Saturday, 20 October 2018 14:09

አለማወቄን ለማወቅ ያነሳኋቸው ጥያቄዎች?!

Written by  ከኮ ሸዋዬ አድማሱ (ጡ/ፖ)
Rate this item
(2 votes)

 በቅርቡ “የትውልድ አደራ” በሚል ርእስ በልዑል ራስ መንገሻ ሥዩም ተደርሶ በኢትዮጵያ አካዳሚ ፕሬስ የታተመ መጽሐፍ አየሁ፡፡ ስማቸውን ሳይ ልኡልን ያየሁባቸው አጋጣሚዎች ትዝ አሉኝ፡፡
ልዑል ራስ መንገሻ እኔን አያውቁኝም፤ እኔ ለመጀመሪያ ጊዜ ያየኋቸው በስራ አጋጣሚ በ1949 ዓ.ም የሲዳሞ ጠቅላይ ገዢ በነበሩበት ጊዜ ነው። ግርማዊነታቸው ጠቅላይ ግዛቱን ለመጎብኘት በአውሮፕላን ይሄዱ ስለነበረ በቅድሚያ የሜዳውን አመችነት እንድናይ፣ ከአንድ ጓደኛዬ ጋር ታዘን፣ ጃንሆይ ይበሩባታል በተባለችው  ዲ 3 አውሮፕላን፣ በአንድ አሜሪካዊ አብራሪነት፣ ከአሮጌው አውሮፕላን ማረፊያ ተነስተን ወደ አዋሳ በረርን፡፡
እኔና ጓደኛዬ አውሮፕላን ላይ ለመውጣት የመጀመሪያ ጊዜያችን ነበረ፡፡ መሬት ለቀን መሬት እስከምንነካ ድረስ ማለትም አዋሳ እስከምንደርስ፣ አብራሪው ለእኛ ብሎ ይሁን ወይ ለራሱ በጣም ዝቅ ብሎ ነበር የሚበረው፡፡ የአዲስ አበባን ባህር ዛፍ ለአዲስ አበባ ትተን፣ ጥቅጥቅ ባለው የተፈጥሮ ጫካ ላይ እያንዣበብን፣ በጫካው ውስጥ የአራዊቱን መተራመስ ፤ በሀይቆች ዙሪያ የተለያዩ የአአእዋፋትን ህብረ ቀለማት እያየን እየተደነቅን፣ አዋሳ ደረስንና ለአውሮፕላን ማረፊያ ተብሎ አዲስ ተጠርጎ በተደለደለ ሜዳ ላይ አረፍን፡፡
በምናርፍበት ጊዜ አንድ የሰሌን ባርኔጣ ያደረገ ሰው ሜዳውን በግሬደር ያስተካክል ነበር፡፡ እኛ ከአውሮፕላን ስንወርድ፣ ያ ግሬደር ላይ የነበረው ሰው ወርዶ ወደ እኛ መጣ፡፡ ለካስ ጠቅላይ ገዥው ደጃዝማች መንገሻ ስዩም ናቸው፡፡ ማንነታቸውን አውቀን ሰላምታ ከተለዋወጥን በኋላ በአየር ማረፊያውና ስለ ሌላውም የጸጥታ ጉዳይ ተነጋግረን፣ ወዲያውኑ ወደ አዲስ አበባ በረርን፡፡
እኔና ጓደኛዬ አንድ ጠቅላይ ገዢ በዚያ ሙቀት በላብ ተጠምቆ፣ አቧራ ለብሶ፣ ያን ስራ ሲሰራ በማየታችን መደነቃችን ትዝ ይለኛል፡፡ ለሁለተኛ ጊዜም ያየኋቸው እንደዚሁ በስራ አጋጣሚ፣ በ1954 ዓ.ም በልኡል ራስነት ማእረግ፣ የትግራይ ጠቅላይ ገዢ በነበሩበት ጊዜ ነው። ጃንሆይ ትግራይን ይጎበኙ ስለነበረ አንድ የጥበቃ ቡድን ቀደም ብሎ ወደ መቀሌ ሲላክ፣ እኔም የቡድኑ አባል ሆኜ ሄጄ ነበር፡፡ መቀሌ በቆየንባቸው ቀናት ሁሉ ልዑል ራስ መንገሻ፤ የመቀሌን ከተማ ዘመናዊ ለማድረግ እራሳቸው የግሬደር ኦፕሬተር ሆነው፣ የሰሌን ባርኔጣቸውን አድርገው፣ የሚፈርሰውን እያፈረሱ፣ የሚቆፈረውን እየቆፈሩ ድንጋይ ሲፈነቅሉ፣ አፈሩን ሲዝቁ፣ መሬቱን ሲደለድሉ እናያቸው ነበር፡፡
በእነዚህ ሁለት አጋጣሚዎች ያየሁት የልዑል ራስ መንገሻ ማንነት ማለትም፣ የልዑልነት አክሊላቸውን በከብት እረኛ ባርኔጣ ለውጠው፣ ለስራ ክቡርነት ልእልና ሰጥተው፣ እንደ ተራ ቅጥር ሰራተኛ ሲሰሩ በማየቴ ከማእረግና ከትውልድ አቻዎቻቸው ጋር እያወዳደርኩ ሳደንቃቸው እኖር ነበር፡፡
