Saturday, 27 October 2018 09:58

“የሶማሌ ክልልን ከኢትዮጵያ መገንጠል የማይታሰብ ነው” - የክልሉ ፕሬዚዳንት

Written by  አለማየሁ አንበሴ
Rate this item
(8 votes)

የሶማሌ ህዝብ ከኢትዮጵያውያን ወንድሞቹ ጋር በሰላም ለመኖር የሚፈልግ ህዝብ በመሆኑ ከኢትዮጵያ የመገንጠል ጉዳይ የማይታሰብ ነው ሲሉ አዲሱ የሶማሌ ክልል ፕሬዚዳንት አቶ ሙስጠፋ ኦማር አስገነዘቡ፡፡  
“ሰሞኑን ከኦጋዴን ብሔራዊ ነፃነት ግንባር (ኦብነግ) ጋር በአስመራ በተፈፀመ ስምምነት የሶማሌ ህዝብ የራስን ዕድል በራስ የመወሰን መብቱን ተጠቅሞ፣ ህዝበ ውሳኔ እንዲያደርግ ከስምምነት ላይ ተደርሷል” በሚል በተለያዩ መገናኛ ብዙኃን የቀረበው ዘገባ ሃሰተኛ መረጃ መሆኑን የገለጹት አቶ ሙስጠፋ፤ “በስምምነቱ ወቅት ስለ ህዝበ ውሳኔም ሆነ ስለ መገንጠል ጉዳይ ለውይይት አልቀረበም፤ ስምምነትም አልተፈረመበትም” ብለዋል፡፡
አስመራ ላይ በተደረገው ስምምነት ኦብነግ እንደ ሌሎቹ ትጥቅ ይዘው ሲንቀሳቀሱ እንደነበሩ ተቃዋሚዎች የትጥቅ ትግሉን አቁሞ በሰላማዊ መንገድ፣ በሃገር ውስጥ ገብቶ እንዲንቀሳቀስ ነው የተስማማው ያሉት የክልሉ ፕሬዚዳንት፤የህዝበ ውሳኔና የመገንጠል ጉዳይ ፈፅሞ አለመነሳቱን አስታውቀዋል፡፡
በምስራቅ ኢትዮጵያ በኩል ያለው ሉአላዊነት የሚጠበቀው በሶማሌ ህዝብ ፍቃድና ፍላጎት ብቻ መሆኑን ያስገነዘቡት ፕሬዚዳንቱ፤ በቅርቡ በጅግጅጋ ተፈጥሮ የነበረውን ግጭትና ግድያ ከቀድሞ የክልሉ ፕሬዚዳንት አብዲ መሃመድ ጀርባ ሆነው ያነሳሱ ኮንትሮባንዲስቶች አሁንም አካባቢውን ለመረበሽ ፍላጎት እንዳላቸው ያመላክታል ብለዋል፡፡
የክልሉን ሰላም የማይሹ ኃይሎች አስመራ ላይ ከኦብነግ ጋር የተደረሰው ሰላም የሚያመጣ ስምምነት እያስደሰታቸው አይደለም ያሉት አቶ ሙስጠፋ፤ በዶ/ር ዐቢይ አህመድ የተጀመረውን ለውጥ ለማደናቀፍና ለማኮላሸት የሚደረግ ማናቸውም ጥረት ተቀባይነት እንደሌለው አስገንዝበዋል፡፡  “በግጭትና በአለመረጋጋት በሚታወቀው የሶማሌ ክልል በአሁኑ ወቅት ሰላማዊ የፖለቲካ ትግል የሚደረግበትን ምዕራፍ ጀምረናል” ያሉት ፕሬዚዳንቱ፤ “ሁሉን በእኩል አካታችና ዲሞክራሲያዊት ኢትዮጵያ እንድትፈጠር ጠንክረን እንታገላለን” ብለዋል-በማህበራዊ ድረ ገጻቸው ባሰፈሩት መልዕክት፡፡


Read 8082 times