሳዝናል?
“እባክሽ ውዴ ተይ!” ተለማመጥኳት፡፡
“ያንተ አይነቶቹ ናቸው መብታቸውን አስረግጠው፣ ለባርነት የሚዳርጉን!” ብላ ገለማመጠችኝ፡፡ መልስ አልሰጠኋትም፡፡ ያሰብኩበት ሳልደርስ “ወራጅ አለ!” ስል “አትወርድም” ብላ ያዘችኝ፡፡ ምን ላድርግ? ከዚያ ድንገት ሾፌሩን “አቁም - በህግ አምላክ!” አለችው፡፡ ደነገጠ፡፡
ወያላው፣ ምንም አታመጣም ብሎ ሲያስብ፤ “ትራፊክ!” ብላ ተጣራች፡፡ መታወቂያዋን አሳየችው፤
“መንጃ ፍቃድ!” አለው ሾፌሩን፡፡
“ሾፌሩን አይደለም፤ በህግ ሊጠየቅ የሚገባው እርሱ ነው! ወንጀለኛ ነው! … ዘፋኝ ብሎ ተሳድቧል!” ስትል ለፖሊሱ ከሰሰችው፡፡
“ዘፋኝ ማለት ስድብ አይደለም!” አለ ወያላው፡፡
“ከያኒ ማለት ነው” አለ ሌላው፡፡
“ንግግሬን ነው ዘፈን ያለው! ስለ መብት መከራከርን ዘፈን ያደረገው ማነው?! …”
ወያላው ሳቀ፡፡
“አትሳቅ! ጥርስህ ይርገፍ!” አለ ትራፊኩ በቁጣ፡፡
“መሳደብ ህጉ አይፈቅድም! … ሰብዐዊ መብቱን ሳትጥስ መብታችንን አስከብርልን!” ወደ ትራፊክ ፖሊሱ ዞረችበት፡፡
ትራፊኩም ሳቀ፡፡ ነገረ ሥራዋ ገረመውና፤ “አንቺ መኪና መግዛት አለብሽ፡፡ አለዚያ ብስጭቱን አትችይውም!” አላትና ትከሻዋን መታት፡፡
“ያለ ፍቃዱ የሰው አካል አይነካም! … የሴቶችን መብት መዳፈር ነው!” አለችው በቁጣ፡፡
ከዚህ ሁሉ ጭቅጭቅ በኋላ ሃምሳ ሳንቲሟን ተቀብላ ሄደች፡፡ ያ ሁሉ ሰዓት መባከኑ ለኔም ለእርሷም ስንት ገቢ እንዳሳጣን ሁለታችንም አናጣውም! …. ግን ምን ያደርጋል? ይሄ ህግ ህግ የሚያሰኛት ሰይጣን መውጣት አለበት፡፡ ያለበለዚያ መለያየታችን የግድ ነው፡፡ እንለያይስ ብላት ምን ህግ እንደምትጠቅስ፣ ምን አንቀፅ እንደምትጠራ በምን አውቃለሁ? …. እኔም በትርፍ ጊዜዬ ህግ ልማር ይሆን? መቼም ሌላ መላ የለኝም!
አብሮ መኖርም መፍታትም ካልተቻለ፣ መጨረሻዬ ምን ሊሆን ነው? ጠማማ ዕድሌ? በዚያ ላይ ጆንኤፍ ኬኔዲን እየጠቀሰች፤ “ለተጣላኸው ሰው ይቅርታ አድርግለት፣ ግን ስሙን እንዳትረሳው!” ትለኛለች - ደጋግማ፡፡
ለእርሷ ቂምና ነገር ሕይወቷ ሆኗል፡፡ እንደ እኔ አትሸበርም፤ እንደ እኔ አትደነግጥም፡፡ ሳቋ አይነጠቅም። እኔ ፈርዶብኝ “ወንድሙን የሚጠላ ነፍሰ ገዳይ ነው” የሚለው የመጽሐፉ ቃል ያስደነብረኛል፡፡ “ጥላቻ ከሰይፍ ያላነሰ መሳሪያ ነው” እያሉ አባቴ የሰበኩልኝ ትምህርት በጆሮዬ ይደውላል፡፡
የእርሷ አባት ፖሊስ ናቸው፡፡ ሥራቸው ወንጀለኛ ማጥመድ ነው፡፡ የኔ አባት ካህን ናቸው፡፡ ሥራቸው ሰውን ወደ ፈጣሪው መመለስ ነው፡፡ ግን እኔና እሷ መጋባት አልነበረብንም ይሆን? እህል ውሃ አገናኝቶን ከሆነስ? በዚህ ነገር እንኳን እርግጠኛ አይደለሁም፡፡
የመጨረሻው ገጠመኛችን ፍቅሬን ያመማት ቀን ነው፡፡ ያንን ሁሉ የወንጀለኛና የፍትሃ ብሄር ህግ የምትጠቅስ ሚስቴ አልጋ ላይ ወደቀች፡፡ በጣም የሚያሳዝነው፣ በሽታው በቀላሉ የማይድን መሆኑ ነው፡፡ ሁለቱ ኩላሊቶችዋ ከአገልግሎት ውጭ ሆነዋል። ጳውሎስ ሆስፒታል ሄደን ሁሉን ነገር ተረዳን። ደነገጥኩኝ! በዚያ ላይ አንድ ልጅ ወልደናል። መቸም በልጁም ምክንያት ያልጠቀሰችው ሕግ የለም፡፡ በገዛ ልጄ፤ “የሕፃናት መብት!” ምናምን ብላኝ ነበር፡፡ ይቅር ይበላት! የልጅዋ ነገር ያሳሰባት መሰለኝ፡፡ እርሱም ሕግ መጥቀስ ጀምሮ ነበር፡፡
ህክምናው በሀገር ውስጥ እንደሚጠናቀቅ ቢነግሩንም፣ ኩላሊት ማግኘት ቀላል አልነበረም፡፡ ከተማና ገጠር የስጋ ዘመድ ፍለጋ ዋተትን፡፡ ይሁንና ብዙዎቹ በእርሷ ደስተኛ ስላለሆኑ አልቀረቡልንም ነበር፡፡
በዚህ ጉዳይ ላይ ግን ሕግ አልጠቀሰችም፡፡
ህክምናውን አጠናቅቃ ስትነሳ “ፍቅሬ!?” አልኳት።
“ወዬ” አለች!
“አየሽ?”
“ምኑን?”
“ህግ ብቻ ህይወት እንደማይሆን?!”
ፈገግ አለችና፤ “ሕግ ግን ያስፈልጋል!”
“ፍቅር የህግ ፍፃሜ ነው!” አልኳት፡፡
ፍቅር ይታገሳል፤ ፍቅር የራሱን አይፈልግም፤ ፍቅር ሕይወቱን ያካፍላል፡፡
“ስለ ኩላሊቱ አልነገርከኝም … ከየት ተገኘ?”
“ያልነገርኩሽ አውቄ ነው!”
“ለምን?”
“ኩላሊቱን የሰጠሽ የተጣላሻቸው የጎረቤትሽ ልጅ ስለሆነ!”
ለአፍታ በዝምታ ተዋጠች - በድንጋጤ፡፡
“ታደሰ?”
“አዎ …  እኔ ያለ እናት ነው ያደግሁት፤ የሷ ልጇ ያለ እናት እንዳያድግ ኩላሊቴን እሰጣታለሁ!” አለ፡፡
ተለቃቀስን፡፡
ደገምኩላት፡- “ፍቅር የህግ ፍፃሜ ነው!”   

Read 2932 times