ይህ ትዝታዬ 61ኛ አመቱን ካከበረ በኋላ ልዑል ስለ ራሳቸው የህይወት ታሪክ በመጻፋቸው ተደስቼ፣ ያ በጨረፍታ ያየሁት ማንነታቸው፣ ምን ይዞ እንደዘለቀ፣ ከራሳቸው ለመረዳት መጽሐፉን ለማንበብ ጓጓሁ። መጽሀፉ በእጄ እንደገባ በተጋባዥ ምሁር የተዘጋጀውን ቀዳሚ ቃል አንብቤ፣ የመጽሐፉን ጠቅላላ ይዘት ተረዳሁ፡፡ ደራሲውም በመግቢያ ጽሁፋቸው፤ ለድርሰታቸው ህልውና፣ ከጽንሰት እስከ ልደት በልዩ ልዩ መልኩ ተሳትፎ ያደረጉላቸውን ሰዎች በስም እየጠቀሱ ያቀረቡላቸውን ምስጋና አነበብኩ፡፡
በመግቢያው መጨረሻ የኢትዮጵያ ሳይንስ አካዳሚ ስራ አስፈጻሚ ረቂቁን በምሁራን አስገምግሞ ለህትመት ስላበቃላቸው፣ ሌላው ምሁር ቀዳሚ ቃል ስለጻፉላቸው እንደዚሁም ሌላው ምሁር የሽፋኑን አስተያየት ስለጻፉላቸው፣ በመጨረሻም የአካዳሚው አርታኢ በግምገማው መሰረት የሚያስፈልገውን ማሻሻያ በማድረግ ረቂቁ የመጨረሻውን ገጽ መጽሐፍ እንዲይዝ ስለ አደረጉላቸው ስም በመጥቀስ የገለጡትን አነበብኩ፡፡
የማንበብ ስሜቴን ከላይ በጠቀስኩት ቀዳሚ ቃልና መግቢያ አሟሽቼ ንባቤን ቀጠልኩ፡፡ በግርድፉም ዘለቅሁት፡፡ በግርድፉ ንባቤ የጨበጥኩትን ጨብጬ፣ ወደ መሰለቅ ተመለስኩ፡፡ ደጋግሜ ያነበብኩት ከምዕራፍ አንድ መጀመሪያ እስከ ምዕራፍ አራት መጨረሻ የተተረከውን ሲሆን ታሪኩን በባለቤትነት ማን እንደሚተርከው ለማወቅ ያስቸግራል፡፡ ደራሲው አንዴ ባለቤት፣ አንዴ ጥገኛ፣ አንዴ ታዛቢ እየሆኑ ይገኛሉ፡፡
ወደ ታሪኩ ይዘት ስንመለስ አንዳንዱ የሚያጠያይቅ፣ አንዳንዱ የሚያከራክር፣ አንዳንዱ ደግሞ የሚያጠራጥር ሆነብኝ፡፡ አስተያየት ለመስጠት ሳስብ በመጽሐፉ መግቢያ ስማቸው የተደረደረው፣ ረቂቁን ያሳሱት፣ ያባዘቱትና የዳመጡት ምሁራን ውዳሴ ትዝ አለኝ። ሆኖም በዚህ ታሪክ ውስጥ ለእኔ የታዩኝ አንዳንድ ማብራሪያ የሚጠይቁ ጉዳዮች ለእነሱ መሰወራቸው ለእኔ ግልጥ አይደለም፡፡ ምናልባት ይህን ልዩነት ያመጣው የእኔ ታሪክ  አለመማር ሊሆን ይችላል። ስለዚህ ያልገባኝን ከሚመለከተው ሁሉ ጠይቄ የመረዳት መብት ስላለኝ ይሉኝታን ሠርዤ የምለውን ለማለት ወሰንኩ፡፡ የጽሑፌንም ርዕስ “አለማወቄን ለማወቅ” አልኩት፡፡
የጽሑፌ አላማ በታሪኩ ውስጥ ተሸፋፍነው የታለፉ እሚመስሉት እንዲገለጡ፣ ግድፈቶች እንዲሟሉ፣ አንዳንድ ታሪኮች ለዓመታት የተጻፈባቸውና በሕዝብም የታወቁ ሲሆኑ አሁን ሌላ መልክ ይዘው ስለመጡ ነጥረው እንዲወጡ ለማሳሰብ ነው፡፡
አቀራረቤ አስተያየት የማቀርብበት ጉዳይ በመጽሐፉ ውስጥ የሚገኝበትን ምዕራፍና ገጽ አሳውቄ፣ አርእስቱ እንደ መጽሐፉ ሆኖ፣ ሌላው ሀተታ ቃል በቃል ሳይሆን ፍሬ ሀሳቡን ብቻ በመንቀስ ባጭሩ በማቀነባበር ነው። አንባቢ ከመጽሐፉ የተውጣጣ ፍሬ ሀሳቡን የያዘ መሆኑን እንዲገነዘብ፣ በሌላው ጽሑፍ ሳይዋጥ፣ ከግራ ጠርዝ  ገባ ብሎ ሰፍሮአል፡፡

ክፍል አንድ
ከምዕራፍ አንድ የተወሰደ
ልደት፤ ዕድገት፤ ሹመት
 ሀ. ልደት
ደራሲው ከአባታቸው ከልዑል ራስ ሥዩም መንገሻ ዮሐንስና ከእናታቸው ከወ/ሮ ታየች ኃይለማርያም ሕዳር 29 ቀን 1919 ዓ.ም አዲስ አበባ ቀበና ሠፈር ተወለዱ፡፡
ስለእናታቸው የዘር ሐረግ ሲጠቅሱ፤ አያታቸው በዚያን ዘመን በወረኢሉ የእስልምና ሃይማኖት ይከተሉ ከነበሩ ባላባቶች አንዱ እንደነበሩ፣ ወሎ ሰባት ቤት ኦሮሞ ከሚባሉት ወገኖች እንደ ሆኑም ገልጠዋል። ቅድመ አያቶቻቸውም አገሩን ሁሉ ካቀኑት የአንዱ የሴሩ ጓንጉል ዝርያዎች ነን  ብለዋል፡፡
