Saturday, 27 October 2018 09:57

ለማንነት ጥያቄዎች መንግስት አፋጣኝ ምላሽ እንዲሰጥ ሰማያዊ ፓርቲ ጠየቀ

Written by  አለማየሁ አንበሴ
Rate this item
(6 votes)

“በመብት ጠያቂዎች ላይ የሚፈፀም ግድያ አለመቆሙ አሳሳቢ ነው”

በራያ እና በወልቃይት ለዜጎች ሞትና እንግልት ምክንያት የሆኑ የማንነት ጥያቄዎች በፌደራል መንግስት አፋጣኝ ምላሽ እንዲሰጣቸው የጠየቀው ሰማያዊ ፓርቲ፤ መብታቸውን በተለያየ አግባብ በሚጠይቁ ዜጎች ላይ የሚፈፀመው ግድያ አሁንም አለመቆሙ አሳሳቢ ነው ብሏል፡፡
ፓርቲው በወቅታዊ ጉዳዮች ላይ በሰጠው ጋዜጣዊ መግለጫው፤ በአገሪቱ የተለያዩ አካባቢዎች ዜጎች የአስተዳደርና የማንነት ጥያቄ በሚያነሱበት ወቅት በመንግስት የፀጥታ ኃይሎች የሚወሰደው የኃይል እርምጃ የዜጎችን ሰብአዊ መብት የሚጥስ በመሆኑ ከእንግዲህ መደገም እንደሌለበት አሳስቧል፡፡
በየአካባቢው ለሚነሱ የአስተዳደርና የማንነት ጥያቄዎች፣ በምክክርና በውይይት፣ የህዝብን ፍላጎት መሰረት አድርጎ፣ በመንግስት በኩል አፋጣኝ ምላሽ እንዲሰጥም ጠይቋል - ፓርቲው፡፡
ጥያቄ አንግበው አደባባይ በወጡ ዜጎች ላይ የኃይል እርምጃ እንዲወሰድ ትዕዛዝ የሰጡና ነፍስ ያጠፉ የፀጥታ ኃይሎች በህግ እንዲጠየቁና ጉዳት ለደረሰባቸው ቤተሰቦች ተገቢው ካሣ በአስቸኳይ እንዲሰጣቸው የጠየቀው ሰማያዊ ፓርቲ፤ “በሀገሪቱ እየተደረገ ያለውን ለውጥ የምደግፈው በየትኛውም መልኩ ዜጎችን በእኩልነት የሚያይና ሰብአዊ መብቶችን የሚያከብር ስርአት እስከሰፈነ ድረስ ብቻ ነው” ብሏል፡፡
“የትኛውንም የህዝብ ጥያቄ በኃይል ማፈን አይቻልም” ያለው ፓርቲው፤ የኃይል እርምጃን በማንኛውም መልኩ አጥብቆ እንደሚቃወምና መገታትም እንደሚገባው  አሳስቧል፡፡
ከሰሞኑ ከራያ የማንነት ጥያቄ ጋር በተያያዘ በተፈጠረ ተቃውሞና ግጭት 5 ሰዎች በፀጥታ ኃይሎች መገደላቸው የተገለፀ ሲሆን በጉዳዩ ላይም የአማራና የትግራይ ክልላዊ መንግስት በየፊናቸው መግለጫ አውጥተዋል፡፡ የአማራ ክልላዊ መንግስት ባወጣው መግለጫ፤ በራያና በወልቃይት የማንነት ጥያቄዎች ተገቢው ህጋዊ ምላሽ እንዲሰጣቸው የጠየቀ ሲሆን በዚህ ሂደትም ከትግራይ ክልላዊ መንግስት ጎን በመሆን ድጋፍ ለማድረግ እንደሚሻ  አስታውቋል፡፡ የትግራይ ክልል በበኩሉ፤”የአማራ ክልል በማያገባው ጉዳይ ላይ መግለጫ ሰጥቷል” ሲል ከስሷል፡፡
  የራያ የማንነት ጥያቄ እስካሁን እንዳልቀረበለት ያስታወቀው የፌዴሬሽን ም/ቤት፤የወልቃይት የማንነት ጥያቄ ግን እንደቀረበለት ጠቁሞ፤ሆኖም የማንነት ጥያቄ አቀራረቡ ህጋዊ ሂደቱን ያልጠበቀ ነው ብሏል፡፡
በሁለቱ አካባቢዎች የሚነሳው የማንነት ጥያቄ በመጀመሪያ ለትግራይ ክልላዊ መንግስት ቀርቦ ምላሽ ካላገኘ ብቻ ወደ ፌዴሬሽን ም/ቤት በይግባኝ ሊመጣ እንደሚገባው የገለፁት የፌዴሬሽን ም/ቤት አፈ ጉባኤ ወ/ሮ ኬርያ ኢብራሂም፤ጥያቄው የሚቀርብለት ክልልም ተገቢውን አፋጣኝ ምላሽ መስጠት እንዳለበት አሳስበዋል፡፡    



Read 6695 times