Saturday, 27 October 2018 09:29

የአእላፋት ድምፅ ኅብረቱ የአስተዳደር ለውጥ አቋሙን ለቅዱስ ሲኖዶሱ አስረዳ

Written by 
Rate this item
(5 votes)

• ሁለንተናዊ ለውጥ ያመጣል የተባለ መሪ ዕቅድ እንዲተገበር ተወስኗል
• ኅብረቱ በትግበራው ለመሳተፍና እስከ ግንቦት ለውጡ እንዲታይ ጠይቋል

  ለኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን የመዋቅርና የአሠራር ችግሮች ኹነኛ መፍትሔ በመስጠት ሁለንተናዊ ለውጥ ለማምጣት እየተንቀሳቀሰ የሚገኘውና በአምባሳደር ካሳ ከበደ
የሚመራው የአእላፋት ድምፅ የካህናትና ምእመናን ኅብረት፣ በቅዱስ ሲኖዶስ ምልዓተ ጉባኤ ፊት ቀርቦ የአስተዳደር ለውጥ አቋሙን አስረዳ፤ ቅዱስ ሲኖዶሱም በጥያቄዎቹ ላይ መክሮ
ምላሽ እንደሚሰጥ ለኅብረቱ ተወካዮች አስታውቋል፡፡ የብዙ ሺሕ ካህናት፣ የሰንበት ት/ቤት ወጣቶች፣ መንፈሳውያን ማኅበራት፣ የአገር ሽማግሌዎችና ታዋቂ ምእመናን ተወካዮች የኾኑና በአምባሳደር ካሳ ከበደ የሚመሩ 9 የኅብረቱ ልኡካን፣ ትናንት፣ ቤተ ክርስቲያኒቱ በመሪ ዕቅድ በመመራትና የምእመናንን ከፍተኛ ተሳትፎ በማረጋገጥ ማምጣት ስላለባት አስተዳደራዊ ለውጥ ያላቸውን አቋም በመካሔድ ላይ
በሚገኘው የቅዱስ ሲኖዶስ ምልዓተ ጉባኤ ስብሰባ ላይ ማስረዳታቸውን ምክትል ሰብሳቢው አርክቴክት ዮሐንስ መኰንን ለአዲስ አድማስ ገልጸዋል፡፡ “ለቤተ ክርስቲያን አስተዳደራዊ ለውጥ የካህናትንና የምእመናንን አቤቱታ ስለማቅረብ” በሚል ርእስ በንባብ በተሰማው ጽሑፍ፣ ለቤተ ክርስቲያኒቱ ችግሮች በጥናት የተደገፈ አስቸኳይ እርምት አለመስጠት፣ ተግባራዊ እንዲኾኑ ውሳኔ የተላለፈባቸው ጥናቶች አስፈጻሚ ማጣትና በስፋት አለመታወቅ ሁከትና ብጥብጥን እያስፋፋና ለህልውናዋ ቀጣይነትም አደጋ እያስከተሉ እንደኾነ ተጠቅሷል፤ ቅዱስ ሲኖዶሱ በአሁኑ ስብሰባው፣ ለቤተ ክርስቲኒቱ ሁለንተናዊ ለውጥ ወሳኝ የኾነው የመሪ ዕቅድ ጥናት፣ የትግበራ ጽ/ቤት ተቋቁሞለት ወደ ሥራ እንዲገባ መወሰኑና የ2.5 ሚሊዮን ብር መነሻ መመደቡን ኅብረቱ አድንቆ፣ በትግበራው ሒደት ቅዱስ ሲኖዶሱ መመሪያ ሊሰጥባቸው ያስፈልጋል ያላቸውን አምስት ዋና ዋና ጥያቄዎቹን ማቅረቡን አርክቴክት ዮሐንስ አስረድተዋል፡፡
የመሪ ዕቅድ ትግበራ ጽ/ቤቱ መቋቋሙን የሚከታተልና የሚያስፈጽም አካል ከብፁዓን ሊቃነ ጳጳሳት እና ከባለሞያ ምእመናን ቅዱስ ሲኖዶሱ በዚሁ ስብሰባው እንዲሠይም፤ ጽ/ቤቱ  ከሚቀጠሩለት መደበኛ ባለሞያዎች ባሻገር አስፈላጊውን የሰው ኃይል ማሟላት እንዲችልና ተግባሩን በአግባቡ እንዲወጣ ሙሉ ነፃነትና ሥልጣን እንዲሰጠው፤ አባላቱም እንደ ሞያቸው  በባለቤትነት መሳተፍ እንዲችሉ ኅብረቱ ጠይቋል፡፡ መሪ ዕቅዱ ቢያንስ፣ በግንቦት ወር እስከሚካሔደው የቅዱስ ሲኖዶስ ምልአተ ጉባኤ ድረስ ዋና መሥሪያ ቤት በኾነው በጠቅላይ ቤተ ክህነቱ ጽ/ቤትና የአህጉረ ስብከት ማዕከል  በኾነው በአዲስ አበባ ሀገረ ስብከት ደረጃ ተተግብሮ የለውጡ ተስፋና ምልክት መታየት እንዲጀምር ኅብረቱ አመልክቷል፡፡ በመንበረ ፓትርያርክ በየዓመቱ በሚካሔደው አጠቃላይ ጉባኤ  ላይ የምእመናን ውክልና በሕጉ መሠረት እንዲጠበቅና የምእመናን ተሳትፎ በከፍተኛ ደረጃ የሚረጋገጥበት ሥርዐትና አሠራር በሚዘረጋበት ኹኔታ ላይ ቅዱስ ሲኖዶሱ ትኩረት ሰጥቶ
እንዲመክር ኅብረቱ ጠይቋል፡፡
የኅብረቱን ጥያቄዎች ምልዓተ ጉባኤው እንደሰማ የገለጹት ርእሰ መንበሩ ብፁዕ ወቅዱስ ፓትርያርክ አቡነ ማትያስ፣ ቅዱስ ሲኖዶሱ በጥያቄዎቹ ላይ መክሮ ውሳኔውን እንደሚያስታውቅ
መናገራቸውን የኅብረቱ ልኡካን ገልጸዋል፡፡
ከ2006 እስከ 2009 ዓ.ም፤ ሊቃነ ጳጳሳትን፣ ሊቃውንተ ቤተ ክርስቲያንን ጨምሮ የቤተ ክርስቲያኒቱ አስተዳደራዊ ለውጥ የሚገዳቸው ከፍተኛ ኤክስፐርቶች በሦስት ጥራዝ
አጥንተው ያቀረቡት የቤተ ክርስቲያን አስተዳደር ማዘመኛ ጥናት በቅዱስ ሲኖዶስ ተቀባይነት ካገኘ በኋላ እንዳይተገበር ለውጡን በማይፈልጉ አካላት ታግዶ መቆየቱን የኅብረቱ
ም/ሰብሳቢ አርክቴክት ዮሐንስ መኮንን ለአዲስ አድማስ አስረድተዋል፡፡

Read 6772 times