ለ. እድገት
ተወልጄ ዘጠኝ ወር እስኪሆነኝ ድረስ አዲስ አበባ ቀበና እንደ ቆየሁ ይነግሩኛል ይሉና ከዚህ በኋላ ወደ ትግራይ ክልል እንዲሄዱ ስለተወሰነ ከእናታቸው ጋር በወረኢሉ በኩል አድካሚ ጉዞ ተጉዘው፣ ትግራይ ደንጎላት ከሚባል ሥፍራ በአባታቸው ጉልት፣ ከእናታቸው ጋር ይኖሩ ጀመር፡፡
በአራት አመታቸው እናታቸው በሕመም ምክንያት ሞቱ፡፡ እናታቸው እንደሞቱ በአጥር አሸጋግረው ሌሊት ወስደዋቸው አባ እንቆባህርይ፣ የሚባሉ አባት ዋና ሞግዚት ሆነው፣ ዘጂ ወደሚባል ገዳም ይዘዋቸው ሄዱ።
በገዳሙ ለአንድ ዓመት ሲቀመጡ የሚመገቡትና የሚጠጡት ብርዝ ሎሚ፣ ዝንጅብል ንፍሮ እንደነበር፣ የሚደረገውን ሁሉ ከመቀበል በቀር ሌላ ምርጫ እንዳልነበራቸው ጽፈዋል፡፡
በተወለዱ በአምስት ዓመታቸው ወደ አድዋ ተወስደው፣ ለመጀመሪያ ጊዜ ከአባታቸው ጋር ተገናኙ፣ አባታቸውም መልካቸውን አይተው፣ “አባቴን ትመስላለህ” ብለው መንገሻ ብለው ጠሯቸው፡፡
የጋብቻቸው ጊዜ ባይታወቅም፣ አባታቸው ልዕልት አፀደ አስፋውን አግብተው አድዋ ስለመጡ፣ የሚወዱኝ የእንጀራ እናት አገኘሁ ይላሉ፡፡ የልዕልትንም የዘር ሀረግ፣ ልዕልት አፀደ የደጃች አስፋው ዳርጌ ልጅ፣ የራስ ዳርጌ የልጅ ልጅ ናቸው በማለት ገልጠዋል፡፡
ሐ. የመጀመሪያው ሹመት
በዚሁ ዘመን ጠላት ይመጣል፣ በዚህ ገባ በዚህ ወጣ እየተባለ ይወራ ነበር፡፡ በዚህ ጊዜ ነበር በእኔ ሕይወት ላይም ለውጥ የመጣው፤ ሰባት ዓመት እንደሞላኝ ልዑል ጌታዬ ደጃዝማችነት ማዕረግ ይሰጠው ብለው ወሰኑ፡፡ ሹመቱ በይፋ የሚገለጥበት ሥርአት ተጀመረ፤ በቁመቴ ልክ ካባ ላንቃ የሚባል በሙካሽ የተንቆጠቆጠ ሠይፍ ተሰራ፤ ሠይፉም በልኬ እንዲሆን ተደረገ፤ ልብሴም ሁሉ በደንብ ተዘጋጀ፤ ሹመቴ ለግርማዊነታቸው በስልክ ተነገረ፤ ሹመቱ በአደባባይ በተነገረበት ዕለት ልብሴን ለብሼ ነጋሪት እየተመታ፣ አዋጅ አዋጅ እየተባለ ደጃዝማችነት ማዕረግ ሰጥቸዋለሁ፤ የሚል መልእክት ተነገረ፡፡ እኔን አንስተው መረሻት እተጫነች በቅሎ ላይ አስቀመጡኝ፤ ራሴ ላይ አንድ አረንጓዴ ጨርቅ ተደርጓል ይሉና፣ ታጅበው ወደ ግብር አዳራሽ መሄዳቸውን ገልጠዋል፡፡ ተምቤን የሳቸው ግዛት ነው ተባለና በሞግዚት አስተዳዳሪ ተሾመ፡፡
አስተያየት
ልደታቸውና ዕድገታቸውን በሚመለከት
ደራሲው በተወለድኩ  በዘጠኝ ወሬ ትግራይ ክፍለ ሀገር እንድሄድ ስለተወሰነ፣ ከእናቴ ጋር በወረኢሉ በኩል አድርገን፣ ደንጎላት አባቴ ጉልት ተቀመጥን ብለዋል፡፡ ይህ ውሳኔ ምርምር ያስፈልገዋል፡፡
ደርግ ነፍሱን ይማረውና፣ የዘውድ አገዛዝ ስርዓትን ከእነ ጉቶው ነቅሎ እስከጣለው ድረስ በነጋሲ ዘሮች፣ በመኳንንት በመሳፍንት ቤተሰቦች ዘንድ ይደረግ የነበረው ጋብቻ ሁለት ጥንዶች ተፈቃቅደው ትዳር የሚመሰርቱበት ሳይሆን ሥልጣን አጠናካሪ ወገን የሚፈጥሩበት የአገዛዝ አንድ ዘርፍ እንደነበረ ይታወቃል፡፡
ሴት ልጆች የጀግና ማባበያ እየሆኑ በጨቅላነታቸው ይዳራሉ፡፡ የተዳረችዋ ሴት፤ ባሌን ወድጀዋለሁ ማለት አትችልም፣ በታዘዘች  ጊዜ ታገባለች፤ በታዘዘች ጊዜ ትፋታለች፡፡ ለምሳሌ የደጃዝማች ተፈሪና የወ/ሮ መነንን ጋብቻ እንመልከት (የቀ/ኃ/ሥ እና የእቴጌ መነንን ለማለት ነው)፡፡
ወ/ሮ መነን ቢትወደድ ሉልሰገድን አግብተው ይኖሩ ነበር፤ ልጅ ኢያሱ ከሞቀ ትዳራቸው አስወጥተው ለደጃዝማች ተፈሪ አሉበት ድረስ ሚስት ትሁንህ ብለው ላኩላቸው፤ ክፉ እድል ግን አልገጠማቸውም። ወደ ልዑል ራስ ሥዩምም ስንመለስ፣ የራስነት ማዕረግ የሰጧቸው ንጉስ ሚካኤል ናቸው፤ ልጃቸውን ወ/ሮ ተዋበችን ድረውላቸው ነበር፡፡ ልጅ ኢያሱ አባታቸውን ይዘው ሲወድቁ፣ የራስ ስዩምም ጋብቻ ከግዛታቸው አስነስቷቸዋል፡፡ ወ/ሮ ተዋበችም ፈተው ሌላ አገቡ፡፡
በመጽሐፉ እንደተገለጠው፤ ወ/ሮ ታየች ከወሎ እጅግ ከታወቁ ባላባቶች የተወለዱ ናቸው፣ ጋብቻው ሲፈጸም ይህ ታሳቢ ተደርጎ መሆን እንዳለበት አያጠራጥርም፡፡ በዚህ የዘር ሐረግ የሚገኘው ጠቀሜታ ስላበቃ ሊሆን ይችላል የዘጠኝ ወር ሕፃን አስታቅፈው፣ ከአዲስ አበባ አስወጥተው ገጠር ያስቀመጧቸው፡፡
ደራሲው በሕፃንነታቸው የተደረገውን ሁሉ እገሌ እንዳለው፣ እገሌ እንደነገረኝ እያሉ እንደገለጹቱት ሁሉ፣ ስለ እናታቸውም የአኗኗር ሁኔታ መግለጥ ሲገባቸው፣ “ታመመች ሞተች፤ እኔን በአጥር አዘልለው ወስደው ገዳም አስቀመጡኝ” በማለት አጠቃለውታል፡፡ ቢያንስ የተቀበሩበትን ቦታ መግለጥ ነበረባቸው፡፡
እሳቸውም በአራት ዓመት እድሜአቸው ወደ ገዳም ተወስደው፣ በገዳም ኑሮ መቆራመዳቸው ምክንያቱ ምን ይሆን? ስለ ኑሮአቸው ሲገልጡ የሚደረገውን ሁሉ ተቀብዬ ከማድረግ በስተቀር ሌላ ምርጫ አልነበረኝም ብለዋል፡፡ የሚያስጠጋ ዘመድ ጠፍቶ ይሆን?
አባታቸው የቀድሞዋን ወይዘሮ ሚስት ገፍተው ባለ አፍላ ልዕልት ታቀፉ፡፡ ኑሮም ቀጠለ፡፡
ከላይ የጠቃቀስኳቸው ጠቃሚ ነጥቦች ሁሉ በደራሲው ዘንድ በጥልቀት ተጠንተው የሚታመን ታሪክ ለትውልድ መተላለፍ ሲገባው ባለመደረጉ፣ በበኩሌ፣ ታሪኩ ከምላቱ ወደ ጉድለቱ ያደላል እላለሁ፡፡
የመጀመሪያ ሹመታቸውን በሚመለከት
ስለ ሹመቱ አሰጣጥ በመጽሐፉ የተገለጠውን በአጭሩ አውጣጥቼ ለአንባብያን ለማሳወቅ ሞክሬአለሁ፡፡     ደራሲው ልዑል ራስ መንገሻ የዘውድ አገዛዙን የቤተ መንግሥት ሥርዓት በባይተዋርነት ሳይሆን በባለቤትነት እንደሚያውቁት አያጠራጥርም፡፡ “የትውልድ አደራ” ብለው መጽሐፋቸውን ሲሰይሙ፣ አስረካቢና ተረካቢ ትውልድ መኖሩን ተገንዝበው፣ አስረካቢው ለተረካቢው በዘመኑ የገጠመውን ለትውልድ ሊተላለፍ የሚገባውን በመሰለው መንገድ ማስተላለፍ አለበት፤ እኔም ድርሻዬን ልወጣ በማለት ይመስለኛል፡፡
በዚህ አጋጣሚ በግል የፈጸሙት ሥራ እንደተጠበቀ ሆኖ፣ በነጋሲ  ዘርነታቸው ከደጃዝማችነት እስከ ልዑል ራስነት የደረሱበትን ሥርአት፣ የሹመቱን የሽልማቱን የጌጡን የመሳሪያውን ስምና ደረጃውን ጠቅለል ባለ መልኩ ቢገልጡት የሚጠበቅ ነበር፡፡  እሳቸው ግን በዚህ መልኩ መመልከታቸው ይቅርና በተሾሙበት ጊዜ የራሳቸውን አለባበስና ትጥቅ በአግባቡ የገለጡት አይመስለኝም፡፡
እንደሳቸው አገላለጥ
ካባ ላንቃ የሚባል በሙካሽ የተንቆጠቆጠ ሠይፍ ተሠራ፤ ሠይፉ በልኬ እንዲሆን ተደረገ፤ ራሴ ላይ አንድ አረንጓዴ ጨርቅ ተደረገ---የሚል ነው፡፡ እኔ ከሥርዓቱ እጅግ በጣም በርቀት ላይ ያለሁ ስለ ስርዓቱ ሲነገር እንደሰማሁት፤ ካባ ላንቃ ማለት ካባ ሆኖ አንገቱና ትከሻው ደረቱ በወርቀዘቦ  በሚያምር ሐረግ የተጠለፈ፣ ወርቃማነቱ እጅግ ደምቆ የሚታይ ከፍተኛ የማዕረግ ልብስ ነው፡፡ ዛሬ የኪነት ሰዎች በመድረክ ላይ ለብሰው የሚዘፍኑበት ዓይነት ማለት ነው፡፡ ስለሆነም ካባ ላንቃ የሚለበስ እንጂ ሰይፍ አይደለም፡፡ ሰይፍ የሰይፍነትን ስም ለመያዝ ርዝመቱ፣ ስፋቱ፣ ቅርጹ፣ የሰይፍነቱን ደረጃ ጠብቆ የሚሰራ እንጂ እንደ ልብስ በአካል አይለካም፡፡
በመጽሐፉ እንደተገለጠው፤ የሰባት ዓመት ልጅ ሆነው በልክ ከተሠራ ጩቤ እንጂ ሰይፍ አይባልም። ራሴ ላይ ተደረገ ያሉት አረንጓዴ ጨርቅ፣ የክብር ስም ባለው በራስ ላይ የሚጠመጠም እንጂ እንደ ፀሐይ መከላከያ በራስ ላይ ጣል የሚደረግ አይደለም፡፡ እንግዲህ ሥርዓቱን አያውቁትም እንዳይባል ባለቤት ናቸው፡፡ ንቀውት ነው እንዳይባል በስሙ አሁንም ይጠሩበታል፤ ታዲያ ምክንያቱ ምን ይሆን?
ደራሲው መጽሐፉን በረቂቅነቱ ለተለያዩ ባለሙያዎች አቅርበው አስገምግመው፣ ተወድሶ መታተሙ ተደጋግሞ ተገልጧል፡፡ ይግረማችሁና የመጽሐፉን ቀዳሚ ቃል የጻፉት የታሪክ ምሁር ካባ ላንቃ የሚባል ሰይፍ መኖሩን አምነው “ካባ ላንቃ የሚባል ሠይፍ ተሠራ” የሚለውን በትምህርተ ጥቅስ አጉልተው፣ ምስክርነት የሰጡበትን ተመለከትኩና ገረመኝ፡፡
ክፍል ሁለት
ከምዕራፍ ሁለትና ሦስት የተውጣጣ
የፋሽስት ጣልያን ወረራ
በዚህ አርእስት (ምዕራፍ) ስለ ጦርነቱ ከተገለጠው ሰፊ ትረካ አጠያያቂ የመሰሉኝን ቃል በቃል ሳይሆን ፍሬ ሀሳቡን በመንቀስ፣ ከገጽ 13-32 ያለውን እንመልከት፡፡
ልዑል ራስ ስዩምና ልዑል ራስ ካሳ ተምቤን ላይ ባደረጉት ውጊያ ስለተጠቁ ረዳትም ሊላክላቸው ስላልቻለ፣ ጃንሆይ ወደሚገኙበት ወደማይጨው ሄደው ከንጉሱ ተገናኙ፤ ማይጨው ላይ ትልቅ ምክር ተደርጎ፣ ጃንሆይ ወደ ሊግ ኦፍ ኔሽን ሄደው እርዳታ እንዲጠይቁ ተወሰነ፡፡
ንጉሱ ወደ መሀል አገር ሲመለሱ ጠላት ተከታትሎ እንዳያጠቃቸው ልዑል ራስ ሥዩም ቀርተው እንዲከላከሉ ተደረገ፤ ሆኖም ጠላት የንጉሱን መሄድና የራስ ስዩምን ብቸኝነት ተረድቶ ከበባ በማድረግ ማረካቸው፡፡ በምርኮኛነት ከእነ ቤተሰባቸው ወደ አሥመራ ተወሰዱ፤ አስመራ እያሉ ሙሶሊኒ “ሥዩም ወደ ሮም እንዲመጣ ያስፈልጋል” ስላለ ከ20 ቤተሰብ በላይ ይዘው በመርከብ ወደ ሮም ተወሰዱ። ሮማ እንደ ደረሱ የጣልያን ጀኔራሎች ልዑል ራስ ሥዩምን ወንጅለው፣ በሮም አደባባይ እንዲሰቀሉ ሲሉ ለሙሶሎኒ አመለከቱ፡፡ ሙሶሎኒ ግን ራስ ሥዩምን ጀግና ነው፤ እኛ ያመጣነው እዚያ ሆኖ ጤና ስለማይሰጠን ነው፤ እዚህ በግዞት ይቀመጥ፤ ሁሉን ነገር አሟልታችሁለት ይቀመጥ ብሎ ወሰነ፡፡ በሮማ ከተማ በተሟላ ኑሮ ከቤተሰባቸው ጋራ አራት ዓመት ካሳለፉ በኋላ ወደ አዲስ አበባ መልሰዋቸው፣ በራሳቸው ቤት ተደላድለው ተቀመጡ፡፡
አዲስ አበባ መኖር እንደ ጀመሩ ልጆቻቸው ይማሩ ተብሎ ደጃዝማች መንገሻና ሌሎች የዘመድና የቤተሰብ ልጆች የባላባት ልጆች በሚል በተከፈተ ት/ቤት ገብተው ትምህርት ቀጠሉ፡፡ ልዕልት ወለተ እስራኤል፤ ከእስራኤል ተመልሰው ካባታቸው ጋር ይኖሩ ስለነበረ ልጃቸው ደጃዝማች ዘውዴ ገ/ሥላሴ አብረው ተምረዋል፡፡
አስተያየት
የኢትዮጵያ ጦር በየግንባሩ እንደተሸነፈ እየታወቀ ራስ ስዩምን “አትከተለኝ እዚሁ ተከላከል” ብለው ንጉሱ ጥለዋቸው ሲሄዱ፣ ሞት እንደፈረዱባቸው ቆጥረው ይሆን በቀላሉ ለጠላት እጅ የሰጡ?
ሙሶሎኒ፤ ራስ ስዩም 10800 የጣልያን ጦር ፈጅቶብናል እያለ በተቃራኒው፣ ታሪካቸውን እስከ አያታቸው ጠቅሶ በክብር ከእነ ቤተሰባቸው ማኖሩ፣ በመሃላቸው ምን ዓይነት ድርድር ተደርጎ አስማምቶአቸው ይሆን?  ለመማረክ ልዑል ራስ እምሩ ኃ/ሥላሴም ተማርከዋል፤ ለአመታትም በጣልያኖች ቁጥጥር ሥር ቆይተዋል፤ በአያያዝ በኩል ግን የራስ ስዩም ዓይነት ዕድል የገጠማቸው አይመስለኝም። ልዑል ራስ ሥዩም ወደ አዲስ አበባ ተመልሰው ሰፊ ቤተሰብ ይዘው፣ በራሳቸው ቤት ሲቀመጡ መተዳደሪያቸው ምን ነበር?
ደራሲው የገቢ ምንጫቸውን ባይገልጡትም፣ ተድላ ዘዩሐንስ የተባሉ ደራሲ “የኢትዮጵያ ታሪክ፤ ኢጣልያ በኢትዮጵያ” በሚል ርዕሰ በጻፉት መጽሐፍ፣ በገጽ 254 “የትግራይ ተጋድሎ” ብለው ስለ ራስ ሥዩም የሚከተለውን ጽፈዋል፡-
“ጠላት ከሌሎች ክፍላተ ሀገራት ሁሉ አስቀድሞ የገባበትና የተጥለቀለቀበት ሀገር ትግራይ….  ጦርነቱ ከማንም አገር የከፋ ነበር፡፡ በዚህ ላይ የጠላት ስብከት አንድ አንዶችን አታሎ ነበር…ቢሆንም የትግሬ ሕዝብ በቃኝ ብሎ ከትግሉ ጎራ አልወጣም… ሠራዊቱ ራስ ሥዩምን መሪ አድርጎ ወደ ሀገሩ ተመለሰ፤ ጣልያን በሌሎች አርበኞች ባደረገው ዓይነት በራስ ሥዩም መንገሻ ላይ ተጽዕኖ አደረገ፡፡ ካልገቡለት ሕዝቡን እንደሚፈጅ፣ ከገቡ ግን እሳቸውን በክብር እንደሚያስተዳድራቸው ቃል ገባ፡፡ በአርበኛው ዘንድ ምክር ተደረገ፤ እኩሉ እንግባ አለ፣ ራስ ስዩም ወደ ጣልያን የመግባት አዝማሚያ አሳዩ፤ ደጅአዝማች ዐባይ ካሳ “የዩሐንስን ዘውድ ለቅቀው እንደምን ለጣልያን ይገባሉ” ብለው ተቆጡ፤ እሳቸው ግን አርበኝነት ቀጠሉ፤ በምክሩ ግን ሁሉም እንደ ፍላጎቱ እንዲያደርግ ተወስኖ፣ በሰላም ሠራዊቱ ተበተነ፡፡ ራስ ሥዩም ለጣልያን ሕዳር 7 ቀን 1929 ዓ.ም ገባ፤ ጣልያን በክብር ተቀብሎ ቃሉን በመጠበቅ ወደ አዲስ አበባ አመጣው፤ ከራስ ኃይሉ ቀጥሎ ባለሟል አደረገው”
የተድላ ዘዮሐንስ መጽሐፍ፣ ከዚህ  በላይ ላቀረብኩት ጥያቄ መልስ የሰጠ ይመስላል፡፡ ይኸው መጽሐፍ በገጽ 300 ላይ ጣሊያኖች በወቅቱ አዲስ አበባ ውስጥ ስለከፈቱአቸው ት/ቤቶች አመሠራረት የሚከተለውን ይላል፡-
“ጣልያኖች ደማቸውን ያፈለሱበትን የራሳቸውን ጥቅም የመገንባት ሥራ በአዲስ አበባም ያዙ፤ ባሳር በመከራ የተቋቋሙ ት/ቤቶች ተዘጉ፤ የዳግማዊ ምኒልክ ት/ቤት የጣልያን ዓየር ኃይል ሰፈር በመሆን ተገጣጣሚ ቤቶች በተጨማሪ ተሠሩበት፤ አሮጌው ት/ቤት የወታደርና የቁስለኛ መታከሚያ ሆነ፡፡
“የተፈሪ መኮንን ት/ቤት የጣልያን ልጆች እንዲማሩበት ተደረገ፤ ከኢትዮጵያውያን ስድስት የሚሆኑ የታላላቅ መኳንንት ልጆች ብቻ ጉለሌ ደጃዝማች ይገዙ ሰፈር ለፋስሽት ልጆች ማስተማሪያ ተብሎ ከተሠራው ት/ቤት ገቡ፡፡ ከእነሱም ውስጥ የራስ ጌታቸውና የራስ ሥዩም ልጆች ነበሩባቸው፤ ለሌላው ኢትዮጵያዊ የትምህርት ዕድል የለም” የሚል ይነበባል፡፡
ከዚህ በላይ ከተድላ ዘዮሐንስ መጽሐፍ ለዋቢነት የጠቀስኩት፣ ያ ጊዜ እንዴት እንደታለፈ ለአንባቢ ፍንጭ የሚሰጥ ይመስለኛል፡፡
ልዕልት ወለተ እስራኤል
የልዕልት ወለተ እስራኤልን ጉዳይ ለየትና ጎላ አድርጌ ለማቅረብ እሞክራለሁ፡፡ ልዕልት ወለተ እስራኤል ሥዩም፤ ከልዑል መርዕድ አዝማች አስፋ ወሰን ጋር በታላቅ ሥነ ሥርዓት፣ በተክሊልና በቁርባን ጋብቻ ፈጽመው ልጅም ወልደዋል፡፡ ጣልያን ሲገባ ከንጉሳውያን ቤተሰቦች ጋር ወደ እስራኤል ተሰደው ነበር፡፡
ልዑል ራስ መንገሻ በመጽሐፋቸው፤ ልዕልት ወለተ እስራኤል ከእስራኤል መጥተው ከእኛ ጋር ይኖሩ ነበር በማለት ብቻ አልፈውታል፡፡ እኔ ግን የልዕልት ወለተ እስራኤል ማንነት ሰፋ ብሎ ሊገለጥ የሚገባው  ስለመሰለኝ ስለ ጋብቻው ከመርስዔ ሃዘን ወልደቂርቆስ መጽሐፍ፤ ስለ ስደታቸው ከልጃቸው ከዶ/ር ደጃዝማች ዘውዴ ገ/ሥላሴ መጽሐፍ ያገኘሁትን አጣቅሼ አቅርቤዋለሁ፡፡
መርስዔ ሃዘን ወልደቂርቆስ፤ “ቀዳማዊ ኃይለስላሴ 1922-1927” በሚል ርዕስ በጻፉት መጽሐፍ፣ በገጽ 107፣ የቤተ ነጋሲ ሰርግ በሚል ንዑስ ርዕስ ከጻፉት የሚከተለው ይገኝበታል፡-
“የኢትዮጵያ አልጋ ወራሽ ልዑል መርዕድ  አዝማች አስፋ ወሰን ኃይለሥላሴ፣ የትግሬውን መስፍን የልዑል ራስ ሥዩም መንገሻን ልጅ፣ ልዕልት ወለተ እስራኤልን በተክሊል አገቡ” ይሉና ስለ ሥነ ሥርዓቱ ሲገልጡ፡-
“ሚያዝያ 30 ቀን 1924 ዓ.ም ዕሁድ የዳግም ትንሳኤ ዕለት ማታ የሙሽራው የቃል ኪዳን አባት ቢትወደድ ወልደ ፃድቅ ጎሹ የማጫ ስጦታ ወርቅና ብር ፈረስና በቅሎ…….” በማለት የአሰጣጡን ሥርአት በሰፊው ከገለጡ በኋላ የጥሎሹን ዝርዝር ሲገልጡ፤ “በማጫው ስጦታ አሥር ሺህ ብር፤ በጥሩ ዕቃ የተጫኑ  70 (ሰባ) ፈረሶችና በቅሎዎች ፤የመቶ ደንገጡሮች እጅግ ያማረ ልብስና ጌጥ ይገኝበታል፡፡
“የአባት ልብስና የእናት ልብስ የሙሽራይቱ ልብስ ይሆን ዘንድ የቀረበውም ልብስ በወርቅ የጠለቀና እጅግ ያማረ ነበር፡፡ በበነጋው ግንቦት አንድ ቀን ሰኞ፣ ጃንሆይና እቴጌ፣ መሳፍንትና መኳንንት በተገኙበት መታሰቢያ ቤት፣ በአታ ቤተ ክርስቲያን፣ ሊቀጳጳሳቱ አቡነ ቄርሎስ ቃል ኪዳን አቀባብለው፣ የተክሊል ፀሎት አደረሱላቸው፤ ከዚያም ቀጥሎ ቅዳሴ ተከተለና ሙሽሮቹ ቅዱስ ቁርባን ተቀበሉ” በማለት ገልጠውታል። ብላታ መርስዔ ሃዘን ወልደ ቂርቆስ የሰርጉን ሥርኣት ብቻ ሳይሆን ልጅ መውለዳቸውንም ከላይ በተገለጠው መጽሐፍ፣ በገጽ 182 እንደሚከተለው ጽፈውታል፡-
ልዕልት ወለተ እስራኤል ሴት ልጅ በደህና ስለ መገላገላቸው
“የልዑል አልጋ ወራሽ መርድ አዝማች አስፋው ወሰን ባለቤት ልዕልት ወለተ እሥራኤል ሥዩም ደሴ ላይ እንዳሉ ነሐሴ 29 ቀን 1926 ዓ.ም ማክሰኞ ሴት ልጅ በደህና መገላገላቸው… በቴሌግራም ስለተሰማ፣ በአዲስ አበባ ቤተ መንግስት ታላቅ ደስታ ሆነ…. ከግርማዊ ጃንሆይና ከግርማዊት እቴጌ ለልዕልቷ የደስታ መግለጫ ቴሌግራም ተላለፈ፤ በማግስቱ ነሐሴ 30 ቀን ከጧቱ 12 ሰዓት፣ 19 ጊዜ መድፍ ተተኮሰ…    መሳፍንት መኳንንት፣ ሚኒስትሮች፣ ወይዛዝሮች፣ ኮር ዲፕሎማቶች የማዕረግ ልብሳቸውን እየለበሱ ወደ ታላቁ ቤተመንግስት መጥተው፣ ለግርማዊና ለግርማዊት፣ ለልዑል አልጋ ወራሽ ደስታቸውን ገለጡ” በሚል ጽፈውታል፡፡
ይህን አዱኛ ያሳለፉ ልዕልት በጣልያን ወረራ ምክንያት ከንጉሳውያን ቤተሰቦች ጋር ወደ እስራኤል ተሰደው ሲኖሩ ምንም እንኳ ዝርዝር ጉዳዩ ባይታወቅም፣ ከንጉሳውያን ቤተሰብ ተለይተው፣ የግል ልጃቸውን ይዘው ወደ ግብፅ በረሐ ተሰደዋል። የግል ልጃቸው ዶ/ር ደጃዝማች ዘውዴ ገ/ሥላሴ፤ “የኢትዮጵያና የኤርትራ ግጭት መንስኤና መፍትሔ” በሚል ርዕስ በጻፉት መጽሐፍ፤ ዶ/ር ኃይሉ ሀብቱ  የተባሉ በመግቢያ መልክ በጻፉት ማስታወሻ “ደጃዝማችን በቅርበት” ይሉና “ስደት በልጅነት” በማለት እንዲህ ይላሉ፡-
“ከደጃዝማች እንደተረዳሁት ከሁሉም የሕይወት ዘመናቸው ማንነታቸውን የቀረጸው የልጅነት ስደት ነው፡፡ ፋሽስት  ጣልያን አገራችንን ወሮ ንጉሳውያን ቤተሰብ ከሌሎች መሳፍንትና መኳንንት ጋር ወደ ስደት ሲሄዱ ደጃዝማች ከልዕልት እናታቸው ጋር በስደት ለመኖር ወደ እስራኤል ሄዱ፤ ያን ጊዜ ገና የዘጠኝ ዓመት ለጋ ሕፃን ነበሩ” ይሉና፣ በኢየሩሳሌም ያሳለፉትን መልካም ጊዜ ገልጠው በመቀጠል፤ “ከኢየሩሳሌም በኋላ ከእናታቸው ጋር ወደ ግብፅ አመሩ፤ ወላጅ እናታቸው እጅግ በጣም ሃይማኖታዊት ስለነበሩ ልጃቸውን ይዘው በግብፅ ምዕራባዊ በረሃ ወደሚገኘው ወደ ገዳመ አስቄጥስ ሄዱ፡፡ ገዳሙ በክርስትና ሃይማኖት ታሪክ ውስጥ የመጀመሪያው የብህትውና ኑሮ የተመሰረተበት ነው፡፡---መስራቹ ቅዱስ እንጦንስ ይባላል፤ እዚያ ገዳመ አስቄጥስ አካባቢ ታዲያ የባላገሮች (የፈላሂኖች) መንደር አለ፤ ከዚያ አንዱ ባላገር ቤት በእንግድነት ሰፈሩ፤ በበነጋው ጧት እናታቸው ደጃዝማችን ቤቱን ጥረግ ቢሏቸው ለካ ተኩራርተዋል፡፡ እንዴት መስፍን ሆኜ ቤት እጠርጋለሁ በሚል ስሜት ይመስላል በጨቅላ ሕሊናቸው የተቀረጸው የአንድ መስፍን ልዑል ቤት የመጥረግ ሥራን የማይጨምር በመሆኑ ደጃዝማች ለገሙ፡፡ ልዕልት ወለተ እስራኤል፤ ትጠርግ እንደሁ ጥረግ አንተ ማን ሆነህ የቤቱ ባለቤት ማን ሆኖ ይሉና አይቀጡ ቅጣት ይቀጧቸዋል፡፡--
 ከገዳመ አስቄጥስ ተመልሰው ካይሮ ት/ቤት ገቡ … ከአምስት ዓመት ስደት በኋላ ደጃዝማች ወደ አገራቸው ተመለሱ ይሉና፣ የስደቱን ጉዳይ በዚሁ ያጠቃልሉታል፡
ከላይ የሠርጉን ድምቀት የጥሎሹን ብዛትና ዓይነት፣ ልጅ ሲወልዱም መድፍ እስከ መተኮስ የደረሰውን ደስታ ተመልክተናል፡፡ ጠላት ሲመጣም ከንጉሳውያን ቤተሰብ አንዷ በመሆን ተሰደዋል፡፡ ወደ ጋብቻው ስንመለስም፣ ጋብቻው በተክሊልና በቁርባን የተፈፀመ ስለሆነ፣ፈግጠው ፈግጭው በሚል በቀላሉ የሚፈርስ አልነበረም፡፡ ታዲያ ልዕልት ወለተ እሥራኤል ይህን ሁሉ ጥሰው፣ የግል ልጃቸውን ብቻ ይዘው ከጋራ ስደት ወደ ግል ስደት በማያውቁት የግብፅ በረሀ እንዲገቡ ምን አስገድዶአቸው ይሆን? ምናልባት የአባታቸው የልኡል ራስ ሥዩም አቋም እሳቸውም ላይ አንጸባርቆ  ይሆን? ማይጨው ላይ ንጉስ ነገሥቱ ራስ ሥዩምን ለጠላት አጋፍጠዋቸው መሄዳቸው የሚታወስ ነው፡፡


Read 1367 times